About

Saturday, November 14, 2020

ህዳር 6 ቁስቋም ማርያም



ህዳር 6 ቁስቋም ማርያም ስደቷን ጨርሳ የገባችበት 

❇️ የአርያም ንግሥት፣ የፍጥረታት ሁሉ እመቤት ድንግል ማርያም የባሕርይ አምላክ ልጇን አዝላ ወደ ምድረ ግብጽ ወርዳለች።

❇️በወንጌል ላይ (ማቴ. ፪፥፩-፲፰) እንደተጻፈው ጌታችን በተወለደ በሁለት ዓመቱ የጥበብ ሰዎች (ሰብአ ሰገል) ወደ ቤተ ልሔም መጥተው ሰግደውለት ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤውን ገበሩ፤ አገቡለት። 

❇️ንጉሥ ተወልዷል መባሉን የሰማ ሄሮድስ መቶ አርባ አራት ሺህ ሕፃናትን ሲፈጅ በቅዱስ ገብርኤል ትዕዛዝ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አንድ አምላክ ልጇን አዝላ በአንዲት አህያ ጥቂት ስንቅ ቋጥራ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ስደት ወጣች። 

❇️ከገሊላ ተነስታ በጭንቅ፣ በመከራ፣ በረሃብና በጥም፣ በሐዘንና በድካም፣ በላበትና በእንባ ተጉዛ ምድረ ግብጽ ገብታለች። 

❇️የአምላክ እናቱ እሳትን አዝላ በብርድ ተንገላታለች። ለእኛ የሕይወት እንጀራን ተሸክማ እርሷ ተራበች። የሕይወትን ውኃ ተሸክማ ተጠማች። የሕይወት ልብስን ተሸክማ ተራቆተች። የሕይወት ፍስሐን ተሸክማ አዘነች። እመ አምላክ ተራበች፣ ተጠማች፣ ታረዘች፣ ደከመች፣ አዘነች፣ አለቀሰች፣ እግሯ ደማ፣ ተንገላታች። ለሚገባው ይህ ሁሉ የተደረገው ለእኛ ድኅነት ነው። 

❇️በእውነት ይህንን እያወቀ ለድንግል ማርያም ክብር የማይሰጥ ሰይጣን ብቻ ነው። አራዊት፣ ዕፅዋትና ድንጋዮች እንኳ ለአምላክ እናት ክብር ይሰጣሉ። አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍና ቅድስት ሰሎሜ ደግሞ የክብር ክብር ይገባቸዋል። 

❇️ከአምላክ እናት ከድንግል ማርያምና ከቸር ልጇ ጋር መከራ መቀበልን መርጠዋልና። "መድኃኔ ዓለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተሰደደ? ለምን ስደቱን ወደ ግብጽና ኢትዮጵያ አደረገ?" ፩.ትንቢቱን ይፈጽም ዘንድ። በፈጣን ደመና ወደ ግብጽ እንደሚወርድ ተነግሯልና። (ኢሳ. ፲፱፥፩ ፣ ዕን. ፫፥፯) 

፪.ምሳሌውን ለመፈጸም። የሥጋ አባቶቹ እነ አብርሃም፣ ያዕቆብ (እሥራኤል)፣ ኤርምያስ ወደዚያው ተሰደዋልና። 

፫.ከግብጽ ጣዖት አምልኮን ያጠፋ ዘንድ። (ኢሳ. ፲፱፥፩) 

፬.የግብጽና የኢትዮጵያ ገዳማትን ይቀድስ ዘንድ። 

፭.ሰው መሆኑ በአማን እንጂ ምትሐት እንዳልሆነ ለማጠየቅ። (ሰው ባይሆን ኑሮ አይሰደድም ነበር። ሄሮድስ ቢያገኘው ደግሞ ሊገድለው አይችልም። ያለ ፈቃዱና ያለ ዕለተ ዓርብ ደሙ አይፈስምና።) 

፮.ስደትን ለሰማዕታት ባርኮ ለመስጠት እና 

፯.የአዳምን ስደት በስደቱ ለመካስ ነው። 

❇️እመ ብርሃን ድንግል ማርያም ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር (ለአርባ ሁለት ወራት) በስደት የቆየችባቸው ቦታዎች አሉ። ድንግል ማርያም ከርጉም ሄሮድስ ስትሸሽ መጀመሪያ የሔደችው ከገሊላ ወደ ሶርያ ድንበር (ደብረ ሊባኖስ) ነው። 

❇️በዚያ የሸሸጋት ቅዱስ ጊጋር መስፍኑ በሄሮድስ ሲገደል ወደ ምድረ ግብጽ ወረደች። 

❇️በግብጽም ለብዙ ጊዜ ከአንዱ ወደ ሌላው ስትሸሽ ቆየች። "እንዘ ከመ በግዕት ግድፍት አመ ሳኮይኪ ውስተ ምድረ በዳ" እንዲል። 

❇️(እሴብሕ ጸጋኪ) ቀጥላም በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ገብታ ደብረ ቢዘን ላይ (አሁን ኤርትራ ውስጥ ነው።) ዐረፈች። ከደብረ ቢዘን በደብረ ዳሞ፣ አክሱም፣ ደብር ዓባይ፣ ዋልድባ አድርጋ እየባረከች ጣና ደርሳለች። በጣና ገዳማትም በተለይ በጣና ቂርቆስ ለመቶ ቀናት ቆይታ ቀጥታ በጐጃም ወደ ሽዋ ሒዳ ደብረ ሊባኖስን ቀድሳለች። ቀጥላም እስከ ደብረ ወገግና ደብረ ሐዘሎ ደርሳለች። በእግሯ ያልደረሰችባቸውን የሃገራችን ክፍሎች በደመና ተጭና ዐይታ ባርካቸዋለች። ከልጇም በአሥራትነት ተቀብላለች። 

❇️ሄሮድስ መሞቱን መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የነገራትም እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን ትውፊት ያሳያል። 

❇️እመ ብርሃንም ከሃገራችን ሰዎች (ከሰብአ ኦፌር) የተቀበለችውን ስንቅና ስጦታ በአምስት ግመሎች ጭና ከቅዱሳኑ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር በዚህች ቀን ደብረ ቁስቋም ውስጥ ገብተው ከድካም ዐርፈዋል፤ ሐሴትንም አድርገዋል። ዳግመኛም ከክርስቶስ ስደት አራት መቶ ዓመታት በኋላ በዚህች ቀን የግብጿ ደብረ ቁስቋም ታንጻ ተቀድሳለች። የቅዱሳን ማደሪያም ሁናለች። 

❇️ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ፫፻፺ዎቹ አካባቢ ድንግል እናቱን፣ ቅዱሳን ሐዋርያትን፣ አእላፍ መላእክትን፣ ጻድቃንንና ሰማዕታትን አስከትሎ ወረደ። 

❇️የወቅቱ የግብጽ ፓትርያርክ ቅዱስ ቴዎፍሎስና ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ ቤተ ክርስቲያኑን አንጸው ሕዝቡን ሰብስበው ይጠብቁት ነበርና ወርዶ ቀድሶላቸው ታላቅ ደስታ ሁኗል። ስደቷን መሳተፍን ሽተው አበው፦ "እመ ኀሎኩ በጐይዮቱ ውእተ መዋዕለ እምተመነይኩ ኪያሁ በዘባንየ ሐዚለ ወበልሳንየ እልሐስ ዘአእጋሪሁ ጸበለ ወከመ አዕርፍ ምስሌሁ በትረ ዮሴፍ ኀበ ተተክለ ለወልደ ማርያም በሐጸ ፍቅሩ ልቡናየ ቆስለ።" እንዳሉ። (ሰቆቃወ ድንግል) እኛም እመ ብርሃንን ልንሻት ያስፈልገናል። 

❇️ይህ ቀን ለእኛ ለክርስቲያኖች ሁሉ እጅግ የደስታ ቀን ነውና ሐሴትን እናድርግ። የሰማይና የምድር ጌታ ለእኛ ሲል ካደረገው ስደቱ በዚህች ቀን ተመልሷልና። ስደቷን አስበን ካዘንን፣ መመለሷን አስበን ደስ ልንሰኝ ይገባልና። "አብርሒ አብርሒ ናዝሬት ሃገሩ ንጉሥኪ በጽሐ ዘምስለ ማርያም መጾሩ።" ልንልም ይገባል።

⚪️ ወስብሐት ለእግዚአብሔር⚪️
©senkesar apk

No comments:

Post a Comment

ታህሳስ 6 ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ

GEDELEKIDUSAN ታህሳስ 3 ቅድስት አርሴማ(ቅዳሴ ቤቷ) ✝እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው።  ✝መድኃኒታችን ክር...