About

Friday, December 11, 2020

ታህሳስ 1 ቅዱስ ነቢዩ ኤልያስ


ታህሳስ 1
ነቢዩ ኤልያስ የተወለደበት ቀን

❇️ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ቀጥላ ቅዱስ ኤልያስን ታከብራለች። "ርዕሰ ነቢያት - የነቢያት ራስም" ትለዋለች። እርሱ ሰማይን የለጐመ፣ እሳትን ያዘነመ፣ ፍጥረትንም በቃሉ ያዘዘ አባት ነውና። ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ ቅዱሱ ትውልዱ (ነገዱ) ኢዮርብዓም ነጥሎ ከወሰዳቸው እስራኤል (አሥሩ ነገድ) ሲሆን አባቱ "ኢያስኑዩ" እናቱ ደግሞ "ቶና (ቶናህ)" ይባላሉ። በጐ አምልኮ ነበራቸውና እግዚአብሔር ማኅጸነ ቶናህን ቀድሶ ይህንን ቅዱስ ፍሬ ፈጠረ። 

❇️ቅዱስ ኤልያስ በተወለደ ቀን በቤታቸው ብርሃን ተሞልቶ ታይቷል። ብርሃን የለበሱ አራት ሰዎች (መላእክት) መጥተውም በእሳት ሰፋድል (መጐናጸፊያ) ሲጠቀልሉት ወላጆቹ በማየታቸው ደንግጠው ለነቢያትና ለካህናት ነገሯቸው። ካህናቱ ግን ነገሩ ቢረቅባቸው "ምን ዓይነት ፍጥረት ይሆን? በእስራኤል ይነግሥ ይሆን! ወይስ ነቢይ ይሆን?" ብለውም አድንቀዋል። ቅዱስ ኤልያስ ከልጅነቱ ጀምሮ ኮስታራ፣ ቁም ነገረኛ፣ ንጽሕናንም የሚወድ እስራኤላዊ ነው።

❇️ ወቅቱ (ከክርስቶስ ልደት ዘጠኝ መቶ ዓመት በፊት) ሕዝቡና ነገሥታቱ የከፉበት፣ እግዚአብሔር ተክዶ ጣዖት የሚመለክበት ነበር። ድሮ በኢሎፍላውያን እጅ የነበሩት ጣዖታት (ዳጐንና ቤል) በዚያ ዘመን ወደ እስራኤል ገብተው ነበር። ቅዱስ ኤልያስ ግን በዚህ ክፉ ትውልድ መካከል ሆኖም ሥርዓተ ኦሪትን የጠነቀቀ የንጽሕናና የአምልኮ ሰው ነበር። በዚያ ወራትም እግዚአብሔር ለነቢይነት ጠራው። እርሱም "እሺ" ብሎ ታዝዞ የእግዚአብሔርን የጸጋ ጥሪ ተቀበለ። ቅዱሱ ብዙ ጊዜ ለጉዳይ ካልሆነ ከሰው ጋር መዋል ማደርን አይወድምና መኖሪያውን በተራሮችና በዱር አደረገ። በተለይ ደብረ ቀርሜሎስ ለእርሱ ቤቱ ነበር። በዚህ ሕይወቱም ከመልከ ጼዴቅ ቀጥሎ፦ ፩.ለድንግልና (ድንግል ነበርና) ፪.ለብሕትውና (ብቸኛ ነበርና) ፫.ለምንኩስና (ተሐራሚ ነበርና) በብሉይ ኪዳን መሠረትን የጣለ ነቢይ ይባላል። መቼም በብሉይ ኪዳን የቅዱስ ኤልያስን፣ በዘመነ ክርስቶስ የመጥምቁ ዮሐንስን፣ በዘመነ ሊቃውንት ደግሞ የአፈ ወርቅ ዮሐንስን ያህል ደፋርና መገሥጽ አስተማሪ አልነበረም። በጊዜው ደግሞ አክአብና ኤልዛቤል የሚባሉ ክፉ ባልና ሚስት በእስራኤል ላይ ነግሠው ሕዝቡን ጣዖት አስመለኩት። ይባስ ብለው ደግሞ በወይኑ እርሻ አማካኝነት ኢይዝራኤላዊው ናቡቴን በሃሰት ምስክር ደሙን አፈሰሱት። ናቡቴም "የአባቶቼን ርስት አልሸጥም፤ አልለውጥም።" በማለቱ እንደ ሰማዕት ይቆጠራል። ኤልያስ ግን ይህንን ሲሰማ ወደ አክአብና ኤልዛቤል ቀርቦ "የናቡቴ ደም በእናንተ ላይ አይቀርም። የአንቺንም ደም ውሻ ይልሰዋል።" አላቸው። በዚህ ምክንያትም ኤልዛቤል ልትገድለው ብትፈልገውም እርሱ የእግዚአብሔር ነውና አላገኘችውም። በዚህ ብስጭትም ይመስላል አንድ ሺህ ነቢያትን ሰብስባ "ፍጇቸው" አለች። ዘጠኝ መቶው ሲታረዱ አንድ መቶውን ግን ቅዱስ አብድዩ በዋሻ ውስጥ ደብቆ እየመገበ አተረፋቸው። በእስራኤል ውስጥ ግን ዓመጻና ኃጢአት እየተስፋፋ ሔደ። 

❇️የእግዚአብሔርን ስጦታ እየተመገበ ሕዝቡ ለቤል (ለበዓል) ሰገደ። ይህን ጊዜ ግን ቅዱስ ኤልያስ እንዲህ አለ፦ "ሕያው እግዚአብሔር አምላከ ኃይል ዘቆምኩ ቅድሜሁ ከመ ኢይረድ ጠል በእላ መዋዕል ዘእንበለ በቃለ አፉየ።" ብሎ ዝናም ከሰማይ እንዳይወርድ ከለከለ። ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ዝናም ለዘር ጠል ለመከር ከመስጠት ተከለከለ። ሕዝቡ በኃጢአቱ ምክንያት ተጐዳ። እርሱን ቁራ ይመግበው፣ ምንጭ ፈልቆለት ይጠጣ ነበር። ይሔው ቢቀርበት ጸለየ። እግዚአብሔርም ከፈለገ ኮራት ወደ ሰራፕታ እንዲወርድ አዘዘው። በዚያም የነቢዩ ዮናስ እናት እንጐቻ ጋግራ ብታበላው ቤቷ በበረከት ተሞላ። ልጇ ሕፃኑ ዮናስ ቢሞትም በጸሎቱ አስነሳላት። 

❇️ቀጥሎም ሰባት ጊዜ በትጋት ጸልዮ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር የዘጋውን ሰማይ ከፍቶታል። ሕዝቡም ዕለቱኑ ከበረከቱ ቀምሰዋል። ከዚያ አስቀድሞ ግን ከኤልዛቤል ስምንት መቶ ሃምሳ ነቢያተ ሐሰትና ካህናተ ጣዖት ጋር ተወዳድሮ አሸንፏቸዋል። መስዋዕት ሰውተው የእርሱን ብቻ እሳት ከሰማይ ወርዳ በልታለታለችና ሕዝቡ ስምንት መቶ ሃምሳውን ሐሰተኛ ነቢያት በወንዝ ዳር በሰይፍ መትተዋቸዋል። ይህንን የሰማች ኤልዛቤልም ትገድለው ዘንድ አሳደደችው። "አቤቱ ከአባቶቼ አልበልጥምና ውሰደኝ! ብቻየን ቀርቻለሁና።" ብሎ ቢጸልይ እግዚአብሔር ለጣዖት ያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎችን እንዳተረፈ እርሱንም ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደሚወስደው ብሥራትን ነገረው። ደክሞት ተኝቶ ሳለም ቅዱስ መልአክ (ሚካኤል) ቀስቅሶ ታየው። እንጐቻ ባገልግል ውኃ በመንቀል አቅርቦ "ብላ! ጠጣ!" አለው። በላ፣ ጠጣ፣ ተኛ። እንደ ገና ቀስቅሶ አበላው። በሦስተኛው ግን "ብላዕ እስከ ትጸግብ እስመ ርሑቅ ፍኖትከ - ጐዳናህ ሩቅ ነውና እስክትጠግብ ብላ።" አለው። ኤልያስም ለአርባ ቀናት ያለ ምግብ ተጉዟል። ከዚያ በኋላም ምድራዊ ሕብስትን አልተመገበም። እግዚአብሔር አክአብና ኤልዛቤልን ከተበቀላቸው በኋላም ቅዱስ ኤልያስ በክፋተኞች ላይ ሁለት ጊዜ እሳትን አዝንሟል። የሚያርግበት ጊዜ ሲደርስም ደቀ መዝሙሩን ኤልሳዕን "የምትሻውን ለምነኝ።" ቢለው "እጥፍ መንፈስህን።" አለው። ሦስት ጊዜ ከመንገድ ሊያስመልሰው ሞከረ። ቅዱስ ኤልሳዕ ግን በብርታት ተከተለው። ዮርዳኖስን ከፍለው ከተሻገሩ በኋላ ግን ቅዱስ ኤልያስን ሠረገላ እሳት ወርዶ ነጠቀው። ለኤልሳዕም እኩሉን ግምጃውን ጣለለት። ዛሬ ቅዱስ ኤልያስ በብሔረ ሕያዋን ያለ ሲሆን በዘመነ ሐሳዌ መሲሕ መጥቶ በሰማዕትነት ከቅዱስ ሄኖክ ጋር ያርፋል። ለተጨማሪ ንባብ (ከ፩ነገ. ፲፯ - ፪ነገ. ፪ እና ዕርገተ ኤልያስን ያንብቡ።) ነቢዩ ኤልያስ በእውነት ታላቅ ነው! 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment

ታህሳስ 6 ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ

GEDELEKIDUSAN ታህሳስ 3 ቅድስት አርሴማ(ቅዳሴ ቤቷ) ✝እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው።  ✝መድኃኒታችን ክር...