About

Wednesday, December 2, 2020

ህዳር 24 ሀያአራቱ ካህናተ ሰማይ


ህዳር 24
ሀያአራቱ ካህናተ ሰማይ /ደብረ ሊባኖስ/

❇️እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን ሲፈጥራቸው በነገድ መቶ በክፍለ ነገድ አሥር አድርጓቸዋል። አቀማመጣቸውንም በሦስት ሰማያትና በአሥር ከተሞች (ዓለማት) አድርጓል። መላእክት ያሉባቸው ከተሞች ከታች ወደ ላይ 'ኤረር፣ ራማና ኢዮር' ይባላሉ። አሥሩ ክፍለ ነገድ ደግሞ ከነ አለቆቻቸው ይህንን ይመስላሉ። 
፩.አጋእዝት (የቀድሞ አለቃቸው ሳጥናኤል ሲሆን አሁን የተረፉት በቅዱስ ሚካኤል ሥር ናቸው።) ፪.ኪሩቤል (አለቃቸው ኪሩብ) ፫.ሱራፌል (አለቃቸው ሱራፊ) ፬.ኃይላት (አለቃቸው ሚካኤል) ፭.አርባብ (አለቃቸው ገብርኤል) ፮.መናብርት (አለቃቸው ሩፋኤል) ፯.ሥልጣናት (አለቃቸው ሱርያል) ፰.መኳንንት (አለቃቸው ሰዳካኤል) ፱.ሊቃናት (አለቃቸው ሰላታኤል) ፲.መላእክት (አለቃቸው አናንኤል) ናቸው። ከእነዚህም አጋእዝት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌልና ኃይላት መኖሪያቸው በኢዮር (በሦስተኛው ሰማይ) ነው። አርባብ፣ መናብርትና ሥልጣናት ቤታቸው ራማ (ሁለተኛው ሰማይ) ነው። መኳንንት፣ ሊቃናትና መላእክት ደግሞ የሚኖሩት በኤረር (በአንደኛው) ሰማይ ነው። መላእክት ተፈጥሯቸው እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ ነው። አይራቡም፣ አይጠሙም፣ አይዋለዱም፣ አይሞቱም። ተፈጥሯቸውም ረቂቅ ነው። ተግባራቸው ዘወትር "ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ" እያሉ ፈጣሪያቸውን ማመስገን ነው። ምግባቸውም ይሔው ነው። ዕረፍት ብሎ ነገርን አያውቁም። "አኮቴቶሙ ዕረፍቶሙ፣ ወዕረፍቶሙ አኮቴቶሙ" እንዲል። በተጨማሪም መልአክ ማለት ተላላኪ (አገልጋይ) ነውና ከፈጣሪ ወደ ሰው ልጆች ለምሕረትም፣ ለመዓትም ይላካሉ። ምሕረትን ያወርዳሉ። ልመናን ያሳርጋሉ። ቅጡ ሲባሉም ይቀጣሉ። ስነ ፍጥረት (አራቱ ወቅቶች) እንዳይዛቡ ይጠብቃሉ። ዘወትርም ስለ ሰው ልጆች ያማልዳሉ። (ዘካ. ፩፥፲፪) ምሥጢርን ይገልጣሉ። (ዳን. ፱፥፳፩) ይረዳሉ። (ኢያ. ፭፥፲፫) እንዳንሰናከል ይጠብቃሉ። (መዝ. ፺፥፲፩) ያድናሉ። (መዝ. ፴፫፥፯) ስግደት ይገባቸዋል። (መሳ. ፲፫፥፳ ፣ ኢያ. ፭፥፲፫ ፣ ራዕ. ፳፪፥፰) በፍርድ ቀንም ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያሉ። (ማቴ. ፳፭፥፴፩) በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ሕይወትና ድኅነት ሲባል ከፈጣሪያቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ሲጠብቁና ፈቃዱን ሲፈጽሙ ይኖራሉ። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህች ዕለት የሃያ አራቱን ቅዱሳን ካህናተ ሰማይን መታሰቢያ ታደርጋለች። እኒህ ቅዱሳን መላእክት በነገድ አሥር ሲሆኑ "ሱራፌል" እየተባሉ ይጠራሉ። መኖሪያቸው በኢዮር ነው። ነገር ግን ሃያ አራቱ አለቆቻቸው ተመርጠው በመሪያቸው በቅዱስ ሱራፊ አለቅነት በጽርሐ አርያም ያገለግላሉ። በቀናች ሃይማኖት ትምህርት ሁሉም ቅዱሳን መላእክት ለእግዚአብሔር ቅርብ ቢሆኑም በነጠላ የቅዱስ ሚካኤልን ያህል በነገድ ደግሞ የኪሩቤል (አራቱ እንስሳ) እና የሱራፌልን (ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ) ያህል ቅርብ የለም። ሃያ አራቱ ቅዱሳን ካህናት ሥራቸው፦ ፩.እንደ ሞገድ ከአንደበታቸው ምስጋና እየወጣ ጧት ማታ ፈጣሪያቸውን ይቀድሱታል። (ኢሳ. ፮፥፩ ፣ ራእይ ፬፥፲፩ ፤ ፭፥፲፩) ፪.የሥላሴን መንበር ያለ ማቋረጥ ያጥናሉ። (ራእይ ፭፥፰) ፫.የሰው ልጆችን በተለይም የቅዱሳንን ጸሎት በማዕጠንታቸው ያሳርጋሉ። (ራእይ ፰፥፫) ፬.የረከሱትን ይቀድሳሉ። (ኢሳ. ፮፥፮) ፭.ዘወትርም ለሰው ልጆች ምሕረትን ሲለምኑ ይኖራሉ። (ዘካ. ፩፥፲፪) ስለ እነዚህ ቅዱሳን ካህናት (ሱራፌል) ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ብዙ ይላል። ለምሳሌ፦ ዐቢይ ነቢይ ወልዑለ ቃል ኢሳይያስ ፈጣሪው ተቀይሞት በነበረበትና ዖዝያን በሞተበት ወራት ግሩማን ሆነው ሥላሴን "ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ" እያሉ ዙሪያውን ከበው ሲያመሰግኑ ሰምቷል። ከእነርሱም አንዱ (ሱራፊ) መጥቶ በጉጠት እሳት ከንፈሩን ዳስሶ ከለምጹ አንጽቶታል። (ኢሳ. ፮፥፩) አቡቀለምሲስ የተባለ ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ በግርማ በአምሳለ አረጋዊ ተመልክቷቸዋል። (ራእይ ፬፥፬) አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን የመሰሉ ቅዱሳን ሊቃውንት ደግሞ በጣዕመ ምስጋናቸው ሲገልጿቸው፦ "ካህናተ ሰማይ ቅውማን በዐውዱ አክሊላቲሆሙ ያወርዱ ቅድመ መንበሩ እንዘ ይሰግዱ ይርዕዱ ከመ ኢይዝብጦሙ ሶበ ይበርቅ ነዱ።" ብለዋል። (መጽሐፈ ሰዓታት) ትርጉሙም "በፈጣሪ መንበር ዙሪያ የሚቆሙ የሰማይ ካህናት አክሊለ ክብራቸውን አውርደው በመንበሩ ፊት ይሰግዳሉ። 

❇️መብረቀ መለኮቱ በተገለጠ ጊዜም በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ።" ማለት ነው። ግሩም ባሕርየ ሥላሴን ሊቋቋመው የሚችል ፍጡር የለምና። ቅዱሳን ካህናተ ሰማይ በምስጋናቸው፣ በማዕጠንታቸውና በምልጃቸው ክቡራን ናቸውና ዘወትር ልናከብራቸው ይገባናል። የረከሰ ማንነታችንን ይቀድሱ ዘንድ፣ በምልጃቸውም ዘንድ እንድንታሰብ፣ ጸሎታችንንም ያሳርጉልን ዘንድ እንለምናቸው። ኅዳር ፳፬ ቀን ዓመታዊ በዓላቸው ነው ማለት በየወሩ በ፳፬ ወርኀዊ በዓላቸው መሆኑን ያሳያልና ዘወትር ልናስባቸው ይገባል። በተለይ ያዘነን ልብ ደስ ያሰኛሉና እንደ ሊቃውንት እንዲህ ብለን እንጠራቸዋለን። "ሰላም ለክሙ ካህናተ ሕጉ ወትዕዛዙ ለእግዚአብሔር ቃል ዘጶዴሬ ሥጋ አራዙ እምነቅዐ አፉክሙ ሐሴት ዘኢይነጽፍ ዉሒዙ ኪያየ ኅዙነ ወትኩዘ ልብ ናዝዙ ወበክንፍክሙ ብርሃናዊ ዐውድየ ሐውዙ።" (አርኬ ዘኅዳር ፳፬) 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment

ታህሳስ 6 ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ

GEDELEKIDUSAN ታህሳስ 3 ቅድስት አርሴማ(ቅዳሴ ቤቷ) ✝እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው።  ✝መድኃኒታችን ክር...