About

Friday, December 11, 2020

ታህሳስ 3 በዓታ ለ ማርያም

 
ታህሳስ 3
በአታ ለማርያም እመቤታችን በሶስት አመቷ ቤተመቅደስ የገባችበት

❇️ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ (አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ በሕጉ ጸንተው በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር። ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም።" በሚል ይናቁ ነበር። ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት - ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር። ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ። እነርሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም። የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው። አንድ ቀን ርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች። "እንስሳትና አራዊትን፣ እጽዋትን ሳይቀር በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች። ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ። ለአርባ ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ። በአርባኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ። እርሱ፦ ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ በሐና ቀኝ ጆሮ ገብታ በማኅጸኗ ስትደርስ አየ። እርሷ ደግሞ፦ የኢያቄም በትር አብቦ፣ አፍርቶ፣ ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች። ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን።" አሉ። ለሰባት ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ። 

❇️በሰባተኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ ፯) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ። "ዓለም የሚድንባት የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ።" ብሏቸው ተሠወራቸው። እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ። እንደ ሥርዓቱም አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች። "ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ..... ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም።" እንዳለ ሊቁ። (ቅዳሴ ማርያም) "ለጽንሰትኪ በከርሥ እንበለ አበሳ ወርኩስ ወለልደትኪ እማኅጸን ቅዱስ..... ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው። የተወለድሽበት ማኅጸንም ቅዱስ ነው።....." (መጽሐፈ ሰዓታት ፣ ኢሳ. ፩፥፱) "ኢያቄም ወሐና ወለዱ ለነ ሰማየ ሰማዮሙኒ አስረቀት ለነ ፀሐየ። ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱልን። ሰማያቸው ደግሞ ፀሐይን አወጣችልን፤ (ወለደች - አስገኘችልን።)" የዓለማችን ወላጆች ነቢያት ሐዋርያትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ወልደው ከብረዋል፤ ተመስግነዋል። ኢያቄምና ሐና ግን ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ቢሰበሰብ በእግሯ የረገጠችውን ትቢያ እንኳ መሆን የማይችል የሰማይና የምድር ንግሥት የእግዚአብሔርን እናት እመቤታችን ማርያምን ወለዱልን። ኢያቄም ወሐና ለእግዚአብሔር የሥጋዌ አያቶቹም ተባሉ። ቅዱሳኑ እስኪያረጁ ድረስ በመካንነት አዝነው ጸልየዋል። ንጽሕናቸውና ደግነታቸው ተመስክሮላቸው ድንግል ማርያምን አግኝተዋል። እመቤታችን ነሐሴ ፯ ቀን ተጸንሳ ግንቦት ፩ ቀን ተወልዳለች። ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተወለደች የመጀመሪያዋ ሰው ድንግል ማርያም ሆናለች። 

❇️(ኢሳ. ፩፥፱) የእመቤታችን የዘር ሐረግ፦ አዳም-ኖኅ-አብርሃም-ይስሐቅ-ያዕቆብ በእናቷ፦ ሌዊ-ቀዓት-እንበረም-አሮን-ቴክታና በጥሪቃ-ሔኤሜን-ዴርዴን-ቶና-ሲካር-ሔርሜላና ማጣት-ሐና። በአባቷ በኩል፦ ይሁዳ-ፋሬስ-ሰልሞን-ቦኤዝ-እሴይ-ዳዊት-ሰሎሞን-ሕዝቅያስ-ዘሩባቤል-አልዓዛር-ቅስራ-ኢያቄም ይሆናል። ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች። 

❇️ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና ድንግል እመ ብርሃንን ከወለዱ በኋላ ለሦስት ዓመታት እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ፣ ነዳያንንም ሲጠግኑ ኖሩ። በእነዚህ ዓመታትም ቅድስት ሐና ድንግል ማርያምን ከእቅፏ አውርዳት አታውቅም። ቅዱሳን መላእክትም ዘወትር እየመጡ ያጫውቷት ይንከባከቧትም ነበር። 

❇️ሦስት ዓመት በሞላት ጊዜም በቅድስት ሐና አሳሳቢነት ብጽዓታቸውን (ስዕለታቸውን) ይፈጽሙ ዘንድ ተዘጋጁ። እንደ ሥርዓቱ የሚዘጋጀውን (መባውን) ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ሲደርሱ አበው ካህናትና የመቅደሱ አገልጋዮች ሁሉ ሊቀበሏቸው ወጡ። ሕዝቡ፣ ሊቃነ ካህናት ቅዱሳን ዘካርያስና ስምዖን፣ ኢያቄም ወሐና ከድንግል ማርያም ጋር ቆመው ሳሉም ሊቀ መላእክት ፋኑኤል ከሰማይ ወርዶ ረቦ ታየ። 

❇️ከቅዱስ ዘካርያስ ጀምሮ ሁሉም ሰው ሕብስትና ጽዋዑን ለመቀበል ቀረበ፤ ግን መልአኩ ራቀ። ድንግል ማርያም በቀረበች ጊዜ ግን ከመሬት አፈፍ አድርጐ አንስቶ ክንፉን ጋርዶ ሰማያዊውን ማዕድ መገባት። በዚህ ደስ የተሰኙ ካህናትና ሕዝቡ እየዘመሩ በታኅሣሥ ሦስት ቀን ወደ ቤተ መቅደስ አስገብተዋታል። አማናዊት መቅደሰ መለኮት ድንግል ማርያም ወደ ኦሪቱ ቤተ መቅደስ በገባችበት ዕለት ጸሎታችን እንድትሰማን እንደ ሊቃውንቱ፦ "ማርያም አንቲ ሰዋስው ዘምድረ ሎዛ ዲቤኪ ትዕርግ ጸሎትየ ከመ ጼና ሠናይ መዓዛ ኀበ ለነፍስየ ታሰስል ትካዛ።" እንላለን። 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment

ታህሳስ 6 ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ

GEDELEKIDUSAN ታህሳስ 3 ቅድስት አርሴማ(ቅዳሴ ቤቷ) ✝እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው።  ✝መድኃኒታችን ክር...