About

Monday, December 14, 2020

ታህሳስ 6 ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ

ታህሳስ 3
ቅድስት አርሴማ(ቅዳሴ ቤቷ)

✝እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው። 

✝መድኃኒታችን ክርስቶስ በወንጌል እንዳለው "በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትምና።"(ማቴ. ፭፥፲፩) የሰማዕቷ ሕይወት በፊታችን እንደ ብርሃን ተገልጦ ይታያል። ቅድስት አርሴማ እንደ ልጅ ወላጆቿን በመታዘዝ ደስ ያሰኘች ቡርክት ናት። ቅድስት አርሴማ ይህ ቀረሽ የማይሏት ውብ ናት። ቅድስት አርሴማ ድንግል ናት። ቅድስት አርሴማ ባሕታዊት ጻድቅ ናት። ቅድስት አርሴማ ኃያል ሰማዕት ናት። ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ አበው በትውፊት እንደ ነገሩን ቅዱሱ ጐርጐርዮስ የታላቋ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ ትልቅ ወንድም ነው። በዜና ሰማዕታት ተጽፎ እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት፦ ፩.ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት ፪.ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት ፫.የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት። ቅዱሱ ሦስቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ። ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት። 

✝መከራው ገፍቶ እስከ መጣበት ጊዜ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ፣ ይጾሙ፣ ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር። ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስን ጻድቃን የምንላቸው። በኋላ ግን ማኅደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ በመልኳ ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ። በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና በጸሎት ለጥቂት ጊዜ ቆዩ። ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው። የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለ መኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ። በዚያም በድርጣድስ ቤተ መንግሥት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ። በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር። መከራው ግን አለቀቃቸውም። ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው። ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ "ካላገባሁሽ" አላት። ድንግሊቱ ግን "እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ፤ አይሆንም።" አለችው። ሊያስፈራራት ሞከረ። ዓይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው። አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው። እጅግ ስላፈረ አስገረፋት፣ አሰቃያት፣ ዓይኗንም አወጣ። በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት። ከነገር ሁሉ በኋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀየራቸው። 

✝የንጉሡ እንስሳ (አውሬ) መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን ፈጠረ። የንጉሡ እኅት ስታለቅስ በራእይ "ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን - ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም።" አላቸው። ወዲያውም ቆፍረው አወጡት። ቅዱሱ እንደ ወጣ ዕረፍትን አልፈለገም። ለአሥራ አምስት ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው። ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሒዶ ፈወሳቸው። የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ አጽም በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሌሎች ሰማዕታት አጽም ጋር ኢትዮጵያ እንደ መጣ አባቶቻችን በትውፊት ነግረውናል። ለዚህም ነው ቡርክቷ እናታችን ከሌሎች ሃገራት ለይታ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ፍቅር ያላት። 

✝በዋናው ገዳሟ (ወሎ /ኩላማሶ/ ስባ ውስጥ የሚገኝ ነው።) ጨምሮ ስሟ በተጠራበት ሁሉ ኃይልን ታደርጋለችና። ነገር ግን ወንድሞቼና እኅቶቼ በቅድስቷ እናታችን ስም የሚነግዱ ሥጋውያን ሰዎች በዝተዋልና እንጠንቀቅ። የሰማዕቷ ክብር ብዙ ነውና በሕልም ላይ ብቻ አንታመን። አባ እንጦንስ እንዳሉት "በሕልሙ የሚታመን ሰው ከንቱ ነውና።" (መዝ. ፸፭፥፭) በዚህ ዕለት ከሰማዕቷ ጋር የመንፈስ እናቷን ቅድስት አጋታን ልናስባት ይገባናል። ይህች እናት እመ ምኔት ስትሆን ቅድስት አርሴማን ታስተምራት፣ ታጸናት፣ ከጐኗም ትቆምላት ነበር። 

✝ረሃቧን፣ ጥሟን፣ ስደቷን፣ መከራዋንም ሁሉ አብራት ተሳትፋለች። በፍጻሜውም አብራት ተሰይፋለች። ይህች ዕለት ለቅድስት አርሴማና ለተከታዮቿ ሰማዕታት የፍልሰትና የቅዳሴ ቤት መታሰቢያ ናት። 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Friday, December 11, 2020

ታህሳስ 3 በዓታ ለ ማርያም

 
ታህሳስ 3
በአታ ለማርያም እመቤታችን በሶስት አመቷ ቤተመቅደስ የገባችበት

❇️ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ (አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ በሕጉ ጸንተው በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር። ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም።" በሚል ይናቁ ነበር። ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት - ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር። ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ። እነርሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም። የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው። አንድ ቀን ርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች። "እንስሳትና አራዊትን፣ እጽዋትን ሳይቀር በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች። ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ። ለአርባ ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ። በአርባኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ። እርሱ፦ ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ በሐና ቀኝ ጆሮ ገብታ በማኅጸኗ ስትደርስ አየ። እርሷ ደግሞ፦ የኢያቄም በትር አብቦ፣ አፍርቶ፣ ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች። ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን።" አሉ። ለሰባት ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ። 

❇️በሰባተኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ ፯) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ። "ዓለም የሚድንባት የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ።" ብሏቸው ተሠወራቸው። እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ። እንደ ሥርዓቱም አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች። "ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ..... ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም።" እንዳለ ሊቁ። (ቅዳሴ ማርያም) "ለጽንሰትኪ በከርሥ እንበለ አበሳ ወርኩስ ወለልደትኪ እማኅጸን ቅዱስ..... ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው። የተወለድሽበት ማኅጸንም ቅዱስ ነው።....." (መጽሐፈ ሰዓታት ፣ ኢሳ. ፩፥፱) "ኢያቄም ወሐና ወለዱ ለነ ሰማየ ሰማዮሙኒ አስረቀት ለነ ፀሐየ። ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱልን። ሰማያቸው ደግሞ ፀሐይን አወጣችልን፤ (ወለደች - አስገኘችልን።)" የዓለማችን ወላጆች ነቢያት ሐዋርያትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ወልደው ከብረዋል፤ ተመስግነዋል። ኢያቄምና ሐና ግን ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ቢሰበሰብ በእግሯ የረገጠችውን ትቢያ እንኳ መሆን የማይችል የሰማይና የምድር ንግሥት የእግዚአብሔርን እናት እመቤታችን ማርያምን ወለዱልን። ኢያቄም ወሐና ለእግዚአብሔር የሥጋዌ አያቶቹም ተባሉ። ቅዱሳኑ እስኪያረጁ ድረስ በመካንነት አዝነው ጸልየዋል። ንጽሕናቸውና ደግነታቸው ተመስክሮላቸው ድንግል ማርያምን አግኝተዋል። እመቤታችን ነሐሴ ፯ ቀን ተጸንሳ ግንቦት ፩ ቀን ተወልዳለች። ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተወለደች የመጀመሪያዋ ሰው ድንግል ማርያም ሆናለች። 

❇️(ኢሳ. ፩፥፱) የእመቤታችን የዘር ሐረግ፦ አዳም-ኖኅ-አብርሃም-ይስሐቅ-ያዕቆብ በእናቷ፦ ሌዊ-ቀዓት-እንበረም-አሮን-ቴክታና በጥሪቃ-ሔኤሜን-ዴርዴን-ቶና-ሲካር-ሔርሜላና ማጣት-ሐና። በአባቷ በኩል፦ ይሁዳ-ፋሬስ-ሰልሞን-ቦኤዝ-እሴይ-ዳዊት-ሰሎሞን-ሕዝቅያስ-ዘሩባቤል-አልዓዛር-ቅስራ-ኢያቄም ይሆናል። ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች። 

❇️ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና ድንግል እመ ብርሃንን ከወለዱ በኋላ ለሦስት ዓመታት እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ፣ ነዳያንንም ሲጠግኑ ኖሩ። በእነዚህ ዓመታትም ቅድስት ሐና ድንግል ማርያምን ከእቅፏ አውርዳት አታውቅም። ቅዱሳን መላእክትም ዘወትር እየመጡ ያጫውቷት ይንከባከቧትም ነበር። 

❇️ሦስት ዓመት በሞላት ጊዜም በቅድስት ሐና አሳሳቢነት ብጽዓታቸውን (ስዕለታቸውን) ይፈጽሙ ዘንድ ተዘጋጁ። እንደ ሥርዓቱ የሚዘጋጀውን (መባውን) ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ሲደርሱ አበው ካህናትና የመቅደሱ አገልጋዮች ሁሉ ሊቀበሏቸው ወጡ። ሕዝቡ፣ ሊቃነ ካህናት ቅዱሳን ዘካርያስና ስምዖን፣ ኢያቄም ወሐና ከድንግል ማርያም ጋር ቆመው ሳሉም ሊቀ መላእክት ፋኑኤል ከሰማይ ወርዶ ረቦ ታየ። 

❇️ከቅዱስ ዘካርያስ ጀምሮ ሁሉም ሰው ሕብስትና ጽዋዑን ለመቀበል ቀረበ፤ ግን መልአኩ ራቀ። ድንግል ማርያም በቀረበች ጊዜ ግን ከመሬት አፈፍ አድርጐ አንስቶ ክንፉን ጋርዶ ሰማያዊውን ማዕድ መገባት። በዚህ ደስ የተሰኙ ካህናትና ሕዝቡ እየዘመሩ በታኅሣሥ ሦስት ቀን ወደ ቤተ መቅደስ አስገብተዋታል። አማናዊት መቅደሰ መለኮት ድንግል ማርያም ወደ ኦሪቱ ቤተ መቅደስ በገባችበት ዕለት ጸሎታችን እንድትሰማን እንደ ሊቃውንቱ፦ "ማርያም አንቲ ሰዋስው ዘምድረ ሎዛ ዲቤኪ ትዕርግ ጸሎትየ ከመ ጼና ሠናይ መዓዛ ኀበ ለነፍስየ ታሰስል ትካዛ።" እንላለን። 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ታህሳስ 1 ቅዱስ ነቢዩ ኤልያስ


ታህሳስ 1
ነቢዩ ኤልያስ የተወለደበት ቀን

❇️ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ቀጥላ ቅዱስ ኤልያስን ታከብራለች። "ርዕሰ ነቢያት - የነቢያት ራስም" ትለዋለች። እርሱ ሰማይን የለጐመ፣ እሳትን ያዘነመ፣ ፍጥረትንም በቃሉ ያዘዘ አባት ነውና። ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ ቅዱሱ ትውልዱ (ነገዱ) ኢዮርብዓም ነጥሎ ከወሰዳቸው እስራኤል (አሥሩ ነገድ) ሲሆን አባቱ "ኢያስኑዩ" እናቱ ደግሞ "ቶና (ቶናህ)" ይባላሉ። በጐ አምልኮ ነበራቸውና እግዚአብሔር ማኅጸነ ቶናህን ቀድሶ ይህንን ቅዱስ ፍሬ ፈጠረ። 

❇️ቅዱስ ኤልያስ በተወለደ ቀን በቤታቸው ብርሃን ተሞልቶ ታይቷል። ብርሃን የለበሱ አራት ሰዎች (መላእክት) መጥተውም በእሳት ሰፋድል (መጐናጸፊያ) ሲጠቀልሉት ወላጆቹ በማየታቸው ደንግጠው ለነቢያትና ለካህናት ነገሯቸው። ካህናቱ ግን ነገሩ ቢረቅባቸው "ምን ዓይነት ፍጥረት ይሆን? በእስራኤል ይነግሥ ይሆን! ወይስ ነቢይ ይሆን?" ብለውም አድንቀዋል። ቅዱስ ኤልያስ ከልጅነቱ ጀምሮ ኮስታራ፣ ቁም ነገረኛ፣ ንጽሕናንም የሚወድ እስራኤላዊ ነው።

❇️ ወቅቱ (ከክርስቶስ ልደት ዘጠኝ መቶ ዓመት በፊት) ሕዝቡና ነገሥታቱ የከፉበት፣ እግዚአብሔር ተክዶ ጣዖት የሚመለክበት ነበር። ድሮ በኢሎፍላውያን እጅ የነበሩት ጣዖታት (ዳጐንና ቤል) በዚያ ዘመን ወደ እስራኤል ገብተው ነበር። ቅዱስ ኤልያስ ግን በዚህ ክፉ ትውልድ መካከል ሆኖም ሥርዓተ ኦሪትን የጠነቀቀ የንጽሕናና የአምልኮ ሰው ነበር። በዚያ ወራትም እግዚአብሔር ለነቢይነት ጠራው። እርሱም "እሺ" ብሎ ታዝዞ የእግዚአብሔርን የጸጋ ጥሪ ተቀበለ። ቅዱሱ ብዙ ጊዜ ለጉዳይ ካልሆነ ከሰው ጋር መዋል ማደርን አይወድምና መኖሪያውን በተራሮችና በዱር አደረገ። በተለይ ደብረ ቀርሜሎስ ለእርሱ ቤቱ ነበር። በዚህ ሕይወቱም ከመልከ ጼዴቅ ቀጥሎ፦ ፩.ለድንግልና (ድንግል ነበርና) ፪.ለብሕትውና (ብቸኛ ነበርና) ፫.ለምንኩስና (ተሐራሚ ነበርና) በብሉይ ኪዳን መሠረትን የጣለ ነቢይ ይባላል። መቼም በብሉይ ኪዳን የቅዱስ ኤልያስን፣ በዘመነ ክርስቶስ የመጥምቁ ዮሐንስን፣ በዘመነ ሊቃውንት ደግሞ የአፈ ወርቅ ዮሐንስን ያህል ደፋርና መገሥጽ አስተማሪ አልነበረም። በጊዜው ደግሞ አክአብና ኤልዛቤል የሚባሉ ክፉ ባልና ሚስት በእስራኤል ላይ ነግሠው ሕዝቡን ጣዖት አስመለኩት። ይባስ ብለው ደግሞ በወይኑ እርሻ አማካኝነት ኢይዝራኤላዊው ናቡቴን በሃሰት ምስክር ደሙን አፈሰሱት። ናቡቴም "የአባቶቼን ርስት አልሸጥም፤ አልለውጥም።" በማለቱ እንደ ሰማዕት ይቆጠራል። ኤልያስ ግን ይህንን ሲሰማ ወደ አክአብና ኤልዛቤል ቀርቦ "የናቡቴ ደም በእናንተ ላይ አይቀርም። የአንቺንም ደም ውሻ ይልሰዋል።" አላቸው። በዚህ ምክንያትም ኤልዛቤል ልትገድለው ብትፈልገውም እርሱ የእግዚአብሔር ነውና አላገኘችውም። በዚህ ብስጭትም ይመስላል አንድ ሺህ ነቢያትን ሰብስባ "ፍጇቸው" አለች። ዘጠኝ መቶው ሲታረዱ አንድ መቶውን ግን ቅዱስ አብድዩ በዋሻ ውስጥ ደብቆ እየመገበ አተረፋቸው። በእስራኤል ውስጥ ግን ዓመጻና ኃጢአት እየተስፋፋ ሔደ። 

❇️የእግዚአብሔርን ስጦታ እየተመገበ ሕዝቡ ለቤል (ለበዓል) ሰገደ። ይህን ጊዜ ግን ቅዱስ ኤልያስ እንዲህ አለ፦ "ሕያው እግዚአብሔር አምላከ ኃይል ዘቆምኩ ቅድሜሁ ከመ ኢይረድ ጠል በእላ መዋዕል ዘእንበለ በቃለ አፉየ።" ብሎ ዝናም ከሰማይ እንዳይወርድ ከለከለ። ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ዝናም ለዘር ጠል ለመከር ከመስጠት ተከለከለ። ሕዝቡ በኃጢአቱ ምክንያት ተጐዳ። እርሱን ቁራ ይመግበው፣ ምንጭ ፈልቆለት ይጠጣ ነበር። ይሔው ቢቀርበት ጸለየ። እግዚአብሔርም ከፈለገ ኮራት ወደ ሰራፕታ እንዲወርድ አዘዘው። በዚያም የነቢዩ ዮናስ እናት እንጐቻ ጋግራ ብታበላው ቤቷ በበረከት ተሞላ። ልጇ ሕፃኑ ዮናስ ቢሞትም በጸሎቱ አስነሳላት። 

❇️ቀጥሎም ሰባት ጊዜ በትጋት ጸልዮ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር የዘጋውን ሰማይ ከፍቶታል። ሕዝቡም ዕለቱኑ ከበረከቱ ቀምሰዋል። ከዚያ አስቀድሞ ግን ከኤልዛቤል ስምንት መቶ ሃምሳ ነቢያተ ሐሰትና ካህናተ ጣዖት ጋር ተወዳድሮ አሸንፏቸዋል። መስዋዕት ሰውተው የእርሱን ብቻ እሳት ከሰማይ ወርዳ በልታለታለችና ሕዝቡ ስምንት መቶ ሃምሳውን ሐሰተኛ ነቢያት በወንዝ ዳር በሰይፍ መትተዋቸዋል። ይህንን የሰማች ኤልዛቤልም ትገድለው ዘንድ አሳደደችው። "አቤቱ ከአባቶቼ አልበልጥምና ውሰደኝ! ብቻየን ቀርቻለሁና።" ብሎ ቢጸልይ እግዚአብሔር ለጣዖት ያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎችን እንዳተረፈ እርሱንም ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደሚወስደው ብሥራትን ነገረው። ደክሞት ተኝቶ ሳለም ቅዱስ መልአክ (ሚካኤል) ቀስቅሶ ታየው። እንጐቻ ባገልግል ውኃ በመንቀል አቅርቦ "ብላ! ጠጣ!" አለው። በላ፣ ጠጣ፣ ተኛ። እንደ ገና ቀስቅሶ አበላው። በሦስተኛው ግን "ብላዕ እስከ ትጸግብ እስመ ርሑቅ ፍኖትከ - ጐዳናህ ሩቅ ነውና እስክትጠግብ ብላ።" አለው። ኤልያስም ለአርባ ቀናት ያለ ምግብ ተጉዟል። ከዚያ በኋላም ምድራዊ ሕብስትን አልተመገበም። እግዚአብሔር አክአብና ኤልዛቤልን ከተበቀላቸው በኋላም ቅዱስ ኤልያስ በክፋተኞች ላይ ሁለት ጊዜ እሳትን አዝንሟል። የሚያርግበት ጊዜ ሲደርስም ደቀ መዝሙሩን ኤልሳዕን "የምትሻውን ለምነኝ።" ቢለው "እጥፍ መንፈስህን።" አለው። ሦስት ጊዜ ከመንገድ ሊያስመልሰው ሞከረ። ቅዱስ ኤልሳዕ ግን በብርታት ተከተለው። ዮርዳኖስን ከፍለው ከተሻገሩ በኋላ ግን ቅዱስ ኤልያስን ሠረገላ እሳት ወርዶ ነጠቀው። ለኤልሳዕም እኩሉን ግምጃውን ጣለለት። ዛሬ ቅዱስ ኤልያስ በብሔረ ሕያዋን ያለ ሲሆን በዘመነ ሐሳዌ መሲሕ መጥቶ በሰማዕትነት ከቅዱስ ሄኖክ ጋር ያርፋል። ለተጨማሪ ንባብ (ከ፩ነገ. ፲፯ - ፪ነገ. ፪ እና ዕርገተ ኤልያስን ያንብቡ።) ነቢዩ ኤልያስ በእውነት ታላቅ ነው! 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Thursday, December 3, 2020

ህዳር 26 ፃዲቁ አቡነ ሀብተ ማርያም


ህዳር 26
አቡነ ሀብተማርያም /ደብረሊባኖስ/

❇️እኒህ ጻድቅ ደግሞ የሃገራችን ኮከበ ገዳም ናቸው። "ጽድቅና ትሩፋት እንደ ሃብተ ማርያም" እንዲሉ አበው። ባሕር ከሆነ ጣዕመ ሕይወታቸው ጥቂቱን ለበረከት እንካፈል። ጻድቁ መካነ ሙላዳቸው ሽዋ (የራውዕይ) ውስጥ ሲሆን አባታቸው ፍሬ ቡሩክ እናታቸው ደግሞ ቅድስት ዮስቴና ትባላለች። በተለይ ቅድስት ዮስቴና እጅግ ደመ ግቡ፣ ምጽዋትን ወዳጅ፣ ቡርክት ሴት ነበረች። እንዲያውም ከጻድቁ መወለድ በፊት መንና ጭው ካለ በርሃ ገብታ ነበር። ግን የበቃ ግኁስ አግኝቷት "ከማኅጸንሽ ደግ የሥላሴ ባርያ አለና ተመለሽ።" ብሏት እንደ ገና ተመልሳለች። 

❇️ጻድቁን ወልዳ አሳድጋም እንደ ገና መንና በተጋድሎ ኑራ ሰባት አክሊላትን ተቀብላ ዐርፋለች። ወደ ጻድቁ ዜና ሕይወት ስንመለስ አቡነ ሃብተ ማርያም ገና ሕፃን እያሉ ከእናታቸው ጋር ቆመው ሲያስቀድሱ "እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ" ሲባል ይሰማሉ። 

❇️ይህችን ጸሎት በሕፃን አንደበታቸው ይዘው ሌሊት ሌሊት እየተነሱ "ማረን እባክህን?" እያሉ ይሰግዱ ነበር። የአምስት ዓመት ሕፃን እንዲህ ሲያደርግ ማየቱ በእውነት ይደንቃል። ትንሽ ከፍ ብለው በእረኝነት ሳሉም ፍጹም ተሐራሚና ጸዋሚ ነበሩ። ጸጋው ስለ በዛላቸውም ልጅ ሆነው ብዙ ተአምራትን ሰርተዋል። የፈጣሪውን ስም ያቃለለውን አንድ እረኛም በዓየር ላይ ሰቅለው አውለውታል። 

❇️ከዚያ ግን ለአካለ መጠን ሲደርሱ ወደ ትምህርት ቤት ገብተው መጻሕፍትን አጥንተው መንነዋል። በአባ መልከ ጼዴቅ እጅ ከመነኮሱ በኋላ የሠሩትን ትሩፋትና የነበራቸውን ተጋድሎ ግን የኔ ብጤ ደካማ ሰው ሊዘረዝረው አይችልም። ባሕር ውስጥ ሰጥመው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ። በየቀኑ አራቱን ወንጌልና መቶ ሃምሳውን መዝሙረ ዳዊት ይጸልያሉ።

❇️ (መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ታላቅ ጸሎት ነው።) በአርባ ቀናት ቀጥሎም በሰማንያ ቀን አንዴ ብቻ ይመገባሉ። ምግባቸው ደግሞ ሣርና ቅጠል ብቻ ነው። በየዕለቱ ያለ ማስታጐል ማዕጠንት ያሳርጋሉ። (ካህን ናቸውና) ዘወትር በንጽሕና ቅዱስ ሥጋውን ይበላሉ፤ ክቡር ደሙን ይጠጣሉ። በፍጹም በልባቸው ውስጥ ቂምን፣ መከፋትን አላሳደሩም። 

❇️በእነዚህና በሌሎች ትሩፋቶቻቸው ደስ የተሰኘ ጌታም ለጻድቁ የእሳትና የብርሃን ሠረገላን ሰጥቷቸው በዚያ እየበረሩ ኢየሩሳሌም ይሔዱ ነበር። ከብዙ የተጋድሎ ዘመናት በኋላም የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ አዕላፍ መላእክትን አስከትሎ መጥቶ አላቸው። "ስለ እኔ ረሃብና ጥምን ስለ ታገስክ፣ ስለ ምናኔህ፣ ስለ ተባረከ ምንኩስናህ፣ ስለ ንጹሕ ድንግልናህ፣ ቂምና በቀልን ስላለመያዝህ፣ ስለ ንጹሕ ክህነትህና ማዕጠንትህ፣ ቅዱስ ወንጌልን በፍቅር ስለ ማንበብህ ሰባት አክሊላትን እሰጥሃለሁ።" "በሰማይም ከመጥምቁ ዮሐንስ ጐን አምስት መቶ የእንቁ ምሰሶዎች ያሉበትን አዳራሽ ሰጥቼሃለሁ። በስምህ የሚለምኑ፣ በቃል ኪዳንህ የሚማጸኑትንም ሁሉ እንድምርልህ 'አማንየ! በርእስየ!' ብዬሃለሁ።" አላቸው። ቅዱሳን መላእክትም "ሃብተ ማርያም ወንድማችን" ሲሉ አቀፏቸው። ጌታ ግን በዚያች ሰዓት አንድም ሦስትም ሆኖ ታያቸውና አቅፎ ሦስት ጊዜ ሳማቸው። ከፍቅሩ ጽናትም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች፤ በዝማሬም ወሰዷት። 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Wednesday, December 2, 2020

ህዳር 24 ሀያአራቱ ካህናተ ሰማይ


ህዳር 24
ሀያአራቱ ካህናተ ሰማይ /ደብረ ሊባኖስ/

❇️እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን ሲፈጥራቸው በነገድ መቶ በክፍለ ነገድ አሥር አድርጓቸዋል። አቀማመጣቸውንም በሦስት ሰማያትና በአሥር ከተሞች (ዓለማት) አድርጓል። መላእክት ያሉባቸው ከተሞች ከታች ወደ ላይ 'ኤረር፣ ራማና ኢዮር' ይባላሉ። አሥሩ ክፍለ ነገድ ደግሞ ከነ አለቆቻቸው ይህንን ይመስላሉ። 
፩.አጋእዝት (የቀድሞ አለቃቸው ሳጥናኤል ሲሆን አሁን የተረፉት በቅዱስ ሚካኤል ሥር ናቸው።) ፪.ኪሩቤል (አለቃቸው ኪሩብ) ፫.ሱራፌል (አለቃቸው ሱራፊ) ፬.ኃይላት (አለቃቸው ሚካኤል) ፭.አርባብ (አለቃቸው ገብርኤል) ፮.መናብርት (አለቃቸው ሩፋኤል) ፯.ሥልጣናት (አለቃቸው ሱርያል) ፰.መኳንንት (አለቃቸው ሰዳካኤል) ፱.ሊቃናት (አለቃቸው ሰላታኤል) ፲.መላእክት (አለቃቸው አናንኤል) ናቸው። ከእነዚህም አጋእዝት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌልና ኃይላት መኖሪያቸው በኢዮር (በሦስተኛው ሰማይ) ነው። አርባብ፣ መናብርትና ሥልጣናት ቤታቸው ራማ (ሁለተኛው ሰማይ) ነው። መኳንንት፣ ሊቃናትና መላእክት ደግሞ የሚኖሩት በኤረር (በአንደኛው) ሰማይ ነው። መላእክት ተፈጥሯቸው እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ ነው። አይራቡም፣ አይጠሙም፣ አይዋለዱም፣ አይሞቱም። ተፈጥሯቸውም ረቂቅ ነው። ተግባራቸው ዘወትር "ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ" እያሉ ፈጣሪያቸውን ማመስገን ነው። ምግባቸውም ይሔው ነው። ዕረፍት ብሎ ነገርን አያውቁም። "አኮቴቶሙ ዕረፍቶሙ፣ ወዕረፍቶሙ አኮቴቶሙ" እንዲል። በተጨማሪም መልአክ ማለት ተላላኪ (አገልጋይ) ነውና ከፈጣሪ ወደ ሰው ልጆች ለምሕረትም፣ ለመዓትም ይላካሉ። ምሕረትን ያወርዳሉ። ልመናን ያሳርጋሉ። ቅጡ ሲባሉም ይቀጣሉ። ስነ ፍጥረት (አራቱ ወቅቶች) እንዳይዛቡ ይጠብቃሉ። ዘወትርም ስለ ሰው ልጆች ያማልዳሉ። (ዘካ. ፩፥፲፪) ምሥጢርን ይገልጣሉ። (ዳን. ፱፥፳፩) ይረዳሉ። (ኢያ. ፭፥፲፫) እንዳንሰናከል ይጠብቃሉ። (መዝ. ፺፥፲፩) ያድናሉ። (መዝ. ፴፫፥፯) ስግደት ይገባቸዋል። (መሳ. ፲፫፥፳ ፣ ኢያ. ፭፥፲፫ ፣ ራዕ. ፳፪፥፰) በፍርድ ቀንም ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያሉ። (ማቴ. ፳፭፥፴፩) በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ሕይወትና ድኅነት ሲባል ከፈጣሪያቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ሲጠብቁና ፈቃዱን ሲፈጽሙ ይኖራሉ። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህች ዕለት የሃያ አራቱን ቅዱሳን ካህናተ ሰማይን መታሰቢያ ታደርጋለች። እኒህ ቅዱሳን መላእክት በነገድ አሥር ሲሆኑ "ሱራፌል" እየተባሉ ይጠራሉ። መኖሪያቸው በኢዮር ነው። ነገር ግን ሃያ አራቱ አለቆቻቸው ተመርጠው በመሪያቸው በቅዱስ ሱራፊ አለቅነት በጽርሐ አርያም ያገለግላሉ። በቀናች ሃይማኖት ትምህርት ሁሉም ቅዱሳን መላእክት ለእግዚአብሔር ቅርብ ቢሆኑም በነጠላ የቅዱስ ሚካኤልን ያህል በነገድ ደግሞ የኪሩቤል (አራቱ እንስሳ) እና የሱራፌልን (ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ) ያህል ቅርብ የለም። ሃያ አራቱ ቅዱሳን ካህናት ሥራቸው፦ ፩.እንደ ሞገድ ከአንደበታቸው ምስጋና እየወጣ ጧት ማታ ፈጣሪያቸውን ይቀድሱታል። (ኢሳ. ፮፥፩ ፣ ራእይ ፬፥፲፩ ፤ ፭፥፲፩) ፪.የሥላሴን መንበር ያለ ማቋረጥ ያጥናሉ። (ራእይ ፭፥፰) ፫.የሰው ልጆችን በተለይም የቅዱሳንን ጸሎት በማዕጠንታቸው ያሳርጋሉ። (ራእይ ፰፥፫) ፬.የረከሱትን ይቀድሳሉ። (ኢሳ. ፮፥፮) ፭.ዘወትርም ለሰው ልጆች ምሕረትን ሲለምኑ ይኖራሉ። (ዘካ. ፩፥፲፪) ስለ እነዚህ ቅዱሳን ካህናት (ሱራፌል) ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ብዙ ይላል። ለምሳሌ፦ ዐቢይ ነቢይ ወልዑለ ቃል ኢሳይያስ ፈጣሪው ተቀይሞት በነበረበትና ዖዝያን በሞተበት ወራት ግሩማን ሆነው ሥላሴን "ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ" እያሉ ዙሪያውን ከበው ሲያመሰግኑ ሰምቷል። ከእነርሱም አንዱ (ሱራፊ) መጥቶ በጉጠት እሳት ከንፈሩን ዳስሶ ከለምጹ አንጽቶታል። (ኢሳ. ፮፥፩) አቡቀለምሲስ የተባለ ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ በግርማ በአምሳለ አረጋዊ ተመልክቷቸዋል። (ራእይ ፬፥፬) አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን የመሰሉ ቅዱሳን ሊቃውንት ደግሞ በጣዕመ ምስጋናቸው ሲገልጿቸው፦ "ካህናተ ሰማይ ቅውማን በዐውዱ አክሊላቲሆሙ ያወርዱ ቅድመ መንበሩ እንዘ ይሰግዱ ይርዕዱ ከመ ኢይዝብጦሙ ሶበ ይበርቅ ነዱ።" ብለዋል። (መጽሐፈ ሰዓታት) ትርጉሙም "በፈጣሪ መንበር ዙሪያ የሚቆሙ የሰማይ ካህናት አክሊለ ክብራቸውን አውርደው በመንበሩ ፊት ይሰግዳሉ። 

❇️መብረቀ መለኮቱ በተገለጠ ጊዜም በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ።" ማለት ነው። ግሩም ባሕርየ ሥላሴን ሊቋቋመው የሚችል ፍጡር የለምና። ቅዱሳን ካህናተ ሰማይ በምስጋናቸው፣ በማዕጠንታቸውና በምልጃቸው ክቡራን ናቸውና ዘወትር ልናከብራቸው ይገባናል። የረከሰ ማንነታችንን ይቀድሱ ዘንድ፣ በምልጃቸውም ዘንድ እንድንታሰብ፣ ጸሎታችንንም ያሳርጉልን ዘንድ እንለምናቸው። ኅዳር ፳፬ ቀን ዓመታዊ በዓላቸው ነው ማለት በየወሩ በ፳፬ ወርኀዊ በዓላቸው መሆኑን ያሳያልና ዘወትር ልናስባቸው ይገባል። በተለይ ያዘነን ልብ ደስ ያሰኛሉና እንደ ሊቃውንት እንዲህ ብለን እንጠራቸዋለን። "ሰላም ለክሙ ካህናተ ሕጉ ወትዕዛዙ ለእግዚአብሔር ቃል ዘጶዴሬ ሥጋ አራዙ እምነቅዐ አፉክሙ ሐሴት ዘኢይነጽፍ ዉሒዙ ኪያየ ኅዙነ ወትኩዘ ልብ ናዝዙ ወበክንፍክሙ ብርሃናዊ ዐውድየ ሐውዙ።" (አርኬ ዘኅዳር ፳፬) 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ህዳር 24 ፃዲቁ አቡነ ተክለሃይማኖት


ህዳር 24 
አቡነ ተክለኃይማኖት 

❇️በዚች ቀን አባታችን አቡነ ተክለሀይማኖት በዳዊት ፀሎት ከነቢያት ምስጋና ሌሊቱን ሙሉ ይተጉ ነበር በያንዳንዱ መዝሙርም 10፣ 10 ስግደትን ይሰግዱ ነበር፡፡ በሕዳር 24 ቀን ቅዱስ ሚካኤል ወደ ላይ ነጠቃቸው (አወጣቸው) ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር 25ኛ ካህን ሆነው የሥላሴን መንበረን “አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” በማለት አጥነዋል፡፡

❇️አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የሥሉስ
ቅዱስን መንበር እንዳጠኑ፡- አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አቡነ
ኢየሱስ ሞዐ መጥተው በሐይቁ ዳር ቆመው ሳለ ሊቀ መላእክት
ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦላቸው ነው በእግሩ በውኃው ላይ እየሄደ
እያሳያቸው ተከትለውት እንዲሄዱ የነገራቸው። አባታችን አቡነ
ተክለ ሃይማኖትም መልአኩን ተከትለው ሐይቁን በእግራቸው
ተራምደው ተሻግረው አቡነ ኢየሱስ ሞዐን አገኟቸው፡፡

❇️እርሳቸውም አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ እርሳቸው እየመጡ
እንደሆነ በመንፈስ ዐውቀው ነበርና ሲያገኟቸው በጣም
ተደስተው ከተቀበሏቸው በኋላ አመነኩሰዋቸዋል፡፡
ከዚህም በኋላ አባታችን በዚያው በሐይቅ በታላቅ ተጋድሎ
መኖር ጀመሩ፡፡ አክፍሎትንም በየሳምንቱ ያከፍላሉ፣ ከእሁድና
ከቅዳሜ በቀር ምንም አይቀምሱም ነበር፡፡ 

❇️በእነዚህም ዕለት
የአጃ ቂጣ ወይም የዱር ቅጠል ይመጉ ነበር፡፡ ወዛቸው እንደ
ውኃ ፈስሶ ምድሪቷን እስኪያርሳት ድረስ እስከ 70 ሺህ
ዓይነቱ ተጋድሎ ላይ ሳሉ ነው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል
ድንገት ነጥቆ ወስዶ ከሥሉስ ቅዱስ ዙፋን ፊት ያቆማቸው፡፡
ከዚህ በኋላ ስለሆነው ነገር ራሳቸው አባታችን ተክለ ሃይማኖት
ሲናገሩ ‹‹…ከዚህ በኋላ መልአኩ ወደ ሰማይ አውጥቶ
ከመጋረጃው ውስጥ አስገብቶ ከሥላሴ ዙፋን ፊት አቆመኝና
ሰገድኩለት፡፡ ከዚያ አስቀድሞ በማላውቀው በሌላ ምስጋና
አመሰገንኩት፡፡ ‹ተክለ ሃይማኖት ክፍልህ ከ24ቱ ካህናቶቼ ጋር
ይሁን› የሚል ቃል ከዙፋኑ ውስጥ ወጣ፡፡ የወርቅ ጽና
አምጥተው ሰጡኝና ከእነርሱ ጋር አንድነት አጠንሁ፡፡ ምስጋናዬ
ከምስጋናቸው ጋር ልብሴም እንደልብሳቸው ሆነ፡፡ ፈጣሪዬንም
በሦስትነቱ ተገልጦ አየሁት፡፡ 

❇️በጸሎትህ የሚታመን ሰው ሁሉ
ስለአንተ ይድናል አለኝ…..›› (ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገጽ216-223)
ይህንን ታላቅ በዓል ነው ዛሬ የምናከብረው፡፡ አቡነ
ተክለሃይማኖት እንኳን አንደበታቸው የለበሱትም ልብሳቸውም
ጭምር እግዚአብሔርን በሰው አንደበት እንደሚያመሰግን
በቅዱስ ገድላቸው ላይ ተጽፏል፡፡ አባታችን ለአቡነ ሀብተማርያምም በዚህ ክብራቸው እንዳሉ በአካል
ተገልጠውላቸዋል፡፡ ‹‹አቡነ ተክለሃይማኖት ከእርሳቸው በኋላ
በመንበራቸው ከተሾሙት ከስምንቱ መምህራን ጋር
ለሀብተማርያም ተገለጡላቸው፡፡ እነርሱም ኤልሳዕ፣ ፊሊጶስ፣
ሕዝቅያስ፣ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ዮሐንስ ከማ፣ እንድርያስና
መርሐ ክርስቶስ ናቸው፡፡ እነዚህም መልካቸው እንደ ፀሐይ
ያበራ ልብሳቸው እንደ መብረቅ ያንጸባርቅ ነበር፡፡ አቡነ ተክለ
ሃይማኖትም ልብሳቸው የእሳት ላንቃ የከበበው መልኩም ነጭ
የሆነ የሚያስደንቅ ሆኖ ‹በቅድምና ለነበረ ለአብ በቅድምና
ለነበረ ለወልድ በቅድምና ለነበረ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና
ይገባል› እያለ ልብሳቸው በሰው አንደበት ያመሰግን ነበር፡፡››
ተብሎ ነው በገድለ አቡነ ሀብተማርያም ላይ የተጻፈው፡፡

❇️ከዚህም በኋላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለአቡነ ሀብተማርያም
ከተገለጡላቸው በኋላ ‹‹ልጄ ሀብተማርያም ሆይ! ፈጣሪዬ
እግዚአብሔር ስለወደደህ ብዙ ምርኮ እንዳገኘህ በአንተ ፈጽሞ
ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን የምለምንህ ነገር አለና እሺ በለኝ
ከተቀበርኩበት ቦታ እንድትቀበር ቃል ኪዳን ግባልኝ›› በማለት
በደጃቸው እንዲቀበሩ ቃል አስገብተዋቸዋል፡፡ በዋናነት ግን
ማየት የፈለኩት ጉዳይ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በሞት ካረፉ በኋላአቡነ ሀብተማርያ ደግሞ ገና በሕይወት ሳሉ አባታችን
ሲገለጡላቸው በምን ዓይነት ክብር እንዳዩአቸው ነው፡፡ 

❇️ ‹‹አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ልብሳቸው የእሳት ላንቃ የከበበው መልኩም
ነጭ የሆነ የሚያስደንቅ ሆኖ ‹በቅድምና ለነበረ ለአብ በቅድምና
ለነበረ ለወልድ በቅድምና ለነበረ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና
ይገባል› እያለ ልብሳቸው በሰው አንደበት ያመሰግን ነበር፡፡››
ጌታችን ለአቡነ ተክለሃይማኖት ‹‹ክፍልህ ከሃያ አራቱ ካህናቶቼ
ጋር ይሁን›› ብሎ አስቀድሞ ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋልና አባታችን
ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር ሆነው አንደበታቸውም ብቻ
ሳይሆን የእሳት ላንቃ ያለው ልብሳቸውም የሥሉስ ቅዱስን ስም እያመሰገነ ይኖራል፡፡ 

የአባታችን በረከታቸው ይደርብን ጸሎታቸው ያስምረን፡፡

ህዳር 21 ፅዮን ማርያም

ህዳር 21
ፅዮን ማርያም/የእመቤታችን በዓል/

❇️"ጽዮን" ማለት "ጸወን - አምባ - መጠጊያ" ማለት ነው። አንድም በምሥጢሩ "ማሕደረ አምላክ" ማለት ነው። ጽዮን የሚለው ስም በቁሙ ለቅዱስ ዳዊት ተራራና ለኪዳኑ ጽላት ሲያገለግል በትንቢታዊ ምሥጢሩ ግን ለድንግል ማርያም፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለዘላለማዊት ርስት ያገለግላል። እግዚአብሔር ከዘመነ አበው በኋላ በጊዜው ለእስራኤላውያን ክብር፣ ሞገስ፣ አምባ የምትሆናቸውን ታቦተ ጽዮንን በቅዱስ ሙሴ አማካኝነት ሰጥቷቸዋል። (ዘጸ. ፴፩፥፲፰) ከዚያም ለአምስት መቶ ዓመታት ከእነርሱ ጋር በመሆኗ በፈጣሪና በእነርሱ መካከል ድልድይ ሆና ኖራለች። ከዚያም ባለቤቱ ሲፈቅድ በዘመነ ሳባ በቀዳማዊ ምኒልክ (እብነ መለክ - እብነ ሐኪም) አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ መጥታለች። 

❇️እነሆ በሃገራችን የሦስት ሺህ ዓመት ቆይታዋን ልትደፍን የቀራት ጥቂት ዓመታት ብቻ ናቸው። ጌታ እንደ ፈቀደ ቅዱስ መስቀሉንና ታቦተ ጽዮንን ይዘን ይሔው በቸርነቱ እንኖራለን። ያም ሆኖ ታቦተ ጽዮንን መስረቅ የሚፈልጉ ብዙ ቀሳጢዎች እንዳሉ እናውቃለን። ግን አንጨነቅም። ምክንያቱም የመጣችውም የምትጠበቀውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነውና እንጸልያለን እንጂ አንጨነቅም። በተለያየ ወሬም ራሳችንን አናማጥንም። ባለቤቱ እንድትሔድ ከፈቀደ ደግሞ ማንም ጉልበተኛ አያስቀራትም። 

❇️ታቦተ ጽዮን ብዙ ጊዜ "ጽላተ ኪዳን፣ ታቦተ ሕጉ" እየተባለች ትጠራለች። "ጽሌ" ማለት "ሰሌዳ" እንደ ማለት ሲሆን "ጽላት" ደግሞ በብዙ ቁጥር ነው። "ኪዳን" ደግሞ በፈጣሪና በሰው ልጆች መካከል ያለ "ውል - ስምምነት" ነው። "ታቦት" ማለት "ማሕደር - ማደሪያ" እንደ ማለት ነው። ሕጉ የተጻፈባቸውን ሰላድው "ጽላት" ስንላቸው የጽላቱ ማደሪያ ደግሞ "ታቦት" ይባላል። ጽላት (ታቦትን) ያመጣ ፈጣሪ ነው። በሐዲስ ኪዳንም ምሥጢርና ሐተታ ቢኖረውም ሁለት ቦታ ላይ ስለ ታቦት ተጠቅሶ እናገኛለን። (፪ቆሮ. ፮፥፲፮ ፣ ራእይ. ፲፩፥፲፱) በመጨረሻም ኅዳር ፳፩ ቀን ጽዮን ማርያምን የምናከብርባቸውን ምክንያቶች እንመለከታለን። 

❇️በዚህች ቀን፦ ፩.ታቦተ ጽዮን (ጽላተ ኪዳን) ለሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ መሰጠቷን እናስባለን። ይህ ሲሆንም ቅዱስ ሙሴ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ጾሞ እንደ ተቀበለ ሳንዘነጋ ማለት ነው። (ዘጸ. ፴፩፥፲፰ ፣ ዘዳ. ፱፥፲፱) ፪.በዘመነ ኤሊ ሊቀ ካህናት ታቦተ ጽዮን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሕዛብ (ኢሎፍላውያን) እጅ ተማርካለች። ግን ደግሞ ዳጐንን ቀጥቅጣዋለች። (፩ሳሙ. ፭፥፩) ፫.በዘመነ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በአሚናዳብ ሠረገላ ሁና ከአቢዳራ ቤት ስትመጣ ቅዱሱ ንጉሥ በታላቅ ሐሴት በፊቷ ዘመረ፤ አገለገለ። ምድራዊ ክብሩን እስኪረሳ ድረስ ለታቦተ አምላክ ተቀኘላት። በዚህም ሜልኮል ንቃው ማኅጸኗ ተዘግቷል። (፩ዜና. ፲፭፥፳፭) ሊቃውንትም "ድንግል እመቤታችን ማርያም በትንቢት መነጽር ተመልክቷል።" ብለውናል። "ሰላም ለኪ ማርያም እምነ ዘሰመይናኪ ጸወነ ሶበ እምርሑቅ ርእየ ዘጽላሎትኪ ስነ ለቢሶ ዳዊት ልብሰ ክብር ዘየኀይድ ዓይነ ቅድመ ታቦተ ሕግ ኀለየ ወዓዲ ዘፈነ።" እንዲል። (አርኬ ዘኅዳር ፳፩) ፬.በዘመነ ንጉሥ ሰሎሞን (መፍቀሬ ጥበብ) ግሩም የሆነ ቤተ መቅደስ ተሰርቶላት ስትገባ ታላቅ ሐሴት ተደርጓል። 

❇️እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ንጉሡን አነጋግሯል። (፪ዜና. ፭፥፩ ፣ ፩ነገ. ፰፥፩) ፭.በዚያው ዘመንም በፈጣሪ ፈቃድ ንጉሥ ምኒልክ ቀዳማዊ (ዕብነ ሐኪም) ታቦተ ጽዮንን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል። 
፮.በዘመነ አፄ ባዜን (በ፬ ዓ/ም አካባቢ) አማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያም ወደ አክሱም ጽዮን በስደት መጥታ ገብታለች። በዚህ ጊዜም ሁለቱ ጽዮኖች ሲገናኙ ታላቅ ብርሃን አክሱምን ውጧታል። 

፯.በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ነገሥት ጻድቃን አብርሐ ወአጽብሐ አሥራ ሁለት መቅደሶች ያሏትን ግሩም ቤተ ክርስቲያን ለእመ ብርሃን ሠርተው በዚሁ ቀን በጌታችን ተቀድሷል። 

፰.በተጨማሪም በየጊዜው ማለትም በዮዲት ጉዲትና በግራኝ አማካኝነት ስትፈርስ ወደ ዝዋይ ትሰደድ ነበር። ተመልሳ ስትታነጽም ቅዳሴ ቤቷ የሚከበረው ኅዳር ፳፩ ቀን ነው። በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ይህ በዓል ልዩ ነው። አማናዊት ጽዮን እመ ብርሃን ድንግል ማርያምን እንዲህ እንላታለን። "ቅድስት" የሚለው ቃል ለሁሉም ቅዱሳት እናቶች ቢሰጥም ቅሉ ለድንግል ማርያም ሲሰጥ ግን ትርጉሙ ይለያል። እርሷ "ቅድስተ ቅዱሳን፣ ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቡርክት እምቡሩካን፣ ኅሪት እምኅሩያን" ናትና። ከሰው ልጆችም ሁሉ ትበልጣለች። ይቅርና የሰው ልጅን ንጹሐን መላእክትንም በንጽሕናና በቅድስና ትበልጣቸዋለች። እርሷ እመ ብርሃን፣ የአምላክ እናቱ፣ የሰውነታችን መመኪያ ናትና። እመቤታችንን "ቅድስት" ስንል "ጽንዕት፣ ንጽሕት፣ ክብርት፣ ልዩ" ማለታችን ነው። 

፩."ንጽሕት" ትባላለች። ሌሎች ቅዱሳን ቢነጹ ከገቢር፣ ከነቢብ ኃጢአት ነው እንጂ ከኃልዮ ኃጢአት አይደለም። እርሷ ግን ከነቢብ፣ ከገቢር፣ ከኃልዮ ንጽሕት ናት። "ለመኑ ተውኅቦ ተደንግሎ ኅሊና ለመላእክትሂ ኢተክህሎሙ - ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ከሰው ልጆች ለማን ተሰጠው? ይህስ ለመላእክትም አልተቻላቸውም።" እንዲል። (ተአምረ ማርያም) 

፪."ጽንዕት" እንላታለን። ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው እንጂ በኋላ በጊዜው ተፈትሆ አለባቸው። እመቤታችን ግን ቅድመ ጸኒስ፣ ጊዜ ጸኒስ፣ ድኅረ ጸኒስ፤ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና። "ጽንዕት በድንግልና አልባቲ ሙስና" እንዳላት። (ቅዱስ ያሬድ) ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም "ወትረ ድንግል ማርያም - ማርያም ዘላለማዊት ድንግል ናት።" እንዳለ። (መጽሐፈ ቅዳሴ) ፫.ድንግልን "ክብርት" እንላታለን። 
ሌሎች ሴቶች ቢከብሩ ጻድቃን ሰማዕታትን፣ ነቢያት ሐዋርያትን ወልደው ነው። እመቤታችንን ግን የምናከብራት "ወላዲተ አምላክ - የአምላክ እናቱ" ብለን ነውና። 

፬.እመቤታችንን "ልዩ" እንላታለን። ከእርሷ በቀር እናት ሁና ድንግል፣ እመቤት ሁና አገልጋይ የሆነች፣ በድንግልና ወልዳ ወተትን (ሐሊበ ድንግልናዌን) ያስገኘች ሌላ ሴት የለችምና። 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ታህሳስ 6 ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ

GEDELEKIDUSAN ታህሳስ 3 ቅድስት አርሴማ(ቅዳሴ ቤቷ) ✝እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው።  ✝መድኃኒታችን ክር...