About

Wednesday, December 2, 2020

ህዳር 21 ፅዮን ማርያም

ህዳር 21
ፅዮን ማርያም/የእመቤታችን በዓል/

❇️"ጽዮን" ማለት "ጸወን - አምባ - መጠጊያ" ማለት ነው። አንድም በምሥጢሩ "ማሕደረ አምላክ" ማለት ነው። ጽዮን የሚለው ስም በቁሙ ለቅዱስ ዳዊት ተራራና ለኪዳኑ ጽላት ሲያገለግል በትንቢታዊ ምሥጢሩ ግን ለድንግል ማርያም፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለዘላለማዊት ርስት ያገለግላል። እግዚአብሔር ከዘመነ አበው በኋላ በጊዜው ለእስራኤላውያን ክብር፣ ሞገስ፣ አምባ የምትሆናቸውን ታቦተ ጽዮንን በቅዱስ ሙሴ አማካኝነት ሰጥቷቸዋል። (ዘጸ. ፴፩፥፲፰) ከዚያም ለአምስት መቶ ዓመታት ከእነርሱ ጋር በመሆኗ በፈጣሪና በእነርሱ መካከል ድልድይ ሆና ኖራለች። ከዚያም ባለቤቱ ሲፈቅድ በዘመነ ሳባ በቀዳማዊ ምኒልክ (እብነ መለክ - እብነ ሐኪም) አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ መጥታለች። 

❇️እነሆ በሃገራችን የሦስት ሺህ ዓመት ቆይታዋን ልትደፍን የቀራት ጥቂት ዓመታት ብቻ ናቸው። ጌታ እንደ ፈቀደ ቅዱስ መስቀሉንና ታቦተ ጽዮንን ይዘን ይሔው በቸርነቱ እንኖራለን። ያም ሆኖ ታቦተ ጽዮንን መስረቅ የሚፈልጉ ብዙ ቀሳጢዎች እንዳሉ እናውቃለን። ግን አንጨነቅም። ምክንያቱም የመጣችውም የምትጠበቀውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነውና እንጸልያለን እንጂ አንጨነቅም። በተለያየ ወሬም ራሳችንን አናማጥንም። ባለቤቱ እንድትሔድ ከፈቀደ ደግሞ ማንም ጉልበተኛ አያስቀራትም። 

❇️ታቦተ ጽዮን ብዙ ጊዜ "ጽላተ ኪዳን፣ ታቦተ ሕጉ" እየተባለች ትጠራለች። "ጽሌ" ማለት "ሰሌዳ" እንደ ማለት ሲሆን "ጽላት" ደግሞ በብዙ ቁጥር ነው። "ኪዳን" ደግሞ በፈጣሪና በሰው ልጆች መካከል ያለ "ውል - ስምምነት" ነው። "ታቦት" ማለት "ማሕደር - ማደሪያ" እንደ ማለት ነው። ሕጉ የተጻፈባቸውን ሰላድው "ጽላት" ስንላቸው የጽላቱ ማደሪያ ደግሞ "ታቦት" ይባላል። ጽላት (ታቦትን) ያመጣ ፈጣሪ ነው። በሐዲስ ኪዳንም ምሥጢርና ሐተታ ቢኖረውም ሁለት ቦታ ላይ ስለ ታቦት ተጠቅሶ እናገኛለን። (፪ቆሮ. ፮፥፲፮ ፣ ራእይ. ፲፩፥፲፱) በመጨረሻም ኅዳር ፳፩ ቀን ጽዮን ማርያምን የምናከብርባቸውን ምክንያቶች እንመለከታለን። 

❇️በዚህች ቀን፦ ፩.ታቦተ ጽዮን (ጽላተ ኪዳን) ለሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ መሰጠቷን እናስባለን። ይህ ሲሆንም ቅዱስ ሙሴ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ጾሞ እንደ ተቀበለ ሳንዘነጋ ማለት ነው። (ዘጸ. ፴፩፥፲፰ ፣ ዘዳ. ፱፥፲፱) ፪.በዘመነ ኤሊ ሊቀ ካህናት ታቦተ ጽዮን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሕዛብ (ኢሎፍላውያን) እጅ ተማርካለች። ግን ደግሞ ዳጐንን ቀጥቅጣዋለች። (፩ሳሙ. ፭፥፩) ፫.በዘመነ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በአሚናዳብ ሠረገላ ሁና ከአቢዳራ ቤት ስትመጣ ቅዱሱ ንጉሥ በታላቅ ሐሴት በፊቷ ዘመረ፤ አገለገለ። ምድራዊ ክብሩን እስኪረሳ ድረስ ለታቦተ አምላክ ተቀኘላት። በዚህም ሜልኮል ንቃው ማኅጸኗ ተዘግቷል። (፩ዜና. ፲፭፥፳፭) ሊቃውንትም "ድንግል እመቤታችን ማርያም በትንቢት መነጽር ተመልክቷል።" ብለውናል። "ሰላም ለኪ ማርያም እምነ ዘሰመይናኪ ጸወነ ሶበ እምርሑቅ ርእየ ዘጽላሎትኪ ስነ ለቢሶ ዳዊት ልብሰ ክብር ዘየኀይድ ዓይነ ቅድመ ታቦተ ሕግ ኀለየ ወዓዲ ዘፈነ።" እንዲል። (አርኬ ዘኅዳር ፳፩) ፬.በዘመነ ንጉሥ ሰሎሞን (መፍቀሬ ጥበብ) ግሩም የሆነ ቤተ መቅደስ ተሰርቶላት ስትገባ ታላቅ ሐሴት ተደርጓል። 

❇️እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ንጉሡን አነጋግሯል። (፪ዜና. ፭፥፩ ፣ ፩ነገ. ፰፥፩) ፭.በዚያው ዘመንም በፈጣሪ ፈቃድ ንጉሥ ምኒልክ ቀዳማዊ (ዕብነ ሐኪም) ታቦተ ጽዮንን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል። 
፮.በዘመነ አፄ ባዜን (በ፬ ዓ/ም አካባቢ) አማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያም ወደ አክሱም ጽዮን በስደት መጥታ ገብታለች። በዚህ ጊዜም ሁለቱ ጽዮኖች ሲገናኙ ታላቅ ብርሃን አክሱምን ውጧታል። 

፯.በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ነገሥት ጻድቃን አብርሐ ወአጽብሐ አሥራ ሁለት መቅደሶች ያሏትን ግሩም ቤተ ክርስቲያን ለእመ ብርሃን ሠርተው በዚሁ ቀን በጌታችን ተቀድሷል። 

፰.በተጨማሪም በየጊዜው ማለትም በዮዲት ጉዲትና በግራኝ አማካኝነት ስትፈርስ ወደ ዝዋይ ትሰደድ ነበር። ተመልሳ ስትታነጽም ቅዳሴ ቤቷ የሚከበረው ኅዳር ፳፩ ቀን ነው። በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ይህ በዓል ልዩ ነው። አማናዊት ጽዮን እመ ብርሃን ድንግል ማርያምን እንዲህ እንላታለን። "ቅድስት" የሚለው ቃል ለሁሉም ቅዱሳት እናቶች ቢሰጥም ቅሉ ለድንግል ማርያም ሲሰጥ ግን ትርጉሙ ይለያል። እርሷ "ቅድስተ ቅዱሳን፣ ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቡርክት እምቡሩካን፣ ኅሪት እምኅሩያን" ናትና። ከሰው ልጆችም ሁሉ ትበልጣለች። ይቅርና የሰው ልጅን ንጹሐን መላእክትንም በንጽሕናና በቅድስና ትበልጣቸዋለች። እርሷ እመ ብርሃን፣ የአምላክ እናቱ፣ የሰውነታችን መመኪያ ናትና። እመቤታችንን "ቅድስት" ስንል "ጽንዕት፣ ንጽሕት፣ ክብርት፣ ልዩ" ማለታችን ነው። 

፩."ንጽሕት" ትባላለች። ሌሎች ቅዱሳን ቢነጹ ከገቢር፣ ከነቢብ ኃጢአት ነው እንጂ ከኃልዮ ኃጢአት አይደለም። እርሷ ግን ከነቢብ፣ ከገቢር፣ ከኃልዮ ንጽሕት ናት። "ለመኑ ተውኅቦ ተደንግሎ ኅሊና ለመላእክትሂ ኢተክህሎሙ - ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ከሰው ልጆች ለማን ተሰጠው? ይህስ ለመላእክትም አልተቻላቸውም።" እንዲል። (ተአምረ ማርያም) 

፪."ጽንዕት" እንላታለን። ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው እንጂ በኋላ በጊዜው ተፈትሆ አለባቸው። እመቤታችን ግን ቅድመ ጸኒስ፣ ጊዜ ጸኒስ፣ ድኅረ ጸኒስ፤ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና። "ጽንዕት በድንግልና አልባቲ ሙስና" እንዳላት። (ቅዱስ ያሬድ) ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም "ወትረ ድንግል ማርያም - ማርያም ዘላለማዊት ድንግል ናት።" እንዳለ። (መጽሐፈ ቅዳሴ) ፫.ድንግልን "ክብርት" እንላታለን። 
ሌሎች ሴቶች ቢከብሩ ጻድቃን ሰማዕታትን፣ ነቢያት ሐዋርያትን ወልደው ነው። እመቤታችንን ግን የምናከብራት "ወላዲተ አምላክ - የአምላክ እናቱ" ብለን ነውና። 

፬.እመቤታችንን "ልዩ" እንላታለን። ከእርሷ በቀር እናት ሁና ድንግል፣ እመቤት ሁና አገልጋይ የሆነች፣ በድንግልና ወልዳ ወተትን (ሐሊበ ድንግልናዌን) ያስገኘች ሌላ ሴት የለችምና። 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment

ታህሳስ 6 ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ

GEDELEKIDUSAN ታህሳስ 3 ቅድስት አርሴማ(ቅዳሴ ቤቷ) ✝እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው።  ✝መድኃኒታችን ክር...