About

Tuesday, November 24, 2020

ህዳር 16 ቅዱስ አቡናፍር ገዳማዊ


ህዳር 16
ቅዱስ አቡናፍር ገዳማዊ

❇️ጻድቁ ተወልዶ ያደገው በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምድረ ግብጽ ነው። ወቅቱ ሥርዓተ መነኮሳት የሚጠበቅበት፣ አበው ባሕታውያን እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝተው የደመቁበት ነበር።

❇️ታላቁ አቡናፍርም ከክርስቲያን ወላጆቹ ተወልዶ፣ በሥርዓት አድጎ፣ መጻሕፍትንም ተምሮ ገና በወጣትነቱ መንኗል። 

❇️ሥርዓተ መነኮሳትን ከአባ ኤስድሮስ ታላቁ አጥንቶ ገዳሙንና መምህሩን እየረዳ ለብዙ ዓመታት በጾምና በጸሎት ኑሯል።
መነኮሳቱ ስለ ትሕትናውና ስለ ታዛዥነቱ ፈጽመው ያከብሩት ነበር። ከዕለታት በአንዱ ቀን አረጋውያን መነኮሳት ጭው ባለ በርሃ ስለሚኖሩ ባሕታውያን ሲጨዋወቱ፣ ሲያደንቋቸውም ሰማ።

❇️እርሱ በዚያ ወቅት ባሕታውያን በበርሃ መኖራቸውን አያውቅም ነበርና ሒዶ መምህሩን አባ ኤስድሮስን ጠየቃቸው። እርሳቸውም "አዎ ልጄ! ከዚህ በጣም ርቅው፣ ንጽሕናቸውን ጠብቀው፣ ከሰውና ከኃጢአት ተለይተው የሚኖሩ ገዳማውያን አሉ።" አሉት።

❇️ቅዱስ አቡናፍር "በዚህ ካሉት መነኮሳትና በበርሃ ካሉት ማን ይበልጣል?" ቢላቸው "እነርሱ በጣም ይበልጣሉ። ዓለም እንኳ ከነ ክብሯ የእግራቸውን ሰኮና አታህልም።" አሉት። ይህንን የሰማው ቅዱስ አባ አቡናፍር ጊዜ አላጠፋም፤ ከመምህሩ ቡራኬ ተቀብሎ ወደ በርሃ ሔደ። ለብዙ ቀናት ከተጓዘ በኋላ አንድ ባሕታዊ አግኝቶ አብሯቸው ተቀመጠ። ከእርሳቸው ዘንድም ሥርዓተ ባሕታውያንን ተምሮ እንደገና ወደ ዋናው በርሃ ጉዞውን ቀጠለ።
ከብዙ ቀናት መንገድ በኋላም አንድ ሠፊ ሜዳ ላይ ደረሰ። አካባቢው የውኃ ጠብታ የማይገኝበት ይቅርና መጠለያ ዛፍ የሣር ዘር እንኳ የሌለበት ወይም በልሳነ አበው "ዋዕየ ፀሐይ የጸናበት፣ ልምላሜ ሣዕር የሌለበት፣ ነቅዐ ማይ የማይገኝበት" ቦታ ነበር። 

❇️በዚህ ቦታ ይቅርና የሰው ልጅ አራዊትም አይኖሩበትም።
ለአባ አቡናፍር ግን ተመራጭ ቦታ ነበር። ቅዱሳኑን ይህ አያሳስባቸውም። ምክንያቱም ለእነርሱ ምግባቸውም፣ ልብሳቸውም ፍቅረ ክርስቶስ ነውና።

❇️አባ አቡናፍር ወደ ፈጣሪ ጸለዩ። በእግዚአብሔር ቸርነት ከጎናቸው አንዲት ዘንባባ (በቀልት) በቀለች። ከእግራቸው ሥርም ጽሩይ ማይ (ንጹሕ ምንጭ) ፈለቀች።
ጻድቁ ተጋድሏቸውን ቀጠሉ፤ ዓመታት አለፉ። ልብሳቸውን ፀሐይና ብርድ ጨርሶት ቅጠል ለበሱ። በዚያ ቦታም የሰው ዘርን ሳያዩ ለስልሳ ዓመታት በተጋድሎ ኖሩ። የሚያርፉበት ጊዜ ሲደርስ እግዚአብሔር አባ በፍኑትዮስን (የባሕታውያንን ዜና የጻፈ አባት ነው።) ላከላቸው።
ቃለ እግዚአብሔርን እየተጨዋወቱ ሳለ የአባ አቡናፍር አካሉ ተለወጠ፤ እንደ እሳትም ነደደ።

❇️አባ በፍኑትዮስም ደነገጠ። ታላቁ ገዳማዊ ግን እጆቻቸውን ዘርግተው ጸለዩ፣ ሰገዱና አማተቡ። ነፍሳቸውም ከሥጋቸው በፍቅር ተለየች። ቅዱሳን መላእክትም በዝማሬና በማኅሌት አሳረጓት። የሚገርመው ደግሞ አባ በፍኑትዮስ ይህን ሲያይ ቆይቶ ዘወር ቢል ዛፏ ወድቃለች፤ ምንጯም ደርቃለች።
አምላከ ቅዱሳን ጸጋውን ክብሩን፣ አእምሮውን፣ ለብዎውን ያሳድርብን። ከወዳጆቹ በረከትም ያሳትፈን።
ኅዳር ፲፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

፩.ቅዱስ አኖሬዎስ ጻድቅ (ንጉሠ ሮም)

፪.አባ ዳንኤል ገዳማዊ

፫.ቅዱስ አውሎጊስ መነኮስ

፬.ቅድስት ጣጡስ ሰማዕት

፭.አባ አቡናፍር ገዳማዊ

፮.ቅዱስ ኪስጦስ ሰማዕት

፯.ቅዱስ ፊቅጦር ምዑዝ

፰.አባ ዮሐንስ መሐሪ
ወርኀዊ በዓላት

፩.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)

፪.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)

፫.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮጵያ

፬.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
"ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ። በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።" (፩ዮሐ ፪፥፲፭-፲፯) 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ስንክሳር 

ህዳር 16 ቅድስት ጣጡስ ሰማዕት



ህዳር 16
ቅድስት ጣጡስ ሰማዕት

❇️በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደዚህች ቅድስት ወጣት መልከ መልካም አልነበረም። 

❇️ቅድስት ጣጡስ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (በዘመነ ሰማዕታት) የነበረች ሮማዊት ክርስቲያን ስትሆን መልኳን ያየ ሁሉ ይደነቅ፣ ይደነግጥም ነበር።

❇️እርሷ ግን ለወንድሞቿ እንቅፋት እንዳትሆን በፊቷ ላይ ዓይነ ርግብ ጣል አድርጋና እንደ ነገሩ ለብሳ ትኖር ነበር። (እንዲህ ነበሩ እናቶቻችን!) ታዲያ በዘመኑ እስክንድሮስ የሚባል አረማዊ "ለጣዖት ስገዱ።" እያለ ክርስቲያኖችን ሲገድል የእርሷ ተራ ደረሰ።
በዐውደ ስምዕ (በምስክርነት አደባባይ) ላይ አቁሟት "ፊቷን ግለጡልኝ።" አለ። ቢገልጧት ከመልኳ ማማር የተነሳ ፈዘዘ። 

❇️እጅግ በመፍጠንም "ላግባሽ?" አላት። "ሙሽርነቴ ሰማያዊ ነውና አይሆንም!" አለችው። ለመናት አልሰማችውም። አስፈራራት አልደነገጠችም።
ከዚያ ግን አስገረፋት። ከአካሏም ስለ ደም ፈንታ ወተት ፈሰሰ። ተበሳጭቶ ለአራዊት ጣላት። እነርሱ ግን ሰገዱላት። በእሳትም ፈተናት። እርሷ ሁሉንም ታግሣ ጸናች። በመጨረሻው ግን በዚህች ቀን አስገደላት። ፈጣሪዋ ክርስቶስም በሰማያዊ አክሊል ከለላት። 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ህዳር 15 ቂርቆስ እየሉጣ


ህዳር 15
ቂርቆስ እየሉጣ

❇️ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካሏት ዐበይት ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ቂርቆስ ነው። በተለይ በዘመነ ሰማዕታት ተነስተው እንደ ከዋክብት ካበሩትም አንዱ ነው።

ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል፦

"መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራል።"

(ማቴ. ፯፥፲፯)
❇️መልካም ዛፍ ቅድስት ኢየሉጣ መልካም ፍሬ ብፁዕ ቂርቆስን አፍርታ ተገኝታለችና ክብር ይገባታል። ቡርክተ ማኅጸንም እንላታለን። የተባረከ ማኅጸኗ የተባረከ ልጅን ለዘጠኝ ወር ተሸክሟልና።

❇️በዚያ ክርስቲያን መሆን መከራ በነበረበት ዘመን ይህንን ደግ ሕፃን እርሷን መስሎ እርሷንም አህሎ እንዲገኝ አስችላለችና። አበው በትውፊት እንዳቆዩልን ከሆነ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዚህች ቀን እናታችን ቅድስት ኢየሉጣ ብጹዕ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስን ወልዳለች።
ፈጣሪ ቢያቆየን የሰማዕትነት ዜናቸውን ጥር ፲፭ ቀን የምንመለከት ነንና የዚያ ሰው እንዲለን እንማጸነዋለን።

❇️አምላከ ሰማዕታት በምሕረቱ ይማረን። በይቅርታው ኃጢአታችን ይተውልን። ከበረከተ ሰማዕታትም ይክፈለን።


ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Sunday, November 22, 2020

ህዳር 14 አባ ዳንኤል


ህዳር 14 አባ ዳንኤል 

††† እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አባ ዳንኤል ወአባ መርትያኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ ዳንኤል ገዳማዊ †††

††† በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ በፋርስ (የአሁኗ ኢራን) ውስጥ ብዙ አስቸጋሪ ነገሥታት ተነስተው ነበር:: ከእነዚህ አንዱ የሆነው የዘመኑ መሪ ክርስቶስን የማያውቅ: መምለኬ ጣኦት የሆነና በጠንቅ ዋዮች ተከቦ የሚኖር ነበር::

❇️እግዚአብሔር ለሁሉም የጥሪ ቀን አለውና ለሕይወት ይጠራው ዘንድ ይህንን ንጉሥ በደዌ ጐበኘው:: የአምላክ ጥሪው አንዳንዴ እንደዚህ: አንዳንዴም እንዲያ ነውና:: ንጉሡ እንደ ታመመ ጠቢባነ ፋርስ ሊያድኑት ሞከሩ:: ግን አልቻሉም:: ሕመሙ እየባሰ ሒዶ ንጉሡ መጻጉዕ ሆነ::
በጊዜው ከመተተኞች ሁሉ በጣም የሚያቀርበው አንድ ጠንቅ-ዋይ በቤተ መንግስት አካባቢ ነበርና ንጉሡ አስጠራው:: "አድነኝ" አለው:: እንደማይችለው ሲያውቅ ዝም አለው:: ንጉሡ መልሶ "ስማ! በቤቴ ውስጥ ከብረህ: ገነህ: የበላሁትን በልተህ: የጠጣሁትን ጠጥተህ የምትኖረው ለዚህ ላትሆነኝ ነው?" ብሎ ተቆጣው::

❇️የንጉሡን ቁጣ ያየው መተተኛ እንደሚገድለው ባወቀ ጊዜ "ንጉሥ ሆይ! እኔኮ አታደርገውም ብዬ ነው እንጂ መድኃኒቱን አውቀዋለሁ:: "ኅሥሥ ሕጻነ ዘዋሕድ ለአቡሁ ወእሙ-ለእናት አባቱ አንድ የሆነ ሕጻን ፈልግ:: እናቱ አስራው አባቱ ይረደውና በደሙ ታጥበህ ትድናለህ" አለው::
መተተኛው እንዲህ ያለው: "ሲሆን ንጉሡ እንዲህ አያደርግም:: ካልሆነ ግን እንዲህ ዓይነት ወላጆች አይገኙም" ብሎ ነው:: ንጉሥ ግን ላስፈልግ ባለ ጊዜ የሚያጣው ነገር የለምና አንድ ልጅ ብቻ ያላቸው ርጉማን ወላጆችን አገኘ::
"1 ሺህ ወቄት ወርቅ ልስጣችሁ እና ልጃችሁን ሰውልኝ" ቢላቸው "እሺ" ብለው ወደ ንጉሡ አደባባይ ወጡ:: በዚያም ሕዝብ ተሰብስቦ: ንጉሡም በዙፋኑ ተቀምጦ ሳለ የ5 ዓመት ሕጻን ልጃቸውን ለገንዘብ ይሰውት ዘንድ ወላጆቹ ቀረቡ:: እናቱ አጥብቃ አሰረችው:: አባቱ ደግሞ ቢላውን አስሎ ቀረበ::
በዚያች ሰዓት ግን ሕጻኑ ወደ ሰማይ ዐይኑን አቅንቶ: እንባው እየፈሰሰ ሲጸልይ ከንፈሮቹ ይንቀሳቀሱ ነበርና ንጉሡ ተመልክቶ ልቡ ራራ:: "እንዳትነኩት" ሲልም ጮኾ ተናገረ:: "ፍቱት" ብሎ ሕጻኑን አስፈትቶ በዙፋኑ ፊት ጠየቀው::

❇️"ምን እያደረክ ነበር?" ቢለው "ለሕጻን ልጅ ጋሻዎቹ ወላጆቹ ናቸው:: በደል ሲያገኘኝ ወደ ወላጆቼ እንዳልጮህ ገዳዮቼ እነሱው ናቸው:: ወደ ዳኛም አቤት እንዳልል አስገዳዩ ዳኛው ራሱ ነው:: ስለዚህም ተስፋየ አንዱ አምላክ እግዚአብሔር ብቻ ነበርና ወደ እርሱ በልቤ ጮህኩ" ሲል መለሰለት:: በዚህ የተገረመው ንጉሡ 1ሺ ወቄት ወርቁን ከወላጆቹ ቀምቶ ለሕጻኑ ሰጥቶ በሰላም አሰናበተው::

❇️ራርቶ ሕጻኑን የፈታው ንጉሥ ሕመሙ ቢጠናበት "የዚህ ሕጻን አምላክ እኔንም እርዳኝ!" ሲል ጮኸ:: በዚህ ጊዜ ጩኸቱ ወደ መንበረ ጸባኦት ደረሰለት:: የእግዚአብሔር ድምጽም ወደ ታላቁ ገዳማዊ ሰው ወደ አባ ዳንኤል መጣ:: "ሒደህ ፈውሰው" አለው::

❇️አባ ዳንኤል ማለት በዘመኑ ከነበሩ ዓበይት ጻድቃን አንዱ ሲሆን መንኖ በርሃ ከገባባት ቀን ጀምሮ በፍጹም ተጸምዶ: በጾም: በጸሎትና በትሕርምት የኖረ አባት ነው:: በዚያች ሰዓትም ጻድቁ በደመና ተጭኖ ከበርሃ ብሔረ ፋርስ ደረሰ:: ከንጉሡም ጋር ተነጋገረ::
ንጉሡ "አድነኝ?" ቢለው "እንድትድን በእውነተኛው አምላክ ማመን አለብህ" አለው:: "ክርስቶስ አምላክ መሆኑን በምን አውቃለሁ?" ብሎ በመጠየቁ ጻድቁ በፊቱ ብዙ ተአምራትን በስመ ክርስቶስ አደረገለት::

❇️ንጉሡም በክርስቶስ አምኖ በተጠመቀ ሰዓት አካሉ ታድሶ: ከደዌው ድኖ ተነሳ:: ሠራዊቱና ሕዝቡም እንዲሁ ተጠመቁ:: አባ ዳንኤልም በደመና ወደ በርሃ ተመልሶ ከተጋድሎ በኋላ በዚህች ቀን ዐርፏል::
††† አባ መርትያኖስ †††
††† ይህ ቅዱስ ሰው የነበረው በዚያው በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን በትውልዱ ሶርያዊ ነው:: ብዙ ጊዜም "መርትያኖስ ካልዕ" (ሁለተኛው) እየተባለ ይጠራል:: ምክንያቱም ቀዳማዊ መርትያኖስ (ታላቁ) ስላሉ ነው::
አባ መርትያኖስ በምድረ ሶርያ ከክርስቲያን ወላጆቹ ጋር አድጐ: የቀናውን የሃይማኖት ትምሕርት ተምሮ: በጐውን ጐዳና መርጧል:: ወቅቱ አርዮሳውያን የበዙበት በመሆኑ ወገኖቹን ይጠቅም ዘንድ ያስተምር ነበር::
በየሥፍራውም እየሔደ ውሉደ አርዮስ (መናፍቃንን) እየተከራከረ ምላሽ ያሳጣቸው ነበር:: በዚህ የተበሳጩ መናፍቃንም አንድ ቀን አሳቻ መንገድ ላይ ጠብቀው በበትር ደበደቡት:: በሞትና በሕይወት መካከልም ትተውት ሔዱ:: እነሱ በዚህ እናስተወዋለን መስሏቸው ነበር::
እርሱ ግን በእግዚአብሔር ኃይል ድኖ እንደ ገና በሰው ፊት ምላሽ አሳጥቶ አሳፈራቸው:: እነርሱም መንገድ ላይ ጠብቀው እየደበደቡ ጐተቱት:: ለብዙ ጊዜም ሲደበድቡት ወደ በርሃ ሸሸ:: በዚያም ገዳማዊ ሰው ሆኖ በጾምና በጸሎት ኖረ:: በዓቱንም በኤርትራ ባሕር ዳርቻ አካባቢ ባለች አንዲት በርሃ አደረገ::

❇️እርሱ ግን በእግዚአብሔር ኃይል ድኖ እንደ ገና በሰው ፊት ምላሽ አሳጥቶ አሳፈራቸው:: እነርሱም መንገድ ላይ ጠብቀው እየደበደቡ ጐተቱት:: ለብዙ ጊዜም ሲደበድቡት ወደ በርሃ ሸሸ:: በዚያም ገዳማዊ ሰው ሆኖ በጾምና በጸሎት ኖረ:: በዓቱንም በኤርትራ ባሕር ዳርቻ አካባቢ ባለች አንዲት በርሃ አደረገ::
እግዚአብሔር ግን ይህንን ሐዋርያዊ ሰው ይፈልገዋልና እንደ ገና ወደ ከተማ የሚመለስበትን ምክንያት ፈጠረ:: በዘመኑ የሃገሩ ጠራክያ ጳጳስ ዐርፎ "ማንን እንሹም" ብለው ሲጨነቁ ፈጣሪ ጻድቁን በኅሊናቸው ሳለባቸው:: እንደ ምንም ብለው ፈልገው አገኙትና አሥረው አምጥተው የጠራክያ ኤጲስ ቆጶስ አደረጉት::
አሁን ስብከተ ወንጌል ሠመረ:: ምክንያቱም አርዮሳውያኑ እርሱ የመንጋው እረኛ ነውና መንካት አይችሉም:: ቢያደርጉትም እጅግ ተወዳጅ ስለ ሆነ ጠቡ ከሕዝብ ጋር ነው:: በዚሁ መንገድ አባ መርትያኖስ ተጋድሎውን ሳይገታ በሠመረ ስብከቱ ብዙዎችን አሳምኖ ወደ መንጋው ቀላቀለ::
ከሠራቸው ብዙ ተአምራትም አንዱን እነሆ:-
*አንዴ ቅዱሱ መንገድ ሲሔድ ጭቅጭቅ ሰምቶ ቀረበ:: በቦታው የተጋደመ ሬሳ አለ:: "ምንድን ነው ችግሩ?" ቢላቸው የሟች ወገኖች ወደ አንድ ጐረምሳ እየጠቆሙ "አላስቀብር አለን" አሉት::

❇️ያንን ጐረምሳ "ለምን?" ቢለው "ብድር ነበረበትና ካልከፈሉኝ አይቀበርም" አለው:: ጻድቁ ፈጣሪውን ጠይቆ ጐረምሳው በአጋጣሚው ሊያታልል መፈለጉን ተረዳ:: "ልጄ! ተወው ይቀበር" ብሎ ቢለምነው "አይሆንም! ምን ታመጣለህ?" አለው::
ያን ጊዜ አባ መርትያኖስ ጸልዮ የሞተውን "በስመ እግዚአብሔር ተነስ" ሲል አዘዘው:: የሞተውም አፈፍ ብሎ ተነሳ:: በዚህ ጊዜ ያ ሐሰተኛ በድንጋጤ ወድቆ ሞተ:: ለዚህኛው በተዘጋጀው መቃብርም ላይ ቀበሩት:: ከሞት የተነሳው ግን በደስታ ከወገኖቹ ጋር ሔደ:: አባ መርትያኖስም ከዘመናት በኋላ በዚህች ቀን ዐርፏል::
††† አምላከ አበው ኃይለ ተአምሩን: ረድኤተ ምሕረቱን አያርቅብን:: ከአባቶቻችን በረከትም ይክፈለን::
††† ኅዳር 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ ዳንኤል ገዳማዊ
2.አባ መርትያኖስ ካልዕ (ዘጠራክያ)
3.አባ ዮሐንስ ዘደብረ ቢዘን (ኤርትራ)
4.ቅድስት ደብረ ቀልሞን
††† ወርሐዊ በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.አባ ስምዖን ገዳማዊ
3.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
4.እናታችን ቅድስት ነሣሒት
5.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
6.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
7.ቅዱስ ሙሴ መርዓዊ

††† "ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ: ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ: ለአንዱም ትንቢትን መናገር: ለአንዱም መናፍስትን መለየት: ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር: ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ይሰጠዋል:: ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርገዋል::" †††
(፩ቆሮ. ፲፪፥፱)

ዝክረ ቅዱሳን 

Saturday, November 21, 2020

ህዳር 13 አዕላፍት መላእክት


ህዳር 13 - አዕላፍ መላእክት

❇️እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን ሲፈጥራቸው በነገድ መቶ በክፍለ ነገድ አሥር አድርጓቸዋል። አቀማመጣቸውንም በሦስት ሰማያትና በአሥር ከተሞች (ዓለማት) አድርጓል። 

❇️መላእክት ያሉባቸው ከተሞች ከታች ወደ ላይ 'ኤረር፣ ራማና ኢዮር' ይባላሉ። አሥሩ ክፍለ ነገድ ደግሞ ከነ አለቆቻቸው ይህንን ይመስላሉ። 

፩.አጋእዝት (የቀድሞ አለቃቸው ሳጥናኤል ሲሆን አሁን የተረፉት በቅዱስ ሚካኤል ሥር ናቸው።) 

፪.ኪሩቤል (አለቃቸው ኪሩብ) 

፫.ሱራፌል (አለቃቸው ሱራፊ) 

፬.ኃይላት (አለቃቸው ሚካኤል) 

፭.አርባብ (አለቃቸው ገብርኤል) 

፮.መናብርት (አለቃቸው ሩፋኤል) 

፯.ሥልጣናት (አለቃቸው ሱርያል) 

፰.መኳንንት (አለቃቸው ሰዳካኤል) 

፱.ሊቃናት (አለቃቸው ሰላታኤል) 

፲.መላእክት (አለቃቸው አናንኤል) ናቸው። 

❇️ከእነዚህም አጋእዝት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌልና ኃይላት መኖሪያቸው በኢዮር (በሦስተኛው ሰማይ) ነው። አርባብ፣ መናብርትና ሥልጣናት ቤታቸው ራማ (ሁለተኛው ሰማይ) ነው። መኳንንት፣ ሊቃናትና መላእክት ደግሞ የሚኖሩት በኤረር (በአንደኛው) ሰማይ ነው። 

❇️መላእክት ተፈጥሯቸው እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ ነው። አይራቡም፣ አይጠሙም፣ አይዋለዱም፣ አይሞቱም። ተፈጥሯቸውም ረቂቅ ነው። ተግባራቸው ዘወትር "ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ" እያሉ ፈጣሪያቸውን ማመስገን ነው። ምግባቸውም ይሔው ነው። ዕረፍት ብሎ ነገርን አያውቁም። "አኮቴቶሙ ዕረፍቶሙ፣ ወዕረፍቶሙ አኮቴቶሙ" እንዲል። በተጨማሪም መልአክ ማለት ተላላኪ (አገልጋይ) ነውና ከፈጣሪ ወደ ሰው ልጆች ለምሕረትም፣ ለመዓትም ይላካሉ። ምሕረትን ያወርዳሉ። ልመናን ያሳርጋሉ። ቅጡ ሲባሉም ይቀጣሉ። ስነ ፍጥረት (አራቱ ወቅቶች) እንዳይዛቡ ይጠብቃሉ። ዘወትርም ስለ ሰው ልጆች ያማልዳሉ። (ዘካ. ፩፥፲፪) ምሥጢርን ይገልጣሉ። (ዳን. ፱፥፳፩) ይረዳሉ። (ኢያ. ፭፥፲፫) እንዳንሰናከል ይጠብቃሉ። (መዝ. ፺፥፲፩) ያድናሉ። (መዝ. ፴፫፥፯) ስግደት ይገባቸዋል። (መሳ. ፲፫፥፳ ፣ ኢያ. ፭፥፲፫ ፣ ራዕ. ፳፪፥፰) በፍርድ ቀንም ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያሉ። (ማቴ. ፳፭፥፴፩) በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ሕይወትና ድኅነት ሲባል ከፈጣሪያቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ሲጠብቁና ፈቃዱን ሲፈጽሙ ይኖራሉ። ይህ ዕለት በሊቃውንት አንደበት "አእላፍ" እየተባለ ይጠራል። በሃይማኖት፣ በተልእኮትና በምስጋና የሚኖሩ ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት በአንድ ላይ የሚከበሩበት ቀን ነው። ምንም እንኳን የጐንደሩን ፊት ሚካኤልን ጨምሮ በአንዳንድ አድባራት ታቦቱ ቢኖርም ሲያነግሡ ተመልክቼ አላውቅም። ሊቃውንቱ በማኅሌት፣ ካህናቱም በቅዳሴ እንደሚያከብሯቸው ግን ይታወቃል። ኅዳር ፲፫ ቀን ዓመታዊ በዓላቸው ነው ማለት በየወሩ በአሥራ ሦስት ወርኀዊ በዓላቸው መሆኑን ያሳያልና ዘወትር ልናስባቸው ይገባል። ቅዱስ መጽሐፍ ቅዱሳን መላእክትን በስምና በማዕረግ እንደሚነግረን ሁሉ በማኅበር (በትዕይንት) አገልግሎታቸውም ይነግረናል። ለምሳሌ፦ ያዕቆብ በረዥም መሰላል ሲወጡና ሲወርዱ ተመልክቷል። (ዘፍ. ፳፰፥፲፪) ኤልሳዕ ለግያዝ አሳይቶታል። (፪ነገ. ፮፥፲፯) ዳንኤል ተመልክቷል። (ዳን. ፯፥፲) በልደት ጊዜ በዝማሬ መገለጣቸውን ቅዱስ ሉቃስ ጽፏል። (ሉቃ. ፪፥፲፫) ዮሐንስ በራዕዩ አይቷቸዋል። (ራዕይ. ፭፥፲፩) ከዚህም በላይ በብዙ የመጻሕፍት ክፍል ተጠቅሰዋል። 

❇️ቅዱሳን መላእክተ ብርሃን፣ መንፈሳውያን፣ ሰባሕያን፣ መዘምራን፣ መተንብላን (አማላጆች) ተብለውም ይጠራሉና ያስቡን ዘንድ ልናስባቸው ይገባል። 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ስንክሳር

Friday, November 20, 2020

ህዳር 12 ሊቀ-መላእክት ቅዱስ ሚካኤል



ህዳር 12 
ሊቀ-መላእክት ቅዱስ ሚካኤል


❇️ቅዱስ ሚካኤል በጥንተ ተፈጥሮ በኢዮር ኃይላት በተባሉት ነገደ መላእክት ተሹሞ ነበር። ሳጥናኤል በካደ ጊዜ እግዚአብሔር ባወቀ አንድም በትሕትናውና ደግነቱ በዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ላይ ሁሉ ተሹሟል። 

❇️ከፍጥረት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የቅዱስ ሚካኤልን ያህል ክብርና ርኅሩኅ የለም። በምልጃውም፣ በረዳትነቱም የታወቀ መልአክ ነው። 

❇️መጽሐፍ "መልአከ ምክሩ ለእግዚአብሔር" ይለዋል። "ወስሙ መስተሣሕልም" ይለዋል። ቂም የሌለው ለምሕረት የሚፋጠን ደግ መልአክ ነውና። በብሉይ ኪዳን በመከራ ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ሞገስ፣ ረዳትና አዳኝ ቢሆናቸው "መጋቤ ብሉይ" ተሰኝቷል። 

❇️እስራኤልን አርባ ዘመን በበርሃ መርቷል፤ መግቧልም። ቅዱስ መጽሐፍ ስለ እርሱ ብዙ ይላል። (ዘፍ. ፵፰፥፲፮ ፣ ኢያ. ፭፥፲፫ ፣ መሳ. ፲፫፥፲፯ ፣ ዳን. ፲፥፳፩ ፤ ፲፪፥፩ ፣ መዝ. ፴፫፥፯ ፣ ራዕይ. ፲፪፥፯) ደስ የሚለው ደግሞ ርኅሩኁ መልአክ ከእመቤታችን ጋር ልዩ ፍቅር አለው። ከእናቷ ማኅጸን ጀምሮ እስከ ዛሬ እነሆ አብሯት አለ። ደስ ብሎት ይታዘዛታል። ማማለድ ሲፈልግም "እመቤቴ ሆይ! ቅደሚ።" ይላታል። ወደ እሳት መጋረጃ አብረው ገብተው ለዓለም ምሕረትን፣ በረከትን ያወርዳሉ።

❇️ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን አስተምህሮ ህዳር 12 ቀን ታላቁ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል በኢዮር ባለችው በአራተኛይቷ ከተማ በሚኖሩት ኃይላት እና በአሥሩ ነገደ መላእክት ላይ አለቃ ሆኖ የተሾመበት ቀን ነው፡፡እግዚአብሔር ሳጥናኤልን በትዕቢቱ ምክንያት ከሥልጣኑ ገፍፎ ወደ ምድር ሲጥለው ቅዱስ ሚካኤል በእርሱ ቦታ በዐሥሩ ከተማ በመቶውም ነገደ መላእክት ላይ ተሹሟል፡፡(ይህን ሁለተኛውን ሹመት ያገኘው በሚያዚያ 2 እንደሆነ አክሲማሮስ በሚባለው የቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ አናገኛለን፡፡)
የቅዱስ ሚካኤል ሹመት በነገደ መላእክት ላይ ብቻ ግን አይደለም ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይም ጭምር ነው ፡፡

❇️ እንዲሁም ይህ ዕለት ቅዱስ ሚካኤል ሕዝበ እስራኤልን ከግብፅ ምድር ጀምሮ ከነዓን እስኪገቡ ድረስ እየመራ እየጠበቀ አብሯቸው በመጓዝ ምድረ ርስት እንዲገቡ ያደረገበት መታሰቢያ ነው:: በዚሁ ዕለት በመጽሐፈ ኢያሱ 5:13 በተጠቀሰው መሠረት ቅዱስ ሚካኤል የተመዘዘ ሰይፍ በመያዝ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ ለኢያሱ ተገልጦለታል:: ኢያሱም አይቶ ሰግዶለታል:: በ እርሱ ላይ? እንዲህ ይላል:- "ሁልግዜ ከ እግዚአብሔር ዙፋን ፊት ቆሞ ለሰው ሁሉ የሚማልድ መልአክ ነው:: የነዌ ልጅ ኢያሱ በንጉሥ የጦር ቤት ወዳጅ፣ አምሳል፣ ክቡር፣ ገናና ሆኖ ያየው ይህ ሚካኤል ነው:: ባየውም ጊዜ ከግርማው የተነሣ ደነገጠ:: በግንባሩም ከምድር ላይ ወድቆ ሰገደለት:: 

❇️ጌታዬ ሆይ ከሰማይ ሠራዊት ወገን አንዱ ከአለቆች አንዱ ነኝ"፡ብሎ ቅዱስ ሚካኤል መለሰለት::

❇️ ተራዳኢው መልአክ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ህዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት እየመራ ወደ ከነአን እንዳስገባቸው በስደት በባዕድ ሃገር የሚሰቃዩትን ወገኖቻችንን እየመራ ወደ ሃገራችን ያስገባልን! ጥላ ከለላ ሆኖ ይጠብቅልን! እኛንም ዛሬ ከተያዝንበት የመለያየት እና የመከፋፈል ባርነት ወደ አንድነት፣ ወደ ሰላም ፣ ወደ ፍቅርና ዘላለማዊ ህይወትን ወደምንወርስበት ወደ ንስሃ ህይወት ይምራን!!! አማላጅነቱ እና ጥበቃው አይለየን!!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ስንክሳር 

Thursday, November 19, 2020

ህዳር 11 ቅድስት ሀና


ህዳር 11 ቅድስት ሀና

"ሐና" ማለት በዕብራይስጥኛው "የእግዚአብሔር ስጦታ" እንደ ማለት ነው። "ሐና፣ ዮሐና፣ ሐናንያ" የሚሉ የዕብራይስጥ ስሞች ትርጉማቸው ተወራራሽ ነው።

❇️የዚህችን ቅድስት እናት ክብሯን መናገር የሚችል የለም። እርሷ ሰማይና ምድርን ለፈጠረ ለእግዚአብሔር ወልድ በሥጋ አያቱ ተብላለችና። አንድም ለሰማይና ለምድር ንግሥት ለድንግል ማርያም ወላጅ እናቷ ናትና። 

❇️ከዓለም ሴቶች ሁሉ የቅድስት ሐና ማኅጸን እንደ ምን ይከብር! በፍጥረት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥንተ አብሶ (የአዳም በደል) መተላለፍ የቀረው በማኅጸነ ሐና ውስጥ ነውና። (ለዚህ አንክሮ ይገባል!) ይስሐቅን የተሸከመ የሣራ ማኅጸን ቡሩክ ከተባለ የቅድስት ሐናማ እንደምን አይባል! ከፍጥረታት ሁሉ እግዚአብሔር ድንግል ማርያምን እንደ መረጠ ሁሉ ቅድስት ሐናንም ለአያትነት መርጧታል። 

❇️ቅድስት ሐና ትውልዷ፣ ነገዷ ከላይ ከቅዱስ አብርሃም፣ ከታች ደግሞ ከነገደ ካህናት ነው። ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ አብርሃም ይስሐቅን፣ ይስሐቅ ያዕቆብን፣ ያዕቆብ ደግሞ ሌዊንና አሥራ አንድ ወንድሞቹን ይወልዳል። ሌዊ ቀዓትን፣ ቀዓት እንበረምን፣ እንበረም አሮን ካህኑን ይወልዳሉ። ቅዱስ አሮን አልዓዛርን፣ አልዓዛር ፊንሐስን እያለ ትውልዱ እስከ ቴክታና በጥሪቃ ይወርዳል። 

❇️ቴክታና በጥሪቃም ልጅ በማጣት ኖረው የእንቦሳዎች፣ የፀሐይና የጨረቃን ምሥጢር ተመልክተው ሄኤሜንን ይወልዳሉ። ሄኤሜን ዴርዴን፣ ዴርዴ ቶናሕን፣ ቶናሕ ሲካርን፣ ሲካርም ሔርሜላን ይወልዳሉ። 

❇️ሔርሜላም ከክርስቶስ ልደት ዘጠና ዓመታት በፊት ማጣት ("ጣ" ጠብቆ ይነበብ) የሚባል ደግ ሰው ከካህናት ወገን አግብታ በስርዓተ ኦሪት ትኖር ነበር። እግዚአብሔር ለዚህች ደግ ሴት የተባረኩ ሦስት ሴቶች ልጆችን ሰጣት። የመጀመሪያዋን "ማርያም" አለቻት። 

❇️ይህቺውም የአረጋዊው ዮሴፍ ሚስትና የቅድስት ሰሎሜ ቡርክት እናት ናት። 
ሁለተኛዋን "ሶፍያ" አለቻት። እርሷም ቅድስት ኤልሳቤጥን (የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን እናት) ወልዳለች። በመጨረሻ የወለዷትን ግን "ሐና" አሏት።

❇️ይህቺውም የፈጣሪ የሥጋ አያቱ፣ የድንግል ማርያምም እናቷ ትሆን ዘንድ የተመረጠችውና ስም አጠራሯ የከበረው ዛሬ የምናከብራት እናት ናት። 

❇️መጽሐፈ ስንክሳርን ስመለከት እንዲህ የሚል ዓረፍተ ነገር አየሁ። "ለዛቲ ቅድስት ኢያዕመርነ ገድላቲሃ ዘትገብሮን በኅቡዕ ከመ ንዝክሮን" ይላል። ትርጉሙም "የዚህችን ቅድስት ገድሏንና ትሩፋቷን እንዳንዘረዝር አላወቅነውም።" እንደ ማለት ነው። የሚገርመው አበው እንዲህ ያሉት ክብሯን መግለጹን አልጠግብ ብለው ነው። 

❇️እኛም በመጠናችን የብጽዕት ሐናን ሕይወት በአጭሩ ቀጥለን እንመልከት። ብጽዕት ሐና ወላጆቿ (ማጣትና ሔርሜላ) ከካህናት ወገን በመሆናቸው ልጆቻቸውን በጥንቃቄ በሥርዓተ ኦሪት እንዳሳደጉ ይታመናል። ቅድስት ሐናንም ለአቅመ ሔዋን እስክትደርስ ድረስ በሕጉ፣ በሥርዓቱ አሳድገዋታል። 

❇️በወቅቱ በፈቃደ እግዚአብሔር ትውልዱ ከነገደ ይሁዳ የሚሆን አንድ ደግ ሰው አጩላት። ይህ ሰው "ኢያቄም" ይባላል። 

❇️አንዳንዴም "ሳዶቅ" ወይም "ዮናኪር" እየተባለ ይጠራል። ቅዱስ ኢያቄም ማለት ክፉ ከአንደበቱ የማይወጣው፣ ምጽዋትን የሚወድ፣ አምላከ እስራኤልን በንጹሕ ልቡ የሚያመልክ ሰው ነበረ። እንደ ኦሪቱ ሥርዓት ሁለቱ (ኢያቄም ወሐና) ከተጋቡ በኋላ ቶሎ መውለድ አልቻሉም። 

❇️ይህ ደግሞ የወቅቱ ከባድ ፈተና ነው። በዘመድ የከበሩ፣ በጠባያቸው የተመሰገኑ፣ መልካምንም የሚሠሩ ሰዎች ልጅ ስለሌላቸው ብቻ "ኅጡአነ በረከት" እየተባሉ ከቤተ እግዚአብሔር ይገፉ፣ በአደባባይም ይነቀፉ ነበር። ምክንያቱም በብሉይ ኪዳን ልጅ አለመውለድ እንደ ኃጢአተኛ ያስቆጥር ነበር። ደግነቱ የወቅቱ ሊቀ ካህናት ቅዱስ ዘካርያስ (የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አባት) እንደ እነሱ ልጅ ያጣ በመሆኑ አብረው ይጽናኑ ነበር። 

❇️የሆነው ሆኖ እኒህ ቡሩካን ሰዎች አምላከ እስራኤልን ከመለመንና ከማመስገን በቀር ሌላ ትርፍ አልተገኘባቸውም። ምንም የሞላቸውና የደላቸው ባይሆኑም ደሃን ሳያጐርሱ አይበሉም ነበር። ቅድስት ሐናን ግን "ቢወልዷት እንጂ አትወልድ።" 
እያሉ ጐረቤቶቿ ይሳለቁባት ነበር። ከማልቀስ በቀር ደግሞ መልስ አልነበራትም። 

❇️አንድ ቀን ግን ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ሲጫወቱ ተመልክታ "ፈጣሪ ሆይ! የእንስሳትን ማኅጸን የምትከፍት ዕፅዋትንም ከባሕርያቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ:: እውነትም ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ስትል አለቀሰች። 
ቅዱስ ኢያቄምም ወደ ተራራ ወጥቶ ለአርባ ቀናት አለቀሰ፤ ተማለለ። ይህ ሲሆን ሁለቱም አርጅተው ነበር። ሐምሌ ሠላሳ ቀን ግን ነጭ ርግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ በማኅጸነ ሐና ስታድር አዩ። ደስ ብሏቸው ለሰባት ቀናት ሱባኤ ይዘው ቅድስት ሐና እመቤታችንን ነሐሴ ሰባት ቀን ጸነሰቻት። ይህም ለእነርሱም ለወገኖቻቸውም ታላቅ ተድላ ሆነ። ብጽዕት ሐና ግን ፈጣሪዋን ታከብረው ዘንድ በጐነትንና ንጽሕናን አበዛች። 

❇️ጸንሳ ሳለም ዕውራንን አበራች፤ ድውያንን ፈወሰች። የጦሊቅ ልጅ በሞተ ጊዜም እያለቀሰች ስትዞረው ጥላዋ ቢያርፍበት አፈፍ ብሎ ተነስቶ፦ "ሰላም ለኪ እሙ ለፀሐየ ጽድቅ" ብሎ ድንግል ማርያምን "ወሰላም ለኪ እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ" ብሎ ቅድስት ሐናን አመስግኗል። ትርጉሙም ድንግልን "የፀሐየ ጽድቅ እናቱ" ሐናን "ሰማይና ምድርን ለፈጠረ አያቱ" ማለት ነው። 

❇️ይህንን ያዩ አይሁድ ቅድስት ሐናን ሊገድሉ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል። ግን መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል አልፈቀደላቸውም። ግንቦት ፩ ቀንም የሰማይና የምድር ንግሥትን ሊባኖስ ተራራ ላይ ወልዳ ሽሙጥን ከሁላችንም አራቀች። ስሟን "ማርያም - የአምላክ ስጦታ" ብለው ሰይመው ለሦስት ዓመታት አሳድገዋታል። የሚገርመው በሦስቱ ዓመታት ውስጥ ቅድስት ሐና ድንግል ማርያምን ከክንዷ አውርዳት አታውቅም ነበር። 

❇️አንድ ጊዜም መላእክት ወስደውባት ፍጹም አልቅሳለች። ኋላ ግን መልሰውላታል። ሌላኛው የሚደንቀው እግዚአብሔር የዓለም ውዱን ስጦታ እመ ብርሃንን ሰጣቸው። እነርሱም ይህችን ውድ ስጦታ ሳይሰስቱ ለፈጣሪ መለሱለት። "እምቅድሜክሙ አልቦ ወእምድኅሬክሙ አልቦ ከመዝ መስዋዕት ለእግዚአብሔር ዘወሃቦ።" እንዲል። ቅድስት ሐና ድንግል ወደ ቤተ መቅደስ ከገባች በኋላ የእናትነት ፍቅሯ እያገበራት ለአምስት ዓመታት እየተመላለሰች ትጐበኛት፤ ትስማት ነበር። 

❇️እመቤታችን ስምንት ዓመት በሞላት ጊዜ ግን የእግዚአብሔር ጥሪ ወደ ቅድስት ሐና ደረሰ። ከክርስቶስ ልደት ስምንት ዓመታት አስቀድማ ብጽዕት እናት ሐና በዚህች ቀን ዐረፈች። ትንሽ ቆይቶም ባለቤቷ ቅዱስ ኢያቄም ተከተላት እኛም ልጆቿ "ብጽዕት ሐና ብጽዓን ይገባሻል!" እያልን እናመስግናት። 

❇️ሊቃውንቱ ለእርሷ እንዲህ ብለዋልና፦ "ሰላም ለኪ ለጸሎተ ኩሉ ምዕራጋ ከመ አስካለ ወይን ዲበ ሐረጋ ሐና ብጽዕት ተፈስሒ እንበለ ንትጋ እስመ ረከብኪ ሞገሰ ወአድማዕኪ ጸጋ እምሔውተ አምላክ ትኩኒ በሥጋ።

❇️" (አርኬ) አምላከ ብጽዕት ሐና በምልጃዋ ከዘላለም እሳት ያድነን። 

❇️ጸጋ በረከቷንም ይክፈለን።

ስንክሳር

Monday, November 16, 2020

ህዳር 8 ፃዲቁ አቡነ ኪሮስ

ህዳር 8 አቡነ ኪሮስ



❇️በዚህች ቀን ከሮም ነገስታት ወገን የሆነው አባ ኪሮስ አረፈ፡፡ አባ ኪሮስ አባቱ ንጉስ ዮናስ እናቱ አንስራ ይባላሉ፡፡ ሀገሩ ሮም ነው፡፡ 

❇️ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ቅዱሳን ነበሩና አቡነ ኪሮስ በታህሳስ 8 ወለዱ፡፡ 

❇️አቡነ ኪሮስ የመጀመሪያ ስሙ ዲላሶር ይባል ነበር፡፡ በኋላ አባቱ ከሞተ በኋላ ሀብቱን ከወንድሙ ተካፍሎ ለድሆች መጽውቶ ዓለምን ንቆ መንኖ ሄደ፡፡ ከአባ በቡነዳ ገዳም ገባ፡፡ በ17 ዓመቱ ሥርዓተ ምነኩስናን ተማረ፡፡ በአባ በቡነዳ እጅ መነኮሰ፡፡ ከዚህ በኋላ በጾም በጸሎት ተወስኖ ኖረ፡፡ስለ ዓለም መከራ ለ40 ዘመን ተኝተው ሲጸልዩ እላያቸው ላይ ሳር በቅሎባቸው ሳለ መላእክት መጥተው ተነስ ቢሉት አዳም የፍጡር ቃል ሰምቶ ወድቀዋል ጌታዬ ድምጹን ያሰማኝ አላቸው በኋላ ኪሩቤል አንስቶ ወስዶ ገነት አሳይተውት ጌታችንም ቃል ኪዳን ሰቷቸዋል፡፡
ቃል ኪዳናቸውም ፡- መካኖች ልጀ የሌላቸው ገድሉን አቅፈው ቢያለቅሱ ጸበሉን ቢጠጡ ስምህን ቢጠሩ፤ የመካኒቱን ማህጸን እከፍታለሁ፡፡ የሚሞትባቸውን እንዳይሞተባቸው አደርጋለሁ፡ በንጹ ገንዘቡ ቂምና በቀል ሳይዝ በህግ በስጋውና በደሙ የጸና ሰው በስምህም በተሠራው ቤተክርስቲያን ጧፍ ዘይት ያበራ መገበሪያ ያመጣውን ልጅ አሰጠዋለሁ፡፡ 
❇️ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ከዚም በኋላ በተወለዱ 270 ዓመቱ ሐምሌ 8 አርፏል፡፡
አባታችን አቡነ ኪሮስ በመዲናችን አዲስ አበባ በኮተቤ መስመር በስማቸው ታላቅ ቤተክርስቲያን አላቸው ሐምሌ 8 ታቦታቸው ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፡፡ 

❇️ልጅ የሌላቸው እናትና እህቶቻችን ገድላቸውን አዝለው ልጅ እንዲሰጧቸው ስለት ይሳላሉ በዓመቱም ልጅ አዝለው መጥተው ስለታቸውን ይከፍላሉ፡፡ ይህንንም በአይናችን አይተን በጆሯችን ሰምተን ይኸው እንመሰክራለን ፡፡ ከቅዱሳን ሁሉ ረድኤታቸውንና በረከታቸውን ይደርብን፡፡

Sunday, November 15, 2020

ህዳር 7 ሠማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ


❇️ህዳር 7 ሠማእቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ 

በዚህች ቀን የፋርስና የልዳ ፀሐይ የተርሴስና የቤሩት ኮከብ የባህርና የየብሰ ብርሃን የጌታችን የመድሐኒታችን የእየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ምስክር የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት ቀን ነው፤ ይህንንም ቀን በመላ ኢትዮጰያ በተለይም በመዲናችን የሚገኘው አንጋፋው ገነተ ጽጌ አራዳ ጊዮርጊስ ታቦተ ህጉ ወጥቶ በደማቁ ይከበራል። ታሪኩ በአጭሩ እንዲህ ነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሚያዚያ 23 ቀን በሰማዕትነት ከሞተ በኃላ አጋልጋዮቹ እጅግ የከበሩ ልብሶችና ያማሩ ሽቶዎች አዘጋጁ በከበረ አገናነዝም ገነዙት በመርከብም ጭነው ወደ ትውልድ አገሩ ልዳ አመጡት ነገር ግን ቤተሰቦቹ በሙሉ ማለትም አባቱ ዘሮንቶስ እናቱ ቴዎብስታ እህቶቹ ማርታና እስያ እንዲሁም አጭተውለት የነበረች እጮኛው ሁሉም ሞተው አገኙዋቸው፤ እንድርያስ የሚባል አጎት ነበረው ስጋውን ተቀበላቸው አገሬው ተሰበሰበ የእየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳስ አባ ቴዎድሮስ ተጠርቶ መጣ ቤተክርስቲያኑን አነጹለት ስጋውንም በዚያ በክብር አኖሩት፤ በዚህች ቀን እጅግ ብዙ የሆነ ድንቅ ታአምራትና ታላላቅ ኃይላት ተደረጉ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤተክርስቲያን ይህንን ቀን ታከብረዋለች። 

❇️ታሪክ ብልሁ ንጉሳችን እምዬ ምኒሊክ አራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንን ሲሰሩ ከዚሁ ከልዳ የቅዱስ ጊዮርጊስ መቃብር ካለበት አፈሩን በመርከብ ከዚያም በበቅሎ አስጭነው አምጥተው ለቤተክርስቲያኑ መሰረት አድርገውታል ቅጥሩን ዙርያውንም ነስንሰውታል ይላል።

❇️ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚከበርባቸው ሚያዚያ 23 እረፍቱ ህዳር 7 ቅዳሴ ቤቱ ጥር 23 ዝርዎተ አጽሙ ናቸው፤ በረከቱን ያድለን።

ምንጭ ገድለ ጊዮርጊስ ምዕራፍ9


Saturday, November 14, 2020

ዓመታዊ በዓላት/ቅዱሳን/

ዓመታዊ በዓላት/ቅዱሳን

”በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ።”ኢሳ.56:

“የቅዱሳን መታሰቢያ ለበረከት ነው።” ምሳ 10፤7

እግዚአብሄር ለቅዱሳን በቸርነቱ ከሰጣቸው በረከት ለመሳተፍ መታሰቢያቸውን ማድረግ የግድ ነው “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል።

ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።”/ማቴ 10፤40-46/

ይላልና ይህም የተባለው በነብያት፣ በጻድቃንና በሌሎችም ቅዱሳን ስም መታሰቢያ ማድረግ እንደሚገባ ለመግለጽ ነው።

መታሰቢያ አንድ ሰው ለሀገሩ በስራው መልካም ስራ፡ ላበረከተው አስተዋፅኦ በጀግንነቱ ታይቶ በዚህች ኃላፊ ጠፊ ዓለም በስሙ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል ፣መንገድ ተሰርቶለት ሲዘከር ይኖራል ፡፡ እሱ ሕይወት ባይኖርም ስሙ ህያው ሆኖ ሲወሳ ይቆያል፡፡ ሰው ሁሉ እንዲያሲታውሰውም ይደረጋል፡፡ የእነዚህ አርበኝነት ምድራዊ ሃላፊ ጠፊ ነው።

የቅዱሳን መታሰቢያ ስንለል ግን ፤ጻድቁን ለማስታወስ በቅዱሱ ስም የሚገነባውን ቤተክርስትያን ፣ የሚከበረውን በአል ነው። ከምድራዊው መታሰቢያ ለየት የሚያደርገው ምድራዊ መታሰቢያቸው ከሰው ሳይሆን ከሰማያዊ አምላክ ፈቃድ በመሆኑ ሥራው ነው። “ምስጋናና ግርማ ነው፤ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል። ለተአምራቱ መታሰቢያን አደረገ፤ እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው።

ለሚፈሩት ምግብን ሰጣቸው፤ ኪዳኑንም ለዘላለም ያስባል።”መዝ.111:3

ዓመታዊ በዓላት

መስከረም
    1. ቅዱስ ራጉኤል (ርእስ አውደ ዓመት)
      -ሊቀ መላእክት ቅዱስ ራጉኤል የተሾመበት ክብረ በዓል እና የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ
    2. ቅዱስ ዮሀንስ /አንገቱ የተቆረጠበት ቀን/
      ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል። ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል፦ "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ። ይላቸዋል። (ሉቃ. ፩፥፮) የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል! እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ ዘጠና የዘካርያስ ደግሞ መቶ ደርሶ ነበር። ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. ፵፥፫ ፣ ሚል. ፫፥፩) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው። ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ። ቅድስቲቷ ግን መስከረም ሃያ ስድስት ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለስድስት ወራት ራሷን ሠወረች። በስድስተኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች። ሁለቱ ቅዱሳት የእኅትማማች ልጆች ናቸው። የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና ዮሐንስ ደግሞ ገና በማኅጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ)። ከዚህ በኋላ ሰኔ ሠላሳ ተወልዶ አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል። ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕፃናትን ሄሮድስ ቁዝ አስፈጀ። ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሄሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕፃን ነገሩት። "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕፃን አለና እሱንም ግደል።" አሉት። እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል። አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕፃኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለሦስት (አምስት) ዓመታት ቆይታለች። ቅዱስ ዮሐንስ አምስት (ሰባት) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች። ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት። ሕፃኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው። እርሷም ስደት ላይ ነበረችና። ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው። ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው። ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ።" አላት። ባርካው አጽናንታውም ተለያዩ። ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በኋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ። ለሃያ አምስት (ሃያ ሦስት) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም። ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም። ከዚህ በኋላ ሠላሳ ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው፦ "ሒድ! የልጄን ጐዳና ጥረግ።" አለው። ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና። (ኢሳ. ፵፥፫ ፣ ሚል. ፫፥፩) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕፃን ነቢየ ልዑል ትሰመይ እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ።" (ሉቃ. ፩፥፸፮) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና። ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ። ያዩት ሁሉ ፈሩት፤ አከበሩት። ቁመቱ ቀጥ ያለ፣ ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ፣ ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ፣ መልኩ የተሟላ፣ ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና። ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሐ ሰበከ። ለንስሐም በርካቶችን አጠመቃቸው። በዚህ አገልግሎት ለስድስት ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ። ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ ምድርን ከነ ልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ።' ብሎ ሲመጣ ደነገጠ፤ የሚገባበትም ጠፋው። "እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ?" አለው። ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ።" አለው፤ አጠመቀው። በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "መጥምቀ መለኮት" ሲባል ይኖራል። ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሄሮድስን ገሰጸው፤ ንጉሡም ተቀይሞ ለሰባት ቀናት አሠረው። በዚህች ቀንም ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሄሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው። እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት። አበው "እምሔሶ ለሄሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሄሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር።" ይላሉ። የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል። (ማቴ. ፫፥፩ ፣ ማር. ፮፥፲፬ ፣ ሉቃ. ፫፥፩ ፣ ዮሐ. ፩፥፮) ርጉም ሄሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በኋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት ደብረ ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች። ቅዱሳንሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት። ከዚሕ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት። በመላው ዓለም ለአሥራ አምስት ዓመታት ስትሰብክ ኑራ በዚህች ቀን ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች። አስማተ-ዮሐንስ መጥምቅ (የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች)  ፩.ነቢይ ፪.ሐዋርያ ፫.ሰማዕት ፬.ጻድቅ ፭.ካሕን ፮.ባሕታዊ/ገዳማዊ ፯.መጥምቀ መለኮት ፰.ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ) ፱.ድንግል ፲.ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ።) ፲፩.ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ) ፲፪.መምሕር ወመገሥጽ ፲፫.ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ) ጌታችን መድኃኔ ዓለም ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ብሎ ይቅር ይበለን። ጸጋውን፣ በረከቱንና ክብሩንም ያሳድርብን።
    10. ፀደኒያ ማርያም
      በዚህች ቀን ቅዱስ ሉቃስ የሣላትና ሥጋን የለበሰችው፣ ከፊቷም ወዝ የሚወጣትና ድውያንን የምታድነው የድንግል ማርያም ሥዕለ አድኅኖ ወደ ጼዴንያ ከወዳጇ ከብጽዕት ማርታ ዘንድ ገብታለች። ቅድስት ማርታ ሃብት ንብረቷን በአብርሃማዊ ተግባር (በምጽዋትና እንግዳን በመቀበል) ላይ ያዋለች ክብርት ሴት ናት። ለእመ ብርሃን ካላት ፍቅር የተነሳ እንቅልፍ አልነበራትም። ተግታ ታገለግላትም ነበር። ሥዕሏን እንዲያመጣላት የላከችው ኢትዮጵያዊው መነኩሴ አባ ቴዎድሮስ የሥዕሏን ተአምራት ባየ ጊዜ ለራሱ ለመውሰድ ሞክሮ ነበር። (እርሱ ምን ያድርግ! እኔም ብሆን ይህንኑ ነበር የማደርገው።) ነገር ግን ከሁሉም በተሻለ የምትወዳት ቅድስት ማርታ ነበረችና በድንቅ ተአምር በዚህች ቀን ወደ ጼዴንያ ገብታለች። ቅድስት ማርታም ያለ ዕረፍት ስታገለግላት ኑራ ዐርፋለች። ይህቺ ክብርት ሥዕለ አድኅኖ የአሁን መገኛ አራት መረጃዎች አሉ፦ ፩.ያለችው ኢትዮጵያ ውስጥ (ደብረ ዘመዳ በሚባል ገዳም) ነው። የመጣችውም ከግማደ መስቀሉ ጋር ነው። ፪.ያለችው በቀደመ ቦታዋ ነው። ፫.የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ወስደዋታል። ፬.በፈጣሪ ጥበብ ተሰውራለች።
    15. ቅዱስ እስጢፋኖስ(የተሾመበት) (ይህ በዓል ከመስቀል በዓል ጋር የሚታሰብ ነው)
      በሕገ ወንጌል (ክርስትና) የመጀመሪያው ሊቀ ዲያቆናትና ቀዳሚው ሰማዕት ይህ ቅዱስ ነው። ቅዱሱ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን አስገራሚ ማንነት ከነበራቸው እሥራኤላውያን አንዱ ነበር። ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ የቅዱስ እስጢፋኖስ ወላጆቹ ስምዖንና ማርያም ይባላሉ። (ሌሎች ናቸው የሚሉም አሉ።) ገና ከልጅነቱ ቁም ነገር ወዳድ የነበረው ቅዱስ በሥርዓተ ኦሪት አድጐ እድሜው ሲደርስ ወደ ት/ቤት ገባ። የወቅቱ ታላቅ መምህር ገማልያል ይባል ነበር። ይህ ሰው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፭፥፴፫ ላይ ተጠቅሷል። በትውፊት ትምህርት ደግሞ ይህ ደግ (ትልቅ) ሰው በርካታ ቅዱሳንን (እስጢፋኖስን፣ ጳውሎስን፣ ናትናኤልን፣ ኒቆዲሞስን...) አስተምሯል። በጌታችን መዋዕለ ስብከት ጊዜም ከፈጣሪያችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እየቀረበ ይጨዋወት ነበር፤ በፍጻሜውም አምኗል። ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ እስጢፋኖስ ከዚህ ምሑር ዘንድ ተምሮ ኦሪቱን ነቢያቱን ጠንቅቆ ወጣ። ወቅቱ አስቸጋሪና ለኃጢአት ሕይወት የተመቸ ቢሆንም ቅዱሱ ግን የመሲህን መምጣት በጸሎትና በተስፋ ይጠባበቅ ነበር። በወቅቱ ደግሞ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀትን እየሰበከ መምጣቱን የተመለከተ ቅዱስ እስጢፋኖስ ነገሩን መረመረ። ከእግዚአብሔር ሆኖ ቢያገኘው የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆነ። ለስድስት ወራትም በትጋት ቅዱስ ዮሐንስን አገለገለ። ለስድስት ወራት ከቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ ከተማረ በኋላ ለስም አጠራሩ ስግደት ይድረሰውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠመቀ። በወቅቱ የተደረገውን ታላቅ ተአምር ልብ ያለው ቅዱስ እስጢፋኖስ መምህሩን ቅዱስ ዮሐንስን እንዲያስረዳው ጠየቀው። "ከእኔ ይልቅ ከፈጣሪው አንደበት ይስማው።" በሚል ላከው። ቅዱሱም ከጌታ ዘንድ ሔዶ እጅ ነስቶ ተማረ። (ሉቃ. ፯፥፲፰) በዚያውም የጌታ ደቀ መዝሙር ሆኖ ቀረ። ጌታም ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ አድርጐት ለአገልግሎት ላከው፤ አጋንንትም ተገዙለት። (ሉቃ. ፲፥፲፯) ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታችን መድኃኔ ዓለም ከዋለበት እየዋለ ካደረበት እያደረ ወንጌልን ተማረ፤ ምሥጢር አስተረጐመ። ጌታ በፈቃዱ ስለ እኛ ሙቶ ከተነሳ በኋላ ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱን በአንብሮ እድ ባርኳል። በዚህ ጊዜም ቅዱሱ እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ቅስናን (ጵጵስናን) ተሹሟል። በበዓለ ሃምሳም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የእርሱን ያህል ልሳን የበዛለት፣ ምሥጢርም የተገለጠለት የለም። በፍጹም ድፍረትም ወንጌልን ይሰብክ ገባ። በመጀመሪያይቱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከማዕድ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ፈተና ሲመጣ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ ሰባቱ ዲያቆናት ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር። አልፎም የስድስቱ ዲያቆናት አለቃ እና የስምንት ሺህው ማኅበር መሪ (አስተዳዳሪ) ሆኗል። ስምንት ሺህ ሰውን ከአጋንንት ፈተና መጠበቅ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለማወቅ አባቶቻችንን መጠየቅ ነው። አንድን ሰው ተቆጣጥሮ ለድኅነት ማብቃት እንኳ እጅግ ፈተና ነው። መጽሐፍ እንደሚል ግን 'መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ማኅደረ እግዚአብሔር' ነውና ለእርሱ ተቻለው። (ሐዋ. ፮፥፭) አንዳንዶቻችን ቅዱስ እስጢፋኖስ 'ሊቀ ዲያቆናት' ሲባል እንደዘመኑ ይመስለን ይሆናል። እርሱ በመጀመሪያ ሐዋርያና ካህን ነው። ዲቁናው ለእርሱ 'በራት ላይ ዳረጐት' ነው እንጂ እንዲሁ ዲያቆን ብቻ አይደለም። ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጌታ ዕርገት በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ስምንት ሺህውን ማኅበር እየመራ ወንጌልን እየሰበከ ቢጋደል ኦሪት 'እጠፋ እጠፋ' ወንጌል ደግሞ 'እሰፋ እሰፋ' አለች። በዚህ ጊዜ 'ክርስትናን ለማጥፋት መፍትሔው ቅዱስ እስጢፋኖስን መግደል ነው።' ብለው አይሁድ በማመናቸው ሊገልድሉት አስበውም አልቀሩ ገደሉት። እርሱ ግን ፊቱ እንደ እግዚአብሔር መልአክ እያበራ ፈጣሪውን በብዙ ነገር መሰለው። በመጨረሻውም ስለ እነሱ ምሕረትን እየለመነ በድንጋይ ወገሩት። ደቀ መዛሙርቱም ታላቅ ለቅሶን እያለቀሱ ቀበሩት። ቅዱስ እስጢፋኖስ ካረፈ ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ በኢየሩሳሌም የሚኖር አንድ ደግ ሰው ነበር። ስሙም ሉክያኖስ ይባል ነበር። በተደጋጋሚ በራእይ ቅዱሱ እየተገለጠ "ሥጋዬን አውጣ።" ይለው ነበርና ሒዶ ለጳጳሱ ነገረው። ጳጳሱም ደስ ብሎት ካህናትና ምዕመናንን ሰብስቦ ወደ አጸደ ገማልያል (የመምህሩ ርስት ነው።) ሔደ። ቦታውንም በቆፈሩ ጊዜ ታላቅ መነዋወጥ ሆነ። መላእክት ሲያጥኑ በጐ መዓዛ ሸተተ። ዝማሬ መላእክትም ተሰማ። ሕዝቡና ጳጳሱም በቅዱስ እስጢፋኖስ ፊት ሰግደው በታላቅ ዝማሬና በሐሴት ዐጽሙን ከዚያ አውጥተው በጽርሐ ጽዮን (በተቀደሰችው ቤት) አኖሩት። እለ እስክንድሮስ የተባለ ደግ ሰውም ቤተ ክርስቲያን አንጾለት ወደዚያ አገቡት። ከአምስት ዓመታት በኋላም እለ እስክንድሮስ ሲያርፍ በሳጥን አድርገው በቅዱሱ ጐን ስለ ፍቅሩ አኖሩት። ሚስቱ ወደ ሃገሯ ቁስጥንጥንያ ስትመለስ የባሏ ሥጋ መስሏት የቅዱስ እስጢፋኖስን ቅዱስ ሥጋ በመርከብ ጭና ወሰደችው። መንገድ ላይ ከሳጥኑ ውስጥ ዝማሬ ሰምታ ብታየው ያመጣችው የቅዱሱን ሥጋ ነው። እጅግ ደስ አላት፤ አምላክ ለዚህ አድሏታልና። እርሷም ወስዳ ለታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ አስረከበች። በከተማውም ታላቅ ሐሴት ተደረገ። ሥጋውን ሊያኖሩት በበቅሎ ጭነው ሲወስዱትም በቅሎዋ በሰው ልሳን ተናግራ ማረፊያውን አሳወቀች። በዚያም ላይ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ታንጾለታል። ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲመቱ ጥቅምት ፲፯፣ ዕረፍቱ ጥር ፩፣ ፍልሠቱ ደግሞ መስከረም ፲፭ ቀን ነው።
    17. ቅዱስ እስጢፋኖስ
    17. በዓለ መስቀል
      ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ቸር አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ከሰማያዊ ክብሩ ወደ ምድር ወርዶ፣ በማኅጸነ ማርያም እግዝእት በኪነ ጥበቡ ተጸንሶ፣ በኅቱም ድንግልና ተወልዶ፣ በፈቃዱ መከራ መስቀልን ተቀብሎ፤ ከግራ ቁመት፣ ከገሃነመ እሳት፣ ከሰይጣን ባርነት፣ ከኃጢአት ቁራኝነትም አድኖናል። እምእቶነ እሳት ዘይነድድ አንገፈነ እንዳለ ሊቁ። ምንም መስቀል በብሉይ የወንጀለኞች መቅጫ ሆኖ ቢቆይም እግዚአብሔር ለዓለም መዳኛነት የመረጠው ነውና ሕብረ ትንቢቶች ሲነገሩለት በብዙ ሕብረ አምሳልም ሲመሰል ኑሯል። ከተፈጥሯችን ጀምሮ ዓለም ራሷ አርአያ ትዕምርተ መስቀል ናት። እግዚአብሔር ለቃየን እንዳይገድሉት ከሰጠው ምልክት (ዘፍ. ፬፥፲፭) ጀምሮ ይስሐቅ ሊሰዋ የተሸከመው እንጨት (ዘፍ. ፳፪፥፮)፣ ቅዱስ ያዕቆብ ያያት የወርቅ መሰላል (ዘፍ. ፳፰፥፲፪)፣ ያዕቆብ የዮሴፍን ልጆች የባረከበት መንገድ (ዘፍ. ፵፰፥፲፬)፣ ባሕረ ኤርትራን የከፈለችው የሙሴ በትር (ዘጸ. ፲፬፥፲፭)፣ የናሱ ዕባብ የተሰቀለበት እንጨት (ዘኁ. ፳፩፥፰) ጨምሮ በርካታ ምሳሌዎች ለቅዱስ መስቀሉ መኖራቸውን መተርጉማን ተናግረዋል። ቅዱስ ዳዊትን የመሰሉ ነቢያት ደግሞ "ለሚፈሩህ ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ምልክትን ሰጠሃቸው" እያሉ መስቀሉን ከርቀት ተመልክተዋል። (መዝ. ፶፱፥፬) በሐዲስ ኪዳን ግን ምሳሌው ገሃድ ሆኖ ጌታ በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥጋውን ቆረሰበት፤ ደሙን አፈሰሰበት፤ ዓለምንም አዳነበት። ስለዚህም "መስቀል ብርሃን ለኩሉ ዓለም መሠረተ ቤተ ክርስቲያን" ተብሎ የሚመሰገን ሆኗል። ቅዱስ ያሬድ ሊቁ አክሎ "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር ያድኅነነ እምጸር" ብሎ ጠላትን ማሳፈሪያ መሆኑን ይነግረናል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ስለ መስቀሉ አምልቶ አጉልቶ አስተምሯል፤ መመኪያችን ነውና። (፩ቆሮ. ፩፥፲፰፣ ገላ. ፮፥፲፬) አንዳንዶቹ እኛን "የተሰቀለውን ትታችኋ።" ይሉናል። የተሰቀለውማ የጌቶች ጌታ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ የአማልክት አምላክ፣ ሁሉ በእጁ የተያዘ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ከኦርቶዶክስ በላይ የሚያመልክ በወዴት አለና። ነገር ግን መስቀሉን ንቆ የተሰቀለውን ማክበር አይቻልምና እኛ ለመስቀሉ የጸጋ ስግደትን እንሰግዳለን፣ እናመሰግነዋለን፣ እናከብረዋለን። "ቤዛ፣ ጽንዕ፣ መድኃኒት፣ ኃይል" እያልንም እንጠራዋለን። አባቶቻችን በመስቀሉ ምርኩዝነት ማዕበለ ኃጢአትን፣ ባሕረ እሳትን ተሻግረዋል። በመስቀሉ ቢመኩ አጋንንትን ድል ነስተዋል፤ ጠላትንም አሳፍረዋል። እኛም በመስቀሉ አምነን፣ ከብረን፣ ገነን እንኖራለን። ተጠቅመንበታልና ከራሳችን ሕይወት በላይ ምስክርን አንፈልግም። መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ካረገ ከዓመታት በኋላ አይሁድ በአንድ ነገር ተቸገሩ። የክርስቶስን ሐዋርያት እያሳደዱ ቢገድሉም ከመስቀሉና ሥጋ ክርስቶስ አርፎበት ከነበረው ጐልጐታ ላይ የሚደረገውን ተአምር ግን መግታት አልተቻላቸውም። መቼም ለተንኮል አያርፉምና ቅዱስ መስቀሉን ሽፍቶቹ ከተሰቀሉባቸው ጋር ደርበው አርቀው ቀበሩት። አካባቢው የጉድፍ መጣያ እንዲሆንም አዋጅ ነገሩ። ለክፋት ሲሆን ተባባሪው ብዙ ነውና ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል ቆሻሻ ቢጥሉበት ተራራ ሆነ። ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ እናታችን ቅድስት እሌኒ (ሔለና) በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት፣ በቅዱስ ኪራኮስ መሪነት፣ በቅዱስ ሚካኤል ረዳትነት ደመራ አስደምራ እጣን አጢሳ መካነ መስቀሉን አገኘች። መስከረም ፲፯ ቀን የተጀመረው ቁፋሮ መጋቢት ፲ ቀን ተጠናቆ ንጹሕ መስቀሉ ወጥቶ ብርሃን በርቷል፤ ሙታን ተነስተዋል። ከአሥር ዓመት በኋላም የመስቀሉ ቤተ መቅደስ ታንጾ መስከረም ፲፯ ቀን ተቀድሷል። ይህ ቅዱስ ዕፀ መስቀልም በደጉ አፄ ዳዊት ዘመን ወደ ሃገራችን መጥቶ በጻድቁ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ አማካኝነት በደብረ ከርቤ (ግሸን ማርያም) ተለብጦ ተቀምጧል።
    21. መናገሻ ማርያም ፡ግሼን ማርያም ፡እንጦጦ ማርያም
      ሃገራችን ኢትዮጵያ ሃገረ እግዚአብሔር መሆኗን ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክራል። (መዝ. ፷፯፣ አሞጽ. ፱፥፯) ሕዝቦቿም የድንግል ማርያምና የቅዱሳን አሥራት ናቸው። የኢትዮጵያውያንን ያህል ድንግል ማርያምን የሚወድ፣ ለቅዱስ መስቀሉ ክብርን የሚሰጥ፣ ቅዱሳንንም የሚዘክር ያለ አይመስለኝም። እመ ብርሃንም ፈጽማ ትወደናለች። ለዚህ ደግሞ ቅንጣት ታህል አንጠራጠርም። ለዓለም እስከ አሁን ድረስ የሁለቱ (የታቦተ ጽዮንና የቅዱስ ዕፀ መስቀሉ) መገኛ እንቆቅልሽ ነው። ለእኛ ግን ሁለቱም ያሉት በቤታችን ውስጥ ነውና እንመሠክራለን። ክብር ለቀደምት አበው ይድረሳቸውና አስፈላጊውን መንፈሳዊና ሥጋዊ ዋጋ ከፍለው ታቦተ ጽዮንን እና ቅዱስ ዕፀ መስቀሉን አምጥተውልናል። በዚህች ዕለትም የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በደብረ ከርቤ ግሼን ማረፉን አስበን በዓልን እናከብራለን። ይኸውም ደጉ አፄ ዳዊት በሠይፈ አርዕድ የተጀመረውን ጥረት ቀጥለው በኃይለ እግዚአብሔር አሕዛብን አስደንግጠው እመ ብርሃንንም በጸሎት ጠየቁ። የአምላክ እናትም ረድታቸው ቅዱስ ዕፀ መስቀሉን ከኩርዓተ ርዕሡ፣ ወንጌላዊ ቅዱስ ሉቃስ ከሳላት ምስለ ፍቁር ወልዳ እና ከብዙ ንዋያተ ቅዱሳት ጋር ተላከላቸው። እርሳቸው መስከረም ፲ ቀን መስቀሉን ተቀብለው በዓሉን በተድላ አክብረው በመንገድ በ፲፫፻፺፮ ዓ/ም ዐርፈዋል። አፄ ዳዊት ካረፉ በኋላ ቅዱስ መስቀሉ ለሠላሳ ዓመታት ተቀምጧል። አፄ ዘርዓ ያዕቆብ እስከ ነገሠበት ፲፬፻፳፮ ዓ/ም ድረስም ከስድስት በላይ ነገሥታት አልፈዋል። አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ከነገሠ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ለቅዱስ መስቀሉ በመካነ ንግሡ ደብረ ብርሃን ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ ሲያስብ ጌታችን በራዕይ "አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል" አለው። ከዚህ ቀን ጀምሮ ደጉ ንጉሥ የመካነ መስቀሉን ቦታ ይፈልግ ዘንድ ከሠራዊቱ ጋር ብዙ ደክሟል። በመጨረሻም በነገሠ በአሥር ዓመታት ግሼንን አምባሰል (ወሎ) ውስጥ አግኝቷት ሐሴትን አድርጓል። ቦታዋ በሥላሴ ፈቃድ በትእምርተ መስቀል የተፈጠረች ናትና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያንን አንጾ መስቀሉን በብረት፣ በመዳብ፣ በናስ፣ በብርና በወርቅ ለብጦ አፈር እንዳይነካውም አድርጐ አኑሮታል። በቦታውም ተአምራት ተደርገዋል። ጻድቁ ዘርዓ ያዕቆብም 'ጤፉት' የሚባል መጽሐፍን ጽፎ እዚያው አኑሮታል። መጽሐፉ እንደሚለው በሃገራችን ያለው ግማደ መስቀሉ (የቀኝ እጁ) ብቻ ሳይሆን ሙሉው ዕፀ መስቀል ነው። ይህ የተደረገውም መስከረም ፳፩ ቀን ነው።
    29. ቅድስት አርሴማ
      እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው። መድኃኒታችን ክርስቶስ በወንጌል እንዳለው "በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትምና።" የሰማዕቷ ሕይወት በፊታችን እንደ ብርሃን ተገልጦ ይታያል። ቅድስት አርሴማ እንደ ልጅ ወላጆቿን በመታዘዝ ደስ ያሰኘች ቡርክት ናት። ቅድስት አርሴማ ይሕ ቀረሽ የማይሏት ውብ ናት። ቅድስት አርሴማ ድንግል ናት። ቅድስት አርሴማ ባሕታዊት ጻድቅ ናት። ቅድስት አርሴማ ኃያል ሰማዕት ናት። ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ አበው በትውፊት እንደ ነገሩን ቅዱስ ጐርጐርዮስ የታላቋ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ ትልቅ ወንድም ነው። በዜና ሰማዕታት ተጽፎ እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት። ፩.ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት። ፪.ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት። ፫.የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት። ቅዱሱ ሦስቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ። ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት። መከራው በጣም ገፍቶ እስከ መጣበት ጊዜ ድረስ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ፣ ይጾሙ፣ ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር። ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስ ጻድቃን የምንላቸው። በኋላ ግን ማኅደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ በመልኳ ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ መቶ ሃያ ሰባት ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ። በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና በጸሎት ለጥቂት ጊዜ ቆዩ፤ ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው። የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለ መኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ። በዚያም በድርጣድስ ቤተ መንግስት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ። በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር። መከራው ግን አለቀቃቸውም። ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው። ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ "ካላገባሁሽ" አላት። ድንግሊቱ ግን "እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ፤ አይሆንም።" አለችው። ሊያስፈራራት ሞከረ። ዓይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው። አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው። እጅግ ስላፈረ አስገረፋት፣ አሰቃያት፣ ዓይኗንም አወጣ። በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት። ከነገር ሁሉ በኋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀዬራቸው። የንጉሡ እንስሳ (አውሬ) መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን ፈጠረ። የንጉሡ እኅት ስታለቅስ በራዕይ "ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን - ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም።" አላቸው። ወዲያውም ቆፍረው አወጡት። ቅዱሱ እንደ ወጣ ዕረፍትን አልፈለገም። ለአሥራ አምስት ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው። ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሒዶ ፈወሳቸው። የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ አጽም በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሌሎች ሰማዕታት አጽም ጋር ወደ ሃገራችን እንደ መጣ አባቶቻችን በትውፊት ነግረውናል። ለዚህም ይመስላል ቡርክቷ እናታችን ከሌሎች ሃገራት ለይታ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ፍቅር ያላት። በዋናው ገዳሟ (ወሎ/ኩላማሶ/ስባ/ ውስጥ የሚገኝ ነው።) ጨምሮ ስሟ በተጠራበት ሁሉ ኃይልን ታደርጋለችና። ነገር ግን ወንድሞቼና እኅቶቼ በቅድስቷ እናታችን ስም የሚነግዱ ሥጋውያን ሰዎች በዝተዋልና እንጠንቀቅ። የሰማዕቷ ክብር ብዙ ነውና በሕልም ላይ ብቻ አንታመን። አባ እንጦንስ እንዳሉት "በሕልሙ የሚታመን ሰው ከንቱ ነውና።" በዚህ ዕለት ከሰማዕቷ ጋር የመንፈስ እናቷን ቅድስት አጋታን ልናስባት ይገባናል። ይህች እናት እመ-ምኔት ስትሆን ቅድስት አርሴማን ታስተምራት፣ ታጸናት፣ ከጐኗም ትቆምላት ነበር። ረሃቧን፣ ጥሟን፣ ስደቷን፣ መከራዋንም ሁሉ አብራት ተሳትፋለች። በፍጻሜውም አብራት ተሰይፋለች።
ጥቅምት
    5. አቡነ ገብረመንፈስ
      ጻድቁ የተወለዱት ግብጽ (ንሒሳ አካባቢ) ሲሆን አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ይባላሉ። አባታችን ገብረ ሕይወት የጻድቃን አለቃ፣ የቅዱሳን የበላይ፣ ተጋድሎአቸውና ድንቅ ተአምራቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ቅዱስ ሰው ናቸው። የጻድቁን ክብር መናገር የሚችል ምን አንደበት ይኖራል? እንደ ምንስ ባለ ብራና ይጻፋል? ዜናቸውንስ ለመስማት የታደለ እንደ ምን ዓይነት ሰው ይሆን? አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለአምስት መቶ ስልሳ ሁለት ዓመታት በዚህች ዓለም ሲኖሩ እህል ያልቀመሱ (ምግባቸው ምስጋና ነውና።)፣ ልብስ ያልለበሱ (ጠጉር አካላቸውን ይሸፍን ነበርና።)፣ ሐዋርያዊ ሆነው ከግብጽ እስከ ኢትዮጵያ ብዙ ነፍሳትን ያዳኑ አባት፣ ሃገራችንን አስምረው አስራት እንድትሆናቸውም ተቀብለው ምድረ ከብድ አካባቢ አርፈዋል። ጻድቁ ገብረ መንፈስ ቅዱስም፣ ገብረ ሕይወትም ይባላሉ። በአምስት መቶ ስልሳ ሁለት ዓመታት ሕይወታቸው እንደ ሐዋርያት ከምድረ ግብጽ እስከ ኢትዮጵያ ወንጌልን ሰብከዋል። በዚህም በሚሊየን (አእላፍ) ለሚቆጠሩ ነፍሳት የድኅነት ምክንያት ሆነዋል። ጻድቁ እንደ ሰማዕታትም ከከሃዲ ሰዎች ብዙ መከራን ተቀብለዋል። እንደ ባሕታውያን ለብዙ መቶ ዓመታት ሰው ሳያዩ ቆይተዋል። ለየት የሚለው ግን የጽድቅ ሕይወታቸው ነው። ከእልፍ አዕላፍ አጋንንት ጋር ተዋግተው ድል ማድረግ ችለዋልና። የንሒሳው ኮከብ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር አላቸው። ስለ ሃገሪቱና ሕዝቧ ፍቅር ሲሉ ለመቶ ዓመታት በደብረ ዝቋላ መከራን ተቀብለዋል። ምሕረትን ሲለምኑ ሥጋቸው አልቆ በአጥንታቸው ቁመው ነበርና ሃገራችን አሥራት ሆና ተሰጠቻቸው። ስለዚህም ነው በሃገሪቱ ውስጥ ከሁለት ሺህ በላይ የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳማትና አድባራት ዛሬም ድረስ ያሉት። በስምንተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ የተወለዱት አባታችን ያረፉት በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ነው። ፍጥረታትን ሁሉ አዝዘው መጋቢት ፭ ቀን ሲያርፉ ግሩማን መላእክት ገንዘው አካላቸውን ሠውረዋል። ሥላሴን የተሸከመ አካላቸው በጐልጐታ ተቀብሯል የሚሉም አሉ። "ሰላም ለመቃብሪከ ዘኢተከሥተ ለባዕድ ከመ መቃብሩ ለሙሴ ወልደ ዮካብድ ዜና መቃብሪከሰ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸማድ ቦ ዘይቤ በኢየሩሳሌም አጸድ ወቦ ዘይቤ ኀለወ በከብድ።" እንዲል። የጻድቁ በዓል ጥቅምት ፭ ቀን የሚከበረው ብዙ ጊዜ መጋቢት ፭ ዐቢይ ጾም ውስጥ ስለሚውል ተውላጥ (ቅያሪ) ሆኖ ነው።
    9. አባ አትናስዮስ (እረፍቱ)
      ይህ ቅዱስ አባት ደግሞ ባለ አስደናቂ ታሪክ ነው። ዜና ሕይወቱ ሲሰማ ጣዕመ ነፍስን ያድላል። ተወልዶ ባደገባት ሶርያ በመናኝነቱ የሚታወቀው ቅዱስ አትናስዮስ ሕይወቱ በጽሙና የተሞላ ነበር። በገዳም ገብቶም በዓት ለይቶ ሰውነቱን ለእግዚአብሔር ሲያስገዛት ዘመናት አልፈዋል። በዘመኑ የአንጾኪያ ፓትርያርክ አርፎ ነበርና ለመንበሯ የሚገባውን ሰው ፍለጋ በየበርሃው ዞሩ። ነገር ግን ከቅዱሱ አትናስዮስ የተሻለ ሰው አላገኙም። እርሱ መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ ለመንጋውም የሚራራ በጐ እረኛ ነውና ይዘውት ወደ ከተማ መጡ። በሃገራቸው ባሕል መሠረት ሊቀ ጳጳሳት የሚሾመው የሁሉም አሕጉረ ስብከት ጳጳሳት ባሉበት ነውና ጠበቁ። ሁሉ ተገኝቶ በሶርያ የሰልቅ ጳጳስ የነበረው አባ እልመፍርያን ግን ዘገየ። ለሃምሳ ቀናት ጠብቀው አባ አትናስዮስን "ፓትርያርክ ዘአንጾኪያ" ብለው ሹመውት ተለያዩ። በሃምሳ አንደኛው ቀን አባ እልመፍርያን ሲደርስ በዓለ ሲመቱ መጠናቀቁን ሲነግሩት ተቆጣ። "እኔ በሌለሁበት የተሾመው አይሠራምና አትናስዮስን ፓትርያርክ ብሎ የሚጠራ ሁሉ የተወገዘ ይሁን።" ብሎ ወደ ሰልቅ ተመለሰ። ቅዱስ አትናስዮስ ይህንን ነገር ሲሰማ ፈጽሞ አዘነ። ከቀድሞውም አስገድደውት እንጂ እርሱ ሹመቱን ፈልጐ አልመጣም። ልክ በዘመኑ እንደምንመለከተው ቅዱሱ መልሶ ማውገዝ ይችላል። ለዚያውም በሥልጣን ይበልጠዋል። ቅዱሱ ግን ለግል ክብሩ ሲል ቤተ ክርስቲያንና ምዕመናን ሲከፈሉ ማየትን አልወደደም። ደቀ መዝሙሩን ጠራውና "ልጄ! እሺ በለኝ ነፍሴ ትመርቅሃለች። እኔ ለአንድ ዓመት መንገድ ስለምወጣ አንተ በእኔ ፈንታ እዘዝ፣ እሠር፣ ፍታ። ሕዝቡ ከጠየቁህ ወደ ገዳም ሔዷል በላቸው።" ብሎት ከመንበረ ጵጵስናው ወጣ። እጅግ የነተበ የበርሃ ልብሱን ለብሶ ለአንድ ቀን በእግሩ ተጉዞ ሰልቅ ውስጥ ደረሰ። ወደ አባ እልመፍርያን ዘንድ ገብቶም በፊቱ ሰገደ። "አባቴ! ነዳይ ነኝና አስጠጋኝ?" ብሎ ለመነው። አባ እልመፍርያንም ከመነኮሳቱ ጋር እንዲኖር ፈቀደለት። ቅዱስ አትናስዮስ ፓትርያርክ ሲሆን ወገቡን ታጥቆ ያገለግል ገባ። ውኃ ይቀዳል፣ ዳቦ ይጋግራል፣ ቤቶችን ይጠርጋል፣ መጸዳጃ ቤቶችን ያጸዳል፣ የመነኮሳቱን እግር ያጥባል። በዚህ ሁሉ ላበቱ እየተንጠፈጠፈ በሰውነቱ ላይ ይወርድ ነበር። አባቶች ትጋቱንና ትሕትናውን ሲያዩ ለዲቁና አጩት። ጳጳሱም ጠርቶ "ዲቁና ልሹምህ።" ቢለው ፓትርያርኩ ቅዱስ አትናስዮስ አለቀሰ። "ምነው?" ቢለው "አባቴ! በነውር ተይዞብኝ ነው እንጂ ዲቁናስ አለኝ።" አለው። አሁንም ለሰባት ወራት በዲቁና አገልግሎት ቆይቶ ቅስና ተሾም ቢሉት እንደ ቀደመው እያለቀሰ መለሰላቸው። ልክ በዓመቱ ግን ለአንዲት ሃገረ ስብከት ጳጳስ ያደርጉት ዘንድ በዕለተ እሑድ ተሰበሰቡ። ቅዱስ አትናስዮስ እንዲተውት እያለቀሰ ለመናቸው። "ለሹመቱ ትገባለህ።" ብለው ግድ ሲሉት ግን "ምሥጢር ልንገራችሁ።" ብሎ "ፓትርያርኩ አትናስዮስ ይሏችኋል እኮ እኔ ነኝ።" አላቸው። የሰማውን ነገር ማመን ያቃተው አባ እልመፍርያን ደንግጦ በግንባሩ መሬት ላይ ወደቀ፤ እየተንከባለለም አለቀሰ። "ወዬው ለእኔ! ጌታዬን አትናስዮስን እንደ አገልጋይ ላዘዝኩ።" እያለም ተማለለ። በአካባቢው የነበሩ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መነኮሳትና ምዕመናንም ከቅዱስ አትናስዮስ የትሕትና ሥራ የተነሳ ፈጽመው አደነቁ። መንበረ ጵጵስና አምጥተው እየዘመሩ ተሸክመውት ዞሩ። ቅዳሴንም ቀድሶ ሥጋውን ደሙን አቀብሏቸው ታላቅ ደስታ ሆነ። በማግስቱም ቅዱሱን ባማረች በቅሎ ላይ አስቀምጠው አባ እልመፍርያን በእግሩ (በራሱ ፈቃድ) እየተጓዘ በታላቅ ዝማሬ አንጾኪያ ደረሱ። በዚያም ታላቅ የአንድነት በዓል ተከበረ። ታላቁ እረኛ ቅዱስ አትናስዮስ እነሆ በዚህ መንገድ ቤተ ክርስቲያንን ለሁለት ከመከፈል ታደጋት። ቅዱሱ ሲጋደል ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል። ቸሩ አምላክ እንዲህ ለመንጋው የሚራሩ እረኞችን አይንሳን። ከሐዋርያው፣ ከሰማዕቱና ከደጉ ፓትርያርክም ጸጋ በረከትን ይክፈለን።
    12. አባ ዲሜጥሮስ (እረፍቱ)
      ቅዱስ ድሜጥሮስ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተወለደ በመንፈሳዊ ለዛ ከአጐቱ ደማስቆስ ጋር ያደገ የዘመኑ ደግ ሰው ነበር። በዘመኑ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት ያለቁበት በመሆኑ ቤተሰቦቹ የአጎቱን ልጅ ልዕልተ ወይንን እንዲያገባ ግድ አሉት። ቅዱስ ድሜጥሮስ የእነርሱን ፈቃድ ለመፈፀም ጋብቻውን በተክሊል ፈፀመ። የፈጣሪውን ፈቃድ ለመፈፀም ደግሞ ከቅድስት እናታችን ልዕልተ ወይን ጋር ተስማምተው ለአርባ ስምንት ዓመታት በአንድ አልጋ ላይ እየተኙ አንድ ምንጣፍና ልብስ እየተጋሩ በድንግልና ኑረዋል። ቅዱስ ሚካኤልም ስለ ክብራቸው ከመካከላቸው ሆኖ ቀኝ ክንፉን ለእርሱ ግራ ክንፉን ለእርሷ ያለብሳቸው ነበር። ከአርባ ስምንት ዓመታት በኋላ ቅዱስ ድሜጥሮስ የግብጽ አሥራ ሁለተኛ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ተሹሞ ምሥጢር በዝቶለት ባሕረ ሐሳብን ጽፎ ሠርቷል። ሰይጣን በሰዎች አድሮ ቅዱሱን ሚስት አለው በሚል ቤተ ክርስቲያን ላይ ሁከት በመፈጠሩ ቅዱስ ድሜጥሮስ በመልአኩ ትእዛዝ ሕዝቡን ሰብስቦ እሳት አስነድዶ ከቅድስት ልዕልተ ወይን ጋር እሳቱ ውስጥ ገብተው ለረዥም ሰዓት ጸልየዋል። ሕዝቡም ይህን ተአምር አይተው የቅዱሳኑን ንጽሕና ተረድተው ማረን ብለው በፍቅር ተለያዩ። መጋቢት ፲፪ ቀን ድንግልናው ተገልጧል። ቅዱስ ድሜጥሮስና እናታችን ልዕልተ ወይን ተረፈ ዘመናቸውን በቅድስና አሳልፈዋል። በተለይ ሊቀ ጳጳሳቱ ድሜጥሮስ ብዙ ድርሳናትን ደርሷል። እነ አርጌንስ (Origen) ና ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ (Clement of Alexandria) የመሰሉ መናፍቃንንም አውግዟል። ከጣዕመ ስብከቱም የተነሳ አርጅቶ እንኳ ምዕመናን እየተሰበሰቡ ይማሩ ነበር። በአልጋ ተሸክመውትም ይባርካቸው ነበር። ቅዱሱ በመቶ ሰባት ዓመቱ ያረፈው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ በዚህች ቀን ነው። አምላከ ዳዊት ፍቅሩን፣ አምላከ ማቴዎስ አገልግሎቱን፣ አምላከ ድሜጥሮስ ንጽሕናውን ያሳድርብን። ጸጋ በረከታቸውን ደግሞ ያትረፍርፍልን
    13. አባ ዘካርያስ(እረፍቱ)
      ይህ ታላቅ ጻድቅ ባለ ጥዑም ዜና ነው። ወላጆቹ እሱንና አንዲት ሴትን ከወለዱ በኋላ አባቱ መንኖ ገዳም ገባ። ከዘመናት በኋላ ረሃብ በሃገሩ ሲገባ እናቱ ወስዳ ለአባቱ ሰጠችው። ይህን ጊዜ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር። በገዳም ከአባቱ ጋር ሲኖር ከመልኩ ማማር የተነሳ አባቶች መነኮሳት "ይህ ልጅ ይህን መልክ ይዞ እንዴት መናኝ መሆን ይችላል!" ሲሉ ሰማ። በሌሊትም ተነስቶ በሕፃን አንደበቱ "ጌታዬ! መልኬ ካንተ ፍቅር ከሚለየኝ መልኬን አጠፋዋለሁ።" አለ። ከገዳሙም ጠፋ። አባትም በጣም አዘነ። ከአርባ ቀናት በኋላ ግን ሊያዩት የሚያሰቅቅ አካሉ ሁሉ የቆሳሰለ አንድ ነዳይ ሕፃን መጥቶ ወደ ገዳሙ ተጠጋ። ይህ ሕፃን በጾም፣ በጸሎትና በትሕትና ተጠምዶ ለአርባ አምስት ዓመታት አገለገለ። በነዚህ ዓመታት ሁሉ ይህ አካሉ የተለወጠ ሕፃን ቅዱስ ዘካርያስ መሆኑን ያወቀ የለም። እንዲህ የቆሰለውም አሲድነት ካለው የጉድጓድ ውኃ ውስጥ ሰጥሞ ለአርባ ቀናት በመጸለዩ ነው። በመጨረሻ ግን አባቱ በምልክት ለይቶት አለቀሰ። "ልጄ! አንተ ለእኔ አባቴ ነህ።" ብሎታል። አበው መነኮሳትም ተሰብስበው እጅ ነስተውታል። በሰባት ዓመቱ የመነነው አባ ዘካርያስ በሃምሳ ሁለት ዓመቱ በዚህች ቀን ዐርፎ በክብር ተቀብሯል። አምላከ አፈ ወርቅ ዮሐንስ የድንግል እመ ብርሃንን ፍቅሯንና ውዳሴዋን ይግለጽልን። ከአባቶቻችን ክብርና በረከትንም ያሳትፈን።
    14. አቡነ አረጋዊ (የተሰወሩበት)
      በሃገራችን ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ እኒህ ጻድቅ ናቸው። ጻድቁ የተወለዱት በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው "ንጉሥ ይስሐቅ" እና "ቅድስት እድና" ይባላሉ። የተወለዱበት አካባቢም ሮም ነው። ስማቸው ብዙ ዓይነት ነው። ወላጆቻቸው "ዘሚካኤል" ሲሏቸው በበርሃ "ገብረ አምላክ" ተብለዋል። በኢትዮጵያ ደግሞ "አረጋዊ" ይባላሉ። አቡነ አረጋዊ ምንም የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም በልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው ነበርና ጠፍተው ገዳም ገቡ። በዚያም በገዳመ ዳውናስ (ግብጽ) የታላቁ ቅዱስ ጳኩሚስ ደቀ መዝሙር ሆነው ከነ አባ ቴዎድሮስ ጋር ሥርዓተ መነኮሳትን ተምረዋል። ከመነኮሱ ከዓመታት በኋላም ወደ ሃገራቸው ሮም ተመልሰው በማስተማር ሰባት ያህል የቤተ መንግሥት ሰዎችን ወደ ምናኔ ማርከዋል። "የት ልሒድ?" ብለው ሲያስቡም ቅዱስ መልአክ በክንፉ ጭኖ ወስዶ ኢትዮጵያን አሳያቸው። ተመልሰውም ለስምንት ባልንጀሮቻቸው "ሃገርስ ባሳየኋችሁ! ሐዋርያ ሳያስተምራት በሕጉ በሥርዓቱ ጸንታ የምትኖር።" ብለው ከስምንቱ ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጡ። በዚህ ጊዜም እናታቸው ቅድስት እድናና ደቀ መዝሙራቸው አባ ማትያስ አብረው ነበሩ። ወደ ሃገራችን የመጡ በአራት መቶ ሰባዎቹ አካባቢ ሲሆን አልዓሜዳ በክብር ተቀብሏቸዋል። በቤተ ቀጢን (አክሱም) ተቀምጠውም መጻሕፍትን እየተረጐሙ ወንጌልን እየሰበኩ ቆይተዋል። ለሥራ በተለያዩ ጊዜም አቡነ አረጋዊ በዓት ፍለጋ ብዙ ደክመዋል። በመጨረሻ ግን ደብረ ዳሞን (ደብረ ሃሌ ሉያን) አይተው ወደዷት። የሚወጡበት ቢያጡም ጅራቱ ስድሳ ክንድ የሚያህል ዘንዶ ተሸክሞ ከላይ አድርሷቸዋል። እንደ ወጡም "ሃሌ ሉያ ለአብ፣ ሃሌ ሉያ ለወልድ፣ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ" ብለው ቢያመሰግኑ ከሰማይ ሕብስት ወርዶላቸው ተመግበዋል። በዚህም ቦታዋ "ደብረ ሃሌ ሉያ" ተብላለች። ጻድቁ ቦታውን ከገደሙ በኋላ ከተለያየ ቦታ መጥተው ስድስት ሺህ ያህል ሰዎች በእጃቸው መንኩሰዋል። ምናኔን በማስፋፋታቸውና ሥርዓቱን በማስተማራቸውም "አቡሆሙ ለመነኮሳት ዘኢትዮጵያ - የኢትዮጵያ መነኮሳት አባት" ይባላሉ። አቡነ አረጋዊ በሕይወታቸው ከተጋድሎ ባሻገር በወንጌል አገልግሎትና መጻሕፍትን በማዘጋጀትም ደክመዋል። ቅዱስ ያሬድና አፄ ገብረ መስቀልም ወዳጆቻቸው ነበሩ። በተራራው ግርጌ ያለችውን ኪዳነ ምሕረትን ለሴቶች ሲገድሟት ቀዳሚዋ መነኮስ እናታቸው "ንግሥት እድና" ሁናለች። ጻድቁ ንጹሕ ሕይወታቸውን ፈጽመው በተወለዱ በዘጠና ዘጠኝ ዓመታቸው በዚህ ቀን በገዳሙ በስተምሥራቅ አካባቢ ተሰውረው ብሔረ ሕያዋን ገብተዋል። ጌታም አሥራ አምስት ትውልድን የሚያስምር የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል።
    14. ቅዱስ ገብረክርስቶስ መርዓዊ (እረፍቱ)
      ሙሽራው ገብረ ክርስቶስ በሃገራቸው ልሳን "አብደል መሲሕ" ይባላል። ለቅዱስ ሙሴና ለሌሎችም ሙሽርነትን ትቶ መመነንን ያስተማረ እርሱ ነው። አባቱ ታላቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ሲሆን እናቱ መርኬዛ ትባላለች። የጻድቃን ትውልድ የተባረከ ነውና (መዝ. ፻፲፩፥፩) ታላቁ አቡነ ኪሮስ አጐቱ ናቸው። ስለዚህ ቅዱስ ምን እነግራችኋለሁ! ሙሉ ታሪኩ ከቅዱስ ሙሴ ጋር ተመሳሳይ ነውና። ልዩነቱ ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ በገዛ ፍቃዱ አካሉ በመቁሰሉ ምክንያት ሰዎች ሊለዩት አልቻሉም ነበር። በአርማንያ በእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ደጅ ለአሥራ አምስት ዓመታት ሲጋደል ወደ ወላጆቹ ሃገር ቁስጥንጥንያ ተመልሶ ለአሥራ አምስት ዓመታት ተፈትኗል። ምንም የንጉሥ ልጅ ቢሆንም የአባቱ ባሮች በጥፊ ይመቱት፣ ጽሕሙን (ጺሙን) ይነጩት፣ ቆሻሻ ይደፉበትም ነበር። ለእርሱ ወዳጆቹ ውሾች ነበሩ። በአባቱ ደጅ ለአሥራ አምስት ዓመታት መከራን ከተቀበለ በኋላ "ጌታ ሆይ! የአባቴ አገልጋዮች በእኔ ላይ ያደረጉትን ሁሉ በደል አድርገህ አትቁጠርባቸው።" አለ። በዚህች ቀን ሲያርፍም ጌታችን ሰባቱን ሊቃነ መላእክት ከነ ሠራዊታቸው አስከትሎ ወርዶ በክብር አሳርጐታል። አጠቃላይ የገድል ዓመታቱም ሠላሳ ናቸው። አምላከ ቅዱሳን ለእነርሱ ካደለው ፍቅራቸው ለእኛም አይንሳን። በረከታቸውንም ያብዛልን
    14. ኢትዮጰያዊውን ጀንደረባ ያጠመቀውን ዲያቆኑ ፊሊጶስ (እረፍቱ)
      በዘመነ ሐዋርያት በዚህ ስም የሚጠሩ አባቶች ሁለት ነበሩ። አንደኛው ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሲቆጠር ዛሬ የምናከብረው ደግሞ ከሰባ ሁለቱ አርድእት ይቆጠራል። ቅዱስ ፊልጶስ ያደገው የኖረውም በቂሣርያ አካባቢ ሲሆን ባለ ትዳር የልጆች አባት ነው። ጌታ ሲጠራው እንኳ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። ከጌታ ሕማማት በፊት ተልኮ አስተምሯል። ከበዓለ ሃምሳ በኋላም ሰባቱ ዲያቆናት ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር። (ሐዋ. ፮) በቅዱስ እስጢፋኖስ መሪነትም ስምንት ሺህውን ማኅበር አገልግሏል። ቅዱስ እስጢፋኖስ ተገድሎ ስምንት ሺህው ማኅበር ሲበተንም ቅዱስ ፊልጶስ አራቱን ልጆቹን አስከትሎ ወደ ሰማርያ ወርዷል። በዚያም መሠሪ ስምዖንን ጨምሮ የሃገሪቱን ሰዎች አሳምኖ አጥምቋል። መቼም ቢሆን እኛ ኢትዮጵያውያን የማንዘነጋው ግን ጃንደረባውን ባኮስን ማጥመቁን እና ለሃገራችን የወንጌልን ብርሃን መላኩን ነው። ጃንደረባው ቅዱስ ባኮስ ከጉዞ መልስ ትንቢተ ኢሳይያስን (ኢሳ. ፶፫) ሲያነብ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ቀርቦ ምሥጢረ ሥጋዌን አስረድቶታል። ሠረገላውም ቁሞለት ቅዱስ ባኮስን አጥምቆት ተነጥቆ ሔዷል። (ሐዋ. ፰፥፳፮) ቅዱስ ፊልጶስ በቀሪ ዘመኑ ከተባረኩ አራት ደናግል ልጆቹ ጋር ሲሰብክ ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል።
    17. ቅዱስ እስጢፋኖስ(የተሸመበት)
      በሕገ ወንጌል (ክርስትና) የመጀመሪያው ሊቀ ዲያቆናትና ቀዳሚው ሰማዕት ይህ ቅዱስ ነው። ቅዱሱ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን አስገራሚ ማንነት ከነበራቸው እስራኤላውያን አንዱ ነበር። ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ የቅዱስ እስጢፋኖስ ወላጆቹ ስምዖንና ማርያም ይባላሉ። (ሌሎች ናቸው የሚሉም አሉ።) ገና ከልጅነቱ ቁም ነገር ወዳድ የነበረው ቅዱስ በሥርዓተ ኦሪት አድጐ እድሜው ሲደርስ ወደ ትምህርት ቤት ገባ። የወቅቱ ታላቅ መምህር ገማልያል ይባል ነበር። ይህ ሰው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፭፥፴፫ ላይ ተጠቅሷል። በትውፊት ትምህርት ደግሞ ይህ ደግ (ትልቅ) ሰው በርካታ ቅዱሳንን (እስጢፋኖስን፣ ጳውሎስን፣ ናትናኤልን፣ ኒቆዲሞስን.....) አስተምሯል። በጌታችን መዋዕለ ስብከት ጊዜም ከፈጣሪያችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እየቀረበ ይጨዋወት ነበር። በፍጻሜውም አምኗል። ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ እስጢፋኖስ ከዚህ ምሑር ዘንድ ተምሮ ኦሪቱን ነቢያቱን ጠንቅቆ ወጣ። ወቅቱ አስቸጋሪና ለኃጢአት ሕይወት የተመቸ ቢሆንም ቅዱሱ ግን የመሲህን መምጣት በጸሎትና በተስፋ ይጠባበቅ ነበር። በወቅቱ ደግሞ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀትን እየሰበከ መምጣቱን የተመለከተ ቅዱስ እስጢፋኖስ ነገሩን መረመረ። ከእግዚአብሔር ሆኖ ቢያገኘው የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆነ። ለስድስት ወራትም በትጋት ቅዱስ ዮሐንስን አገለገለ። ለስድስት ወራት ከቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ ከተማረ በኋላ ለስም አጠራሩ ስግደት ይድረሰውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠመቀ። በወቅቱ የተደረገውን ታላቅ ተአምር ልብ ያለው ቅዱስ እስጢፋኖስ መምህሩን ቅዱስ ዮሐንስን እንዲያስረዳው ጠየቀው። "ከእኔ ይልቅ ከፈጣሪው አንደበት ይስማው።" በሚል ላከው። ቅዱሱም ከጌታ ዘንድ ሔዶ እጅ ነስቶ ተማረ። (ሉቃ. ፯፥፲፰) በዚያውም የጌታ ደቀ መዝሙር ሆኖ ቀረ። ጌታም ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ አድርጐት ለአገልግሎት ላከው። አጋንንትም ተገዙለት። (ሉቃ. ፲፥፲፯) ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታችን መድኃኔ ዓለም ከዋለበት እየዋለ ካደረበት እያደረ ወንጌልን ተማረ። ምሥጢር አስተረጐመ። ጌታ በፈቃዱ ስለ እኛ ሙቶ ከተነሳ በኋላ ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱን በአንብሮ እድ ባርኳል። በዚህ ጊዜም ቅዱሱ እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ቅስናን (ጵጵስናን) ተሹሟል። በበዓለ ሃምሳም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የእርሱን ያህል ልሳን የበዛለት ምሥጢርም የተገለጠለት የለም። በፍጹም ድፍረትም ወንጌልን ይሰብክ ገባ። በመጀመሪያይቱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከማዕድ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ፈተና ሲመጣ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ ሰባት ዲያቆናት ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር:: አልፎም የስድስቱ ዲያቆናት አለቃ እና የስምንት ሺህው ማኅበር መሪ (አስተዳዳሪ) ሆኗል። ስምንት ሺህ ሰውን ከአጋንንት ፈተና መጠበቅ ምን ያህል ከባድ እንደ ሆነ ለማወቅ አባቶቻችንን መጠየቅ ነው። አንድን ሰው ተቆጣጥሮ ለድኅነት ማብቃት እንኳ እጅግ ፈተና ነው። መጽሐፍ እንደሚል ግን "መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ማሕደረ እግዚአብሔር" ነውና ለእርሱ ተቻለው። (ሐዋ. ፮፥፭) አንዳንዶቻችን ቅዱስ እስጢፋኖስ "ሊቀ ዲያቆናት" ሲባል እንደ ዘመኑ ይመስለን ይሆናል። እርሱ በመጀመሪያ ሐዋርያና ካህን ነው። ዲቁናው ለእርሱ "በራት ላይ ዳረጐት" ነው እንጂ እንዲሁ ዲያቆን ብቻ አይደለም። ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጌታ ዕርገት በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ስምንት ሺህውን ማኅበር እየመራ ወንጌልን እየሰበከ ቢጋደል ኦሪት "እጠፋ እጠፋ" ወንጌል ደግሞ "እሰፋ እሰፋ" አለች። በዚህ ጊዜ "ክርስትናን ለማጥፋት መፍትሔው ቅዱስ እስጢፋኖስን መግደል ነው።" ብለው አይሁድ በማመናቸው ሊገልድሉት አስበውም አልቀሩ ገደሉት። እርሱ ግን ፊቱ እንደ እግዚአብሔር መልአክ እያበራ ፈጣሪውን በብዙ ነገር መሰለው። በመጨረሻውም ስለ እነሱ ምሕረትን እየለመነ በድንጋይ ወገሩት። ደቀ መዛሙርቱም ታላቅ ልቅሶን እያለቀሱ ቀበሩት። ይህች ዕለት ለቅዱስ እስጢፋኖስ በዓለ ሲመቱ ናት። ቅዱሱ መጽሐፍ እንደሚል "ምሉዓ ጸጋ ወሞገስ - ሞገስና ጸጋ የሞላለት" (ሐዋ. ፮፥፭፣ ቅዳሴ ማርያም) ነውና የስድስቱ ዲያቆናት አለቃና የስምንት ሺህው ማኅበር መሪ ሆኖ ተመርጦ እንደሚገባ አገልግሏል። በሰማይ ባለችው መቅደስም የሚያገለግለው በዚሁ ማዕረጉ ነው።
    20. ዮሐንስ ሐፂር(እረፍቱ)
      በቤተ ክርስቲያን ያሉ አበው ሊቃውንት እንደሚሉት ከቅዱሳን በቁመቱ የአባ አርሳኒን ያክል ረዥም አልነበረም። እርሱ እንደ ዝግባ ቀጥ ያለ ነበር። በዚያው ልክ ደግሞ የቅዱስ ዮሐንስን (ዛሬ የምናከብረውን) ያህል አጭር አልነበረም። በዚህ ምክንያት ይሔው ለዘላለም "ዮሐንስ ሐጺር - አጭሩ አባ ዮሐንስ" ሲባል ይኖራል። ሊቃውንትም ቁመቱንና ቅድስናውን በንጽጽር ሲገልጡ፦ "ሰላም ሰላም ዕብሎ በሕቁ ለዮሐንስ ሐጺር ዘነዊኅ ሒሩተ ጽድቁ" ይላሉ። "ቁመቱ እጅግ ያጠረ ጽድቁ ግን ከሰማይ የደረሰ ቅዱስ ዮሐንስን ሰላም ሰላም እንለዋለን።" እንደ ማለት ነው። ቅዱሱ የተወለደው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምድረ ግብጽ ነው። ወላጆቹ ምንም ከሥጋዊ ሃብት ድሆች ቢሆኑም ባለ መልካም ክርስትና ነበሩና በጐውን ሕይወት አስተምረውታል። ወደ ምናኔ የገባው ገና በአሥራ ስምንት ዓመቱ ሲሆን የታላቁ አባ ባይሞይ ደቀ መዝሙር ሆኖ ተጋድሎንና ትሕርምትን ተምሯል። ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር በወቅቱ ከነበሩ ቅዱሳን ከቁመቱ ባሻገር በትሕትናው፣ በትእግስቱና በመታዘዙ ይታወቅ ነበር። አባ ባይሞይ ይጠራውና ያለ ምንም ምክንያት ደብድቦ ያባርረው ነበር። እርሱ ግን "ምን አጠፋሁ?" ብሎ እንኳ ሳይጠይቅ "አባቴ ሆይ! ማረኝ?" እያለ ከእግሩ ሥር ይወድቅ ነበር። ለብዙ ጊዜ በተመሳሳይ ሲደበድበው እርሱም እርሱው ተደብድቦ እርሱው ይቅርታን ሲጠይቅ ኖረ። አንድ ቀን ግን እንደ ልማዱ ሊገርፈው ሲሔድ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ከበውት አይቶ ደንግጦ ተመልሷል። አባ ባይሞይ ይሕንን ሁሉ የሚያደርገው ጠልቶት ወይ ክፉ ሆኖ አይደለም። አንድ ሰው የሌላኛውን ግፍ መቀበል ካልቻለ ሰይጣንን ድል አይነሳም የሚል ትምህርት ስለ ነበረ ነው እንጂ። አንድ ቀን ቅዱስ ዮሐንስ ወደ መምህሩ ቀርቦ "አባቴ ጅብ ካገኘሁ ምን ላድርግ?" ሲል ጠየቀው። (የአካባቢው ጅብ መናጢ ነበር።) አባ ባይሞይ ግን "ይዘህ አምጣልኝ።" አለው። ትዕዛዝ ነውና ቅዱሱ ወደ በርሃ ወርዶ ጅብ አልምዶ ይዞለት መጥቷል። ሌላ ቀን ደግሞ አባ ባይሞይ ቅዱስ ዮሐንስን ጠራውና ተፈልጦ የወደቀ ደረቅ እንጨት ሠጠው። "ምን ላድርገው አባ?" አለው። "ትከለውና እንዲያፈራ አድርገው። ከዚያ አምጥተህ አብላኝ።" ሲል መለሰለት። ይህ ነገር ከተፈጥሮ ሥርዓት ውጪ መሆኑን እያወቀ ቅዱስ ዮሐንስ "እሺ" ብሎ ወስዶ ተከለው። ከዚያም ለሁለት ዓመታት ሳይታክት ውኃ አጠጣው። ውኃውን የሚያመጣበት ቦታ ደግሞ አሥር ኪሎ ሜትር ያህል ከገዳሙ ይርቅ ነበር። ቅዱሱ ላቡን እያፈሰሰ አሁንም ማጠጣቱን ቀጠለ። በሦስተኛው ዓመት ግን ለምልሞ አበበ ደግሞም አፈራ። ካፈራው በኩረ ሎሚም ወስዶ ለመምህሩ "አባቴ! እንካ ብላ።" ብሎ ሰጠው። አባ ባይሞይ ግን ማመን አልቻለም። እጅግ አደነቀ፤ አለቀሰም። ወዲያው ያን ፍሬ ታቅፎ ወስዶ ለገዳሙ መነኮሳት "ንሱ ብሉ፤ በረከትንም አግኙ። ይህ የዛፍ ሳይሆን የመታዘዝ ፍሬ ነው።" አላቸው። ቅዱስ ዮሐንስ አባ ባይሞይ ቢታመም ለአሥራ ሁለት ዓመታት አስታሞታል። መምህሩ ከማረፉ በፊትም መነኮሳቱን ሰብስቦ የቅዱስ ዮሐንስን እጅ አስጨበጣቸው። "ይህ የያዛችሁት እጅ የሰው ሳይሆን የመልአክ እጅ ነው።" ብሏቸው ዐርፏል። ቅዱስ ዮሐንስም ከዓመታት ቆይታ በኋላ የገዳሙ አበ ምኔት ሆኖ አገልግሏል። ብዙ ነፍሳትንም ለቅድስና ማርኳል። መላእክት ንጽሕናው ደስ ስለሚያሰኛቸው አብረውት ይውሉ ነበር። ሲተኛም በተራ በተራ ክንፋቸውን ያለብሱት ነበር። ምጽዋትን በጣም ስለሚወድ ሰፌድ እየሰፋ ይሸጥና ገንዘቡን ለነዳያን ያካፍል ነበር። አንድ ቀን እንደ ልማዱ ወደ ገበያ ወጥቶ ሳለ ተደሞ (ተመስጦ) መጣበት። ሰማያት ተከፍተው ቅዱሳን ሊቃነ መላእክት ሚካኤልና ገብርኤል በግርማ በጌታ ፊት ቆመው ተመለከተ። "እጹብ፣ እጹብ" እያለ ሲያደንቅ አንድ ገዢ መጥቶ "ባለ እንቅብ ዋጋው ስንት ነው?" ቢለው "እኁየ ሚካኤልኑ የዓቢ ወሚመ ገብርኤል - ከሚካኤልና ከገብርኤል ማን ይበልጣል?" ብሎታል። ገዢውም ደንግጦ "እብድ መነኩሴ" ብሎት ሔዷል። ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ወደ ባቢሎን (የአሁኗ ኢራቅ) ሒዶ ከተመለሰ በኋላ በበርበሮች ምክንያት ከአስቄጥስ ወደ ቁልዝም ተሰዷል። በዚያም በአባ እንጦንስ በዓት ውስጥ ዐርፏል። ለአራት መቶ ዓመታት በዚያው ቆይቷል። በ፰፻፳፭ ዓ/ም ግን በአባ ዮሐንስ ፓትርያርክ ዘመን ክቡር ሥጋው ወደ ገዳመ አስቄጥስ ተመልሷል። የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርና የታላቁ ቅዱስ መቃርስ ሥጋ በተገናኙ ጊዜ ግሩም ተአምር ተደርጓል። ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሲገባም ታላቅ የብርሃን ጐርፍ ሲፈስ ታይቷል። ሰማያዊ መዓዛም አካባቢውን ሞልቶታል። ከጳጳሳቱ አንዱ እባረካለሁ ብሎ የቅዱስ ዮሐንስን ሥጋ ቢገልጠው አካባቢው ተናወጠ። መባርቅትም (መብረቆች) ተብለጨለጩ። ደንግጠው ቶሎ ቢያለብሱት ጸጥታ ሆኗል። በዚህ ሁሉ ደስ ያላቸው አበው ቅዱሱን በዝማሬ ሲያወድሱት ውለዋል። ቅዱሱ ያረፈው ዛሬ ነው። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
    21. ነቢየ እግዚአብሔር ኢዩኤል (እረፍቱ)
      22. ቅዱስ ዑራኤል
      22. ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ (እረፍቱ)
        ቅዱስ ሉቃስ፦ *ሐዋርያ ነው። *ወንጌላዊ ነው። *ሰማዕት ነው። *ዓቃቤ ሥራይ (ዶክተር) ነው። *የጥበብ ሰው (ሠዓሊ) ነው። *ዘጋቢ (የሐዋርያትን ዜና ሕይወት የጻፈ) ነው። ይህስ እንደምን ነው ቢሉ፦ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን መነሻ አካባቢ በተወደደች የጌታ ዓመት ከእስራኤላውያን ወገኖቹ ቅዱስ ሉቃስ ተወልዷል። ያደገውም መቄዶንያ አካባቢ ነው። ጌታችን ተጠምቆ ማስተማር ሲጀምር ከተከተሉት የአምስት ገበያ ሕዝብ መካከል መቶ ሃያውን ለቤተሰብነት መምረጡ ይታወቃል። ታዲያ እንዲጠቅም አውቆ ቅዱስ ሉቃስን ከሰባ ሁለቱ አርድእት ደምሮታል። ቅዱስ ሉቃስ ጌታን ከተከተለ በኋላ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከዋለበት እየዋለ ካደረበትም እያደረ የቃሉን ትምህርት የእጆቹን ተአምራት በጥሞና ይከታተል ነበር። ጌታችን ለዓለም ድኅነት ተሰቅሎ ሙቶ ከተነሳ በኋላ ስለዚህ ቅዱስ የሚናገር አንድ የወንጌል ክፍል እናገኛለን። በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፬ ላይ ከምናያቸው የኤማሁስ መንገደኞች አንዱ ይህ ቅዱስ እንደ ሆነ አባቶች አስተምረውናል። በእርግጥ "ቀለዮጳ" የሚለው ስም በዘመኑ የብዙዎች መጠሪያ ቢሆንም እርሱም ጌታን ከመከተሉ በፊት በዚህ ስም ይጠራ እንደ ነበር ይታመናል። በወቅቱ ታዲያ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት (ሉቃስና ኒቆዲሞስ) ወደ ኤማሁስ ሲሔዱ ጌታ መንገድ ላይ ተገልጦ እያጫወታቸው አብሮ ተጉዟል። እነርሱም ማንነቱን አላወቁምና ስለ ራሱ ለራሱ እየሰበኩለት ተጉዘዋል። ከሐዘናቸው ብዛት ማስተዋል ተስኗቸው ቀቢጸ ተስፋም ወሯቸው ነበርና መድኃኒታችን ክርስቶስ የነቢያትን ትንቢት ተረጐመላቸው። በዚህ ጊዜም ከነገሩ ማማር ከምሥጢሩ መሥመር ጋር እየገረማቸው ልቦናቸው ይቃጠል (ይቀልጥባቸው) ነበር። "አኮኑ ይነድደነ ልበነ" እንዲል። ወደ ኤማሁስ ሲደርሱ ግን ደጐች ናቸውና "በቤት ካላደርክ ራት ካልበላህ?" ብለው ግድ አሉት። በማዕድ ሰዓት ግን ቡራኬውን ሰጥቷቸው ቸር አምላክነቱን ገልጦላቸው ተሰወራቸው። እነርሱም በሐሴት ከኤማሁስ ተመልሰው እየሮጡ ኢየሩሳሌም ደርሰው ትንሣኤውን ሰበኩ። የመንገዱ ርዝመትም አልታወቃቸውም ነበር። ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሉቃስ እንደ ሐዋርያቱ መጽሐፈ ኪዳንን፣ ትምሕርተ ኅቡዓትን ተምሮ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል። * ቅዱሱ ዶክተር * በትውፊት ትምህርት እንደ ተማርነው ቅዱስ ሉቃስ ጌታን ከመከተሉ በፊት ሥራው ሐኪምነት (ዶክተር) ነበር:: በዚህም አበው "አቃቤ ሥራይ (ባለ መድኃኒት)" ይሉታል። በተሰጠው ሙያም ብዙዎችን አገልግሏል። የጌታ ደቀ መዝሙር ከሆነ በኋላ ደግሞ "አቃቤ ሥራይ ዘነፍስ - የነፍስ ሐኪም" ተብሏል። እንዲያውም አባቶቻችን ሐዋርያትን ያክማቸው ነበር ይባላል። ከደግነታቸው የተነሳም እልፍ አእላፍ ድውያንን በተአምራት ሲፈውሱ እነርሱ ግን በስቃይ ይኖሩ ነበር። ሕመማቸው ሲጠናባቸው ግን ቅዱሱ ዶክተር ሉቃስ ይራዳቸው ነበር። ይሕንንም ቅዱስ ጳውሎስ በቆላስይስ መልእክቱ ላይ "የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ፣ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።" ሲል ገልጾታል። (ቆላ. ፬፥፲፬) * ዘጋቢው ሐዋርያ * ቅዱስ ሉቃስ እንደ ዛሬው ነገሮች ምቹ ባልነበሩበት ዘመን እጅግ አድካሚ የሆነ ጉዞ አድርጐ የሐዋርያትን ዜና ሕይወት ዘግቦልናል። ልክ ወንጌሉን ለታኦፊላ (ቴዎፍሎስ) ደቀ መዝሙሩ እንደ ጻፈለት ግብረ ሐዋርያትንም ለእርሱ በትረካ መልክ አቅርቦለታል። ሲጽፍለትም "ሰማሁ" እያለ ሳይሆን አብሮ እያለ ያየውንና የተሳተፈበትን ነው። አተራረኩም በአንደኛና በሦስተኛ መደብ አድርጐ እያቀያየረ ነው። ማለትም አንዳንዴ "እኛ" እያለ ሌላ ጊዜ ደግሞ "እነርሱ" እያለ ነበር የሚተርክለት። መጽሐፉም ሃያ ስምንት ምዕራፎች ሲኖሩት በጌታ ዕርገት ጀምሮ በኢየሩሳሌምና በአሕዛብ የነበረውን ስብከተ ወንጌል ገልጦ የቅዱስ ጳውሎስን ጉዞዎች በሰፊው ዳስሶ ይጠናቀቃል። * ወንጌላዊው ሐዋርያ * ቅዱስ ሉቃስ ወንጌልን እንዲጽፉ ከተመረጡ (ከተፈቀደላቸው) ሐዋርያት አንዱ ነው። በቤተ ክርስቲያንም "ዘላሕም" እየተባለ ይጠራል። ለዚህም ምክንያቱ፦ ፩.ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በበረት በላምና በአህያ መካከል መወለዱን በመጻፉ። ፪.ጌታችንን "መግዝአ ላሕም - የሚታረድ ሜልገች (ላም)" ብሎ በመግለጹ እና ፫.ከአራቱ እንስሳ (ኪሩቤል) አንዱ (ገጸ ላሕም) ይራዳው ይጠብቀውም ስለ ነበር ነው። ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈው ጌታ ባረገ በሃያ ሁለተኛው ዓመት ሲሆን ይኼውም በ፶፮ ዓ/ም አካባቢ ማለት ነው። ሲጽፍም ብቻውን አልነበረም። ልክ ቅዱስ ማርቆስ ወንጌሉን የጻፈው ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ጋር እንደ ሆነው ሁሉ ቅዱስ ሉቃስም የጻፈው ከብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ጋር ነው። ምክንያቱም ለረዥም ዓመታት አብረው ለስብከተ ወንጌል ተጉዘዋልና። ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን ሲጽፍ በነ ዘካርያስ ቤተሰብ ጀምሮ ብሥራተ ገብርኤልን፣ ክብረ ድንግል ማርያምን፣ የጌታን ልደት፣ እድገት፣ መጠመቅ፣ ማስተማር፣ መሰቀል፣ መሞት፣ መነሳትና ማረግ በቅደም ተከተል ይተርክልናል። * ጥበበኛው (ሠዓሊው) ሐዋርያ * ቅዱስ ሉቃስን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች ሌላኛው ደግሞ ጐበዝ ሠዓሊ የነበረ መሆኑ ነው። በሐዲስ ኪዳንም የመጀመሪያውን የእመቤታችንን ሥዕል (ምስለ ፍቁር ወልዳን) የሣለው እሱ ነው። አንድ ቀን የአምላክ እናት ባለችበት ከጌታ አስፈቅዶ የሣላት ሥዕለ አድኅኖ ሥጋን የለበሰች፣ ከፊቷ ወዝ የሚወጣ፣ የምታለቅስ፣ ስትወጋ የምትደማና ድውያንን የምትፈውስ ሆና ተገኝታለች። ይህች ሥዕል ዛሬ ሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ አለች ይባላል። * ሰማዕቱ ሐዋርያ * ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ ባለ ሕይወት ሲመላለስ በትጋት (ያለ ዕረፍት) ወንጌልን እየሰበከ ነበር። በ፷፮ እና በ፷፯ ዓ/ም ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ በኔሮን ቄሣር እጅ ሲገደሉ የሮም ግዛት ክርስቲያኖች ኃላፊነት በእርሱ ላይ ነበረ። ከወንጌሉና ግብረ ሐዋርያቱ ባለፈ በመልእክታት አንድም እየዞረ ክርስቲያኖችን አጸና፤ አሕዛብንም አሳመነ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ዝናውን የሰማው ኔሮን ሊገድለው ፈለገ። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ሉቃስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሲላስ የሚባለውን ሽማግሌ መርጦ መጽሐፎቹን ሁሉ አስረከበው። በድፍረትም ወደ ኔሮን ቄሣር ቀርቦ ተናገረው። ንጉሡም "ክርስቶስን አምልኩ የምትል ቀኝ እጅህ መቆረጥ አለባት።" ብሎ እጁን ከትክሻው በሰይፍ ለይቶ መሬት ላይ ጣለው። ሁሉ ሰው ሲደነግጥ ቅዱሱ ተጐንብሶ የወደቀች እጁን አነሳትና እንደ ነበረችው አደረጋት። በዚያ የነበሩ አሕዛብም "ግሩም" አሉ። መልሶ ግን "አሁን እጄ ሥራዋን ስለ ጨረሰች አልፈልጋትም።" ብሎ እንደ ገና ለይቶ ጣላት። "ከመ ያርኢ ኃይለ ቅድመ ኔሮን ወተዓይኑ አስተላጸቃ ወሌለያ ለምትርት የማኑ እስመ ላዕሌሁ ተሰውጠ ለክርስቶስ ሥልጣኑ።" እንዲል። በዚህ ጊዜም ይህንን ድንቅ ያዩ አራት መቶ ሰባ ሰባት ያህል አሕዛብ በክርስቶስ አምነው አብረውት ተሰይፈዋል። የስብከት ዘመኑም ከሠላሳ ስድስት ዓመታት በላይ ነው። አምላከ ቅዱስ ሉቃስ ምሥጢሩን፣ ፍቅሩን፣ ጥበቡን ይግለጽልን። ከሐዋርያው በረከትም ያሳትፈን።
      25. አቡነ ሀቢብ አረፈ
        ይህን ታላቅ ቅዱስ በምን እንመስለዋለን! እኛ ኃጥአን ጣዕመ ዜናውን፣ ነገረ ሕይወቱን ሰምተን ደስ ተሰኝተናል! ቅዱሱ አባታችን "ቡላ - የእግዚአብሔር አገልጋይ" ብለን እንጠራሃለን። ዳግመኛም "አቢብ - የብዙኃን አባት" ብለን እንጠራሃለን። እርሱ ቅሉ አባትነትህ አንተን ለመሰሉ ቅዱሳን ቢሆንም እኛን ኃጥአንን ቸል እንደማትለንም እናውቃለን። አባ! ማነው እንዳንተ የክርስቶስን ሕማማት የተሳተፈ! ማን ነው እንዳንተ በፈጣሪው ፍቅር ብዙ መከራዎችን የተቀበለ! ማንስ ነው እንዳንተ በአንዲት ጉርሻ አማልዶ ርስትን የሚያወርስ! የፍጡራንን እንተወውና በፈጣሪ አንደበት ተመስግነሃልና ቅዱሱ አባታችን ላንተ ክብር፣ ምስጋናና ስግደት በጸጋ ይገባሃል እንላለን። ልደት አባታችን አቡነ አቢብ የተወለደው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ ሮሜ ናት። ወላጆቹ ቅዱስ አብርሃምና ቅድስት ሐሪክ እጅግ ጽኑ ክርስቲያኖች ነበሩ። ልጅ ግን አልነበራቸውም። ዘመነ ሰማዕታት ደርሶ ስደት በሆነ ጊዜ እነርሱም በርሃ ገቡ። በዚያም ሳሉ በቅዱስ መልአክ ብሥራት ሐሪክ ጸንሳ ብሩሕ የሆነ ልጅ ወለደች። ቅዱሱ ሕፃን ሲጸነስ ማንም ሳይተክለው የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ እንዲህ የሚል የብርሃን ጽሑፍ ጽፎበት ወላጆቹ ዐይተዋል። "ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር፣ ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ ዘየኀድር ውስተ ጽዮን" ጥምቀት ቅዱሱ ሕፃን ከተወለደ በኋላ ሳይጠመቅ ለአንድ ዓመት ቆየ። ምክንያቱም ዘመኑ የጭንቅ ነውና ካህናትን እንኳን በዱር በከተማም ማግኘት አይቻልም ነበር። እመቤታችን ግን ወደ ሮሙ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሰለባስትርዮስ ሒዳ 'አጥምቀው' አለችው። ወደ በርሃ ወርዶ ሊያጠምቀው ሲል ሕፃኑ ተነስቶ እጆቹን ዘርግቶ "አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውዕቱ መንፈስ ቅዱስ" ብሎ አመስግኖ ተጠመቀ። ከሰማይም ሕብስትና ጽዋዕ ወርዶላቸው ሊቀ ጳጳሳቱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው። የሕፃኑ ወላጆች "ለልጃችን ስም አውጣልን።" ቢሉት "ቡላ" ብሎ ሰየመው። እነርሱም ምሥጢሩን ያውቁ ነበርና አደነቁ። ሰማዕትነት የቅዱሱ ቡላ ወላጆች ለአሥር ዓመታት አሳድገውት ድንገት ኅዳር ፯ ቀን ተከታትለው ዐረፉ። ሕፃኑን የማሳደግ ኃላፊነትን የአካባቢው ሰዎች ሆነ። ሕፃኑ ቡላ ምንም የአሥር ዓመት ሕፃን ቢሆንም ያለ ማቋረጥ ሲጾም ሲጸልይ ክፉ መኮንን "ለጣዖት ስገዱ።" እያለ መጣ። በዚህ ጊዜ በሕፃን አንደበቱ አምልኮተ ክርስቶስን ሰበከ። በዚህ የተበሳጨ መኮንኑ ስቃያትን አዘዘበት። በጅራፍ ገረፉት፣ በዘንግ ደበደቡት፣ ቆዳውን ገፈፉት፣ በመጋዝ ቆራርጠውም ጣሉት። ነገር ግን ኃይለ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና ሁለት ጊዜ ከሞት ተነሳ። በመጨረሻ ግን ሚያዝያ ፲፰ ቀን ተከልሎ ሰማዕት ሆኗል። ገዳማዊ ሕይወት ቅዱስ ቡላ ሰማዕትነቱን ከፈጸመ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል በአክሊላት አክብሮ ወስዶ በገነት አኖረው። ከሰማዕታትም ጋር ደመረው። በዚያም ቡላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተመልክቶ ተደነቀ። መንፈሳዊ ቅንዐትን ቀንቷልና "እባክህን ወደ ዓለም መልሰኝና ስለ ፍቅርህ እንደ ገና ልጋደል?" ሲል ጌታን ለመነ። ጌታችን ግን "ወዳጄ ቡላ! እንግዲህስ ሰማዕትነቱ ይበቃሃል። ሱታፌ ጻድቃንን ታገኝ ዘንድ ግን ፈቃዴ ነውና ሒድ።" አለው። ቅዱስ ሚካኤልም የቅዱስ ቡላን ነፍስ ከሥጋው ጋር አዋሕዶ ልብሰ መነኮሳትን አልብሶ ግብጽ በርሃ ውስጥ አኖረው። ተጋድሎ አባ ቡላ ወደ በርሃ ከገባ ጀምሮ ዓርብ ዓርብ የጌታን ሕማማት እያሰበ ራሱን ያሰቃይ ገባ። ራሱን ይገርፋል፤ ፊቱን በጥፊ ይመታል፤ ሥጋውን እየቆረጠ ለአራዊት ይሰጣል፤ ከትልቅ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ወደ ታች ይወረወራል። በጭንቅላቱ ተተክሎ ለብዙ ጊዜ ጸልዮ ጭንቅላቱ ይፈሳል። ሌላም ብዙ መከራዎችን የጌታን ሕማማት እያሰበ ይቀበላል። ስለ ጌታ ፍቅርም ምንም ነገር ሳይቀምስ ለአርባ ሁለት ዓመታት ጹሟል። ጌታችንም ስለ ክብሩ ዘወትር ይገለጥለት ነበር። የሚታየውም እንደ ተወለደ፣ እንደ ተጠመቀ፣ እንደ ተሰቀለ፣ እንደ ተነሳ፣ እንዳረገ እየሆነ ነበር። አንድ ቀንም ጌታችን መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! እንዳንተ ስለ እኔ ስም መከራ የተቀበለ ሰው የለም። አንተም የብዙዎች አባት ነህና ስምህ አቢብ (ሃቢብ) ይሁን።" አለው።  "እስከ ይቤሎ አምላክ ቃለ አኮቴት ማሕዘኔ ረሰይከኑ ለባሕቲትከ ኩነኔ ዘመጠነዝ ታጻሙ ነፍስከ በቅኔ" እንዲል። ዕረፍት አቡነ አቢብ ታላቁ ዕብሎን ጨምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርትን አፈራ። ከእመቤታችን ጋርም ዕለት ዕለት እየተጨዋወተ ዘለቀ። በተጋድሎ ሕይወቱም ከአሥር ጊዜ በላይ ሙቶ ተነስቷል። በዚህች ቀን ሲያርፍ ገዳሙ በመላእክት ተሞላ። ጌታም ከድንግል እናቱ ጋር መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! ስምህን የጠራውን፣ መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ። አቅም ቢያጣ 'አምላከ አቢብ ማረኝ።' ብሎ ሦስት ጊዜ በዕለተ ዕረፍትህ የሚለምነኝን በስምህ እንኳ ቁራሽ የሚበላውን ሁሉ እምርልሃለሁ።" ብሎት ነፍሱን በክብር አሳረገ፤ በሰማይም ዕልልታ ተደረገ። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
      27. መድሐኔአለም
        ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ለእኛ ሲል በፈጸመው የማዳን ሥራ ክፉዎች አይሁድ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ጌቴሴማኒ ውስጥ ያዙት። ሙሉውን ሌሊት ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አስረው ሲደበድቡት አድረዋል። ዝም ቢላቸው ዓይኑን ሸፍነው በጥፊ መቱት። ምራቃቸውን ተፉበት፤ ዘበቱበት። ራሱንም በዘንግ መቱት። እርሱ ግን ሁሉን ታገሰ። በጧት ከገዢው ዘንድ ሞት እንዲፈረድበት አቀረቡት። በሠለስት (ሦስት ሰዓት ላይ) አካሉ እስኪያልቅ እየተዘባበቱ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት ገረፉት። ሊቶስጥሮስ አደባባይ ላይ እርጥብ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት። ስድስት ሰዓት ላይ በረዣዥም ብረቶች አምስት ቦታ ላይ ቸንክረው ሰቀሉት። ሰባት ታላላቅ ተአምራት በምድርና በሰማይ ታዩ። ዓለም በጨለማ ሳለች ጌታ በመስቀል ላይ ሰባት ቃላትን ተናገረ። ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ በባሕርይ ሥልጣኑ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ። በዚያች ሰዓትም ወደ ሲዖል ወርዶ የታሠሩትን ሁሉ ፈታ። አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ደጋጉ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብርና ሐዘን ጋር በአዲስ መቃብር ቀበሩት። በዚያች ቀን ድንግል ማርያም ልቧ በሐዘን ተቃጠለ። ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስም ፍፁም ልቅሶን አለቀሰ። ቅዱሳት አንስት በዋይታ ዋሉ። ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለው መጋቢት ፳፯ ቀን ቢሆንም በዓሉ ወደ ጥቅምት እንዲመጣ ያደረጉት አበው ሊቃውንት ናቸው። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ መጋቢት ፳፯ የሚውለው ዓቢይ ጾም ውስጥ በመሆኑና የንግሥ በዓላት በዓቢይ ጾም ስለማይፈቀዱ ነው። ምንም እንኳ በቅርብ ጊዜ በዓቢይ ጾም የሚያነግሡ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም አባቶቻችን ግን እንዲህ ያለውን ሥርዓት አላቆዩልንም። ከበሮና የቸብቸቦ ዝማሬም በወቅቱ የተፈቀደ አይደለም። በዚህም ምክንያት የበዓለ ስቅለት ንግሡ ወደ ጥቅምት ፳፯ ሲመጣ፣ የመጋቢት ፭ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ንግሥ ወደ ጥቅምት ፭፣ የመጋቢት ፲ መስቀል ወደ መስከረም ፲፯ መጥቶ እንዲከበር ሆኗል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
      27. አባ መብዓ ፅዮን (እረፍታቸው)
        ሃገራችን ኢትዮጵያ እጅግ በርካታ ቅዱሳንን ስታፈራ አንዳንዶቹ ደግሞ የተለዩ ናቸው። ጻድቁ አባ መብዓ ጽዮን በአሥራ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሽዋ (ሻሞ) አካባቢ የተነሱ ጻድቅ ናቸው። ገና ከልጅነታቸው የእመቤታችንና የጌታችን ፍቅር የሞላባቸው ነበሩ። በሦስት ዓመታቸው ከእንግዳ የወሰዷት ሥዕለ አድኅኖ ተለይታቸው አታውቅም ነበር። በወጣትነታቸው ጊዜም ብሉያት፣ ሐዲሳትን፣ ቅኔንም ጨምሮ ተምረው ከቤተሰባቸው አስፈቅደው በምናኔ ገዳም ገቡ። ከዚያ በኋላ ያለውን ገድላቸውን ማን ችሎ ይዘረዝረዋል! በተለይ ዓርብ ዓርብ የጌታን አሥራ ሦስት ሕማማት ለማዘከር ሲቀበሉት የኖሩት መከራ እጅግ ብዙ ነው። ድንጋይ ተሸክመው እንባና ላበታቸው እየተንጠፈጠፈ ይሰግዳሉ። በድንጋይ ደረትና ጀርባቸውን ይደቃሉ፤ ራሳቸውን ይገርፋሉ። በዋንጫ ሐሞት (ኮሶ) ሞልተው ይጠጣሉ። ከዚህ ሁሉ በኋላ ወር በገባ በሃያ ሰባት ስለ መድኃኔ ዓለም ጠላ ጠምቀው፣ ንፍሮ ነክረው ወደ ገበያ ይወጡና ይዘክሩ ነበር። ከዝክሩ የነካ ሁሉ ይፈወስ ነበር። ከእንባ ብዛት ዓይናቸው ቢጠፋ ድንግል ማርያም መጥታ ብርሃናዊ ዓይንን ሰጠቻቸው። ስለዚህም "ተክለ ማርያም (በትረ ማርያም)" ይባላሉ። ጌታችንም ስለ ፍቅራቸው በአምሳለ ሕፃን ይገለጽላቸው፤ እርሳቸውም አቅፈው ይስሙት ነበር። ጻድቁ ተናግረን የማንጨርሰውን ተጋድሎ ተጋድለው ጌታ በዚህ ቀን ነፍሳትን ከሲዖል እንዲያወጡበት ሥልጣንን ሰጣቸው። አባታችን ቅዱሱና ጻድቁ መብዓ ጽዮን ከብዙ ትሩፋት በኋላ ዐርፈዋል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
      28. ቅዱስ አማኑኤል
        30. ቅዱስ ማርቆስ /ልደቱ/
          በዚሕች ዕለት ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የሆነ። ወንጌላዊ፣ ሐዋርያ፣ ሰማዕት፣ ዘአንበሳ እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የተባለ ቅዱስ ማርቆስ ተወልዷል። ቅዱስ ማርቆስ እናቱ "ማርያም"፣ አባቱ "አርስጥቦሎስ" ይባላሉ። በልጅነቱ ኦሪትንና የዘመኑን ጥበብ ሥጋዊ በሚገባ ተምሮ ክርስቶስን ከቤተሰቦቹ ጋር ተከትሏል። የመጀመሪያ ስሙ ዮሐንስ ሲሆን ከመቶ ሃያው ቤተሰብ በእድሜ በጣም ትንሹ (ሃያ ዓመት) እርሱ ነበር። ለሦስት ዓመታት ከጌታ እግር ሥር ተምሮ፣ በበዓለ ሃምሳ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ብዙ ደክሟል። በተለይ የግብጽና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አባት ነው። ክህነትን ያገኘን ከእርሱ ነውና። ቅዱስ ማርቆስ አሥራ ስድስት ምዕራፍ ያለውን ወንጌሉን ሲጽፍ ኪሩብ ገጸ አንበሳ በቀኙ፣ ሊቀ ሐዋርያት በግራው ሆነው ይራዱት ነበር። ቅዱሱ ከቅዱስ ጳውሎስ፣ ከበርናባስና ጴጥሮስ ጋር ተጉዟል። ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላ ሰሜን አፍሪካ አካባቢ አረማውያን ገድለውታል።  ዳግመኛ በዚህ ቀን የቅዱስ ማርቆስን ወላጆችን እናስባቸው ዘንድ ይገባል። ቅዱስ አርስጥቦሎስ (አባቱ) የጌታ ቅን አገልጋይ የነበረ፣ ቅድስት ማርያም (እናቱ) ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ ስትሆን ጌታችንን ያገለገለች ቤቷን ለሐዋርያትና ለጌታ በስጦታ ያበረከተች ቅድስት ናት። ቤቷም (ጽርሐ ጽዮን) የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን ይህች ቤት መንፈስ ቅዱስ ወርዶባታል። የእመቤታችን ግንዘትም ተከናውኖባታል። እግዚአብሔር ከቅዱስ ማርቆስ ቤተሰብ በረከትን ያድለን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
        30. ቅዱስ መጥምቁ ዮሐንስ
          ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል። ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል። "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ።" ይላቸዋል።(ሉቃ. ፩፥፮) የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል! እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ ዘጠና የዘካርያስ ደግሞ መቶ ደርሶ ነበር። ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. ፵፥፫ ፣ ሚል. ፫፥፩) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው። ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ። ቅድስቲቷ ግን መስከረም ፳፮ ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለስድስት ወራት ራሷን ሠወረች። በስድስተኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች። ሁለቱ ቅዱሳት የእኅትማማች ልጆች ናቸው። የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና ዮሐንስ ደግሞ ገና በማኅጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ)። ከዚህ በኋላ ሰኔ ፴ ተወልዶ አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል። ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕፃናትን ሄሮድስ ቁዝ አስፈጀ። ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሄሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕፃን ነገሩት። "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ ሲወለድ ደግሞ የከፈተ ዮሐንስ የሚባል ሕፃን አለና እሱንም ግደል።" አሉት። እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል። አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕፃኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለሦስት (አምስት) ዓመታት ቆይታለች። ቅዱስ ዮሐንስ አምስት (ሰባት) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች። ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት። ሕፃኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት ሃገር አልፋ ሰማችው። እርሷም ስደት ላይ ነበረችና። ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው። ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው። ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ።" አላት። ባርካው፣ አጽናንታውም ተለያዩ። ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በኋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ። ለሃያ አምስት (ሃያ ሦስት) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም። ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም። ከዚህ በኋላ ሠላሳ ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው። "ሒድ! የልጄን ጐዳና ጥረግ።" አለው። ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና። (ኢሳ. ፵፥፫ ፣ ሚል. ፫፥፩) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕፃን ነቢየ ልዑል ትሰመይ እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. ፩፥፸፮) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና። ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ። ያዩት ሁሉ ፈሩት፤ አከበሩት። ቁመቱ ቀጥ ያለ፣ ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ፣ ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ፣ መልኩ የተሟላ፣ ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና። ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሐ ሰበከ፤ ለንስሐም በርካቶችን አጠመቃቸው። በዚህ አገልግሎት ለስድስት ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ። ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ ምድርን ከነ ልብሱ የያዘ ፈጣሪ "አጥምቀኝ" ብሎ ሲመጣ ደነገጠ፤ የሚገባበትም ጠፋው። "እንቢ ጌታዬ! አንተ አጥምቀኝ?" አለው። ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው። አጠመቀው። በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "መጥምቀ መለኮት" ሲባል ይኖራል። ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሄሮድስን ገሰጸው። ንጉሡም ተቀይሞ ለሰባት ቀናት አሠረው። ንጉሡ ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሄሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው። እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት። አበው "እምሔሶ ለሄሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሄሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር።" ይላሉ። የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል። (ማቴ. ፫፥፩ ፣ ማር. ፮፥፲፬ ፣ ሉቃ. ፫፥፩ ፣ ዮሐ. ፩፥፮) ርጉም ሄሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በኋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት ደብረ ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች። ቅዱሳን ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት። ከዚህ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ሥልጣን ሰጥቶ አሰናበታት። በመላው ዓለም ለአሥራ አምስት ዓመታት ስትሰብክ ኑራ ዓረቢያ ውስጥ ዐርፋለች። ይህች ዕለት ለቅዱሱ "አስተርዕዮተ ርዕሱ" ወይም ቅድስት ራሱ ከተሰወረችበት የተገለጠችበት ነው። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
      ህዳር
        6. ቁስቋም ማርያም እመቤታችን ስደቷን ጨርሳ የገባችበት
          የአርያም ንግሥት፣ የፍጥረታት ሁሉ እመቤት ድንግል ማርያም የባሕርይ አምላክ ልጇን አዝላ ወደ ምድረ ግብጽ ወርዳለች። በወንጌል ላይ (ማቴ. ፪፥፩-፲፰) እንደተጻፈው ጌታችን በተወለደ በሁለት ዓመቱ የጥበብ ሰዎች (ሰብአ ሰገል) ወደ ቤተ ልሔም መጥተው ሰግደውለት ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤውን ገበሩ፤ አገቡለት። ንጉሥ ተወልዷል መባሉን የሰማ ሄሮድስ መቶ አርባ አራት ሺህ ሕፃናትን ሲፈጅ በቅዱስ ገብርኤል ትዕዛዝ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አንድ አምላክ ልጇን አዝላ በአንዲት አህያ ጥቂት ስንቅ ቋጥራ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ስደት ወጣች። ከገሊላ ተነስታ በጭንቅ፣ በመከራ፣ በረሃብና በጥም፣ በሐዘንና በድካም፣ በላበትና በእንባ ተጉዛ ምድረ ግብጽ ገብታለች። የአምላክ እናቱ እሳትን አዝላ በብርድ ተንገላታለች። ለእኛ የሕይወት እንጀራን ተሸክማ እርሷ ተራበች። የሕይወትን ውኃ ተሸክማ ተጠማች። የሕይወት ልብስን ተሸክማ ተራቆተች። የሕይወት ፍስሐን ተሸክማ አዘነች። እመ አምላክ ተራበች፣ ተጠማች፣ ታረዘች፣ ደከመች፣ አዘነች፣ አለቀሰች፣ እግሯ ደማ፣ ተንገላታች። ለሚገባው ይህ ሁሉ የተደረገው ለእኛ ድኅነት ነው። በእውነት ይህንን እያወቀ ለድንግል ማርያም ክብር የማይሰጥ ሰይጣን ብቻ ነው። አራዊት፣ ዕፅዋትና ድንጋዮች እንኳ ለአምላክ እናት ክብር ይሰጣሉ። አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍና ቅድስት ሰሎሜ ደግሞ የክብር ክብር ይገባቸዋል። ከአምላክ እናት ከድንግል ማርያምና ከቸር ልጇ ጋር መከራ መቀበልን መርጠዋልና። "መድኃኔ ዓለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተሰደደ? ለምን ስደቱን ወደ ግብጽና ኢትዮጵያ አደረገ?" ፩.ትንቢቱን ይፈጽም ዘንድ። በፈጣን ደመና ወደ ግብጽ እንደሚወርድ ተነግሯልና። (ኢሳ. ፲፱፥፩ ፣ ዕን. ፫፥፯) ፪.ምሳሌውን ለመፈጸም። የሥጋ አባቶቹ እነ አብርሃም፣ ያዕቆብ (እሥራኤል)፣ ኤርምያስ ወደዚያው ተሰደዋልና። ፫.ከግብጽ ጣዖት አምልኮን ያጠፋ ዘንድ። (ኢሳ. ፲፱፥፩) ፬.የግብጽና የኢትዮጵያ ገዳማትን ይቀድስ ዘንድ። ፭.ሰው መሆኑ በአማን እንጂ ምትሐት እንዳልሆነ ለማጠየቅ። (ሰው ባይሆን ኑሮ አይሰደድም ነበር። ሄሮድስ ቢያገኘው ደግሞ ሊገድለው አይችልም። ያለ ፈቃዱና ያለ ዕለተ ዓርብ ደሙ አይፈስምና።) ፮.ስደትን ለሰማዕታት ባርኮ ለመስጠት እና ፯.የአዳምን ስደት በስደቱ ለመካስ ነው። እመ ብርሃን ድንግል ማርያም ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር (ለአርባ ሁለት ወራት) በስደት የቆየችባቸው ቦታዎች አሉ። ድንግል ማርያም ከርጉም ሄሮድስ ስትሸሽ መጀመሪያ የሔደችው ከገሊላ ወደ ሶርያ ድንበር (ደብረ ሊባኖስ) ነው። በዚያ የሸሸጋት ቅዱስ ጊጋር መስፍኑ በሄሮድስ ሲገደል ወደ ምድረ ግብጽ ወረደች። በግብጽም ለብዙ ጊዜ ከአንዱ ወደ ሌላው ስትሸሽ ቆየች። "እንዘ ከመ በግዕት ግድፍት አመ ሳኮይኪ ውስተ ምድረ በዳ" እንዲል። (እሴብሕ ጸጋኪ) ቀጥላም በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ገብታ ደብረ ቢዘን ላይ (አሁን ኤርትራ ውስጥ ነው።) ዐረፈች። ከደብረ ቢዘን በደብረ ዳሞ፣ አክሱም፣ ደብር ዓባይ፣ ዋልድባ አድርጋ እየባረከች ጣና ደርሳለች። በጣና ገዳማትም በተለይ በጣና ቂርቆስ ለመቶ ቀናት ቆይታ ቀጥታ በጐጃም ወደ ሽዋ ሒዳ ደብረ ሊባኖስን ቀድሳለች። ቀጥላም እስከ ደብረ ወገግና ደብረ ሐዘሎ ደርሳለች። በእግሯ ያልደረሰችባቸውን የሃገራችን ክፍሎች በደመና ተጭና ዐይታ ባርካቸዋለች። ከልጇም በአሥራትነት ተቀብላለች። ሄሮድስ መሞቱን መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የነገራትም እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን ትውፊት ያሳያል። እመ ብርሃንም ከሃገራችን ሰዎች (ከሰብአ ኦፌር) የተቀበለችውን ስንቅና ስጦታ በአምስት ግመሎች ጭና ከቅዱሳኑ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር በዚህች ቀን ደብረ ቁስቋም ውስጥ ገብተው ከድካም ዐርፈዋል፤ ሐሴትንም አድርገዋል። ዳግመኛም ከክርስቶስ ስደት አራት መቶ ዓመታት በኋላ በዚህች ቀን የግብጿ ደብረ ቁስቋም ታንጻ ተቀድሳለች። የቅዱሳን ማደሪያም ሁናለች። ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ፫፻፺ዎቹ አካባቢ ድንግል እናቱን፣ ቅዱሳን ሐዋርያትን፣ አእላፍ መላእክትን፣ ጻድቃንንና ሰማዕታትን አስከትሎ ወረደ። የወቅቱ የግብጽ ፓትርያርክ ቅዱስ ቴዎፍሎስና ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ ቤተ ክርስቲያኑን አንጸው ሕዝቡን ሰብስበው ይጠብቁት ነበርና ወርዶ ቀድሶላቸው ታላቅ ደስታ ሁኗል። ስደቷን መሳተፍን ሽተው አበው፦ "እመ ኀሎኩ በጐይዮቱ ውእተ መዋዕለ እምተመነይኩ ኪያሁ በዘባንየ ሐዚለ ወበልሳንየ እልሐስ ዘአእጋሪሁ ጸበለ ወከመ አዕርፍ ምስሌሁ በትረ ዮሴፍ ኀበ ተተክለ ለወልደ ማርያም በሐጸ ፍቅሩ ልቡናየ ቆስለ።" እንዳሉ። (ሰቆቃወ ድንግል) እኛም እመ ብርሃንን ልንሻት ያስፈልገናል። ይህ ቀን ለእኛ ለክርስቲያኖች ሁሉ እጅግ የደስታ ቀን ነውና ሐሴትን እናድርግ። የሰማይና የምድር ጌታ ለእኛ ሲል ካደረገው ስደቱ በዚህች ቀን ተመልሷልና። ስደቷን አስበን ካዘንን፣ መመለሷን አስበን ደስ ልንሰኝ ይገባልና። "አብርሒ አብርሒ ናዝሬት ሃገሩ ንጉሥኪ በጽሐ ዘምስለ ማርያም መጾሩ።" ልንልም ይገባል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
        7. ሕንጻ ቤቱ ለጊዮርጊስ/ አጥንቱ ተሰብስቦ መቃብር ቤት የገባበት
          መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው፣ አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰባት ዓመታት ስቃይ በኋላ ተሰይፏል። ይሕስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ፦ ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም (ልዳ) ውስጥ ነው። የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ሃያ ዓመት ሲሞላው የአባቱን ሥልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት (የአሁኗ ቤይሩት - ሊባኖስ) ሰዎች ዘንዶ (ደራጎን) ሲያመልኩ አገኛቸው። እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ፣ አሳምኖ፣ ደራጎኑንም በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና ሰባ ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር። በዚያች ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው። እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) ደረሰ። ከዚያም ለተከታታይ ሰባት ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን ተቀበለ። ሦስት ጊዜ ሙቶ ተነሳ። ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ "የሰማዕታት አለቃቸው"፣ "ፀሐይና የንጋት ኮከብ" በሚል ይጠራል። "ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ።" እንዲል መጽሐፍ። ከሰባት ዓመታት መከራ በኋላም ከብዙ ተአምራት ጋር ተሰይፎ ደም፣ ውኃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል። ሰባት አክሊላትም ወርደውለታል። ይህቺ ዕለት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ኃያል ቅዳሴ ቤቱ ናት። እርሱ በ፫፻፺ዎቹ አካባቢ ሰማዕት ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በዚያው በሃገሩ ደብር አንጸው፣ አጽሙን አፍልሠው በዚህች ቀን ቀድሰዋታል። ቅዱሱ ሰማዕት ከሰማዕትነቱ በፊትም ሆነ በኋላ ተአምረኛ ነውና አንዷን እንመልከት። በዘመኑ የክርስቲያኖችን ደም ሲያፈሱ ከነበሩ አራዊት (ነገሥታት) መካከል አንዱ የሆነው ዲዮቅልጢያኖስ ርጉም የአርባ ሰባት ሚሊየን ክርስቲያኖችን ደም አፍስሶ ነበርና ፈጣሪ ደመ ሰማዕታትን የሚበቀልበት ጊዜ ደረሰ። በ፫፻፭ ዓ/ም አካባቢ አረመኔው ንጉሥ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተአምረኛነት ሰምቶ እንዲያፈርሱት ሠራዊት ላከ። የሠራዊቱ አለቃም ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገብቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል ላይ ተሳለቀ። ከፊቱ የነበረውን ቀንዲል በሰይፍ እመታለሁ ሲል ግን ቀንዲሉ ተገልብጦ መሐል አናቱን መታው። እንደ እብድ ሆኖ ሞተ። ሠራዊቱም ሰምቶ ወደ ንጉሡ ሸሸ። ይህን ሰምቶ የተበሳጨው ዲዮቅልጢያኖስ ግን ራሱ ሊያፈርሰው ሔደ። ከቤተ ክርስቲያኑ በር ላይ ሲደርስ ሚካኤልና ገብርኤል ዓይኑን አጠፉት። እገባለሁ ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከላይ መረዋውን (ደወሉን) ለቀቀበት። ራሱን ቢመታው ደነዘዘ። የብዙ ቅዱሳንን ደም የጠጣው ርጉሙ ንጉሥም አብዶ ለሰባት ዓመታት ፍርፋሪ ሲለምን ኑሮ ሰይጣን ከገደል ጫፍ ወርውሮ ገድሎታል። አምላካችን እግዚአብሔር ከኃያሉ ሰማዕት ጽናትና ትእግስት፣ በረከትም ይክፈለን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
        8. በዓል አርባዕቱ እንስሳ
          እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን ሲፈጥራቸው በነገድ መቶ በክፍለ ነገድ አሥር አድርጓቸዋል። አቀማመጣቸውንም በሦስት ሰማያትና በአሥር ከተሞች (ዓለማት) አድርጓል። መላእክት ያሉባቸው ከተሞች ከታች ወደ ላይ 'ኤረር፣ ራማና ኢዮር' ይባላሉ። አሥሩ ክፍለ ነገድ ደግሞ ከነ አለቆቻቸው ይህንን ይመስላሉ። ፩.አጋእዝት (የቀድሞ አለቃቸው ሳጥናኤል ሲሆን አሁን የተረፉት በቅዱስ ሚካኤል ሥር ናቸው።) ፪.ኪሩቤል (አለቃቸው ኪሩብ) ፫.ሱራፌል (አለቃቸው ሱራፊ) ፬.ኃይላት (አለቃቸው ሚካኤል) ፭.አርባብ (አለቃቸው ገብርኤል) ፮.መናብርት (አለቃቸው ሩፋኤል) ፯.ሥልጣናት (አለቃቸው ሱርያል) ፰.መኳንንት (አለቃቸው ሰዳካኤል) ፱.ሊቃናት (አለቃቸው ሰላታኤል) ፲.መላእክት (አለቃቸው አናንኤል) ናቸው። ከእነዚህም አጋእዝት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌልና ኃይላት መኖሪያቸው በኢዮር (በሦስተኛው ሰማይ) ነው። አርባብ፣ መናብርትና ሥልጣናት ቤታቸው ራማ (ሁለተኛው ሰማይ) ነው። መኳንንት፣ ሊቃናትና መላእክት ደግሞ የሚኖሩት በኤረር (በአንደኛው) ሰማይ ነው። መላእክት ተፈጥሯቸው እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ ነው። አይራቡም፣ አይጠሙም፣ አይዋለዱም፣ አይሞቱም። ተፈጥሯቸውም ረቂቅ ነው። ተግባራቸው ዘወትር "ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ" እያሉ ፈጣሪያቸውን ማመስገን ነው። ምግባቸውም ይሔው ነው። ዕረፍት ብሎ ነገርን አያውቁም። "አኮቴቶሙ ዕረፍቶሙ፣ ወዕረፍቶሙ አኮቴቶሙ" እንዲል። በተጨማሪም መልአክ ማለት ተላላኪ (አገልጋይ) ነውና ከፈጣሪ ወደ ሰው ልጆች ለምሕረትም፣ ለመዓትም ይላካሉ። ምሕረትን ያወርዳሉ። ልመናን ያሳርጋሉ። ቅጡ ሲባሉም ይቀጣሉ። ስነ ፍጥረት (አራቱ ወቅቶች) እንዳይዛቡ ይጠብቃሉ። ዘወትርም ስለ ሰው ልጆች ያማልዳሉ። (ዘካ. ፩፥፲፪) ምሥጢርን ይገልጣሉ። (ዳን. ፱፥፳፩) ይረዳሉ። (ኢያ. ፭፥፲፫) እንዳንሰናከል ይጠብቃሉ። (መዝ. ፺፥፲፩) ያድናሉ። (መዝ. ፴፫፥፯) ስግደት ይገባቸዋል። (መሳ. ፲፫፥፳ ፣ ኢያ. ፭፥፲፫ ፣ ራዕ. ፳፪፥፰) በፍርድ ቀንም ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያሉ። (ማቴ. ፳፭፥፴፩) በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ሕይወትና ድኅነት ሲባል ከፈጣሪያቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ሲጠብቁና ፈቃዱን ሲፈጽሙ ይኖራሉ። ከእነዚህ ቅዱሳን መላእክት መካከል ደግሞ ትልቁን ሥፍራ ዛሬ የምናከብራቸው ነገደ ኪሩቤል (ዐርባዕቱ እንስሳ) ይይዛሉ። መንፈሳውያን ከመሆናቸው በላይ መንበረ ጸባኦትን እንዲሸከሙ ስላደላቸው ክብራቸው ታላቅ ነው። ከመላእክት ወገንም ቅሩባን እነርሱ ናቸው። ዘወትርም ስለ ፍጥረታት (ሰዎች፣ እንስሳት፣ አራዊትና አዕዋፍ) ምሕረትን ይለምናሉ። ለዚህም ነው በአራት እንስሳት (በሰው፣ በንስር፣ በላምና በአንበሳ) መልክ የተሳሉት። ቅዱስ መጽሐፍም ስለ እነርሱ ብዙ ይላል። (ሕዝ. ፩፥፭ ፣ ራዕ. ፬፥፮ ፣ ኢሳ. ፮፥፩) በተለይ ግርማቸው እንደሚያስፈራ ተጽፏል። "ምሉዓነ ዐዕይንት - ዓይንን የተሞሉ" ይላቸዋል። ይህንንም መተርጉማን "ምሥጢር አዋቂነታቸውንና ግርማቸውን ያጠይቃል።" ሲሉ ተርጉመውታል። ዐርባዕቱ እንስሳን አራት ሆነው በሥዕል ብናያቸውም "ከመ ርዕየተ እለ ቄጥሩ" እንዲል እያንዳንዱ ከወገብ በላይ አራት በመሆናቸው ተሸካሚዎቹ አሥራ ስድስት መልክ አላቸው። በሁለት ክንፋቸው ፊታቸውን፣ በሁለቱ እግራቸውን ሸፍነው በሁለት ክንፋቸው ይበራሉ። ይህም ብዙ ምሥጢር ሲኖረው ዋናው ግን አርአያ ትእምርተ መስቀል ነው። "አራቱ" እንስሳ (ኪሩቤል) በሐዲስ ኪዳንም ልዩ ክብር አላቸው። አራቱ ወንጌል ሲጻፍ እየተራዱ ስላጻፉ በስማቸው ተሰይሟል። ቅዱስ ማቴዎስን ገጸ ሰብእ፣ ቅዱስ ማርቆስን ገጸ አንበሳ፣ ቅዱስ ሉቃስን ገጸ ላሕም፣ ቅዱስ ዮሐንስን ገጸ ንስር እየተራዱ ስላጻፏቸው እነሆ እስከ ዛሬ ድረስ "ዘብእሲ ማቴዎስ"፣ "ዘአንበሳ ማርቆስ"፣ "ዘላሕም ሉቃስ" እና "ዘንስር ዮሐንስ" እየተባሉ ይጠራሉ። እነዚህ ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆችን ስለ መራዳታቸውም በብዙ ገድላትና ድርሳናት ላይ ተጽፏል። የራሳቸውን "ድርሳነ ዐርባዕቱ እንስሳን" ጨምሮ በገድለ አባ መቃርስና በገድለ አባ ብስንድዮስ ላይ በስፋት ግብራቸው ተጽፏል። እኛም ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ክብራቸውን፣ ረድኤታቸውንና ምልጃቸውን አምነን ዘወትር እናከብራቸዋለን። አባቶቻችን እንዲህ እያሉ እንደ ጸለዩ፦ "ሰላም ለክሙ ኪሩባውያን አፍራሱ ለመሐይምን ወጻድቅ እንተ ወርቅ አክሊለ ርዕሱ ኀበ ዝ አምላክ ለእለ ትጸውርዎ በአትሮንሱ ለእለ ጌገዩ ወለእለሂ አበሱ ሰአሉ መድኃኒተ ወምሕረተ ኅሡ። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
        8. ክሩቤል ሱራፌል
          8. አባኪሮስ
            11. ዕረፍተ ቅድስት ሀና
              "ሐና" ማለት በዕብራይስጥኛው "የእግዚአብሔር ስጦታ" እንደ ማለት ነው። "ሐና፣ ዮሐና፣ ሐናንያ" የሚሉ የዕብራይስጥ ስሞች ትርጉማቸው ተወራራሽ ነው። የዚህችን ቅድስት እናት ክብሯን መናገር የሚችል የለም። እርሷ ሰማይና ምድርን ለፈጠረ ለእግዚአብሔር ወልድ በሥጋ አያቱ ተብላለችና። አንድም ለሰማይና ለምድር ንግሥት ለድንግል ማርያም ወላጅ እናቷ ናትና። ከዓለም ሴቶች ሁሉ የቅድስት ሐና ማኅጸን እንደ ምን ይከብር! በፍጥረት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥንተ አብሶ (የአዳም በደል) መተላለፍ የቀረው በማኅጸነ ሐና ውስጥ ነውና። (ለዚህ አንክሮ ይገባል!) ይስሐቅን የተሸከመ የሣራ ማኅጸን ቡሩክ ከተባለ የቅድስት ሐናማ እንደምን አይባል! ከፍጥረታት ሁሉ እግዚአብሔር ድንግል ማርያምን እንደ መረጠ ሁሉ ቅድስት ሐናንም ለአያትነት መርጧታል። ቅድስት ሐና ትውልዷ፣ ነገዷ ከላይ ከቅዱስ አብርሃም፣ ከታች ደግሞ ከነገደ ካህናት ነው። ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ አብርሃም ይስሐቅን፣ ይስሐቅ ያዕቆብን፣ ያዕቆብ ደግሞ ሌዊንና አሥራ አንድ ወንድሞቹን ይወልዳል። ሌዊ ቀዓትን፣ ቀዓት እንበረምን፣ እንበረም አሮን ካህኑን ይወልዳሉ። ቅዱስ አሮን አልዓዛርን፣ አልዓዛር ፊንሐስን እያለ ትውልዱ እስከ ቴክታና በጥሪቃ ይወርዳል። ቴክታና በጥሪቃም ልጅ በማጣት ኖረው የእንቦሳዎች፣ የፀሐይና የጨረቃን ምሥጢር ተመልክተው ሄኤሜንን ይወልዳሉ። ሄኤሜን ዴርዴን፣ ዴርዴ ቶናሕን፣ ቶናሕ ሲካርን፣ ሲካርም ሔርሜላን ይወልዳሉ። ሔርሜላም ከክርስቶስ ልደት ዘጠና ዓመታት በፊት ማጣት ("ጣ" ጠብቆ ይነበብ) የሚባል ደግ ሰው ከካህናት ወገን አግብታ በስርዓተ ኦሪት ትኖር ነበር። እግዚአብሔር ለዚህች ደግ ሴት የተባረኩ ሦስት ሴቶች ልጆችን ሰጣት። የመጀመሪያዋን "ማርያም" አለቻት። ይህቺውም የአረጋዊው ዮሴፍ ሚስትና የቅድስት ሰሎሜ ቡርክት እናት ናት። ሁለተኛዋን "ሶፍያ" አለቻት። እርሷም ቅድስት ኤልሳቤጥን (የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን እናት) ወልዳለች። በመጨረሻ የወለዷትን ግን "ሐና" አሏት። ይህቺውም የፈጣሪ የሥጋ አያቱ፣ የድንግል ማርያምም እናቷ ትሆን ዘንድ የተመረጠችውና ስም አጠራሯ የከበረው ዛሬ የምናከብራት እናት ናት። መጽሐፈ ስንክሳርን ስመለከት እንዲህ የሚል ዓረፍተ ነገር አየሁ። "ለዛቲ ቅድስት ኢያዕመርነ ገድላቲሃ ዘትገብሮን በኅቡዕ ከመ ንዝክሮን" ይላል። ትርጉሙም "የዚህችን ቅድስት ገድሏንና ትሩፋቷን እንዳንዘረዝር አላወቅነውም።" እንደ ማለት ነው። የሚገርመው አበው እንዲህ ያሉት ክብሯን መግለጹን አልጠግብ ብለው ነው። እኛም በመጠናችን የብጽዕት ሐናን ሕይወት በአጭሩ ቀጥለን እንመልከት። ብጽዕት ሐና ወላጆቿ (ማጣትና ሔርሜላ) ከካህናት ወገን በመሆናቸው ልጆቻቸውን በጥንቃቄ በሥርዓተ ኦሪት እንዳሳደጉ ይታመናል። ቅድስት ሐናንም ለአቅመ ሔዋን እስክትደርስ ድረስ በሕጉ፣ በሥርዓቱ አሳድገዋታል። በወቅቱ በፈቃደ እግዚአብሔር ትውልዱ ከነገደ ይሁዳ የሚሆን አንድ ደግ ሰው አጩላት። ይህ ሰው "ኢያቄም" ይባላል። አንዳንዴም "ሳዶቅ" ወይም "ዮናኪር" እየተባለ ይጠራል። ቅዱስ ኢያቄም ማለት ክፉ ከአንደበቱ የማይወጣው፣ ምጽዋትን የሚወድ፣ አምላከ እስራኤልን በንጹሕ ልቡ የሚያመልክ ሰው ነበረ። እንደ ኦሪቱ ሥርዓት ሁለቱ (ኢያቄም ወሐና) ከተጋቡ በኋላ ቶሎ መውለድ አልቻሉም። ይህ ደግሞ የወቅቱ ከባድ ፈተና ነው። በዘመድ የከበሩ፣ በጠባያቸው የተመሰገኑ፣ መልካምንም የሚሠሩ ሰዎች ልጅ ስለሌላቸው ብቻ "ኅጡአነ በረከት" እየተባሉ ከቤተ እግዚአብሔር ይገፉ፣ በአደባባይም ይነቀፉ ነበር። ምክንያቱም በብሉይ ኪዳን ልጅ አለመውለድ እንደ ኃጢአተኛ ያስቆጥር ነበር። ደግነቱ የወቅቱ ሊቀ ካህናት ቅዱስ ዘካርያስ (የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አባት) እንደ እነሱ ልጅ ያጣ በመሆኑ አብረው ይጽናኑ ነበር። የሆነው ሆኖ እኒህ ቡሩካን ሰዎች አምላከ እስራኤልን ከመለመንና ከማመስገን በቀር ሌላ ትርፍ አልተገኘባቸውም። ምንም የሞላቸውና የደላቸው ባይሆኑም ደሃን ሳያጐርሱ አይበሉም ነበር። ቅድስት ሐናን ግን "ቢወልዷት እንጂ አትወልድ።" እያሉ ጐረቤቶቿ ይሳለቁባት ነበር። ከማልቀስ በቀር ደግሞ መልስ አልነበራትም። አንድ ቀን ግን ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ሲጫወቱ ተመልክታ "ፈጣሪ ሆይ! የእንስሳትን ማኅጸን የምትከፍት ዕፅዋትንም ከባሕርያቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ:: እውነትም ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ስትል አለቀሰች። ቅዱስ ኢያቄምም ወደ ተራራ ወጥቶ ለአርባ ቀናት አለቀሰ፤ ተማለለ። ይህ ሲሆን ሁለቱም አርጅተው ነበር። ሐምሌ ሠላሳ ቀን ግን ነጭ ርግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ በማኅጸነ ሐና ስታድር አዩ። ደስ ብሏቸው ለሰባት ቀናት ሱባኤ ይዘው ቅድስት ሐና እመቤታችንን ነሐሴ ሰባት ቀን ጸነሰቻት። ይህም ለእነርሱም ለወገኖቻቸውም ታላቅ ተድላ ሆነ። ብጽዕት ሐና ግን ፈጣሪዋን ታከብረው ዘንድ በጐነትንና ንጽሕናን አበዛች። ጸንሳ ሳለም ዕውራንን አበራች፤ ድውያንን ፈወሰች። የጦሊቅ ልጅ በሞተ ጊዜም እያለቀሰች ስትዞረው ጥላዋ ቢያርፍበት አፈፍ ብሎ ተነስቶ፦ "ሰላም ለኪ እሙ ለፀሐየ ጽድቅ" ብሎ ድንግል ማርያምን "ወሰላም ለኪ እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ" ብሎ ቅድስት ሐናን አመስግኗል። ትርጉሙም ድንግልን "የፀሐየ ጽድቅ እናቱ" ሐናን "ሰማይና ምድርን ለፈጠረ አያቱ" ማለት ነው። ይህንን ያዩ አይሁድ ቅድስት ሐናን ሊገድሉ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል። ግን መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል አልፈቀደላቸውም። ግንቦት ፩ ቀንም የሰማይና የምድር ንግሥትን ሊባኖስ ተራራ ላይ ወልዳ ሽሙጥን ከሁላችንም አራቀች። ስሟን "ማርያም - የአምላክ ስጦታ" ብለው ሰይመው ለሦስት ዓመታት አሳድገዋታል። የሚገርመው በሦስቱ ዓመታት ውስጥ ቅድስት ሐና ድንግል ማርያምን ከክንዷ አውርዳት አታውቅም ነበር። አንድ ጊዜም መላእክት ወስደውባት ፍጹም አልቅሳለች። ኋላ ግን መልሰውላታል። ሌላኛው የሚደንቀው እግዚአብሔር የዓለም ውዱን ስጦታ እመ ብርሃንን ሰጣቸው። እነርሱም ይህችን ውድ ስጦታ ሳይሰስቱ ለፈጣሪ መለሱለት። "እምቅድሜክሙ አልቦ ወእምድኅሬክሙ አልቦ ከመዝ መስዋዕት ለእግዚአብሔር ዘወሃቦ።" እንዲል። ቅድስት ሐና ድንግል ወደ ቤተ መቅደስ ከገባች በኋላ የእናትነት ፍቅሯ እያገበራት ለአምስት ዓመታት እየተመላለሰች ትጐበኛት፤ ትስማት ነበር። እመቤታችን ስምንት ዓመት በሞላት ጊዜ ግን የእግዚአብሔር ጥሪ ወደ ቅድስት ሐና ደረሰ። ከክርስቶስ ልደት ስምንት ዓመታት አስቀድማ ብጽዕት እናት ሐና በዚህች ቀን ዐረፈች። ትንሽ ቆይቶም ባለቤቷ ቅዱስ ኢያቄም ተከተላት እኛም ልጆቿ "ብጽዕት ሐና ብጽዓን ይገባሻል!" እያልን እናመስግናት። ሊቃውንቱ ለእርሷ እንዲህ ብለዋልና፦ "ሰላም ለኪ ለጸሎተ ኩሉ ምዕራጋ ከመ አስካለ ወይን ዲበ ሐረጋ ሐና ብጽዕት ተፈስሒ እንበለ ንትጋ እስመ ረከብኪ ሞገሰ ወአድማዕኪ ጸጋ እምሔውተ አምላክ ትኩኒ በሥጋ።" (አርኬ) አምላከ ብጽዕት ሐና በምልጃዋ ከዘላለም እሳት ያድነን። ጸጋ በረከቷንም ይክፈለን።
            11. ያሬድ ካህን
            12. ቅዱስ ሚካኤል
              ቅዱስ ሚካኤል በጥንተ ተፈጥሮ በኢዮር ኃይላት በተባሉት ነገደ መላእክት ተሹሞ ነበር። ሳጥናኤል በካደ ጊዜ እግዚአብሔር ባወቀ አንድም በትሕትናውና ደግነቱ በዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ላይ ሁሉ ተሹሟል። ከፍጥረት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የቅዱስ ሚካኤልን ያህል ክብርና ርኅሩኅ የለም። በምልጃውም፣ በረዳትነቱም የታወቀ መልአክ ነው። መጽሐፍ "መልአከ ምክሩ ለእግዚአብሔር" ይለዋል። "ወስሙ መስተሣሕልም" ይለዋል። ቂም የሌለው ለምሕረት የሚፋጠን ደግ መልአክ ነውና። በብሉይ ኪዳን በመከራ ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ሞገስ፣ ረዳትና አዳኝ ቢሆናቸው "መጋቤ ብሉይ" ተሰኝቷል። እስራኤልን አርባ ዘመን በበርሃ መርቷል፤ መግቧልም። ቅዱስ መጽሐፍ ስለ እርሱ ብዙ ይላል። (ዘፍ. ፵፰፥፲፮ ፣ ኢያ. ፭፥፲፫ ፣ መሳ. ፲፫፥፲፯ ፣ ዳን. ፲፥፳፩ ፤ ፲፪፥፩ ፣ መዝ. ፴፫፥፯ ፣ ራዕይ. ፲፪፥፯) ደስ የሚለው ደግሞ ርኅሩኁ መልአክ ከእመቤታችን ጋር ልዩ ፍቅር አለው። ከእናቷ ማኅጸን ጀምሮ እስከ ዛሬ እነሆ አብሯት አለ። ደስ ብሎት ይታዘዛታል። ማማለድ ሲፈልግም "እመቤቴ ሆይ! ቅደሚ።" ይላታል። ወደ እሳት መጋረጃ አብረው ገብተው ለዓለም ምሕረትን፣ በረከትን ያወርዳሉ። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
            13. እግዚአብሔር አብ
              13. አእላፍ (ዘጠና ዘጠኙ) ነገደ መላእክት=
                እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን ሲፈጥራቸው በነገድ መቶ በክፍለ ነገድ አሥር አድርጓቸዋል። አቀማመጣቸውንም በሦስት ሰማያትና በአሥር ከተሞች (ዓለማት) አድርጓል። መላእክት ያሉባቸው ከተሞች ከታች ወደ ላይ 'ኤረር፣ ራማና ኢዮር' ይባላሉ። አሥሩ ክፍለ ነገድ ደግሞ ከነ አለቆቻቸው ይህንን ይመስላሉ። ፩.አጋእዝት (የቀድሞ አለቃቸው ሳጥናኤል ሲሆን አሁን የተረፉት በቅዱስ ሚካኤል ሥር ናቸው።) ፪.ኪሩቤል (አለቃቸው ኪሩብ) ፫.ሱራፌል (አለቃቸው ሱራፊ) ፬.ኃይላት (አለቃቸው ሚካኤል) ፭.አርባብ (አለቃቸው ገብርኤል) ፮.መናብርት (አለቃቸው ሩፋኤል) ፯.ሥልጣናት (አለቃቸው ሱርያል) ፰.መኳንንት (አለቃቸው ሰዳካኤል) ፱.ሊቃናት (አለቃቸው ሰላታኤል) ፲.መላእክት (አለቃቸው አናንኤል) ናቸው። ከእነዚህም አጋእዝት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌልና ኃይላት መኖሪያቸው በኢዮር (በሦስተኛው ሰማይ) ነው። አርባብ፣ መናብርትና ሥልጣናት ቤታቸው ራማ (ሁለተኛው ሰማይ) ነው። መኳንንት፣ ሊቃናትና መላእክት ደግሞ የሚኖሩት በኤረር (በአንደኛው) ሰማይ ነው። መላእክት ተፈጥሯቸው እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ ነው። አይራቡም፣ አይጠሙም፣ አይዋለዱም፣ አይሞቱም። ተፈጥሯቸውም ረቂቅ ነው። ተግባራቸው ዘወትር "ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ" እያሉ ፈጣሪያቸውን ማመስገን ነው። ምግባቸውም ይሔው ነው። ዕረፍት ብሎ ነገርን አያውቁም። "አኮቴቶሙ ዕረፍቶሙ፣ ወዕረፍቶሙ አኮቴቶሙ" እንዲል። በተጨማሪም መልአክ ማለት ተላላኪ (አገልጋይ) ነውና ከፈጣሪ ወደ ሰው ልጆች ለምሕረትም፣ ለመዓትም ይላካሉ። ምሕረትን ያወርዳሉ። ልመናን ያሳርጋሉ። ቅጡ ሲባሉም ይቀጣሉ። ስነ ፍጥረት (አራቱ ወቅቶች) እንዳይዛቡ ይጠብቃሉ። ዘወትርም ስለ ሰው ልጆች ያማልዳሉ። (ዘካ. ፩፥፲፪) ምሥጢርን ይገልጣሉ። (ዳን. ፱፥፳፩) ይረዳሉ። (ኢያ. ፭፥፲፫) እንዳንሰናከል ይጠብቃሉ። (መዝ. ፺፥፲፩) ያድናሉ። (መዝ. ፴፫፥፯) ስግደት ይገባቸዋል። (መሳ. ፲፫፥፳ ፣ ኢያ. ፭፥፲፫ ፣ ራዕ. ፳፪፥፰) በፍርድ ቀንም ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያሉ። (ማቴ. ፳፭፥፴፩) በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ሕይወትና ድኅነት ሲባል ከፈጣሪያቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ሲጠብቁና ፈቃዱን ሲፈጽሙ ይኖራሉ። ይህ ዕለት በሊቃውንት አንደበት "አእላፍ" እየተባለ ይጠራል። በሃይማኖት፣ በተልእኮትና በምስጋና የሚኖሩ ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት በአንድ ላይ የሚከበሩበት ቀን ነው። ምንም እንኳን የጐንደሩን ፊት ሚካኤልን ጨምሮ በአንዳንድ አድባራት ታቦቱ ቢኖርም ሲያነግሡ ተመልክቼ አላውቅም። ሊቃውንቱ በማኅሌት፣ ካህናቱም በቅዳሴ እንደሚያከብሯቸው ግን ይታወቃል። ኅዳር ፲፫ ቀን ዓመታዊ በዓላቸው ነው ማለት በየወሩ በአሥራ ሦስት ወርኀዊ በዓላቸው መሆኑን ያሳያልና ዘወትር ልናስባቸው ይገባል። ቅዱስ መጽሐፍ ቅዱሳን መላእክትን በስምና በማዕረግ እንደሚነግረን ሁሉ በማኅበር (በትዕይንት) አገልግሎታቸውም ይነግረናል። ለምሳሌ፦ ያዕቆብ በረዥም መሰላል ሲወጡና ሲወርዱ ተመልክቷል። (ዘፍ. ፳፰፥፲፪) ኤልሳዕ ለግያዝ አሳይቶታል። (፪ነገ. ፮፥፲፯) ዳንኤል ተመልክቷል። (ዳን. ፯፥፲) በልደት ጊዜ በዝማሬ መገለጣቸውን ቅዱስ ሉቃስ ጽፏል። (ሉቃ. ፪፥፲፫) ዮሐንስ በራዕዩ አይቷቸዋል። (ራዕይ. ፭፥፲፩) ከዚህም በላይ በብዙ የመጻሕፍት ክፍል ተጠቅሰዋል። ቅዱሳን መላእክተ ብርሃን፣ መንፈሳውያን፣ ሰባሕያን፣ መዘምራን፣ መተንብላን (አማላጆች) ተብለውም ይጠራሉና ያስቡን ዘንድ ልናስባቸው ይገባል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
              13. ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
                14. አባ ዳንኤል እረፍቱ
                  በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ በፋርስ (የአሁኗ ኢራን) ውስጥ ብዙ አስቸጋሪ ነገሥታት ተነስተው ነበር። ከእነዚህ አንዱ የሆነው የዘመኑ መሪ ክርስቶስን የማያውቅ፣ መምለኬ ጣኦት የሆነና በጠንቅ ዋዮች ተከቦ የሚኖር ነበር። እግዚአብሔር ለሁሉም የጥሪ ቀን አለውና ለሕይወት ይጠራው ዘንድ ይህንን ንጉሥ በደዌ ጐበኘው። የአምላክ ጥሪው አንዳንዴ እንደዚህ አንዳንዴም እንዲያ ነውና። ንጉሡ እንደ ታመመ ጠቢባነ ፋርስ ሊያድኑት ሞከሩ፤ ግን አልቻሉም። ሕመሙ እየባሰ ሒዶ ንጉሡ መጻጉዕ ሆነ። በጊዜው ከመተተኞች ሁሉ በጣም የሚያቀርበው አንድ ጠንቅ ዋይ በቤተ መንግሥት አካባቢ ነበርና ንጉሡ አስጠርቶ "አድነኝ" አለው። እንደማይችለው ሲያውቅ ዝም አለው። ንጉሡ መልሶ "ስማ! በቤቴ ውስጥ ከብረህ፣ ገነህ፣ የበላሁትን በልተህ፣ የጠጣሁትን ጠጥተህ የምትኖረው ለዚህ ላትሆነኝ ነው?" ብሎ ተቆጣው። የንጉሡን ቁጣ ያየው መተተኛ እንደሚገድለው ባወቀ ጊዜ "ንጉሥ ሆይ! እኔኮ አታደርገውም ብዬ ነው እንጂ መድኃኒቱን አውቀዋለሁ። "ኅሥሥ ሕፃነ ዘዋሕድ ለአቡሁ ወእሙ - ለእናት አባቱ አንድ የሆነ ሕፃን ፈልግ። እናቱ አስራው አባቱ ይረደውና በደሙ ታጥበህ ትድናለህ።" አለው። መተተኛው እንዲህ ያለው "ሲሆን ንጉሡ እንዲህ አያደርግም። ካልሆነ ግን እንዲህ ዓይነት ወላጆች አይገኙም።" ብሎ ነው። ንጉሥ ግን ላስፈልግ ባለ ጊዜ የሚያጣው ነገር የለምና አንድ ልጅ ብቻ ያላቸው ርጉማን ወላጆችን አገኘ። "አንድ ሺህ ወቄት ወርቅ ልስጣችሁ እና ልጃችሁን ሰውልኝ።" ቢላቸው "እሺ" ብለው ወደ ንጉሡ አደባባይ ወጡ። በዚያም ሕዝብ ተሰብስቦ ንጉሡም በዙፋኑ ተቀምጦ ሳለ የአምስት ዓመት ሕፃን ልጃቸውን ለገንዘብ ይሰውት ዘንድ ወላጆቹ ቀረቡ። እናቱ አጥብቃ አሰረችው። አባቱ ደግሞ ቢላውን አስሎ ቀረበ። በዚያች ሰዓት ግን ሕፃኑ ወደ ሰማይ ዓይኑን አቅንቶ እንባው እየፈሰሰ ሲጸልይ ከንፈሮቹ ይንቀሳቀሱ ነበርና ንጉሡ ተመልክቶ ልቡ ራራ። "እንዳትነኩት!" ሲልም ጮኾ ተናገረ። "ፍቱት" ብሎ ሕፃኑን አስፈትቶ በዙፋኑ ፊት ጠየቀው። "ምን እያደረክ ነበር?" ቢለው "ለሕፃን ልጅ ጋሻዎቹ ወላጆቹ ናቸው። በደል ሲያገኘኝ ወደ ወላጆቼ እንዳልጮህ ገዳዮቼ እነሱው ናቸው። ወደ ዳኛም አቤት እንዳልል አስገዳዩ ዳኛው ራሱ ነው። ስለዚህም ተስፋዬ አንዱ አምላክ እግዚአብሔር ብቻ ነበርና ወደ እርሱ በልቤ ጮህኩ።" ሲል መለሰለት። በዚህ የተገረመው ንጉሡ አንድ ሺህ ወቄት ወርቁን ከወላጆቹ ቀምቶ ለሕፃኑ ሰጥቶ በሰላም አሰናበተው። ራርቶ ሕፃኑን የፈታው ንጉሥ ሕመሙ ቢጠናበት "የዚህ ሕፃን አምላክ እኔንም እርዳኝ!" ሲል ጮኸ። በዚህ ጊዜ ጩኸቱ ወደ መንበረ ጸባኦት ደረሰለት። የእግዚአብሔር ድምጽም ወደ ታላቁ ገዳማዊ ሰው ወደ አባ ዳንኤል መጣ። "ሒደህ ፈውሰው።" አለው። አባ ዳንኤል ማለት በዘመኑ ከነበሩ ዓበይት ጻድቃን አንዱ ሲሆን መንኖ በርሃ ከገባባት ቀን ጀምሮ በፍጹም ተጸምዶ፣ በጾም፣ በጸሎትና በትሕርምት የኖረ አባት ነው። በዚያች ሰዓትም ጻድቁ በደመና ተጭኖ ከበርሃ ብሔረ ፋርስ ደረሰ። ከንጉሡም ጋር ተነጋገረ። ንጉሡ "አድነኝ?" ቢለው "እንድትድን በእውነተኛው አምላክ ማመን አለብህ።" አለው። "ክርስቶስ አምላክ መሆኑን በምን አውቃለሁ?" ብሎ በመጠየቁ ጻድቁ በፊቱ ብዙ ተአምራትን በስመ ክርስቶስ አደረገለት። ንጉሡም በክርስቶስ አምኖ በተጠመቀ ሰዓት አካሉ ታድሶ ከደዌው ድኖ ተነሳ። ሠራዊቱና ሕዝቡም እንዲሁ ተጠመቁ። አባ ዳንኤልም በደመና ወደ በርሃ ተመልሶ ከተጋድሎ በኋላ በዚህች ቀን ዐርፏል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                15. ቅዱስ ሚናስ እረፍቱ
                  ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) በምድረ ግብጽ ተወዳጅ ከሆኑ ሰማዕታት ዋነኛው ነው። ልክ በሃገራችን ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዩ ቦታ እንዳለው ሁሉ ግብጻውያን ማር ሚናስን ጠርተው አይጠግቡትም። ምክንያቱም ከታላላቅ ሰማዕታት አንዱ በመሆኑና ዛሬም ድረስ ለጆሮና ለዓይን ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ስለሚሠራ ነው። በተለይ ለታመመ፣ ለደከመና ለተጨነቀ ፈጥኖ ደራሽ፣ ባለ በጐ መድኃኒት ፈዋሽና አማላጅ ነው። "ግብጽ ውስጥ ቅዱሱን የማያውቅ ሰው ካገኛችሁ እርሱ ኦርቶዶክሳዊ አይደለም ማለት ነው። " ሲባልም ሰምተናል። በነገራችን ላይ ለቅዱሳን ተገቢውን ክብር በመስጠት፣ ታሪካቸውን በመጻፍ፣ በማጥናት፣ በመጽሔት፣ በፊልምና በመሳሰሉት ለሕዝብ በማስተዋወቅ ግብጻውያኑ ከእኛ ብዙ ርቀት ሒደዋል። ዛሬ እንኳ የምንጠቀምበትን ስንክሳር ሰማንያ ከመቶ እጁን ያዘጋጁት እነርሱ ናቸው። አባቶቻችንና እናቶቻችን ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን ግን አብዛኞቹ ተረስተው ቀርተዋል። መጽሐፈ ገድላቸውንም ብል በልቶታል። ዛሬም የቤት ሥራው የእኛ ብቻ ነው። ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ ሚናስ ትርጉሙ ታማኝና ቡሩክ ማለት ነው። በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ የደጋግ ክርስቲያኖች ልጅ። በልጅነቱ የቅድስና ሕይወትን ያጣጣመ። በዘመኑ ሰው እጅግ ተወዳጅ የነበረ። ሃብትን፣ ክብርን፣ ሥልጣንን ንቆ በጾምና በጸሎት የተወሰነ። በመጨረሻም በክርስቶስ ስላመነ አላውያን የገደሉት ሰማዕት ነው። እርሱ ሰማዕት ከሆነ ከበርካታ ዘመናት በኋላ ምዕመናን ክቡር አካሉን ፈልገው ያጡታል። የሚገለጥበት ጊዜ ሲደርስ ግን እርሱ የተቀበረበት ምድረ በዳ የበጐችና የእረኞች መዋያ ነበርና ተአምራትን አደረገ። አንድ እረኛ በጐቹ ድውያን ሆኑበት። በዚያ ሰሞን ከቅዱሱ መቃብር ላይ ጠበል ፈልቆ ነበርና እረኛው ተርታ ውኃ ነው ብሎ በጎቹን ሲያጠጣቸው አንዱ ድውይ በግ ወደ ጠበሉ በመዘፈቁ ዳነ። በዚህ የተገረመው እረኛ ሁሉንም የታመሙ በጐቹን አምጥቶ ነከራቸው፤ እነርሱም ተፈወሱ። ይህ ዜና በምድረ ግብጽ ሲሰማ ድውያን ሁሉ እየመጡ ይፈወሱ ገቡ። ግን እነሱም ሆነ እረኛው ምክንያቱን ማወቅ አልቻሉም። ነገሩ በሮም ንጉሥ ዘንድ ሲሰማ ሴት ልጁን ከሠራዊቱ ጋር ላካት። ምክንያቱም እርሷ ከብዙ ዘመን ጀምራ መጻጉዕ ነበረችና ፈውስን አጥታ ነበር። መጥታ ተጠመቀች፤ ፈጥናም ተፈወሰች። እርሷ ግን እንደ ሌሎች ያዳናትን ማንነት ሳታውቅ መሔድ አልፈለገችምና ሱባዔ ገባች። ቅዱስ ሚናስ በሌሊት ራዕይ መጥቶ ሥጋው እንዳለ ነገራት። እርሷም መሬቱን አስቆፍራ የቅዱሱን አካል በክብር አስወጣች። ከዚያም በንጉሡ ትዕዛዝ ምድረ በዳው ከተማ እንዲሆን ተቀየረ። ስሙም "መርዩጥ" ተባለ። ጠበሉ የነበረበት ቦታም ላይ የማር ሚናስ ቤተ ክርስቲያን ታንጾበት ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                18. ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ እረፍቱ ከ12ተ ሐዋርያት አንዱ
                  እንደ አባቶቻችን ትርጉም 'ፊልጶስ' ማለት 'መፍቀሬ አኃው - ወንድሞችን የሚወድ' ማለት ሲሆን ከአሥራ ሁለቱ ቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ ነው። (ማቴ. ፲፥፫) በዚህ ስም የሚጠራ ሐዋርያ ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ ነበር። እርሱም ጃንደረባውን ባኮስን ያጠመቀው ነው። አንዳንዴ የሁለቱ ታሪክ ሲቀላቀል እንሰማለን። ለሁሉም ይህኛው ቅዱስ ፊልጶስ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሆኖ ምሑራነ ኦሪት ከሚባሉትም አንዱ ነበር። በወቅቱ ገማልያል የሚሉት ክቡርና ምሑረ ኦሪት በርካታ ምሑራነ ኦሪትን አፍርቶ ነበር። እንደ ምሳሌም ቅዱሳኑን "ጳውሎስን፣ ኒቆዲሞስን፣ ናትናኤልን፣ እስጢፋኖስንና ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስን" መጥቀስ እንችላለን። ቅዱስ ፊልጶስ ነገዱ ከእስራኤል ሲሆን ተወልዶ ያደገው በቤተ ሳይዳ ነው። ኦሪትን ተምሮ በመንገድ ዳር ቁጭ ብሎ 'መሲሕ ቀረ' እያለ ሲተክዝ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ ደረሰ። ትክ ብሎ አይቶት "ተከተለኝ" አለው። (ዮሐ. ፩፥፵፬) ቅዱስ ፊልጶስም ያለ ማመንታት ሁሉን ትቶ በመንኖ ጥሪት ተከተለው። በዚህ ዓይነት ጥሪ መድኃኒታችን ቅዱስ ማቴዎስንም ጠርቶታል። (ማቴ. ፱፥፱) ቅዱስ ፊልጶስ ጌታን ከተከተለ በኋላ ሥራ አልፈታም። ወዲያውኑ ሒዶ ለናትናኤል (ቀናተኛው ስምዖን) ሰበከለት እንጂ። "ሙሴ በኦሪት፣ ነቢያትም የተነበዩለትን መሲሕን አግኝቸዋለሁ።" አለው። ይህ አነጋገሩም ምሑረ ኦሪት እንደ ነበር በእርግጥ ያሳያል። (ዮሐ. ፩፥፵፮) ቅዱስ ናትናኤልም ምሑር ነውና "ከናዝሬት ደግ እንዴት ይወጣል?" ቢለው ቅዱስ ፊልጶስም መልሶ "ነዐ ትርአይ - ታይ ዘንድ ና።" አለው። ናትናኤልም ሒዶ በጌታ አመነ። ቅዱስ ፊልጶስ አገልጋይ እንደ መሆኑ መጠን በዮሐንስ ወንጌል ተደጋግሞ ስሙ ተጠቅሷል። በተለይ ደግሞ ጌታ የአምስት ገበያ ሕዝብን አበርክቶ ሲመግብ አስቀድሞ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። እርሱ ግን "ጌታ ሆይ! የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ ብንገዛም አንዘልቀውም።" ብሎ ነበር። በኋላ ግን የጌታን ድንቅ ተአምር ተመለከተ። (ዮሐ. ፮፥፭) በተለይ ደግሞ በሐዋርያት አበው መካከል ለጌታ እንደ እንደራሴ ሆኖ ያገለግል እንደ ነበርም ተጠቅሷል። ሰዎች ጌታን ማግኘት ሲፈልጉ እሱና እንድርያስን ያናግሩ ነበር። (ዮሐ. ፲፪፥፳) አንድ ጊዜ ግን እስካሁን ሊቃውንትን የምታስደምም ጥያቄ ጠይቆ ነበር። አጠያየቁ ደግሞ ፍጹም የዋሕ እንደ ሆነ ያሳያል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ባሕርይ አባቱ አብ እየነገራቸው ሳለ ቅዱስ ፊልጶስ ከመካከል ተነስቶ "እግዚኦ አርእነሁ ለአብ ወየአክለነ" ልክ ወልድን በዓይኑ እንዳየ ሁሉ አብን ሊያይ ቸኩሎ "አቤቱ ስለ አብ የሰማነው ይበቃልና አሳየን?" ብሎታል። (ዮሐ. ፲፰፥፰) ጌታችን ግን "ዘርእየ ኪያየ ርዕዮ ለአብ - እኔን ያየ አብን አይቷል።" (ዮሐ. ፲፬፥፱) ብሎ ምሥጢረ ባሕርዩን፣ አንድነቱን ሦስትነቱን አስረድቶታል። ቅዱስ ፊልጶስም ጌታን እስከ ሕማሙ አገልግሎ፣ ቅድስት ትንሣኤውን አይቶ፣ ለአርባ ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን፣ ትምሕርተ ኅቡዓትን ተምሮ፣ ቅዱስ መንፈሱን ከሰባ ሁለት ልሳን ጋር ነስቶ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል። ቅዱሳን ሐዋርያት ዓለምን በእጣ ሲካፈሉ ለእርሱ አፍራቅያ (አፍሪካ) ደርሳዋለች። ስለዚህም በምድረ አፍሪካ ወንጌልን ከሰበኩ ሐዋርያት አንዱ ነው። በአፍራቅያና በቀድሞው የኃምስቱ አሕጉር ግዛት ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጐ ብዙዎችን ወደ መንጋው (ወደ ክርስትና በረት) ቀላቀለ። ለበርካታ ዓመታትም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተዘዋወረ ወንጌልን ሲሰብክ፣ ብርሃነ ክርስቶስን ሲያበራ፣ ነፍሳትንም ሲማርክ ቆየ። ገድለ ሐዋርያት እንደሚለው የቅዱስ ፊልጶስ ፍጻሜው በሰማዕትነት እንደ ሆነ ቢታወቅም የትኛው ሃገር ውስጥ እንደ ሆነ መለየት አልተቻለም። ዜናው ግን እንዲህ ነው። በአንዲት ሃገር ውስጥ ገብቶ ሰበከ፤ ብዙዎችንም አሳመነ። ያላመኑት ግን ይዘው አሰቃዩት፤ ገረፉት። "በክርስቶስ እመኑ እባካችሁ!" እያለ እየለመናቸው ዘቅዝቀው ሰቅለው ገደሉት። ከዚያም በእሳት እናቃጥላለን ሲሉ ቅዱስ መልአክ ከእጃቸው ነጥቆ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው። በዚህ የደነገጡት ገዳዮቹ ለሦስት ቀናት ጾሙ፤ ተማለሉ። በዚህ ምክንያት የቅዱሱ ሥጋ ተመልሶላቸው ገንዘው ቀብረውት በክርስቶስ አምነዋል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                21. ፅዮን ማርያም/የእመቤታችን በዓል/
                  "ጽዮን" ማለት "ጸወን - አምባ - መጠጊያ" ማለት ነው። አንድም በምሥጢሩ "ማሕደረ አምላክ" ማለት ነው። ጽዮን የሚለው ስም በቁሙ ለቅዱስ ዳዊት ተራራና ለኪዳኑ ጽላት ሲያገለግል በትንቢታዊ ምሥጢሩ ግን ለድንግል ማርያም፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለዘላለማዊት ርስት ያገለግላል። እግዚአብሔር ከዘመነ አበው በኋላ በጊዜው ለእስራኤላውያን ክብር፣ ሞገስ፣ አምባ የምትሆናቸውን ታቦተ ጽዮንን በቅዱስ ሙሴ አማካኝነት ሰጥቷቸዋል። (ዘጸ. ፴፩፥፲፰) ከዚያም ለአምስት መቶ ዓመታት ከእነርሱ ጋር በመሆኗ በፈጣሪና በእነርሱ መካከል ድልድይ ሆና ኖራለች። ከዚያም ባለቤቱ ሲፈቅድ በዘመነ ሳባ በቀዳማዊ ምኒልክ (እብነ መለክ - እብነ ሐኪም) አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ መጥታለች። እነሆ በሃገራችን የሦስት ሺህ ዓመት ቆይታዋን ልትደፍን የቀራት ጥቂት ዓመታት ብቻ ናቸው። ጌታ እንደ ፈቀደ ቅዱስ መስቀሉንና ታቦተ ጽዮንን ይዘን ይሔው በቸርነቱ እንኖራለን። ያም ሆኖ ታቦተ ጽዮንን መስረቅ የሚፈልጉ ብዙ ቀሳጢዎች እንዳሉ እናውቃለን። ግን አንጨነቅም። ምክንያቱም የመጣችውም የምትጠበቀውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነውና እንጸልያለን እንጂ አንጨነቅም። በተለያየ ወሬም ራሳችንን አናማጥንም። ባለቤቱ እንድትሔድ ከፈቀደ ደግሞ ማንም ጉልበተኛ አያስቀራትም። ታቦተ ጽዮን ብዙ ጊዜ "ጽላተ ኪዳን፣ ታቦተ ሕጉ" እየተባለች ትጠራለች። "ጽሌ" ማለት "ሰሌዳ" እንደ ማለት ሲሆን "ጽላት" ደግሞ በብዙ ቁጥር ነው። "ኪዳን" ደግሞ በፈጣሪና በሰው ልጆች መካከል ያለ "ውል - ስምምነት" ነው። "ታቦት" ማለት "ማሕደር - ማደሪያ" እንደ ማለት ነው። ሕጉ የተጻፈባቸውን ሰላድው "ጽላት" ስንላቸው የጽላቱ ማደሪያ ደግሞ "ታቦት" ይባላል። ጽላት (ታቦትን) ያመጣ ፈጣሪ ነው። በሐዲስ ኪዳንም ምሥጢርና ሐተታ ቢኖረውም ሁለት ቦታ ላይ ስለ ታቦት ተጠቅሶ እናገኛለን። (፪ቆሮ. ፮፥፲፮ ፣ ራእይ. ፲፩፥፲፱) በመጨረሻም ኅዳር ፳፩ ቀን ጽዮን ማርያምን የምናከብርባቸውን ምክንያቶች እንመለከታለን። በዚህች ቀን፦ ፩.ታቦተ ጽዮን (ጽላተ ኪዳን) ለሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ መሰጠቷን እናስባለን። ይህ ሲሆንም ቅዱስ ሙሴ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ጾሞ እንደ ተቀበለ ሳንዘነጋ ማለት ነው። (ዘጸ. ፴፩፥፲፰ ፣ ዘዳ. ፱፥፲፱) ፪.በዘመነ ኤሊ ሊቀ ካህናት ታቦተ ጽዮን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሕዛብ (ኢሎፍላውያን) እጅ ተማርካለች። ግን ደግሞ ዳጐንን ቀጥቅጣዋለች። (፩ሳሙ. ፭፥፩) ፫.በዘመነ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በአሚናዳብ ሠረገላ ሁና ከአቢዳራ ቤት ስትመጣ ቅዱሱ ንጉሥ በታላቅ ሐሴት በፊቷ ዘመረ፤ አገለገለ። ምድራዊ ክብሩን እስኪረሳ ድረስ ለታቦተ አምላክ ተቀኘላት። በዚህም ሜልኮል ንቃው ማኅጸኗ ተዘግቷል። (፩ዜና. ፲፭፥፳፭) ሊቃውንትም "ድንግል እመቤታችን ማርያም በትንቢት መነጽር ተመልክቷል።" ብለውናል። "ሰላም ለኪ ማርያም እምነ ዘሰመይናኪ ጸወነ ሶበ እምርሑቅ ርእየ ዘጽላሎትኪ ስነ ለቢሶ ዳዊት ልብሰ ክብር ዘየኀይድ ዓይነ ቅድመ ታቦተ ሕግ ኀለየ ወዓዲ ዘፈነ።" እንዲል። (አርኬ ዘኅዳር ፳፩) ፬.በዘመነ ንጉሥ ሰሎሞን (መፍቀሬ ጥበብ) ግሩም የሆነ ቤተ መቅደስ ተሰርቶላት ስትገባ ታላቅ ሐሴት ተደርጓል። እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ንጉሡን አነጋግሯል። (፪ዜና. ፭፥፩ ፣ ፩ነገ. ፰፥፩) ፭.በዚያው ዘመንም በፈጣሪ ፈቃድ ንጉሥ ምኒልክ ቀዳማዊ (ዕብነ ሐኪም) ታቦተ ጽዮንን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል። ፮.በዘመነ አፄ ባዜን (በ፬ ዓ/ም አካባቢ) አማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያም ወደ አክሱም ጽዮን በስደት መጥታ ገብታለች። በዚህ ጊዜም ሁለቱ ጽዮኖች ሲገናኙ ታላቅ ብርሃን አክሱምን ውጧታል። ፯.በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ነገሥት ጻድቃን አብርሐ ወአጽብሐ አሥራ ሁለት መቅደሶች ያሏትን ግሩም ቤተ ክርስቲያን ለእመ ብርሃን ሠርተው በዚሁ ቀን በጌታችን ተቀድሷል። ፰.በተጨማሪም በየጊዜው ማለትም በዮዲት ጉዲትና በግራኝ አማካኝነት ስትፈርስ ወደ ዝዋይ ትሰደድ ነበር። ተመልሳ ስትታነጽም ቅዳሴ ቤቷ የሚከበረው ኅዳር ፳፩ ቀን ነው። በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ይህ በዓል ልዩ ነው። አማናዊት ጽዮን እመ ብርሃን ድንግል ማርያምን እንዲህ እንላታለን። "ቅድስት" የሚለው ቃል ለሁሉም ቅዱሳት እናቶች ቢሰጥም ቅሉ ለድንግል ማርያም ሲሰጥ ግን ትርጉሙ ይለያል። እርሷ "ቅድስተ ቅዱሳን፣ ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቡርክት እምቡሩካን፣ ኅሪት እምኅሩያን" ናትና። ከሰው ልጆችም ሁሉ ትበልጣለች። ይቅርና የሰው ልጅን ንጹሐን መላእክትንም በንጽሕናና በቅድስና ትበልጣቸዋለች። እርሷ እመ ብርሃን፣ የአምላክ እናቱ፣ የሰውነታችን መመኪያ ናትና። እመቤታችንን "ቅድስት" ስንል "ጽንዕት፣ ንጽሕት፣ ክብርት፣ ልዩ" ማለታችን ነው። ፩."ንጽሕት" ትባላለች። ሌሎች ቅዱሳን ቢነጹ ከገቢር፣ ከነቢብ ኃጢአት ነው እንጂ ከኃልዮ ኃጢአት አይደለም። እርሷ ግን ከነቢብ፣ ከገቢር፣ ከኃልዮ ንጽሕት ናት። "ለመኑ ተውኅቦ ተደንግሎ ኅሊና ለመላእክትሂ ኢተክህሎሙ - ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ከሰው ልጆች ለማን ተሰጠው? ይህስ ለመላእክትም አልተቻላቸውም።" እንዲል። (ተአምረ ማርያም) ፪."ጽንዕት" እንላታለን። ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው እንጂ በኋላ በጊዜው ተፈትሆ አለባቸው። እመቤታችን ግን ቅድመ ጸኒስ፣ ጊዜ ጸኒስ፣ ድኅረ ጸኒስ፤ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና። "ጽንዕት በድንግልና አልባቲ ሙስና" እንዳላት። (ቅዱስ ያሬድ) ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም "ወትረ ድንግል ማርያም - ማርያም ዘላለማዊት ድንግል ናት።" እንዳለ። (መጽሐፈ ቅዳሴ) ፫.ድንግልን "ክብርት" እንላታለን። ሌሎች ሴቶች ቢከብሩ ጻድቃን ሰማዕታትን፣ ነቢያት ሐዋርያትን ወልደው ነው። እመቤታችንን ግን የምናከብራት "ወላዲተ አምላክ - የአምላክ እናቱ" ብለን ነውና። ፬.እመቤታችንን "ልዩ" እንላታለን። ከእርሷ በቀር እናት ሁና ድንግል፣ እመቤት ሁና አገልጋይ የሆነች፣ በድንግልና ወልዳ ወተትን (ሐሊበ ድንግልናዌን) ያስገኘች ሌላ ሴት የለችምና። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                24. ሀያአራቱ ካህናተ ሰማይ /ደብረ ሊባኖስ/
                  እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን ሲፈጥራቸው በነገድ መቶ በክፍለ ነገድ አሥር አድርጓቸዋል። አቀማመጣቸውንም በሦስት ሰማያትና በአሥር ከተሞች (ዓለማት) አድርጓል። መላእክት ያሉባቸው ከተሞች ከታች ወደ ላይ 'ኤረር፣ ራማና ኢዮር' ይባላሉ። አሥሩ ክፍለ ነገድ ደግሞ ከነ አለቆቻቸው ይህንን ይመስላሉ። ፩.አጋእዝት (የቀድሞ አለቃቸው ሳጥናኤል ሲሆን አሁን የተረፉት በቅዱስ ሚካኤል ሥር ናቸው።) ፪.ኪሩቤል (አለቃቸው ኪሩብ) ፫.ሱራፌል (አለቃቸው ሱራፊ) ፬.ኃይላት (አለቃቸው ሚካኤል) ፭.አርባብ (አለቃቸው ገብርኤል) ፮.መናብርት (አለቃቸው ሩፋኤል) ፯.ሥልጣናት (አለቃቸው ሱርያል) ፰.መኳንንት (አለቃቸው ሰዳካኤል) ፱.ሊቃናት (አለቃቸው ሰላታኤል) ፲.መላእክት (አለቃቸው አናንኤል) ናቸው። ከእነዚህም አጋእዝት፣ ኪሩቤል፣ ሱራፌልና ኃይላት መኖሪያቸው በኢዮር (በሦስተኛው ሰማይ) ነው። አርባብ፣ መናብርትና ሥልጣናት ቤታቸው ራማ (ሁለተኛው ሰማይ) ነው። መኳንንት፣ ሊቃናትና መላእክት ደግሞ የሚኖሩት በኤረር (በአንደኛው) ሰማይ ነው። መላእክት ተፈጥሯቸው እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ ነው። አይራቡም፣ አይጠሙም፣ አይዋለዱም፣ አይሞቱም። ተፈጥሯቸውም ረቂቅ ነው። ተግባራቸው ዘወትር "ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ" እያሉ ፈጣሪያቸውን ማመስገን ነው። ምግባቸውም ይሔው ነው። ዕረፍት ብሎ ነገርን አያውቁም። "አኮቴቶሙ ዕረፍቶሙ፣ ወዕረፍቶሙ አኮቴቶሙ" እንዲል። በተጨማሪም መልአክ ማለት ተላላኪ (አገልጋይ) ነውና ከፈጣሪ ወደ ሰው ልጆች ለምሕረትም፣ ለመዓትም ይላካሉ። ምሕረትን ያወርዳሉ። ልመናን ያሳርጋሉ። ቅጡ ሲባሉም ይቀጣሉ። ስነ ፍጥረት (አራቱ ወቅቶች) እንዳይዛቡ ይጠብቃሉ። ዘወትርም ስለ ሰው ልጆች ያማልዳሉ። (ዘካ. ፩፥፲፪) ምሥጢርን ይገልጣሉ። (ዳን. ፱፥፳፩) ይረዳሉ። (ኢያ. ፭፥፲፫) እንዳንሰናከል ይጠብቃሉ። (መዝ. ፺፥፲፩) ያድናሉ። (መዝ. ፴፫፥፯) ስግደት ይገባቸዋል። (መሳ. ፲፫፥፳ ፣ ኢያ. ፭፥፲፫ ፣ ራዕ. ፳፪፥፰) በፍርድ ቀንም ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያሉ። (ማቴ. ፳፭፥፴፩) በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ሕይወትና ድኅነት ሲባል ከፈጣሪያቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ሲጠብቁና ፈቃዱን ሲፈጽሙ ይኖራሉ። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህች ዕለት የሃያ አራቱን ቅዱሳን ካህናተ ሰማይን መታሰቢያ ታደርጋለች። እኒህ ቅዱሳን መላእክት በነገድ አሥር ሲሆኑ "ሱራፌል" እየተባሉ ይጠራሉ። መኖሪያቸው በኢዮር ነው። ነገር ግን ሃያ አራቱ አለቆቻቸው ተመርጠው በመሪያቸው በቅዱስ ሱራፊ አለቅነት በጽርሐ አርያም ያገለግላሉ። በቀናች ሃይማኖት ትምህርት ሁሉም ቅዱሳን መላእክት ለእግዚአብሔር ቅርብ ቢሆኑም በነጠላ የቅዱስ ሚካኤልን ያህል በነገድ ደግሞ የኪሩቤል (አራቱ እንስሳ) እና የሱራፌልን (ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ) ያህል ቅርብ የለም። ሃያ አራቱ ቅዱሳን ካህናት ሥራቸው፦ ፩.እንደ ሞገድ ከአንደበታቸው ምስጋና እየወጣ ጧት ማታ ፈጣሪያቸውን ይቀድሱታል። (ኢሳ. ፮፥፩ ፣ ራእይ ፬፥፲፩ ፤ ፭፥፲፩) ፪.የሥላሴን መንበር ያለ ማቋረጥ ያጥናሉ። (ራእይ ፭፥፰) ፫.የሰው ልጆችን በተለይም የቅዱሳንን ጸሎት በማዕጠንታቸው ያሳርጋሉ። (ራእይ ፰፥፫) ፬.የረከሱትን ይቀድሳሉ። (ኢሳ. ፮፥፮) ፭.ዘወትርም ለሰው ልጆች ምሕረትን ሲለምኑ ይኖራሉ። (ዘካ. ፩፥፲፪) ስለ እነዚህ ቅዱሳን ካህናት (ሱራፌል) ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ብዙ ይላል። ለምሳሌ፦ ዐቢይ ነቢይ ወልዑለ ቃል ኢሳይያስ ፈጣሪው ተቀይሞት በነበረበትና ዖዝያን በሞተበት ወራት ግሩማን ሆነው ሥላሴን "ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ" እያሉ ዙሪያውን ከበው ሲያመሰግኑ ሰምቷል። ከእነርሱም አንዱ (ሱራፊ) መጥቶ በጉጠት እሳት ከንፈሩን ዳስሶ ከለምጹ አንጽቶታል። (ኢሳ. ፮፥፩) አቡቀለምሲስ የተባለ ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ በግርማ በአምሳለ አረጋዊ ተመልክቷቸዋል። (ራእይ ፬፥፬) አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን የመሰሉ ቅዱሳን ሊቃውንት ደግሞ በጣዕመ ምስጋናቸው ሲገልጿቸው፦ "ካህናተ ሰማይ ቅውማን በዐውዱ አክሊላቲሆሙ ያወርዱ ቅድመ መንበሩ እንዘ ይሰግዱ ይርዕዱ ከመ ኢይዝብጦሙ ሶበ ይበርቅ ነዱ።" ብለዋል። (መጽሐፈ ሰዓታት) ትርጉሙም "በፈጣሪ መንበር ዙሪያ የሚቆሙ የሰማይ ካህናት አክሊለ ክብራቸውን አውርደው በመንበሩ ፊት ይሰግዳሉ። መብረቀ መለኮቱ በተገለጠ ጊዜም በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ።" ማለት ነው። ግሩም ባሕርየ ሥላሴን ሊቋቋመው የሚችል ፍጡር የለምና። ቅዱሳን ካህናተ ሰማይ በምስጋናቸው፣ በማዕጠንታቸውና በምልጃቸው ክቡራን ናቸውና ዘወትር ልናከብራቸው ይገባናል። የረከሰ ማንነታችንን ይቀድሱ ዘንድ፣ በምልጃቸውም ዘንድ እንድንታሰብ፣ ጸሎታችንንም ያሳርጉልን ዘንድ እንለምናቸው። ኅዳር ፳፬ ቀን ዓመታዊ በዓላቸው ነው ማለት በየወሩ በ፳፬ ወርኀዊ በዓላቸው መሆኑን ያሳያልና ዘወትር ልናስባቸው ይገባል። በተለይ ያዘነን ልብ ደስ ያሰኛሉና እንደ ሊቃውንት እንዲህ ብለን እንጠራቸዋለን። "ሰላም ለክሙ ካህናተ ሕጉ ወትዕዛዙ ለእግዚአብሔር ቃል ዘጶዴሬ ሥጋ አራዙ እምነቅዐ አፉክሙ ሐሴት ዘኢይነጽፍ ዉሒዙ ኪያየ ኅዙነ ወትኩዘ ልብ ናዝዙ ወበክንፍክሙ ብርሃናዊ ዐውድየ ሐውዙ።" (አርኬ ዘኅዳር ፳፬) ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                26. አቡነ ሀብተማርያም /ደብረሊባኖስ/
                  እኒህ ጻድቅ ደግሞ የሃገራችን ኮከበ ገዳም ናቸው። "ጽድቅና ትሩፋት እንደ ሃብተ ማርያም" እንዲሉ አበው። ባሕር ከሆነ ጣዕመ ሕይወታቸው ጥቂቱን ለበረከት እንካፈል። ጻድቁ መካነ ሙላዳቸው ሽዋ (የራውዕይ) ውስጥ ሲሆን አባታቸው ፍሬ ቡሩክ እናታቸው ደግሞ ቅድስት ዮስቴና ትባላለች። በተለይ ቅድስት ዮስቴና እጅግ ደመ ግቡ፣ ምጽዋትን ወዳጅ፣ ቡርክት ሴት ነበረች። እንዲያውም ከጻድቁ መወለድ በፊት መንና ጭው ካለ በርሃ ገብታ ነበር። ግን የበቃ ግኁስ አግኝቷት "ከማኅጸንሽ ደግ የሥላሴ ባርያ አለና ተመለሽ።" ብሏት እንደ ገና ተመልሳለች። ጻድቁን ወልዳ አሳድጋም እንደ ገና መንና በተጋድሎ ኑራ ሰባት አክሊላትን ተቀብላ ዐርፋለች። ወደ ጻድቁ ዜና ሕይወት ስንመለስ አቡነ ሃብተ ማርያም ገና ሕፃን እያሉ ከእናታቸው ጋር ቆመው ሲያስቀድሱ "እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ" ሲባል ይሰማሉ። ይህችን ጸሎት በሕፃን አንደበታቸው ይዘው ሌሊት ሌሊት እየተነሱ "ማረን እባክህን?" እያሉ ይሰግዱ ነበር። የአምስት ዓመት ሕፃን እንዲህ ሲያደርግ ማየቱ በእውነት ይደንቃል። ትንሽ ከፍ ብለው በእረኝነት ሳሉም ፍጹም ተሐራሚና ጸዋሚ ነበሩ። ጸጋው ስለ በዛላቸውም ልጅ ሆነው ብዙ ተአምራትን ሰርተዋል። የፈጣሪውን ስም ያቃለለውን አንድ እረኛም በዓየር ላይ ሰቅለው አውለውታል። ከዚያ ግን ለአካለ መጠን ሲደርሱ ወደ ትምህርት ቤት ገብተው መጻሕፍትን አጥንተው መንነዋል። በአባ መልከ ጼዴቅ እጅ ከመነኮሱ በኋላ የሠሩትን ትሩፋትና የነበራቸውን ተጋድሎ ግን የኔ ብጤ ደካማ ሰው ሊዘረዝረው አይችልም። ባሕር ውስጥ ሰጥመው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ። በየቀኑ አራቱን ወንጌልና መቶ ሃምሳውን መዝሙረ ዳዊት ይጸልያሉ። (መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ታላቅ ጸሎት ነው።) በአርባ ቀናት ቀጥሎም በሰማንያ ቀን አንዴ ብቻ ይመገባሉ። ምግባቸው ደግሞ ሣርና ቅጠል ብቻ ነው። በየዕለቱ ያለ ማስታጐል ማዕጠንት ያሳርጋሉ። (ካህን ናቸውና) ዘወትር በንጽሕና ቅዱስ ሥጋውን ይበላሉ፤ ክቡር ደሙን ይጠጣሉ። በፍጹም በልባቸው ውስጥ ቂምን፣ መከፋትን አላሳደሩም። በእነዚህና በሌሎች ትሩፋቶቻቸው ደስ የተሰኘ ጌታም ለጻድቁ የእሳትና የብርሃን ሠረገላን ሰጥቷቸው በዚያ እየበረሩ ኢየሩሳሌም ይሔዱ ነበር። ከብዙ የተጋድሎ ዘመናት በኋላም የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ አዕላፍ መላእክትን አስከትሎ መጥቶ አላቸው። "ስለ እኔ ረሃብና ጥምን ስለ ታገስክ፣ ስለ ምናኔህ፣ ስለ ተባረከ ምንኩስናህ፣ ስለ ንጹሕ ድንግልናህ፣ ቂምና በቀልን ስላለመያዝህ፣ ስለ ንጹሕ ክህነትህና ማዕጠንትህ፣ ቅዱስ ወንጌልን በፍቅር ስለ ማንበብህ ሰባት አክሊላትን እሰጥሃለሁ።" "በሰማይም ከመጥምቁ ዮሐንስ ጐን አምስት መቶ የእንቁ ምሰሶዎች ያሉበትን አዳራሽ ሰጥቼሃለሁ። በስምህ የሚለምኑ፣ በቃል ኪዳንህ የሚማጸኑትንም ሁሉ እንድምርልህ 'አማንየ! በርእስየ!' ብዬሃለሁ።" አላቸው። ቅዱሳን መላእክትም "ሃብተ ማርያም ወንድማችን" ሲሉ አቀፏቸው። ጌታ ግን በዚያች ሰዓት አንድም ሦስትም ሆኖ ታያቸውና አቅፎ ሦስት ጊዜ ሳማቸው። ከፍቅሩ ጽናትም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች፤ በዝማሬም ወሰዷት። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                26. አባ ኢየሱስ ሞአ (እረፍቱ)
                  እግዚአብሔር በአሥራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እነ አቡነ ኢየሱስ ሞዐን ባያስነሳ ኑሮ ምናልባትም ዛሬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በምናያት መንገድ ላናገኛት እንችል ነበር። እውነተኛ አባቶቻችን ፈጽሞ ከሚቆረቁራቸው ነገር አንዱ የጻድቅና ሐዋርያዊ አባት አቡነ ኢየሱስ ሞዐ መዘንጋት ነው። እርሳቸው ፍሬ ሃይማኖት ሆነው ከጽድቅ ፍሬአቸው አዕላፍ ቅዱሳንን ወልደው ሃገራችን በወንጌል ትምህርትና በገዳማዊ ሕይወት እንድታሸበርቅ አድርገዋል። እስኪ በዕለተ ዕረፍታቸው ስለ ጻድቁ ጥቂት ነገሮችን እናንሳ። አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ የተወለዱት ጐንደር የድሮው ስማዳ (ዳኅና) አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው ዘክርስቶስና እግዚእ ክብራ ይባላሉ። የተወለዱት በ፲፪፻፲ ዓ/ም ነው። ነገር ግን አንዳንድ ምንጮች በ፲፩፻፺፮ ዓ/ም ያደርጉታል። ጻድቁ ከክርስቲያን ወላጆቻቸው ጋር እንደሚገባ አድገዋል። በልጅነታቸው በብዛት ወላጆቻቸውን ያግዙ ነበር። በትርፍ ጊዜአቸው ደግሞ ትምሕርተ ሃይማኖትንና ሥርዓቱን ያጠኑ ነበር። በ፲፪፻፵ ዓ/ም ግን (ማለትም ሠላሳ ዓመት ሲሞላቸው) ይህቺን ዓለም ይተዋት ዘንድ አሰቡ። አስበውም አልቀሩ ፈጣሪን እየለመኑ ደብረ ዳሕሞ ገቡ። በወቅቱ ዳሞ የትምህርትና የምናኔ ማዕከል ከመሆኑ ባሻገር የአቡነ አረጋዊ አምስተኛ የቆብ ልጅ ካልዕ ዮሐኒ ነበሩና የእርሳቸው ደቀ መዝሙር ሆኑ። አቡነ ኢየሱስ ሞዐ በደብረ ዳሞ በነበራቸው ቆይታ ቀን ቀን ሲታዘዙ፣ ሲፈጩ፣ ውኃ ሲቀዱ ውለው ሌሊት እኩሉን በጸሎት በስግደትና የቀረውን ሰዓት ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመገልበጥ አሳለፉ። በመጨረሻም ልብሰ ምንኩስናን ለበሱ። ይህን ጊዜ ሠላሳ ሰባት ዓመታቸው ሲሆን ዘመኑም ፲፪፻፵፯ ዓ/ም ነው። ወዲያውም በዳሞ ሳሉ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦ "ወደ ወሎ ሐይቅ ሒድ፤ ብዙ የምትሠራው አለና።" አላቸው። በአንዴም ከዳሞ (ትግራይ) ነጥቆ ሐይቅ እስጢፋኖስ (ወሎ) አደረሳቸው። በዚያም ለሰባት ዓመታት በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ መቅደስ በተጋድሎ፣ በስብከተ ወንጌል፣ በማዕጠንትና ሐይቁ ውስጥ ሰጥሞ በመጸለይ ኖሩ። ቅድስናቸውን የተመለከቱ አበውም በግድ አበ ምኔት አድርገው ሾሟቸው። ይህ ነው እንግዲህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ትልቁ መሠረት የተጣለበት አጋጣሚ። ነገሩ እንዲህ ነው፦ ስም አጠራሯ የከፋ ዮዲት ጉዲት ለአርባ ዓመታት ሃገሪቱን እንዳልነበረች ብታደርጋት ክርስትና ተዳከመ፤ ባዕድ አምልኮም ነገሠ። አቡነ ኢየሱስ ሞዐ (ትርጉሙ ኢየሱስ ክርስቶስ አሸነፈ ማለት ነው።) ደግሞ ሃይማኖታቸው የቀና ከስምንት መቶ በላይ ክርስቲያኖችን ሰበሰቡ። በሃገሪቱ ትልቅና የመጀመሪያው ሊባል የሚችል ቤተ መጻሕፍት አደራጁ። እነዚያን አርድእት በቅድስናና በትምህርት አብስለው አመነኮሱና "ሒዱ! ሃገሪቱን ታበሩ ዘንድ ተጋደሉ።" ብለው አሰናበቷቸው። ከእነዚህ መካከልም ታላላቁን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን፣ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልን እና የኋላውን ፍሬ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫን መጥቀስ እንችላለን። በዚህም ምክንያት ጻድቁ "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን - አእላፍ ቅዱሳንን የወለደ" ሲባሉ ይኖራሉ። ጻድቁ ከዚህ በተጨማሪ የወቅቱን ንጉሥ አፄ ይኩኖ አምላክን በማስተማር ለሃገርና ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ ሰው አድርገዋል። በግላቸው ሐይቅ ውስጥ ገብተው ሲጸልዩ የብርሃን ምሰሶ ይወርድላቸው ነበር። ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምንም ከጠፋ ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ አቅንተዋል። እንዲህ ለቤተ ክርስቲያን ሲተጉ በተለይ በአበ ምኔትነት በቆዩባቸው አርባ አምስት ዓመታት ለዓይናቸው እንቅልፍን አላስመኙትም። ጐድናቸውም ከመኝታ ጋር ተገናኝቶ አያውቅም። "እንዘ የኀሊ ዘበሰማያት ዐስቦ መጠነ ዓመታት ሃምሳ ኢሰከበ በገቦ።" እንዲል። ከዚህ በኋላ የሚያርፉበት ዕለት ቢደርስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወርዶ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። በተወለዱ በሰማንያ ሁለት ዓመታቸው (በሰማንያ ስድስት ዓመታቸው የሚልም አለ።) በ፲፪፻፹፪ ዓ/ም በዕለተ ሰንበት ዐርፈው ተቀብረዋል። ጻድቁ ስም አጠራራቸው እጅግ የከበረ ነው! ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                27. አባ ተክለሃዋርያት
                  ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ ሐዋርያት በአሥራ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተነሱ ዓበይት ጻድቃን አንዱ ናቸው። በተለይ በጻድቁ ንጉሥ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን በተባሕትዎም በትሩፋትም እጅግ የተደነቁ አባት ነበሩ። ጻድቁ ሲጠሩ "ዘደብረ ጽሙና" አንዳንዴም "ዘገበርማ" እየተባሉ ነው። ምናልባትም በብዙ ቦታ ላይ ስለ ተጋደሉ በእነዚህ ቦታዎችም ላይ ስለ ነበሩ ሊሆን ይችላል እንደዚህ ተብለው የተጠሩት። በብዛት የሚታወቁት ደግሞ በምድረ ሸዋ፣ ጐጃምና በምድረ አፋር አካባቢ በመኖራቸው ነው። እስኪ አንዳንድ ነገሮቻቸውን እናንሳ፦ ጻድቁ ክርስቶስን በመከራው ይመስሉት ዘንድ ዘወትር ይተጉ ነበር። አንዴ ሥጋ ወደሙ የተቀበለ አንድ ሰው በመንገድ ላይ ሲያስመልሰው ተመልከተው ሁሉ ተጸይፎ ሲሸሽ እሳቸው ግን ደስ እያላቸው ተመግበውታል። ምክንያቱም የእርሳቸው ዓይን የሚመለከተው የፈጣሪን ሥጋና ደም ነው። በዚህ ጊዜም ጌታ ከሰማይ ወርዶ በግንባራቸው ላይ ፀሐይን ስሎባቸዋል። በዚህ ምክንያትም ፊታቸው ያበራ ነበር። አንዴ ደግሞ በገዳማቸው አንድ ዶሮ ለእንግዳ ሊያርዱት ሲሉ "በአባ ተክለ ሐዋርያት ተማጽኛችኋለሁ!" በማለቱ ትተውታል። በአፋር በርሃ አካባቢ ለአሥራ አራት ዓመታት ኑረዋል። በአንድ በዓት ውስጥም ለአርባ አንድ ዓመታት ኑረዋል። ጻድቁ አቡነ ተክለ ሐዋርያት እንዲህ ተመላልሰው በተወለዱ በሰባ አንድ ዓመታቸው በዚህች ቀን ዐርፈዋል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                27. ሐዋርው ቅዱስ ያዕቆብ በሰማዕትነት አረፈ
                  ይህ ስም በቤተ ክርስቲያን እጅግ ዝነኛና ታዋቂ ነው። ቅዱስ ያዕቆብ ቁጥሩ ከዓበይት ሰማዕታት ሲሆን የፋርስ ኮከብ በመባልም ይታወቃል። ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ ("ሙ" ጠብቆ ይነበብ።) ተወልዶ ያደገው በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምድረ ፋርስ (የአሁኗ ኢራን) ውስጥ ነው። ያኔ ይህቺ ሃገር በአንድ ወገን ጠንካራ ክርስቲያኖች በሌላ ወገን ደግሞ ጣዖትን የሚያመልኩ ጨካኝ ነገሥታት ነበሩባት። ቅዱስ ያዕቆብም በክርስትና ትምህርት አድጐ ሚስት አገባ። በዘመኑ ከነበረው ንጉሥ ሠክራድ ጋር በጣም ይዋደዱ ነበርና በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ሹም አድርጐ አስቀመጠው። በቤተ መንግሥት ውስጥ ምቾት የበዛበት ቅዱስ ያዕቆብ የጾምና የጸሎት ሕይወቱ እየቀዘቀዘ መጣ። በሒደትም ንጉሡ የሚለውን ሁሉ የሚፈጽም ሰው ሆነ። አንድ ቀን ግን ሠክራድ ቅዱስ ያዕቆብን "ለእሳትና ለፀሐይ ስገድ፤ እነርሱንም አምልካቸው።" ሲል ጠየቀው። ከመጀመሪያ የተሸረሸረ ነገር ስለ ነበረ "እሺ! ደስ ይበለው።" ብሎ ለፀሐይ ሰገደ፤ እርሷንም አመለከ። ይህቺ ዜና በዘመኑ ክርስቲያኖች ዘንድ ስትሰማ ታላቅ ሐዘንን ፈጠረች። ይልቁኑ እናቱ፣ እኅቱና ሚስቱ ይህንን ሲሰሙ አንጀታቸው አረረ። በዚህ ምክንያትም ሦስቱ ተሰብስበው አንድ ደብዳቤ ጽፈው ተፈራርመው ላኩለት። የደብዳቤው ይዘት እንዲህ ይላል፦ "አንተ ክርስትናህን መካድህን ሰምተን አዘንን። በዚህም ምክንያት ከዚህ በኋላ በአካባቢህ መኖርን አንፈልግም። ለሞተልህ ለክርስቶስ ካልታመንህ እኛ አንተን እንደ ልጅ፣ እንደ ወንድምና እንደ ባል ልናምንህ ይከብደናል።" ይህንን ደብዳቤ ልከውለት እነርሱ አካባቢውን ለቀቁ። ቅዱስ ያዕቆብ ደብዳቤውን ተቀብሎ ወደ ቤቱ ገብቶ ሲያነበው ደነገጠ። በዚህ ምድር ያሉት ዘመዶቹ እናቱ፣ አንዲት እኅቱና ሚስቱ ብቻ ናቸውና ውስጡ ተሸበረ። ተደፍቶም ምርር ብሎ አለቀሰ። ሲመሽም በቤቱ ውስጥ ወደ ነበረው የቀድሞ የጸሎት ቦታ ሒዶ ተንበረከከ። ከንጉሡ ጋር በነበረው ያልተገባ ቅርርብ የፈጸመው ስህተት ሁሉ ቁልጭ ብሎ ታየው። በጌታችን ፊት ቁሞም "ጌታ ሆይ! በምድር ካሉ የሥጋ ዘመዶቼ መለየት እንዲህ ካሸበረኝ ካንተ ፍቅር መለየትማ እንደ ምን ይጨንቅ ይሆን! በሰማያዊ ዙፋንህ ፊትስ እንዴት ብዬ እቆማለሁ!" ሲል አምርሮ አለቀሰ። ሙሉውን ሌሊት በእንባና በጸሎት አድሮ በጠዋት ንስሐ ገባ። ከዚያች ቀን ጀምሮም ፍጹም በክርስቶስ ፍቅር ተጠመደ። ጾምና ጸሎትን ወዳጆቹ አድርጐ ከንጉሡ እልፍኝና አደባባይ ቀረ። ይህንን ያወቀው ንጉሡ ሠክራድ ወደ እርሱ አስጠርቶ "ምን ሆነሃል? ስለ ምንስ በአምልኮ ከእኔ ተለየህ?" አለው። ቅዱስ ያዕቆብም መልሶ "የፈጠረኝን ክርስቶስን ትቼ አንተን በባዕድ አምልኮ አስደስትህ ዘንድ የሚገባ አይደለም።" ሲል ተናገረው። ንጉሡ ቅዱሱን አስቀድሞ ሊያታልለው ሞከረ። እንቢ ሲለው ግን ደሙ በመሬት ላይ እስኪንጠፈጠፍ ድረስ አስገረፈው፤ አስደበደበው። ጭንቅ መከራዎችንም አሳየው። ቅዱስ ያዕቆብ ግን በፍቅረ ክርስቶስ ጸና። በዚህ የተበሳጨው ንጉሡ እንዲቆራርጡት ግን ቶሎ እንዳይገሉት አዘዘ። ከዚያ ቀን በኋላ በቀን በቀን እየገቡ ከአካሉ ይቆርጡ ጀመር። ከጣቶቹ ተነስተው እጆቹን እስከ ክንዱ፣ እግሮቹን እስከ ታፋው ድረስ ቆረጡ። መሃል አካሉ (ወገቡና ራሱ) ብቻ ቀረ። ይህ ሁሉ ሲሆን እርሱ ጌታን ይቀድሰው ይጸልይም ነበር። "የወይን ግንድ ሆይ! እኔን ቅርንጫፍህ አድርገኝ።" (ዮሐ. ፲፭፥፭) ይለው ነበር። ከአካሉ እየቆረጡ የጣሉትም ሲቆጠር አርባ ሁለት ሆነ። አርባ ሦስተኛ ደግሞ የተረፈ አካሉ ነበር። ያን ጊዜ ሊጸልይ ፈልጐ "ጌታ ሆይ!" ብሎ ጮኸ። ይህንን አበው፦ "መንፈቀ አካሉ ጸለየ መዊቶ መንፈቁ" ብለው ገልጸውታል። ግማሽ አካሉ ሙቶ በቀረው ይጸልይ ነበርና ንጉሡም ከጩኸቱ በኋላ አንገቱን በሰይፍ ሲያስመታው ጌታችን ወርዶ ታቅፎ ወደ ሰማይ አሳረገው። እናቱ፣ እኅቱ፣ ሚስቱ ይህንን ሲሰሙ እያለቀሱና እየዘመሩ አካሉን ሰብስበው ገንዘውታል። ሽቱም አርከፍክፈውበታል። የዚህ ቅዱስ ገዳም (ታቦት) በኢትዮጵያ ታች አርማጭሆ በሚባለው በርሃ ውስጥ ይገኛል። ድንቅ የሆነ የበረከት ቦታም ነው። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                29. ተፈፃሚ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ(እረፍቱ)
                  ይህ ቅዱስ የሚታወቀው "ተፍጻሜተ ሰማዕት (የሰማዕታት መጨረሻ)" በሚለው ስሙ ነው። ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ የቅዱሱ ሃገረ ሙላዱ ግብጽ ናት። ዘመኑም ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ወላጆቹ ካህን ቴዎድሮስና ቡርክት ሶፍያ ልጅ አጥተው ሐምሌ ፭ ቀን ወደ ፈጣሪ ቢማጸኑ በራእይ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ተገልጠው ብሥራትን ለሶፍያ ነገሯት። በወለደችው ጊዜም በራእዩ መሠረት "ጴጥሮስ" አለችው። ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜም ለቤተ እግዚአብሔር ሰጥተውት በሊቀ ጳጳሳቱ ቅዱስ ቴዎናስ እጅ አደገና በወጣትነቱ ሊቅ፣ ጥዑመ ቃልና በጐ ሰው ሆነ። ዲቁናና ቅስናን ተሹሞ ሲያገለግል ቅዱስ ቴዎናስ በማረፉ ቅዱስ ጴጥሮስን የግብጽ አሥራ ሰባተኛ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት። ዘመኑ ደግሞ እጅግ ጭንቅ ነበር። ክርስቲያኖች በተገኙበት ስለሚገደሉ አብያተ ክርስቲያናትም ስለ ተቃጠሉ የቅዱሱ መከራ የበዛ ነበር። ለአሥራ አራት ዓመታት በፍጹም ትጋት ከመንጋው ጋር ተጨነቀ። አርዮስን (ተማሪው ነበር) አውግዞ ለየው። ከጌታ ጋርም ብዙ ጊዜ ተነጋገረ። ብዙ ተአምራትንም ሠራ። በዚህ ሁሉ ጊዜ አንድም ቀን በመንበረ ጵጵስናው ላይ አልተቀመጠም። በኋላ ግን ጨካኙ ንጉሥ እንዲገደል አዘዘ። ሕዝቡ "ከእርሱ በፊት እኛን ግደሉን።" በማለታቸው ሁከት እንዳይነሳ ቅዱስ ጴጥሮስ ተደብቆ ሔደና በፈቃዱ ለወታደሮች ተሰጠ። በዚያች ሌሊትም የእርሱ ደም የግፍ ማብቂያ እንዲሆን እያለቀሰ ጮኸ። ከሰማይም "አሜን! ይሁን!" የሚል ቃል መጣ። ያን ጊዜ የእርሱ አንገት ተሰየፈ። ዘመነ ሰማዕታትም አለፈ። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
              ታህሳስ
                1.ነቢዩ ኤልያስ የተወለደበት ቀን
                  ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ቀጥላ ቅዱስ ኤልያስን ታከብራለች። "ርዕሰ ነቢያት - የነቢያት ራስም" ትለዋለች። እርሱ ሰማይን የለጐመ፣ እሳትን ያዘነመ፣ ፍጥረትንም በቃሉ ያዘዘ አባት ነውና። ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ ቅዱሱ ትውልዱ (ነገዱ) ኢዮርብዓም ነጥሎ ከወሰዳቸው እስራኤል (አሥሩ ነገድ) ሲሆን አባቱ "ኢያስኑዩ" እናቱ ደግሞ "ቶና (ቶናህ)" ይባላሉ። በጐ አምልኮ ነበራቸውና እግዚአብሔር ማኅጸነ ቶናህን ቀድሶ ይህንን ቅዱስ ፍሬ ፈጠረ። ቅዱስ ኤልያስ በተወለደ ቀን በቤታቸው ብርሃን ተሞልቶ ታይቷል። ብርሃን የለበሱ አራት ሰዎች (መላእክት) መጥተውም በእሳት ሰፋድል (መጐናጸፊያ) ሲጠቀልሉት ወላጆቹ በማየታቸው ደንግጠው ለነቢያትና ለካህናት ነገሯቸው። ካህናቱ ግን ነገሩ ቢረቅባቸው "ምን ዓይነት ፍጥረት ይሆን? በእስራኤል ይነግሥ ይሆን! ወይስ ነቢይ ይሆን?" ብለውም አድንቀዋል። ቅዱስ ኤልያስ ከልጅነቱ ጀምሮ ኮስታራ፣ ቁም ነገረኛ፣ ንጽሕናንም የሚወድ እስራኤላዊ ነው። ወቅቱ (ከክርስቶስ ልደት ዘጠኝ መቶ ዓመት በፊት) ሕዝቡና ነገሥታቱ የከፉበት፣ እግዚአብሔር ተክዶ ጣዖት የሚመለክበት ነበር። ድሮ በኢሎፍላውያን እጅ የነበሩት ጣዖታት (ዳጐንና ቤል) በዚያ ዘመን ወደ እስራኤል ገብተው ነበር። ቅዱስ ኤልያስ ግን በዚህ ክፉ ትውልድ መካከል ሆኖም ሥርዓተ ኦሪትን የጠነቀቀ የንጽሕናና የአምልኮ ሰው ነበር። በዚያ ወራትም እግዚአብሔር ለነቢይነት ጠራው። እርሱም "እሺ" ብሎ ታዝዞ የእግዚአብሔርን የጸጋ ጥሪ ተቀበለ። ቅዱሱ ብዙ ጊዜ ለጉዳይ ካልሆነ ከሰው ጋር መዋል ማደርን አይወድምና መኖሪያውን በተራሮችና በዱር አደረገ። በተለይ ደብረ ቀርሜሎስ ለእርሱ ቤቱ ነበር። በዚህ ሕይወቱም ከመልከ ጼዴቅ ቀጥሎ፦ ፩.ለድንግልና (ድንግል ነበርና) ፪.ለብሕትውና (ብቸኛ ነበርና) ፫.ለምንኩስና (ተሐራሚ ነበርና) በብሉይ ኪዳን መሠረትን የጣለ ነቢይ ይባላል። መቼም በብሉይ ኪዳን የቅዱስ ኤልያስን፣ በዘመነ ክርስቶስ የመጥምቁ ዮሐንስን፣ በዘመነ ሊቃውንት ደግሞ የአፈ ወርቅ ዮሐንስን ያህል ደፋርና መገሥጽ አስተማሪ አልነበረም። በጊዜው ደግሞ አክአብና ኤልዛቤል የሚባሉ ክፉ ባልና ሚስት በእስራኤል ላይ ነግሠው ሕዝቡን ጣዖት አስመለኩት። ይባስ ብለው ደግሞ በወይኑ እርሻ አማካኝነት ኢይዝራኤላዊው ናቡቴን በሃሰት ምስክር ደሙን አፈሰሱት። ናቡቴም "የአባቶቼን ርስት አልሸጥም፤ አልለውጥም።" በማለቱ እንደ ሰማዕት ይቆጠራል። ኤልያስ ግን ይህንን ሲሰማ ወደ አክአብና ኤልዛቤል ቀርቦ "የናቡቴ ደም በእናንተ ላይ አይቀርም። የአንቺንም ደም ውሻ ይልሰዋል።" አላቸው። በዚህ ምክንያትም ኤልዛቤል ልትገድለው ብትፈልገውም እርሱ የእግዚአብሔር ነውና አላገኘችውም። በዚህ ብስጭትም ይመስላል አንድ ሺህ ነቢያትን ሰብስባ "ፍጇቸው" አለች። ዘጠኝ መቶው ሲታረዱ አንድ መቶውን ግን ቅዱስ አብድዩ በዋሻ ውስጥ ደብቆ እየመገበ አተረፋቸው። በእስራኤል ውስጥ ግን ዓመጻና ኃጢአት እየተስፋፋ ሔደ። የእግዚአብሔርን ስጦታ እየተመገበ ሕዝቡ ለቤል (ለበዓል) ሰገደ። ይህን ጊዜ ግን ቅዱስ ኤልያስ እንዲህ አለ፦ "ሕያው እግዚአብሔር አምላከ ኃይል ዘቆምኩ ቅድሜሁ ከመ ኢይረድ ጠል በእላ መዋዕል ዘእንበለ በቃለ አፉየ።" ብሎ ዝናም ከሰማይ እንዳይወርድ ከለከለ። ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ዝናም ለዘር ጠል ለመከር ከመስጠት ተከለከለ። ሕዝቡ በኃጢአቱ ምክንያት ተጐዳ። እርሱን ቁራ ይመግበው፣ ምንጭ ፈልቆለት ይጠጣ ነበር። ይሔው ቢቀርበት ጸለየ። እግዚአብሔርም ከፈለገ ኮራት ወደ ሰራፕታ እንዲወርድ አዘዘው። በዚያም የነቢዩ ዮናስ እናት እንጐቻ ጋግራ ብታበላው ቤቷ በበረከት ተሞላ። ልጇ ሕፃኑ ዮናስ ቢሞትም በጸሎቱ አስነሳላት። ቀጥሎም ሰባት ጊዜ በትጋት ጸልዮ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር የዘጋውን ሰማይ ከፍቶታል። ሕዝቡም ዕለቱኑ ከበረከቱ ቀምሰዋል። ከዚያ አስቀድሞ ግን ከኤልዛቤል ስምንት መቶ ሃምሳ ነቢያተ ሐሰትና ካህናተ ጣዖት ጋር ተወዳድሮ አሸንፏቸዋል። መስዋዕት ሰውተው የእርሱን ብቻ እሳት ከሰማይ ወርዳ በልታለታለችና ሕዝቡ ስምንት መቶ ሃምሳውን ሐሰተኛ ነቢያት በወንዝ ዳር በሰይፍ መትተዋቸዋል። ይህንን የሰማች ኤልዛቤልም ትገድለው ዘንድ አሳደደችው። "አቤቱ ከአባቶቼ አልበልጥምና ውሰደኝ! ብቻየን ቀርቻለሁና።" ብሎ ቢጸልይ እግዚአብሔር ለጣዖት ያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎችን እንዳተረፈ እርሱንም ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደሚወስደው ብሥራትን ነገረው። ደክሞት ተኝቶ ሳለም ቅዱስ መልአክ (ሚካኤል) ቀስቅሶ ታየው። እንጐቻ ባገልግል ውኃ በመንቀል አቅርቦ "ብላ! ጠጣ!" አለው። በላ፣ ጠጣ፣ ተኛ። እንደ ገና ቀስቅሶ አበላው። በሦስተኛው ግን "ብላዕ እስከ ትጸግብ እስመ ርሑቅ ፍኖትከ - ጐዳናህ ሩቅ ነውና እስክትጠግብ ብላ።" አለው። ኤልያስም ለአርባ ቀናት ያለ ምግብ ተጉዟል። ከዚያ በኋላም ምድራዊ ሕብስትን አልተመገበም። እግዚአብሔር አክአብና ኤልዛቤልን ከተበቀላቸው በኋላም ቅዱስ ኤልያስ በክፋተኞች ላይ ሁለት ጊዜ እሳትን አዝንሟል። የሚያርግበት ጊዜ ሲደርስም ደቀ መዝሙሩን ኤልሳዕን "የምትሻውን ለምነኝ።" ቢለው "እጥፍ መንፈስህን።" አለው። ሦስት ጊዜ ከመንገድ ሊያስመልሰው ሞከረ። ቅዱስ ኤልሳዕ ግን በብርታት ተከተለው። ዮርዳኖስን ከፍለው ከተሻገሩ በኋላ ግን ቅዱስ ኤልያስን ሠረገላ እሳት ወርዶ ነጠቀው። ለኤልሳዕም እኩሉን ግምጃውን ጣለለት። ዛሬ ቅዱስ ኤልያስ በብሔረ ሕያዋን ያለ ሲሆን በዘመነ ሐሳዌ መሲሕ መጥቶ በሰማዕትነት ከቅዱስ ሄኖክ ጋር ያርፋል። ለተጨማሪ ንባብ (ከ፩ነገ. ፲፯ - ፪ነገ. ፪ እና ዕርገተ ኤልያስን ያንብቡ።) ነቢዩ ኤልያስ በእውነት ታላቅ ነው! ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                3. በአታ ለማርያም እመቤታችን በሶስት አመቷ ቤተመቅደስ የገባችበት
                  ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ (አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ በሕጉ ጸንተው በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር። ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም።" በሚል ይናቁ ነበር። ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት - ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር። ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ። እነርሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም። የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው። አንድ ቀን ርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች። "እንስሳትና አራዊትን፣ እጽዋትን ሳይቀር በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች። ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ። ለአርባ ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ። በአርባኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ። እርሱ፦ ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ በሐና ቀኝ ጆሮ ገብታ በማኅጸኗ ስትደርስ አየ። እርሷ ደግሞ፦ የኢያቄም በትር አብቦ፣ አፍርቶ፣ ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች። ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን።" አሉ። ለሰባት ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ። በሰባተኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ ፯) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ። "ዓለም የሚድንባት የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ።" ብሏቸው ተሠወራቸው። እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ። እንደ ሥርዓቱም አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች። "ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ..... ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም።" እንዳለ ሊቁ። (ቅዳሴ ማርያም) "ለጽንሰትኪ በከርሥ እንበለ አበሳ ወርኩስ ወለልደትኪ እማኅጸን ቅዱስ..... ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው። የተወለድሽበት ማኅጸንም ቅዱስ ነው።....." (መጽሐፈ ሰዓታት ፣ ኢሳ. ፩፥፱) "ኢያቄም ወሐና ወለዱ ለነ ሰማየ ሰማዮሙኒ አስረቀት ለነ ፀሐየ። ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱልን። ሰማያቸው ደግሞ ፀሐይን አወጣችልን፤ (ወለደች - አስገኘችልን።)" የዓለማችን ወላጆች ነቢያት ሐዋርያትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ወልደው ከብረዋል፤ ተመስግነዋል። ኢያቄምና ሐና ግን ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ቢሰበሰብ በእግሯ የረገጠችውን ትቢያ እንኳ መሆን የማይችል የሰማይና የምድር ንግሥት የእግዚአብሔርን እናት እመቤታችን ማርያምን ወለዱልን። ኢያቄም ወሐና ለእግዚአብሔር የሥጋዌ አያቶቹም ተባሉ። ቅዱሳኑ እስኪያረጁ ድረስ በመካንነት አዝነው ጸልየዋል። ንጽሕናቸውና ደግነታቸው ተመስክሮላቸው ድንግል ማርያምን አግኝተዋል። እመቤታችን ነሐሴ ፯ ቀን ተጸንሳ ግንቦት ፩ ቀን ተወልዳለች። ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተወለደች የመጀመሪያዋ ሰው ድንግል ማርያም ሆናለች። (ኢሳ. ፩፥፱) የእመቤታችን የዘር ሐረግ፦ አዳም-ኖኅ-አብርሃም-ይስሐቅ-ያዕቆብ በእናቷ፦ ሌዊ-ቀዓት-እንበረም-አሮን-ቴክታና በጥሪቃ-ሔኤሜን-ዴርዴን-ቶና-ሲካር-ሔርሜላና ማጣት-ሐና። በአባቷ በኩል፦ ይሁዳ-ፋሬስ-ሰልሞን-ቦኤዝ-እሴይ-ዳዊት-ሰሎሞን-ሕዝቅያስ-ዘሩባቤል-አልዓዛር-ቅስራ-ኢያቄም ይሆናል። ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች። ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና ድንግል እመ ብርሃንን ከወለዱ በኋላ ለሦስት ዓመታት እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ፣ ነዳያንንም ሲጠግኑ ኖሩ። በእነዚህ ዓመታትም ቅድስት ሐና ድንግል ማርያምን ከእቅፏ አውርዳት አታውቅም። ቅዱሳን መላእክትም ዘወትር እየመጡ ያጫውቷት ይንከባከቧትም ነበር። ሦስት ዓመት በሞላት ጊዜም በቅድስት ሐና አሳሳቢነት ብጽዓታቸውን (ስዕለታቸውን) ይፈጽሙ ዘንድ ተዘጋጁ። እንደ ሥርዓቱ የሚዘጋጀውን (መባውን) ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ሲደርሱ አበው ካህናትና የመቅደሱ አገልጋዮች ሁሉ ሊቀበሏቸው ወጡ። ሕዝቡ፣ ሊቃነ ካህናት ቅዱሳን ዘካርያስና ስምዖን፣ ኢያቄም ወሐና ከድንግል ማርያም ጋር ቆመው ሳሉም ሊቀ መላእክት ፋኑኤል ከሰማይ ወርዶ ረቦ ታየ። ከቅዱስ ዘካርያስ ጀምሮ ሁሉም ሰው ሕብስትና ጽዋዑን ለመቀበል ቀረበ፤ ግን መልአኩ ራቀ። ድንግል ማርያም በቀረበች ጊዜ ግን ከመሬት አፈፍ አድርጐ አንስቶ ክንፉን ጋርዶ ሰማያዊውን ማዕድ መገባት። በዚህ ደስ የተሰኙ ካህናትና ሕዝቡ እየዘመሩ በታኅሣሥ ሦስት ቀን ወደ ቤተ መቅደስ አስገብተዋታል። አማናዊት መቅደሰ መለኮት ድንግል ማርያም ወደ ኦሪቱ ቤተ መቅደስ በገባችበት ዕለት ጸሎታችን እንድትሰማን እንደ ሊቃውንቱ፦ "ማርያም አንቲ ሰዋስው ዘምድረ ሎዛ ዲቤኪ ትዕርግ ጸሎትየ ከመ ጼና ሠናይ መዓዛ ኀበ ለነፍስየ ታሰስል ትካዛ።" እንላለን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                3. አቡነ ዜና ማርቂስ(እረፍቱ)
                  አባ ዜና ማርቆስ በሃገራችን በተለይ በደቡብ ምድረ ጉራጌ ስመ ጥር ሐዋርያዊ ጻድቅ ናቸው። ምድረ ሽዋ ደግሞ እርሳቸውን ጨምሮ የብዙ ቅዱሳን መፍለቂያ ናትና ክብር ይገባታል። ነቢየ ጽድቅ ዳዊት "ትውልደ ጻድቃን ይትባረኩ - የጻድቃን (የቅኖች) ትውልድ ይባረካል።" (መዝ. ፻፲፩) ያለው ነገር በምድረ ዞረሬ (ጽላልሽ) ተፈጽሟል። ሦስት ወንድማማች የተባረኩ ካህናት በስፍራው ነበሩ። ስማቸው ጸጋ ዘአብ፣ እንድርያስና ዮሐንስ ይባላል። ከእነዚህ መካከልም ጸጋ ዘአብ እግዚእ ኃረያን አግብቶ ኮከበ ከዋክብት ተክለ ሃይማኖትን ሲወልድ ካህኑ ዮሐንስ ደግሞ ዲቦራ የምትባል ደግ ሴት አግብቶ ዜና ማርቆስን ወልዷል። የአቡነ ዜና ማርቆስ ጽንሰታቸው ሚያዝያ ፴ በብሥራተ ማርቆስ ወንጌላዊ ሲሆን ልደታቸው ደግሞ ኅዳር ፳፬ ቀን በበዓለ ሱራፌል ካህናተ ሰማይ ነው። ዘመኑም አሥራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ዜና ማርቆስ በተወለዱ በአርባ ቀናቸው አጐታቸው ቀሲስ እንድርያስ (የሰባ ሁለት ዓመት ሽማግሌ ናቸው።) ሊያጠምቁ ቀረቡ። ሕፃኑ ዜና ማርቆስ ግን ከእናታቸው እቅፍ ወርደው ሦስት ጊዜ "እሰግድ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ" እያሉ ቢሰግዱ የመጠመቂያው ገንዳ ውኃ ፈላ። ይህንን የተመለከቱት ካህኑ ደንግጠው ወጥተው ሲሮጡ ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት ተገልጦ "አትፍራ! ይልቁኑ ከጠበሉ ራስህን ተቀባ።" አላቸው። እንዳላቸው ቢያደርጉ ራሰ በራ ነበሩና ጸጉር በቀለላቸው። ሕፃኑ ዜና ማርቆስ ግን አምስት ዓመት ሲሞላቸው ወደ ጉባኤ ቤት ገብተው በአጭር ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቁ። ዲቁናን ተቀብለው ወደ ቤታቸው ሲመለሱም ሽፍቶች አግኝተው በትራቸውን ቀምተው አንገላተው ሰደዋቸዋል። ወዲያው ግን ያቺ በትር እባብ ሁና ሽፍቶችን አጥፍታቸዋለች። ጻድቁ ለቤተሰብ እየታዘዙ፣ ንጽሕናቸውንም እየጠበቁ ኑረው ሠላሳ ዓመት ሲሞላቸው ወላጆቻቸው ግድ ብለው ማርያም ክብራ ለምትባል ወጣት አጯቸው። እርሳቸው ግን በሠርጉ ሌሊት ከጫጉላ ቤት ጠፍተው በርሃ ገቡ። ከዚያም በቅዱስ መልአክ መሪነት ሃገረ ምሑር ደረሱ። በቦታውም ጣዖትን ሰባብረው፣ ተአምራትንም አድርገው፣ ሕዝቡን ወደ ክርስትና መለሱ። መስፍኑ አውጊት ግን ተፈታተናቸው፤ አሠራቸው፤ አሥራባቸው። በጦር እወጋቸዋለሁ ሲል ግን መሬት ተከፍታ ከነ ተከታዮቹ ውጣዋለች። ከአምስት ዓመታት በኋላ ግን ማልደው ከሰጠመበት አውጥተው አጥምቀውታል። ቀጥለውም ምድረ ጉራጌ ወርደው ሕዝቡን አሳምነው አጥምቀዋል። የአዳልን ሕዝብና ንጉሡን አብደልማልን አስተምረው ያጠመቁም እርሳቸው ናቸው። ድል አሰግድ የሚባለውን መስፍንም ያሳምኑ ዘንድ ጠንቅዋዮቹን ድል አድርገው አጥፍተዋል። ጻድቁ ዜና ማርቆስ ከዚህ ሐዋርያዊ ሥራቸው በተጨማሪ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ምንኩስናን ከተቀበሉባት ቀን ጀምረው በጾም፣ በጸሎትና በሰጊድ ኑረዋል። ፀሐይን በምድረ ጉራጌ እስከ ማቆም ደርሰውም ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል። አእላፍ ደቀ መዛሙርትን ሲያፈሩ ሁለት መቶ አንበሶች በቀኝ ሁለት መቶ ነብሮች በግራ ይከተሏቸው ነበር። ደብረ ብሥራትን ጨምሮ ገዳማትን አንጸዋል። በመጨረሻም የምሕረት ቃል ኪዳንን ከፈጣሪ ዘንድ ተቀብለው ታኅሣሥ ሦስት ቀን በመቶ አርባ ዓመታቸው ዐርፈዋል
                4. ሐዋርያው እንድርያስ በሰማዕትነት ያረፈበት
                  ቅዱሱ ሐዋርያ ተወልዶ ያደገው በቤተ ሳይዳ አካባቢ ሲሆን የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ትንሽ ወንድም ነው። አባቱም ዮና ይባላል። ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ዓሣ ማጥመድን ከትልቅ ወንድሙ ተምሯል። እድሜው ከፍ ባለ ጊዜ ኦሪትን ተምሮ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆኗል። ከእርሱም እያገለገለ ለስድስት ወራት ተምሯል። በወቅቱ ከወንጌላዊው (ወልደ ዘብዴዎስ) ዮሐንስ ጋር ቅርብ ባልንጀራም ነበር። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ያን ድንቅ ምሥጢረ ሥላሴ ከተመለከቱትም አንዱ ነው። ጌታ ከጾም (ከገዳመ ቆረንቶስ) በተመለሰ ጊዜ እንድርያስ መንፈስ ቅዱስ አነሳስቶት ተከትሎታል። መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ "ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያዐትት ኃጢአተ ዓለም - የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እነሆ።" ማለቱን ሰምቶ ቅዱስ እንድርያስ ጌታን ተከተለ። በዚህም የመጀመሪያው የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመባል በቃ። (ዮሐ. ፩፥፵፯) ሊቁ ማር ገላውዴዎስም እመቤታችንን ሲያመሰግናት፦ "ለሐዋርያ እንድርያስ ቀዳማዊ ማርያም ሃይማኖቱ - ለመጀመሪያው ሐዋርያ ለእንድርያስ ሃይማኖቱ ማርያም አንቺ ነሽ።" ብሏል። (መልክአ ስዕል) ቅዱሱ ሐዋርያ ስሉጥ (ፈጣን) አገልጋይ እንደ ነበርም ወንጌል ይነግረናል። (ዮሐ. ፮፥፱ ፤ ፲፪፥፳፪) ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታ እግር ሥር ተምሮ በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሎ ምን ሃገረ ስብከቱ ልዳ ብትሆን ብዙ አሕጉረ ዓለምን ሰብኳል። ሐዋርያው ከጌታ ጋር በመርከብ ውስጥ ተነጋገረና ቅዱስ ማትያስን ሰውን ከሚበሉ ሰዎች እጅ አዳነ። ቅዱስ እንድርያስ ሠላሳ ቀናት የሚፈጅ የባሕር ላይ ጉዞ ለማድረግ ከአርድእቱ ጋር ወደ ወደብ ቢሔድም መርከበኞች ሁሉ አናሳፍርም በማለታቸው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወጣት መርከበኛ መስሎ ሐዋርያውንና አርድእቱን የሠላሳውን ቀን መንገድ በሰዓታት ልዩነት እንዲጨርሱ አድርጓል። ቅዱስ እንድርያስም እንዲሁ ሰው መስሎት ለጌታችን ስለ ጌታችን ሰብኮለታል፤ መርቆታልም። መርከበኛው ጌታችን መሆኑን ሲያውቅም ደንግጦ አልቅሷል። "ሶበ አእመረ ኪያሁ ወጠየቀ አምሳሎ ዘተናገርኩ በድፍረት ምስሌከ ኩሎ ሥረይ ሊተ ጌጋይየ ወኅድግ ይቤሎ።" እንዲል "ማረኝ?" ብሎታል። ጌታችንም "አይዞህ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ።" ብሎታል። እንድርያስ ማለት "ተባዕ" (ደፋር፣ ብርቱ) ማለት ነው። ድፍረት ሥጋዊ፣ ድፍረት መንፈሳዊ አለና። "ድፍረት ሥጋዊ" በራስ ተመክቶ ሌሎችን ማጥቃት ለጥቃትም ምላሽ መስጠት ነው። "ድፍረት መንፈሳዊ" ስለ ክርስቶስ፣ ስለ ቀናችው ሃይማኖት ሲሉ በራስ ላይ መጨከን፣ ራስን አሳልፎ መስጠት፣ መከራንም አለመሰቀቅ ነው። ይህንንም አበው "ጥብዓት" ይሉታል። ቅዱስ እንድርያስም ለጊዜው በቤተ እስራኤል መካከል ደፋር የነበረ ሲሆን ለፍጻሜው ግን እስከ ሞት ደርሶ ስመ ክርስቶስን በድፍረት ገልጧልና "ተባዕ (ደፋር)" ይለዋል። "ዘኢያፍርሃከ ምንተ መልአከ ዓመጻ ጽኑዕ አንተኑ እንድርያስ ተባዕ።" እንዲል። (መልክአ ዓቢየ እግዚእ) የቅዱስ እንድርያስ ሃገረ ስብከቱ ልዳ (ልድያ) ናት። ይህቺን ሃገር አስቀድሞ ሊቀ ሐዋርያቱ (ትልቅ ወንድሙ) ቅዱስ ጴጥሮስ አስተምሮባታል። ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ሮም ሲዘልቅ ቅዱስ እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ገብቶ ብዙ ደክሞባታል። በቀደመው ዘመን ልዳ እንደ ዛሬው ትንሽ ሃገር አልነበረችም። ቅዱሱ ሐዋርያ ወደ ቦታው ገብቶ ስመ ክርስቶስን ሰብኮ ብዙዎችን ቢያሳምንም የጣዖቱ ካህናት ግን ተበሳጩ። በእርግጥ እነርሱ የሚያጥኗቸው ድንጋዮች አማልክት እንዳልሆኑ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ነገር ግን ከብረው፣ ገነው፣ ባለ ጠጐችም ሆነው የሚኖሩበት ሐሰት እንዲገለጥ አይፈልጉምና እውነትን ከመቀበል ሐዋርያቱን ማሳደዱን ይመርጡ ነበር። አሁንም የልዳ ከተማ ሕዝብ ማመናቸውን ሲሰሙ በቁጣ ሠራዊት ሰብስበው ጦርና ጋሻን አስታጥቀው ሐዋርያውን ያጠፉ ዘንድ እየተመሙ መጡ። ቅዱስ እንድርያስ ይህንን ሲያውቅ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል "ጥዑመ ቃል" የሚባለውን ቅዱስ ፊልሞናን (ኅዳር ፳፯ ቀን ያከበርነውን ማለት ነው።) ጠርቶ የቅዱስ ዳዊትን መዝሙር ገልጦ መዝሙር ፻፲፫፥፲፪ ላይ ሰጠውና "ጮክ ብለህ አንብብ።" አለው። ቅዱስ ፊልሞናም በቅዱስ መንፈሱ ተቃኝቶ ያነብ ጀመር። "አማልክቲሆሙ ለአሕዛብ ዘወርቅ ወዘብሩር ዓይን ቦሙ ወኢይሬእዩ እዝን ቦሙ ወኢይሰምዑ አንፍ ቦሙ ወኢያጼንዉ የአሕዛብ አማልክት ከወርቅና ከብር የተሠሩ ናቸው። ዓይን አላቸው፤ ግን አያዩም። ጆሮ አላቸው፤ ግን አይሰሙም። አፍንጫ አላቸው፤ ግን አያሸቱም።....." አለ። በፍጻሜውም "ከማሁ ለይኩኑ ኩሎሙ እለ ገብርዎሙ - የሚሰሯቸው ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ።" ብሎ ጸጥ አለ። ይህንን የሰሙት ካህናተ ጣዖትና ሠራዊታቸው የልባቸው መታጠቂያ ተፈታ። በደቂቃዎችም የመንፈስ ቅዱስ ምርኮኛ ሆነው በቅዱስ እንድርያስ ፊት ሰገዱ። እርሱም አጥምቆ ወደ ምዕመናን ማኅበር ቀላቀላቸው። አንድ ጊዜ ደግሞ ከልዳ አውራጃዎች በአንዱ እንዲህ ሆነ። በጨዋታ ላይ ሳሉ የክርስቲያኑ ልጅ የአሕዛቡን ቢገፈትረው ወድቆ ሞተ። የሟቹ አባትም የገዳዩን አባት ዮሐንስን (ቀሲስ ነው።) "ልጅህን በፈንታው እገድለዋለሁ።" አለው። ቀሲስ ዮሐንስ ግን "ለመምህሬ ለእንድርያስ እስክነግረው ድረስ ታገሠኝ።" ብሎ ሒዶ ለሐዋርያው ነገረው። በወቅቱ ቅዱስ እንድርያስ የወንጌል አገልግሎት ላይ ስለ ነበር ቅዱስ ፊልሞናን ላከው። ፊልሞና ወደ አካባቢው ሲደርስ ሁከት ተነስቶ አገረ ገዢው ሕዝቡን ይደበድብ ነበርና ቀርቦ ገሠጸው። "የተሾምከው ሕዝቡን ልታስተዳድርና ልትጠብቅ ነው እንጂ ልታሰቃይ አይደለም።" ስላለው አገረ ገዥው ቅዱሱን አሰቀለው። ተሰቅሎም ሳለ ይገርፉት ነበርና አለቀሰ። ምክንያቱም ቅዱስ ፊልሞና ሕፃን ነበርና። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሲያለቅሱለት ቁራ፣ ወፍና ርግብ ቀርበው አጽናኑት። ከእነርሱም መርጦ ርግብን ወደ ቅዱስ እንድርያስ ላካት። ርግብ በሰው ልሳን ስትናገር የሰማት አገረ ገዢው ተገርሞ ቅዱሱን ከተሰቀለበት አወረደው። ሰይጣን ግን በብስጭት በመኮንኑ ሚስት አድሮ ልጁን አስገደለበት። በሃዘን ላይ ሳሉም ቅዱስ እንድርያስ ደረሰ። በመኮንኑ ሚስት ያደረውን ሰይጣንን ወደ ጥልቁ አስጥሞ የሞተውን አስነሳው። መጀመሪያ የሞተውን ሕፃን ደግሞ ቅዱስ ፊልሞና አስነሳው። በእነዚህ ተአምራትም መኮንኑ፣ ሕዝቡና ሠራዊቱ በክርስቶስ አምነው ተጠመቁ። ቅዱስ እንድርያስ በእድሜው የመጨረሻ ዘመናት ከልድያ ወጥቶ በብዙ አሕጉራት አስተማረ። ስሟ ባልተጠቀሰ አንዲት ሃገር ውስጥ ግን በእሳት ሊያቃጥሉት ሲሉ እሳት ከሰማይ ወርዳ በላቻቸው። ድጋሚ ሌሎች ይዘው አሰሩት፤ ደበደቡት፤ አሰቃዩት። በሌሊትም ጌታ መጥቶ አጽናናው። ታኅሣሥ ፬ ቀን በሆነ ጊዜም ወደ ውጭ አውጥተው ወግረውና ሰቅለው ገድለውታል። እኛም እንደ አባቶቻችን፦ "እዜምር ለከ ወእየብብ በሃሌ ሉያ አንቅሃኒ እምሐኬትየ እንድርያስ ሐዋርያ ከመ በእዴከ ነቅሐት እሙታን ልድያ።" እያልን ቅዱሱን እንጠራዋለን። (አርኬ ዘታኅሣሥ ፬) አምላከ ቅዱስ እንድርያስ ከሞተ ልቡና አንቅቶ ለክብሩ ያድርሰን። ከበረከቱም ያድለን
                6. ቅድስት አርሴማ(ቅዳሴ ቤቷ)
                  እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው። መድኃኒታችን ክርስቶስ በወንጌል እንዳለው "በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትምና።"(ማቴ. ፭፥፲፩) የሰማዕቷ ሕይወት በፊታችን እንደ ብርሃን ተገልጦ ይታያል። ቅድስት አርሴማ እንደ ልጅ ወላጆቿን በመታዘዝ ደስ ያሰኘች ቡርክት ናት። ቅድስት አርሴማ ይህ ቀረሽ የማይሏት ውብ ናት። ቅድስት አርሴማ ድንግል ናት። ቅድስት አርሴማ ባሕታዊት ጻድቅ ናት። ቅድስት አርሴማ ኃያል ሰማዕት ናት። ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ አበው በትውፊት እንደ ነገሩን ቅዱሱ ጐርጐርዮስ የታላቋ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ ትልቅ ወንድም ነው። በዜና ሰማዕታት ተጽፎ እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት፦ ፩.ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት ፪.ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት ፫.የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት። ቅዱሱ ሦስቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ። ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት። መከራው ገፍቶ እስከ መጣበት ጊዜ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ፣ ይጾሙ፣ ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር። ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስን ጻድቃን የምንላቸው። በኋላ ግን ማኅደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ በመልኳ ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ። በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና በጸሎት ለጥቂት ጊዜ ቆዩ። ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው። የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለ መኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ። በዚያም በድርጣድስ ቤተ መንግሥት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ። በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር። መከራው ግን አለቀቃቸውም። ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው። ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ "ካላገባሁሽ" አላት። ድንግሊቱ ግን "እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ፤ አይሆንም።" አለችው። ሊያስፈራራት ሞከረ። ዓይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው። አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው። እጅግ ስላፈረ አስገረፋት፣ አሰቃያት፣ ዓይኗንም አወጣ። በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት። ከነገር ሁሉ በኋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀየራቸው። የንጉሡ እንስሳ (አውሬ) መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን ፈጠረ። የንጉሡ እኅት ስታለቅስ በራእይ "ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን - ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም።" አላቸው። ወዲያውም ቆፍረው አወጡት። ቅዱሱ እንደ ወጣ ዕረፍትን አልፈለገም። ለአሥራ አምስት ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው። ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሒዶ ፈወሳቸው። የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ አጽም በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሌሎች ሰማዕታት አጽም ጋር ኢትዮጵያ እንደ መጣ አባቶቻችን በትውፊት ነግረውናል። ለዚህም ነው ቡርክቷ እናታችን ከሌሎች ሃገራት ለይታ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ፍቅር ያላት። በዋናው ገዳሟ (ወሎ /ኩላማሶ/ ስባ ውስጥ የሚገኝ ነው።) ጨምሮ ስሟ በተጠራበት ሁሉ ኃይልን ታደርጋለችና። ነገር ግን ወንድሞቼና እኅቶቼ በቅድስቷ እናታችን ስም የሚነግዱ ሥጋውያን ሰዎች በዝተዋልና እንጠንቀቅ። የሰማዕቷ ክብር ብዙ ነውና በሕልም ላይ ብቻ አንታመን። አባ እንጦንስ እንዳሉት "በሕልሙ የሚታመን ሰው ከንቱ ነውና።" (መዝ. ፸፭፥፭) በዚህ ዕለት ከሰማዕቷ ጋር የመንፈስ እናቷን ቅድስት አጋታን ልናስባት ይገባናል። ይህች እናት እመ ምኔት ስትሆን ቅድስት አርሴማን ታስተምራት፣ ታጸናት፣ ከጐኗም ትቆምላት ነበር። ረሃቧን፣ ጥሟን፣ ስደቷን፣ መከራዋንም ሁሉ አብራት ተሳትፋለች። በፍጻሜውም አብራት ተሰይፋለች። ይህች ዕለት ለቅድስት አርሴማና ለተከታዮቿ ሰማዕታት የፍልሰትና የቅዳሴ ቤት መታሰቢያ ናት። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                12. አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ
                  ሃገራችን እልፍ አእላፍ ቅዱሳንን አፍርታለች። እንኳን በተባረከው በቀደመው ዘመን ይቅርና ዛሬም ከሃገር ተርፈው ለዓለም የሚጸልዩ በየበርሃውና በየፈርኩታው የወደቁ ብዙ አባቶችና እናቶች አሉን። በኢትዮጵያ ውስጥ ከተነሱ ቅዱሳን "ሳሙኤሎች" ልዩ ቦታ አላቸው። በሃያ ዓመታት ልዩነት ብቻ ስድስቱ ሳሙኤሎች ተነስተው ከቅድስና ሕይወት እስከ ስብከተ ወንጌል ከገዳማዊ ሕይወት እስከ ምናኔ በጐውን ጐዳና አሳይተዋል። እነዚህም፦ ፩.ሳሙኤል ዘዋልድባ ፪.ሳሙኤል ዘጣሬጣ ፫.ሳሙኤል ዘቆየጻ ፬.ሳሙኤል ዘግሺ ፭.ሳሙኤል ዘሃሌ ሉያ እና ፮.ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ናቸው። በተመሳሳይም በግብጽ የደብረ ቀልሞኑን ኮከብ ጨምሮ (መልአኩን ቀውስጦስን ከጌታ ያማለዱት) ብዙ ሳሙኤሎች ተነስተዋል። የድሮ እናቶቻችን በእውነት ስም መሰየሙን ይችሉበታል። "ሳሙኤል" ማለት "ሰምዓኒ እግዚአብሔር ስዕለትየ - እግዚአብሔር ልመናዬን ሰማኝ"። ማለት ነውና። ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ አቡነ ሳሙኤል ዘዋሊ የተወለዱት በአሥራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በ፲፪፻፺፭ ዓ.ም በምድረ አክሱም ነው። ወላጆቻቸውም እስጢፋኖስና ዓመተ ማርያም ይባላሉ። የዘር ሐረጋቸው ከካህናት ወገን ነውና ጻድቁ ገና በልጅነት ምሥጢራተ ሃይማኖትን ጠጥተዋል። ለዚህም ይመስላል ገና ሕፃን ሳሉ ምናኔን የተመኙት። ከልጅነታቸው ጀምረው ወላጆቻቸውን ያገለገሉት ሳሙኤል ትምህርታቸውን ሲፈጽሙ የተጓዙት ወደ ደብረ በንኮል ነበር። በጊዜውም የጻድቁ ወላጆች ዐርፈው እንደ ነበር ይነገራል። ደብረ በንኮል ማለት የታላቁ ኮከብና አበ መነኮሳት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ነው። መድኃኒነ እግዚእ ለሃገር ብርሃን የሆኑ ቅዱሳንን ያፈሩ ዘንድ ሲተጉ እግዚአብሔር ሰባቱን ከዋክብት ሰጣቸው። ከእነዚህ መካከልም ቀዳሚው አቡነ ሳሙኤል ናቸው። ቀሪዎቹ ደግሞ እነ አቡነ ያሳይ ዘመንዳባ፣ ሳሙኤል ዘጣሬጣ፣ ሳሙኤል ዘቆየጻና ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን የመሰሉ ናቸው። አቡነ ሳሙኤል ከስድስቱ ባልንጀሮቻቸው ጋር ሆነው በደብረ በንኮል ተጋድሎን አሐዱ አሉ። እንጨት ይሰብራሉ፣ ውኃ ይቀዳሉ፣ እህል ይፈጫሉ። በፍጹም ልባቸውም ይታዘዛሉ። ጐን ለጐን ደግሞ ከቅዱሱ አበ ምኔት መድኃኒነ እግዚእ ጽንዓትን፣ ትሕትናን፣ ትሕርምትን ይማሩ ሥርዓተ ገዳምንም ያጠኑ ነበር። ከአገልግሎታቸው ማማር የተነሳ ሁሉን ደስ ማሰኘት ቻሉ። በዚህ ጊዜም ጻድቁ አበ ምኔት አቡነ ሳሙኤል ዘዋሊንና ስድስቱን አበው ጠርተው ለምንኩስና አቀረቧቸው። "ይገባችኋል!" ሲሉም ከአሞክሮ ወደ ምንኩስና አሸጋገሯቸው። በዚያች ቀን ሰባቱ ሲመነኩሱ ከሰማይ ብርሃን ወርዶ በመታየቱ ቅዱሳኑ "ከዋክብት ብሩሃን" ተባሉ። ለተወሰነ ጊዜም በዚያው በገዳሙ አገለገሉ። የአቡነ ሳሙኤል ዘመዶች ግን እየመጡ ጻድቁን ስላስቸገሩ ሰባቱም ቅዱሳን ተመካክረው ከአባታቸው መድኃኒነ እግዚእ ተባርከው ከደብረ በንኮል ወጡ። ሁሉም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራቸው ሲሔዱ ሦስቱ (ማለትም ሳሙኤል ዘዋሊ፣ ያሳይ ዘመንዳባና ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤ) ወደ ጣና ሔዱ። በዚያም ለጥቂት ጊዜ አብረው ከቆዩ በኋላ ለአገልግሎት ተለያዩ። አቡነ ያሳይ "መንዳባን"፣ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ "ጉጉቤን" ይዘው እዚያው ጣና አካባቢ ሲቀሩ አባ ሳሙኤል ወደ ዋልድባ ሔዱ። ዋልድባ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በጌታ ፈቃድ የተመሠረተ ሲሆን ስምንት መቶ ስልሳው መሥራች ቅዱሳን በመሠወራቸው እንደ ጠፍ ይቆጠር ነበርና አቡነ ሳሙኤል እንደ ገና አቀኑት። ጻድቁ በዋልድባ የመጨረሻውን ትሕርምት ከመያዛቸው በፊት በጊዜው ከፍተኛ የሆነ የወንጌል አገልግሎት ሰጥተዋል። ቀጥለውም ኑሯቸውን ከግሩማን አራዊት ጋር አድርገዋል። ለዘመናትም በአንበሳ ጀርባ ላይ ተጭነዋል። ጧት ማታም ብዙ ግሩማን አራዊትን እያስከተሉ ለአገልግሎት ደክመዋል። ጻድቁ ከትሕርምት ብዛት እህል ትተው የሻገተ ጐመንና መልኩን የለወጠ ውኃን ለቁመተ ሥጋ ይጠቀሙ ነበር። አንድ ቀንም መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደ እርሳቸው መጥቶ ባረካቸው። አካላቸውንም በቅዱስ ምራቁ አትቦ ቀባቸው። በዚህ ጊዜም ኃይለ መንፈስ ቅዱስን ተመሉ። የክርስቶስን ሕማማት እያሰቡም እልፍ ጊዜ ይሰግዱ ጀርባቸውን ይገርፉም ነበር። እግራቸውን በሰንሰለት አሥረው ይጋደሉም ነበር። በዚህ ግብራቸው አጋንንትን አሳፍረው ፈጣሪያቸውን ደስ አሰኙ። ከቆይታ በኋላም ዋልድባ በመነኮሳት ተሞላ። ደቀ መዛሙርት በዙ። ቀዳሚው ግን አባ ዘሩፋኤል ጻድቅ ነው። አቡነ ሳሙኤል ከድንግል እመቤታችን ጋር ልዩ ፍቅር ነበራቸው። ዘወትር ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን በተመስጦ ያደርሱላት ፈጽመውም ያመሰግኗት ነበር። ይህንን ሲያደርጉ ከመሬት ክንድ ከፍ ብለው ይንሳፈፉ ነበር። ተከታዮቻቸው ሲርባቸውም ውኃውን በቅዳሴ ማርያም ነጭ ሕብስት ያደርጉት ነበር። "ሶበ አተቦ ለማይ በቅዳሴኪ እንዘ ይጼሊ ረሰዮ ሕብስተ ሳሙኤል ጽጌ ሃይማኖት ዘሐቅለ ዋሊ ምሕረተ ወፍትሐ ለተአምርኪ እኅሊ ስረዪ ኃጢአትየ ወዕጸብየ አቅልሊ እስመ ኩሎ ገቢረ ማርያም ትክሊ።" እንዳለ ሊቁ። (ማኅሌተ ጽጌ) እመ ብርሃንም ስለ ፍቅር ነጭ እንቁ ሰጠቻቸው። ሰማያዊ ሕብስትን መገበቻቸው። ንጹሕ ዕጣንንም አበረከተችላቸው። ለአሥራ ሁለት ዓመታትም ከሰማይ ካህናት ጋር አጠኑ። ድንግል ማርያም "እንዳንተ ውዳሴዬንና ቅዳሴዬን በፍቅር የሚደግምልኝን አማልደዋለሁ።" ስትላቸው ጌታ ደግሞ ገዳማቸውን ዋልድባን ቀድሷታል። ቀድሞም በስደቱ ባርኳት ነበር። የጻድቁ ዜና ፈጽሞ ብዙ ነውና ለዛሬ በዚህ ይብቃን። የዋልድባው ኮከብ አቡነ ሳሙኤል ያረፉት ታኅሣሥ ፲፪ ቀን በ፲፫፻፺፭ ዓ/ም ሲሆን ዕድሜአቸውም መቶ ዓመት ነበር። ለጻድቁ ክብር ይገባል! ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                13. ቅዱስ ሩፋኤል
                  15. አባ ጎርጎርዮስ (እረፍቱ) ዘሀገረ አርማንያ
                    19. በዓለ ቅዱስ ገብርኤል
                      ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከሰባቱ ሊቃናት አንዱ፣ በራማ አርባብ በሚባሉ አሥር ነገደ መላእክት ላይ የተሾመ፣ በመጀመሪያዋ የፍጥረት ቀን መላእክትን ያጸና፣ ቅዱሳንን ሁሉ የሚረዳ፣ ሠለስቱ ደቂቅን፣ ዳንኤልንና ሶስናን ከሞት የታደገ ታላቅ መልአክ ነው። ከምንም በላይ ቤተ ክርስቲያን "መጋቤ ሐዲስ" ብላ ታከብረዋለች። የስሙ ትርጓሜ "አምላክ ወሰብእ - እግዚእ ወገብር" ነውና ለሥነ ፍጥረት ሁሉ የሚሆን ሐዲስ ዜናን ወደ እመቤታችን ድንግል ማርያም አምጥቷል። መልአኩ እመቤታችንን ከመጸነሷ ጀምሮ ባይለያትም ከእግዚአብሔር ተልኮ አብስሯታል። ቅዱስ ገብርኤል ዛሬ የብሥራቱ መታሰቢያና ዳናህ በተባለ ሃገር ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት ነው። "ገብርኤል ዜናዊ ምጽዓተ ክርስቶስ አንበሳ ለዛቲ በዓልከ በዘይትሌዓል ሞገሳ በዓለ ማርያም አንበረ ደቅስዮስ በርዕሳ።" እንዲል። (አርኬ) ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን። አዕምሮውን ጥበቡን በልቡናችን አሳድሪብን።
                    22. ብስራተ ገብርኤል /እመቤታችን ክርስቶስን እንደምትወልድ ያበሰረበት/
                      24. አቡነ ተክለሀይማኖት /ልደታቸው/
                        ልደት መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው። እርሱ በክህነቱ እርሷ በደግነቷ፣ በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል። በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል ጸጋ ዘአብን ከሞት እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል። በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል። ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጸነሱት መጋቢት ፳፬ ቀን በ፲፪፻፮ ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን በ፲፪፻፯ ዓ/ም ነው። በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል። ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል። ዕድገት  የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል። ይህንን ስም ይዘው አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል። በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት፣ ሐዲሳትን) ተምረዋል። በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል። ዲቁናም ከወቅቱ ጳጳስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል።  መጠራት  አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑት በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ። የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ። "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን። ከዚህ በኋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ። ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ።" ብሎ በግርማ ዐረገ። ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ በኋላ ሰዓትን አላጠፉም። ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ። አገልግሎት  ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከጳጳሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ። በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ሁለት መልክ ነበራት። ፩ኛ.ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል። ፪ኛው. ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር። ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ። ሕዝቡንና መሳፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው ማርያኖችን (ጠንቋዮችን) አጥፍተዋል።  ገዳማዊ ሕይወት  ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮጵያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል። እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በሦስት ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል። እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለአሥራ ሁለት ዓመታት፣ በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለሰባት ዓመታት፣ በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለሰባት ዓመታት በአጠቃላይ ለሃያ ስድስት ዓመታት አገልግለዋል። በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ (ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለሃያ ሁለት ዓመታት ቆመው ጸልየዋል። በተሰበረ እግራቸውም ስድስት ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለሰባት ዓመታት ጸልየዋል።  ስድስት ክንፍ  ኢትዮጵያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል። ጻድቁ ምድረ እስራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ፣ እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር። የወቅቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል። ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው። ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም። በገሃድ፦ በቤተ መቅደስ ብስራቱን፣ በቤተ ልሔም ልደቱን፣ በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን፣ በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን፣ በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር። የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ። በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ አባታችንን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው። በዚያም፦ የብርሃን ዓይን ተቀብለው፣ ስድስት ክንፍ አብቅለው፣ የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው፣ ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው፣ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው፣ ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው "ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል። ተአምራት  የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው። ሙት አንስተዋል፣ ድውያንን ፈውሰዋል፣ አጋንንትን አሳደዋል፣ እሳትን ጨብጠዋል፣ በክንፍ በረዋል፣ ደመናን ዙፋን አድርገዋል። ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል። በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕፃናት አብረው ኑረዋል። በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና። ዕረፍት  ጻድቅ፣ ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው፣ መከራን በብዙ ተቀብለው፣ እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው በተወለዱ በዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀናቸው ነሐሴ ፳፬ ቀን በ፲፫፻፮ ዓ/ም ዐርፈዋል። ጌታ፣ ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል። አሥር ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                      28. ቅዱስ አማኑኤል በዓለ ልደት ለእግዚእነ ገና
                        የክርስትና ሃይማኖት እጅግ ብዙ ምሥጢራትን ያካትታል። ታላቅ መዝገብ ነውና። ሰዎች እናልፋለን። ዓለምም ታረጃለች እንጂ ምሥጢረ ክርስትና አያረጅም። እዚህ ቦታ ላይ ይጠናቀቃልም አይባልም። "አማኑኤል" የሚለውን ስም መረዳት የሚቻለው በአንድ መንገድ እርሱም ምሥጢረ ሥላሴንና ምሥጢረ ሥጋዌን ጠንቅቆ በመማር ነው። ምሥጢራት ደግሞ በእምነት ለማይኖር በትሕትናም ለማይቀርብ የሚገለጡ አይደሉም። እግዚአብሔር አንድም ነው፤ ሦስትም ነው። ጊዜ ሣይሠፈር ዘመንም ሳይቆጠር እግዚአብሔር በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስትነቱ፤ በባሕርይ፣ በሕልውና፣ በመለኮትና በሥልጣን አንድነቱ የጸና አምላክ ነው። ከዓለም መፈጠር በፊት ስለ ነበረው ነገር የሚያውቅ ራሱ ሥላሴ ብቻ ነው። ዓለምን ከፈጠረ በኋላም ምሥጢረ ሥላሴ (መለኮት) ብለን የምንማረው ትምህርት እንድንና እንጠቀም ዘንድ እርሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ ነው። ይኸውም በየጊዜው እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ቅዱሳኑ የገለጠው ምሥጢር ነው። ከዚህ አልፈን በሥጋዊ አዕምሯችን ጌታን "እንመርምርህ" ብንለው ግን ፍጻሜአችን ሞት ማደሪያችንም ገሃነመ እሳት መሆኑ አይቀርም። ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና እግዚአብሔር በአንድነቱና ሦስትነቱ ሳለ ይህንን ዓለም ፈጠረ። እግዚአብሔር ዓለምን ለምን ፈጠረ ቢሉ፦ ስሙን ቀድሰን ክብሩን እንድንወርስ ነው። ከዚህ የተረፈውን ምክንያት ግን ራሱ ባለቤቱ ያውቃል። እግዚአብሔር በኋለኛው ዘመን ሰው የሆነበት ምሥጢር እኛን ለማዳን ቢሆንም ይሔው ተግባሩ ዓለም ሳይፈጠር ያሰበው እንጂ በአዳም ውድቀት ምክንያት ድንገት የታሰበ አይደለም። እግዚአብሔር አዳምን በሰባት ሃብታት አክብሮ በገነት ቢያኖረው "አትብላ" የተባለውን ዕፀ በለስ በላ። በዚህም ከፈጣሪው ተጣልቶ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈረደበት። በኋላ ግን ንስሐ ስለ ገባ "ከአምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን) በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ።" የሚል ቃል ኪዳንን ሰጠው። ከዚህ በኋላ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት ጊዜ ወደ ታች ይቆጠር ጀመር። ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆንና ዓለምን ማዳንም ትንቢት ይነገር፣ ሱባኤ ይቆጠር፣ ምሳሌም ይመሰል ገባ። ከአዳም እስከ ሙሴ (ዘመነ አበው) ምሳሌያት ይበዛሉ። ከሙሴ እስከ ዳዊት (ዘመነ መሳፍንት) ምሳሌያቱ እየጐሉ መጥተዋል። ከልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እስከ ቅዱስ ሚልክያስ ድረስ (በዘመነ ነቢያት /ነገሥት) ግን ትንቢቶች ስለ ክርስቶስና ስለ ማደሪያ እናቱ እንደ ጐርፍ ፈሰዋል። ነቢያትም የመሲህን መምጣት እየጠበቁ በጾም፣ በጸሎትና በትሕርምት ኑረዋል። እንባቸውንም አፍሰው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶላቸዋል። መድኅን ክርስቶስም ተወልዶ አድኗቸዋል። "አማኑኤል" የሚለው ቃል ከዕብራይስጥ ልሳን (ከጽርዕ የሚሉም አሉ።) በቀጥታ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም "እግዚአብሔር ምስሌነ - እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ።" እንደ ማለት ነው። (ኢሳ. ፯፥፲፬ ፣ ማቴ. ፩፥፳፪) ምሥጢሩ ግን ከዚህ የሠፋ ነው። "አማኑኤል" ማለት "እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋን ከነፍሳችን ነፍስን ነስቶ በፍጹም ተዋሕዶ እኛን መሰለን።" ማለት ነው። በሌላ አነጋገርም "አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰውም አምላክ ሆነ።" እንደ ማለት ነው። ይህንን ሲያደንቁ ቅዱሳን ሊቃውንት "ወዝንቱ ስም ዓቢይ ወኢይደሉ ፈሊጦቶ - ይህ ስም ታላቅ ነው። ወደ ሁለት ሊከፍሉት (ሊለዩት) አይገባም።" ብለው ምሥጢረ ተዋሕዶን አስረድተዋል። (ሃይማኖተ አበው ዘሳዊሮስ) ስለዚህም ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ እኛን ያድን ዘንድ በተለየ አካሉና በከዊነ ቃልነቱ ፍጹም የድንግል ማርያምን ሥጋ ተዋሕዶ የሰውነትንም የአምላክነቱንም ሥራ ሠርቶ አድኖናል። በማኅጸነ ድንግል ከተቀረጸባት ደቂቃ ጀምሮም ፍጹም ተዋሕዶን ፈጽሟልና መቼም መች አምላክም፣ ሰውም ነው እንጂ ወደ ሁለትነት ማለትም አምላክን ለብቻ ሰውን ለብቻ አናደርግም። ስለዚህም ዛሬም ዘወትርም እግዚአብሔር ቃል የተዋሐደው ሥጋችን በዘባነ ኪሩብ ሲሠለስና ሲቀደስ ይኖራል። እርሱ ጌታችን እስከዚህ ድረስ ወዶናልና። ፈጣሪያችን በሦስትነቱ ሥላሴ (አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ) በአንድነቱ እግዚአብሔር፣ ኤልሻዳይ፣ አልፋ፣ ወዖ፣ ቤጣ፣ የውጣ፣ ኦሜጋ..... እያልን እንደምንጠራው ሁሉ በሥጋዌው ምክንያት አማኑኤል፣ መድኃኔ ዓለም፣ ኢየሱስ፣ ክርስቶስ እያልን እንጠራዋለን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                      29. ቅዱስ በዓለ ወለድ /ተዘከረ ልደቱ ለእግዚነ/ገና/
                        ዓለማትን፣ ዘመናትን፣ ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ፣ ወልደ አምላክ ነው። የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ ሲሆን ራሱም እግዚአብሔር ነው። በባሕርየ ሥላሴ መበላለጥ የለምና ወልድ ክርስቶስ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትክክል ነው እንጂ አይበልጥምም አያንስምም። እርሱ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ማዕከለ ዓለም ያለና ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ጌታ ነው። ቀዳማዊና ደኃራዊው አልፋና ኦሜጋ እርሱ ነው። (ዮሐ. ፩፥፩ ፣ ራእይ ፩) ሁሉ በእጁ የተያዘ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክ (ሮሜ. ፱፥፭)፣ የዘላለም አባት፣ የሰላምም አለቃ ነው። (ኢሳ. ፱፥፮) ቅድመ ዓለም ሲሠለስ ሲቀደስ ኑሮ ይህንን ዓለም ፈጠረ። እርሱ ሁሉን ያስገኛል እንጂ ለእርሱ አስገኝ የለውም። አንድ ክርስቲያን ከሁሉ አስቀድሞ ሊያውቀው የሚገባ መሠረተ እምነት ይሔው ነው! መድኃኒታችን ክርስቶስን በዚህ መንገድ የማያምንና የማያመልክ ሁሉ እርሱ ክርስቲያን አይደለም። ምንም ሥጋችንን ተዋሕዶ ብዙ የትሕትና ሥራዎችን ቢሠራም፣ ቢሰቀል፣ ቢሞትም እርሱ እግዚአብሔር ነውና ፍጹም አምላክ ፍጹምም ሰው ብለን ልናመልከው ይገባል። እንደ አርዮስ፣ ንስጥሮስና ልዮን የማይገቡ ነገሮችን መናገር ጐዳናው የሞት መዳረሻውም ገሃነመ እሳት ነው። እንኳን የክብር ባለቤት መድኅን ክርስቶስ ላይ በፍጡር ላይ እንኳ የማይገባ ነገርን የተናገረ ሁሉ የገሃነም ፍርድ አለበት። ለእርሱ የዓለም ፈጣሪ፣ ጌታና ቤዛ ለሆነው መድኅን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለም ምስጋና፣ ጌትነት፣ ውዳሴና አምልኮ ይሁን! እግዚአብሔር አዳምን በሰባት ሃብታት አክብሮ በገነት ቢያኖረው "አትብላ" የተባለውን ዕፀ በለስ በላ። በዚህም ከፈጣሪው ተጣልቶ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈረደበት። በኋላ ግን ንስሐ ስለ ገባ "ከአምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን) በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ።" የሚል ቃል ኪዳንን ሰጠው። ከዚህ በኋላ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት ጊዜ ወደ ታች ይቆጠር ጀመር። ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆንና ዓለምን ማዳንም ትንቢት ይነገር፣ ሱባኤ ይቆጠር፣ ምሳሌም ይመሰል ገባ። ከአዳም እስከ ሙሴ (ዘመነ አበው) ምሳሌያት ይበዛሉ። ከሙሴ እስከ ዳዊት (ዘመነ መሳፍንት) ምሳሌያቱ እየጐሉ መጥተዋል። ከልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እስከ ቅዱስ ሚልክያስ ድረስ (በዘመነ ነቢያት /ነገሥት) ግን ትንቢቶች ስለ ክርስቶስና ስለ ማደሪያ እናቱ እንደ ጐርፍ ፈሰዋል። ነቢያትም የመሲህን መምጣት እየጠበቁ በጾም፣ በጸሎትና በትሕርምት ኑረዋል። እንባቸውንም አፍሰው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶላቸዋል። ልደተ ክርስቶስ እምድንግል  "ጊዜው ሲደርስ አንባ ይፈርስ።" እንዲሉ አበው መድኃኒታችን የጥልን ግድግዳ ያፈርስ ዘንድ፣ ከኃጢአትና ከሞት ቁራኝነት ይፈታን ዘንድ፣ ለሰዎች ቤዛ ይሆን ዘንድ፣ ትንቢተ ነቢያትን ይፈጽም ዘንድ፣ በቀጠሮ (በአምስት ቀን ተኩል) ወደዚህ ዓለም መጣ። የሰማይና የምድር ጌታ በእንግድነት በመጣ ጊዜም እርሱን ለመቀበል በተገባ የተገኘች ንጽሕት ሙሽራ ድንግል ማርያም ሆነች። ከእርሷ በቀር ለዚህ ክብር ሊበቃ የሚቻለው ፍጥረት እንኳን ኃጢአት ካደከመው የሰው ልጅ ከንጹሐን መላእክት ወገን አልተገኘም። በጊዜውም መልአከ ትፍሥሕት ቅዱስ ገብርኤል መጋቢት ፳፱ ቀን ወደ ድንግል ወርዶ የአምላክን ሰው የመሆን ዜና ከውዳሴና ከክብር ጋር ነገራት። (ሉቃ. ፩፥፳፮) ድንግልም ለዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሰማይና ምድር የማይችሉትን መለኮትን ተሸከመች። ልክ ሙሴ በደብረ ሲና እንዳያት ዕጽ ድንግል ማርያምንም ባሕርየ መለኮቱ አላቃጠላትም። ስለዚህም ነገር "ወላዲተ አምላክ፣ ታኦዶኮስ፣ ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቅድስተ ቅዱሳን፣ ንግሥተ አርያም፣ የባሕርያችን መመኪያ....." እያልን እንጠራታለን። ግሩም ድንቅ ጌታን ጸንሳ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን እስኪፈጸም ድረስ ብዙ ተአምራትን ሠራች። መላእክተ ብርሃን እየታጠቁ አገለገሏት፤ አመሰገኗት። ልጇን አምላክ፣ እርሷን እመ አምላክ እያሉ ተገዙላት። ከዚያም በሮሙ ቄሣር በአውግስጦስ ዘመን ሰው ሁሉ ይቆጠር ዘንድ አዋጅ ወጥቷልና እመ ብርሃን ማርያም ከቅዱሳኑ ዘመዶቿ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ወደ አባቷ ዳዊት ከተማ ወደ ቤተ ልሔም ሔደች። በዚያም ሳሉ የምትወልድበት ጊዜ ቢደርስ በፍጹም ድንግልና እንደ ጸነሰችው ሁሉ በፍጹም ድንግልና ወለደችው። (ኢሳ. ፯፥፲፬ ፣ ሕዝ. ፵፬፥፩) ተፈትሖም አላገኛትም። ልማደ አንስትም አልጐበኛትም። ምጥም አልነበረባትም። ድንግል ማርያም ክርስቶስን በወለደች ጊዜ ልጇ አምላክ፣ እርሷም የአምላክ እናት መሆኗ ይታወቅ ዘንድ፦ ፩.የብርሃን ጐርፍ ፈሰሰ፤ ፪.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ወርደው "ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም" እያሉ ዘመሩ፤ ፫.ትጉሐን እረኞች በቅዱስ ገብርኤል መሪነት መጥተው ክብሩን ተካፈሉ፤ ፬.በሰማይም ልዩ ኮከብ ድንግልና ልጇ ተስለውበት ዝቅ ብሎ ታየ፤ ፭.ቅድስት ሰሎሜም በድፍረት የድንግልን ሆድ ዳስሳ እጇ ቢቃጠል እንደ ገና በተአምራት ድኖላታል። በጊዜውም በምሥራቅ የፋርስ፣ የባቢሎንና የሳባ ነገሥት አስቀድሞ ከበለዓም በኋላም ከዠረደሸት በተረዱት መሠረት ኮከቡን በማየታቸው ታጥቀው ተነሱ። ከምሥራቅ አፍሪቃና ከእስያም በተመሳሳይ ኮከቡን በማየታቸው አሥራ ሁለት ነገሥታት በየግላቸው አሥር፣ አሥር ሺህ ሠራዊትን እየያዙ ድንግልንና ንጉሥ ልጇን ፍለጋ ወጡ። አሥራ ሁለቱ ነገሥታት ከነ ሠራዊታቸው ሲሔዱ ስንቃቸው በማለቁ ዘጠኙ ነገሥታት ተስፋ ቆርጠው ተመለሱ። ሦስቱ ግን በፍጹም ጥብዓት ከሠላሳ ሺህ ሠራዊት ጋር በኮከብ እየተመሩ ኢየሩሳሌም ደረሱ። እነዚህም መሊኩ የኢትዮጵያ (የሳባ ንጉሥ ተወላጅ)፣ በዲዳስፋና መኑሲያ (ማንቱሲማር) ደግሞ የፋርስና የባቢሎን ነገሥታት ናቸው። ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርሱም ሄሮድስና ሠራዊቱ ታወኩ። እነርሱ ግን የቤተ ልሔምን ዜና ከጠየቁ በኋላ በጐል ድንግል ማርያምን፣ ክርስቶስን፣ ዮሴፍና ሰሎሜን አገኙ። ለሁለት ዓመታት እነርሱን ፍለጋ ደክመዋል ተንከራተዋልና ደስታቸው ወሰን አጣ። በእመቤታችንና በልጇ ፊት በደስታ ዘለሉ። "አንፈርዓጹ ሰብአ ሰገል" እንዲል። ወርቁን፣ እጣኑንና ከርቤውንም ገብረው በግንባራቸው በፊቱ ሰገዱ። ሦስት ጊዜም እየወጡ እየገቡ ቢመለከቱት በኪነ ጥበቡ አንዴ እንደ ሕፃን፣ በሁለተኛው እንደ ወጣት፣ በሦስተኛው እንደ አረጋዊ ሆኖ ታይቷቸው ፈጽመው አድንቀዋል። ወደ ሃገራቸው ሲመለሱም "ወአስነቀቶሙ ሕብስተ ሰገም" እንዲል የገብስ ዳቦ ጋግራ ድንግል ለሰብአ ሰገል ሰጠቻቸው። እነርሱም ይህንን እየተመገቡ የሁለት ዓመቱን መንገድ በአርባ ቀን ሲጨርሱት ዳቦው ግን ያ ሁሉ ሺህ ሰው ተመግቦት አላለቀም። ተአምራትንም ሠርቷል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                    ጥር
                      1. ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሚ ሰማእት (እረፍቱ)
                        በሕገ ወንጌል (ክርስትና) የመጀመሪያው ሊቀ ዲያቆናትና ቀዳሚው ሰማዕት ይህ ቅዱስ ነው። ቅዱሱ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን አስገራሚ ማንነት ከነበራቸው እስራኤላውያን አንዱ ነበር። ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ የቅዱስ እስጢፋኖስ ወላጆቹ ስምዖንና ማርያም ይባላሉ። (ሌሎች ናቸው የሚሉም አሉ።) ገና ከልጅነቱ ቁም ነገር ወዳድ የነበረው ቅዱስ በሥርዓተ ኦሪት አድጐ እድሜው ሲደርስ ወደ ትምህርት ቤት ገባ። የወቅቱ ታላቅ መምህር ገማልያል ይባል ነበር። ይህ ሰው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፭፥፴፫ ላይ ተጠቅሷል። በትውፊት ትምህርት ደግሞ ይህ ደግ (ትልቅ) ሰው በርካታ ቅዱሳንን (እስጢፋኖስን፣ ጳውሎስን፣ ናትናኤልን፣ ኒቆዲሞስን.....) አስተምሯል። በጌታችን መዋዕለ ስብከት ጊዜም ከፈጣሪያችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እየቀረበ ይጨዋወት ነበር። በፍጻሜውም አምኗል። ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ እስጢፋኖስ ከዚህ ምሑር ዘንድ ተምሮ ኦሪቱን ነቢያቱን ጠንቅቆ ወጣ። ወቅቱ አስቸጋሪና ለኃጢአት ሕይወት የተመቸ ቢሆንም ቅዱሱ ግን የመሲህን መምጣት በጸሎትና በተስፋ ይጠባበቅ ነበር። በወቅቱ ደግሞ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀትን እየሰበከ መምጣቱን የተመለከተ ቅዱስ እስጢፋኖስ ነገሩን መረመረ። ከእግዚአብሔር ሆኖ ቢያገኘው የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆነ። ለስድስት ወራትም በትጋት ቅዱስ ዮሐንስን አገለገለ። ለስድስት ወራት ከቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ ከተማረ በኋላ ለስም አጠራሩ ስግደት ይድረሰውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠመቀ። በወቅቱ የተደረገውን ታላቅ ተአምር ልብ ያለው ቅዱስ እስጢፋኖስ መምህሩን ቅዱስ ዮሐንስን እንዲያስረዳው ጠየቀው። "ከእኔ ይልቅ ከፈጣሪው አንደበት ይስማው።" በሚል ላከው። ቅዱሱም ከጌታ ዘንድ ሔዶ እጅ ነስቶ ተማረ። (ሉቃ. ፯፥፲፰) በዚያውም የጌታ ደቀ መዝሙር ሆኖ ቀረ። ጌታም ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ አድርጐት ለአገልግሎት ላከው። አጋንንትም ተገዙለት። (ሉቃ. ፲፥፲፯) ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታችን መድኃኔ ዓለም ከዋለበት እየዋለ ካደረበት እያደረ ወንጌልን ተማረ። ምሥጢር አስተረጐመ። ጌታ በፈቃዱ ስለ እኛ ሙቶ ከተነሳ በኋላ ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱን በአንብሮ እድ ባርኳል። በዚህ ጊዜም ቅዱሱ እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ቅስናን (ጵጵስናን) ተሹሟል። በበዓለ ሃምሳም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የእርሱን ያህል ልሳን የበዛለት ምሥጢርም የተገለጠለት የለም። በፍጹም ድፍረትም ወንጌልን ይሰብክ ገባ። በመጀመሪያይቱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከማዕድ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ፈተና ሲመጣ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ ሰባት ዲያቆናት ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር። አልፎም የስድስቱ ዲያቆናት አለቃ እና የስምንት ሺህው ማኅበር መሪ (አስተዳዳሪ) ሆኗል። ስምንት ሺህ ሰውን ከአጋንንት ፈተና መጠበቅ ምን ያህል ከባድ እንደ ሆነ ለማወቅ አባቶቻችንን መጠየቅ ነው። አንድን ሰው ተቆጣጥሮ ለድኅነት ማብቃት እንኳ እጅግ ፈተና ነው። መጽሐፍ እንደሚል ግን "መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ማሕደረ እግዚአብሔር" ነውና ለእርሱ ተቻለው። (ሐዋ. ፮፥፭) አንዳንዶቻችን ቅዱስ እስጢፋኖስ "ሊቀ ዲያቆናት" ሲባል እንደ ዘመኑ ይመስለን ይሆናል። እርሱ በመጀመሪያ ሐዋርያና ካህን ነው። ዲቁናው ለእርሱ "በራት ላይ ዳረጐት" ነው እንጂ እንዲሁ ዲያቆን ብቻ አይደለም። ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጌታ ዕርገት በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ስምንት ሺህውን ማኅበር እየመራ ወንጌልን እየሰበከ ቢጋደል ኦሪት "እጠፋ እጠፋ" ወንጌል ደግሞ "እሰፋ እሰፋ" አለች። በዚህ ጊዜ "ክርስትናን ለማጥፋት መፍትሔው ቅዱስ እስጢፋኖስን መግደል ነው።" ብለው አይሁድ በማመናቸው ሊገልድሉት አስበውም አልቀሩ ገደሉት። እርሱ ግን ፊቱ እንደ እግዚአብሔር መልአክ እያበራ ፈጣሪውን በብዙ ነገር መሰለው። በመጨረሻውም ስለ እነሱ ምሕረትን እየለመነ በድንጋይ ወገሩት። ደቀ መዛሙርቱም ታላቅ ለቅሶን እያለቀሱ ቀበሩት። ቅዱስ እስጢፋኖስ ካረፈ ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ በኢየሩሳሌም የሚኖር አንድ ደግ ሰው ነበር። ስሙም ሉክያኖስ ይባል ነበር። በተደጋጋሚ በራእይ ቅዱሱ እየተገለጠ "ሥጋዬን አውጣ።" ይለው ነበርና ሒዶ ለጳጳሱ ነገረው። ጳጳሱም ደስ ብሎት ካህናትና ምዕመናንን ሰብስቦ ወደ አጸደ ገማልያል (የመምህሩ ርስት ነው።) ሔደ። ቦታውንም በቆፈሩ ጊዜ ታላቅ መነዋወጥ ሆነ። መላእክት ሲያጥኑ በጐ መዓዛ ሸተተ። ዝማሬ መላእክትም ተሰማ። ሕዝቡና ጳጳሱም በቅዱስ እስጢፋኖስ ፊት ሰግደው በታላቅ ዝማሬና በሐሴት ዐጽሙን ከዚያ አውጥተው በጽርሐ ጽዮን (በተቀደሰችው ቤት) አኖሩት። እለ እስክንድሮስ የተባለ ደግ ሰውም ቤተ ክርስቲያን አንጾለት ወደዚያ አገቡት። ከአምስት ዓመታት በኋላም እለ እስክንድሮስ ሲያርፍ በሳጥን አድርገው በቅዱሱ ጐን ስለ ፍቅሩ አኖሩት። ሚስቱ ወደ ሃገሯ ቁስጥንጥንያ ስትመለስ የባሏ ሥጋ መስሏት የቅዱስ እስጢፋኖስን ቅዱስ ሥጋ በመርከብ ጭና ወሰደችው። መንገድ ላይ ከሳጥኑ ውስጥ ዝማሬ ሰምታ ብታየው ያመጣችው የቅዱሱን ሥጋ ነው። እጅግ ደስ አላት። አምላክ ለዚህ አድሏታልና። እርሷም ወስዳ ለታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ አስረከበች። በከተማውም ታላቅ ሐሴት ተደረገ። ሥጋውን ሊያኖሩት በበቅሎ ጭነው ሲወስዱትም በቅሎዋ በሰው ልሳን ተናግራ ማረፊያውን አሳወቀች። በዚያም ላይ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ታንጾለታል። ቅዱስ እስጢፋኖስ "ሲመቱ" ጥቅምት ፲፯ ፣ "ዕረፍቱ" ጥር ፩ ፣ "ፍልሠቱ" ደግሞ መስከረም ፲፭ ቀን ነው። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                      4. ቅዱስ ዮሐንስ /ወንጌላዊ/ወልደ ነጎድጓድ
                        አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ እንደነገረን በመንግሥተ ሰማያት ታላቁ ሰው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ነው። ቅዱሱ ሐዋርያ ከዘብዴዎስና ከማርያም ባውፍልያ ተወልዶ በገሊላ አካባቢ አድጐ ገና በወጣትነቱ መድኃኔ ዓለምን ተከትሎታል። (ዮሐ. ፩፥፴፱) ቅዱስ ዮሐንስ ከሐዋርያት ቀድሞ ጌታን ከመከተሉ ባሻገር በምንም ምክንያት ከጐኑ አይጠፋም ነበር። ስለ ንጽሕናውና በጐ የፍቅር ሕሊናው ሕፃን ሳለ በወንድሞቹ ሐዋርያት ዘንድ ሞገሱ ከፍ ያለ ነው። ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ድንግል እመቤታችንን ተቀብሏል። (ዮሐ. ፲፱፥፳፭) ከእርሷ ጋር ለአሥራ አምስት ዓመታት ቢቀመጥ መዝገበ ምሥጢር ሆነ። ስንኳን ከሰው ልጆች ይቅርና ከልዑላኑ መላእክትም ማዕረጉ ከፍ አለ። ሰው ቢበቃ መላእክትን ሊያይ ይቻለዋል። ቅዱስ ዮሐንስን ግን መላእክት ሊያዩት ይከብዳቸዋል። ከፍጥረት ወገን ከእመ ብርሃን ቀጥሎ ክቡር እርሱ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ በታናሽ እስያ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መስበኩ ይታሰባል። ቅዱሱ ከጌታችን ዕርገት በኋላ ለሰባ ዓመታት በዚህ ምድር ሲኖር አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በኤፌሶን አካባቢ ነው። ሕዝቡን ወደ ክርስትና ለማምጣት በአፍም በመጽሐፍም ደክሟል። ሦስት መልእክታት፣ ራእዩንና ወንጌልን ጽፎላቸዋል። ሕይወትን ስለ ሰበከላቸው በፈንታው ብዙ አሰቃይተውታል። ከእሳት እስከ ስለት እስከ መጋዝም በስተእርጅና ደርሶበታል። እርሱ ግን በትእግስቱ ገንዘብ አድርጓቸዋል። ይህች ኤፌሶን የሚሏት ሃገር መገኛዋ በቀድሞው ታናሽ እስያ (አሁን ቱርክ አካባቢ) ሲሆን ብዙ ሐዋርያት አስተምረውባታል። ያም ሆኖ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ያመጣች አልነበረችምና ቅዱስ ዮሐንስ ሊሔድ ተነሳ። ከደቀ መዛሙርቱ መካከልም ቅዱስ አብሮኮሮስን (ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ነው።) አስከትሎ እየጸለዩ በመርከብ ላይ ተሳፈሩ። ሐዋርያት አበው መከረኞች ናቸውና ማዕበል ተነሳባቸው። በጥቂት አፍታም መርከባቸው በማዕበሉ ተበታተነች። ቅዱስ አብሮኮሮስ በስባሪ ላይ ተሳፍሮ ወደ አንዲት ደሴት ደረሰ። ግን ከንጹሑ መምህሩ ቅዱስ ዮሐንስ ተለይቷልና አለቀሰ። ፍቁረ እግዚእ ግን ያለ ምግብና ውኃ ማዕበለ ባሕር እያማታው ለአርባ ቀናት ቆየ። እርሱ በፈጣሪው ፍቅር የተመሰጠ ነበርና አለመመገቡ አልጐዳውም። በአርባኛው ቀን ግን ደቀ መዝሙሩ ወዳለበት ደሴት ማዕበሉ አደረሰው። ሁለቱ ቅዱሳን ተፈላልገው ተገናኙ። እጅግም ደስ ብሏቸው ፈጣሪን አመሰገኑ። አምላካቸው ወደዚህች ደሴት ያመጣቸው በጥበቡ ነውና ሲዘዋወሩ ሁለት ነገርን አስተዋሉ። ፩ኛ.የደሴቷ ሁሉም ነዋሪ የሚያመልኩት ጣዖትን ነው። ፪ኛ.አብዛኞቹ ልዑላን (የቤተ መንግሥት ውላጆች) ናቸው። ሮምና የሚሏት አንዲት ሴት ደግሞ እነዚህን ሁሉ እየመገበች ታስተዳድራለች። ቅዱሳኑ በቦታው በቀጥታ ትምህርተ ወንጌልን ቢናገሩ እንደ ማይቀበሏቸው ስለ ተረዱ ሌላ ፈሊጥን አሰቡ። እንዳሰቡትም ወደ እመቤት ሮምና ቤት ሒደው በባርነት ተቀጠሩ። ለእርሷም "ድሮ የአባትሽ ባሮች የነበርን ሰዎች ነን።" ስላሏት ሁለቱን ቅዱሳን እሳት አንዳጅና ገንዳ አጣቢ አደረገቻቸው። ለሰማይ ለምድሩ የከበዱ እነዚህ ቅዱሳን የካዱትን ይመልሱ ዘንድ በባርነት ግፍን ተቀበሉ። የመከር (የማሳመኛ) ጊዜ ሲደርስም አንዳች አጋጣሚ ተፈጠረ። ቅዱሳኑ ዮሐንስና አብሮኮሮስ ወደ መታጠቢያ ቤቱ ሲገቡ ሰይጣን በውስጥ ኖሮ ደንግጧልና እወጣለሁ ብሎ ሲሮጥ የንጉሡን ልጅ ረግጦ ገደለው። ሮምናና የአካባቢው ሰዎች ከበው ሲላቀሱ ቅዱሳኑ ቀረቡ። ሮምና ግን በቁጣ "ልትሣለቁ ነው የመጣችሁ?" በሚል ቅዱስ ዮሐንስን በጥፊ መታችው። መላእክት እንኳ ቀና ብለው ሊያዩት የሚከብዳቸው ሐዋርያ ይህንን ታገሰ። በጥፊ ወደ መታችው ሴት ቀረብ ብሎም "አትዘኝ! ልጁ ይነሳል።" አላትና ጸለየ። ወደ ሞተውም ቀረብ ብሎ በጌታችን ስም አስነሳው። በዚህ ጊዜም ሮምናን ጨምሮ በሥፍራው የነበሩ ሰዎች ለቅዱስ ዮሐንስ ሰገዱ። እርሱ ግን ሁሉንም አስነስቶ ትምሕርተ ሃይማኖትን፣ ፍቅረ ክርስቶስን ሰበከላቸው። በስመ ሥላሴ አጥምቆ ካህናትን ሹሞ ቤተ ክርስቲያንም አንጾላቸው ወጥቷል። በኋላም ለሮምናና ለደሴቷ ሰዎች ክታብ (መልእክትን) ጽፎላቸዋል። ይህች መልእክት ዛሬ ሁለተኛዋ የዮሐንስ መልእክት ተብላ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትታወቃለች። ቅዱስ ዮሐንስ ቀጥሎ የተጓዘው ወደ ኤፌሶን ነው። በዚህች ከተማ የምትመለክ አርጤምስ (አርጢሞስ) የሚሏት ጣዖት ነበረች። አርጤምስ ማለት መልክ የነበራት ትዕቢተኛ ሴት ስትሆን አስማተኛ ባሏ ነው እንድትመለክ ያደረጋት። ቅዱስ ጳውሎስ ብዙ ምዕመናን ከእርሷ እንዲርቁ ማድረግ ችሏል። ጨርሶ ያጠፋት ግን ቅዱስ ዮሐንስ ነው። በቦታውም ብዙ ግፍ ደርሶበት በርካታ ተአምራትን አድርጓል። ቤተ ጣዖቱንም በተአምራት አፍርሶታል። ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን "የፍቅር ሐዋርያ" ትለዋለች። ለሰባ ዘመናት በቆየ ስብከቱ ስለ ፍቅር ብዙ አስተምሯል። ፍቅርንም በተግባር አስተምሯል። በየደቂቃውም "ደቂቅየ ተፋቀሩ በበይናቲክሙ - ልጆቼ ሆይ! እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።" እያለ ይሰብክ ነበር። በተለይ ደግሞ ከፈጣሪው ክርስቶስ ጋር የነበረው ፍቅር ፍጹም የተለየ ነበር። በዚህ ምክንያትም ጌታ ባረገ ጊዜ እንዲህ ብሎታል፦ "ለፍጡር ከሚገለጥ ምሥጢር ከአንተ የምሠውረው የለኝም።" ቀጥሎም በንጹሕ አፉ ስሞታል። ሊቁ፦ "ሰላም ለአፉከ ለዮሐንስ ዘሰዓሞ ንጽሐ ኅሊናሁ ወልቡ ለዐይነ ፍትወትከ ሶበ አደሞ።" እንዳለው። (መልክአ ኢየሱስ) ቅዱስ ዮሐንስ ከእመቤታችንም ጋር ልዩ ፍቅር ነበረው። እርሷ እንደ ልጇ ስትወደው እርሱ ደግሞ እንደ እናቱ ልቡ እስኪነድ ድረስ ይወዳት ነበር። እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ ተከትሎ ያገኛት እመቤቱ ናትና። ከዚያ ሁሉ ጸጋና ማዕረግ የመድረሱ ምሥጢርም ድንግል ናት። ለአሥራ አምስት ዓመታት በጽላሎተ ረድኤቷ (በረዳትነቷ ጥላ) ተደግፎ አብሯት ሲኖር ብዙ ተምሯል። ከመላእክትም በላይ ከብሯል። ከንጽሕናዋ በረከትም ተካፍሏል። ስለ ድንግል ማርያምም "ነገረ ማርያም" የሚል ድርሰት ሲኖረው "የሰኔ ጐልጐታንም" የጻፈው እርሱ ነው። ድንግል ባረፈችበት ቀንም ልክ እንደ ልጇ ክርስቶስ እርሷም ስማው ታቅፋው ዐርፋለች። ሊቃውንቱ ለዚህ አይደል በንጹሕ ከንፈሮቿ መሳምን (መባረክን) ሲሹ፦ "በከመ ሰዓምኪ ርዕሰ ዮሐንስ ቀዳሚ ስዒሞትየ ማርያም ድግሚ።" ያሉት። ታላቁ ቅዱስ ሐዋርያ ዕድሜው ዘጠና ዓመት በሆነው ጊዜ ተሰውሯል። ከዚያ አስቀድሞም የዓለምን ፍጻሜ ተመልክቷል። ዛሬ ያለበትን የሚያውቅ ቸር ፈጣሪው ነው። እናት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን ስትጠራው እንዲህ ነው፦ ወንጌላዊ ሐዋርያ ሰማዕት ዘእንበለ ደም አቡቀለምሲስ (ምሥጢራትን ያየ) ታኦሎጐስ (ነባቤ መለኮት) ወልደ ነጐድጓድ ደቀ መለኮት ወምሥጢር ፍቁረ እግዚእ ርዕሰ ደናግል (የደናግል አለቃ) ቁጹረ ገጽ ዘረፈቀ ውስተ ሕጽኑ ለኢየሱስ (ከጌታ ጎን የሚቀመጥ) ንስር ሠራሪ ልዑለ ስብከት ምድራዊው መልአክ ዓምደ ብርሃን ሐዋርያ ትንቢት ቀርነ ቤተ ክርስቲያን ኮከበ ከዋክብት..... በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ያደረ የእመቤታችን ድንግል ማርያምና የአንድ ልጇ ፍቅር በእኛም ላይ ይደር። ቅዱስ ዮሐንስን የወደደ ጌታ በፍቅሩ ይጠግነን። ከእናቱ ፍቅር አድርሶ በሐዋርያው በረከት ያስጊጠን።
                      6. ኢየሱስ/ግዝረቱ ለእግዚእነ/እየሱስ ገዳም/
                        በዓለ ግዝረቱ "በዓል" ማለት በቁሙ "ክብር፣ መታሰቢያ" እንደ ማለት ነው። የበዓላት ባለቤት ደግሞ ራሱ እግዚአብሔር ነው። በመጻሕፍተ ኦሪት እንደ ተቀመጠው ጌታ ምርጦቹን (ሕዝቡን) ስለ በዓላት አዝዟል። ከሰንበት ጀምሮ የፋሲካ፣ የእሸት፣ የዳስ.....ወዘተ. በዓላት በብሉይ ኪዳን ይከበሩ ነበር። በእርግጥ አሕዛብም ለጥፋታቸው በዓላትን ሲያከብሩ ኑረዋል። ዛሬም ቀጥለዋል። በዓላት በሐዲስ ኪዳንም ቀጥለዋል። የቅዱሳን ሐዋርያትና ሊቃውንትን ቀኖናዎች መሠረት አድርጋ ቤተ ክርስቲያን በዓላትን ታከብራለች። እነዚህም ከጊዜ (ወቅት) አንጻር፦ የሳምንት የወር እና የዓመት በዓላት ተብለው ሲታወቁ ከተከባሪዎቹ አንጻር ደግሞ፦ የጌታ የእመቤታችን እና የቅዱሳን ተብለው ይከፈላሉ። ጌታ "በዓላትን አክብሩ።" ያለን ሥራ እንድንፈታ ሳይሆን ለአምልኮው እንድንተጋና የጽድቅ ተግባራትን እንድንከውን ነው። ስለዚህም በበዓላት መልካም ይሠራል እንጂ ተተኝቶ አይዋልም። የጌታችን በዓላቱ አሥራ ስምንት ሲሆኑ ዘጠኙ ዐበይት፣ ዘጠኙ ደግሞ ንዑሳን ተብለው ይታወቃሉ። ሁሉም ለእኛ የድኅንት ሥራ የተፈጸመባቸው ናቸው። የጌታ ዐበይት በዓላቱ፦ ፩.ጽንሰቱ (ትስብእቱ) ፪.ልደቱ ፫.ጥምቀቱ ፬.ዑደተ ሆሳዕናው ፭.ስቅለቱ ፮.ትንሣኤው ፯.ዕርገቱ ፰.በዓለ ጰራቅሊጦስ እና ፱.በዓለ ደብረ ታቦር ናቸው። ንዑሳን በዓላቱ ደግሞ፦ ፩.ስብከት ፪.ብርሃን ፫.ኖላዊ ሔር ፬.ጌና ፭.ግዝረት ፮.በዓቱ (በዓለ ስምዖን) ፯.ቃና ዘገሊላ ፰.ደብረ ዘይት እና ፱.በዓለ መስቀል ተብለው ይታወቃሉ። ከእነዚህም አንዱ በዓለ ግዝረት ሁሌም በየዓመቱ ጥር ፮ ቀን ይከበራል። መድኃኒታችን ለእኛ ሲል በተዋሐደው ሥጋ ማርያም ሕግን ሁሉ ፈጽሟል። ራሱ 'ሠራዔ ሕግ' እንደ ሆነው ሁሉ 'ፈጻሜ ሕግ'ም ተብሏል። ለአብርሃም ባዘዘው (ዘፍ. ፲፯፥፱) መሠረትም በተወለደ በስምንተኛ ቀኑ ተገዝሯል። ስሙንም ኢየሱስ (መድኃኒት) ብለውታል። (ሉቃ. ፪፥፳፩) ነገር ግን የተገዘረው እንደ ፍጡር በምላጭ (በስለት) ሳይሆን በኪነ ጥበቡ ነው። "ማርያም ግዝር" እንዲሉ አበው። ልደቱ እንደማይመረመር ሁሉ ግዝረቱም አይመረመርም። ለእኛ ሲል ሁሉን የሆነ መድኃኒታችን ክርስቶስ ለፍቅሩና ለክብሩ ያብቃን። ከበረከተ በዓለ ግዝረቱም አይለየን። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                      6. ነቢዩ ኤልያስ የተሰወረበት ቀን
                        ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ቀጥላ ቅዱስ ኤልያስን ታከብራለች። "ርዕሰ ነቢያት - የነቢያት ራስም" ትለዋለች። እርሱ ሰማይን የለጐመ፣ እሳትን ያዘነመ፣ ፍጥረትንም በቃሉ ያዘዘ አባት ነውና። ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ ቅዱሱ ትውልዱ (ነገዱ) ኢዮርብዓም ነጥሎ ከወሰዳቸው እስራኤል (አሥሩ ነገድ) ሲሆን አባቱ ኢያስኑዩ እናቱ ደግሞ ቶና (ቶናህ) ይባላሉ። በጐ አምልኮ ነበራቸውና እግዚአብሔር ማኅጸነ ቶናህን ቀድሶ ይህንን ቅዱስ ፍሬ ፈጠረ። ቅዱስ ኤልያስ በተወለደ ቀን በቤታቸው ብርሃን ተሞልቶ ታይቷል። ብርሃን የለበሱ አራት ሰዎች (መላእክት) መጥተውም በእሳት ሰፋድል (መጐናጸፊያ) ሲጠቀልሉት ወላጆቹ በማየታቸው ደንግጠው ለነቢያትና ለካህናት ነገሯቸው። ካህናቱ ግን ነገሩ ቢረቅባቸው "ምን ዓይነት ፍጥረት ይሆን? በእስራኤል ይነግሥ ይሆን! ወይስ ነቢይ ይሆን?" ብለውም አድንቀዋል። ቅዱስ ኤልያስ ከልጅነቱ ጀምሮ ኮስታራ፣ ቁም ነገረኛ፣ ንጽሕናንም የሚወድ እስራኤላዊ ነው። ወቅቱ (ከክርስቶስ ልደት ዘጠኝ መቶ ዓመት በፊት) ሕዝቡና ነገሥታቱ የከፉበት እግዚአብሔር ተክዶ ጣዖት የሚመለክበት ነበር። ድሮ በኢሎፍላውያን እጅ የነበሩት ጣዖታት (ዳጐንና ቤል) በዚያ ዘመን ወደ እስራኤል ገብተው ነበር። ቅዱስ ኤልያስ ግን በዚህ ክፉ ትውልድ መካከል ሆኖም ሥርዓተ ኦሪትን የጠነቀቀ የንጽሕናና የአምልኮ ሰው ነበር። በዚያ ወራትም እግዚአብሔር ለነቢይነት ጠራው። እርሱም "እሺ" ብሎ ታዝዞ የእግዚአብሔርን የጸጋ ጥሪ ተቀበለ። ቅዱሱ ብዙ ጊዜ ለጉዳይ ካልሆነ ከሰው ጋር መዋል ማደርን አይወድምና መኖሪያውን በተራሮችና በዱር አደረገ። በተለይ ደብረ ቀርሜሎስ ለእርሱ ቤቱ ነበር። በዚህ ሕይወቱም ከመልከ ጼዴቅ ቀጥሎ፦ ፩.ለድንግልና (ድንግል ነበርና) ፪.ለብሕትውና (ብቸኛ ነበርና) ፫.ለምንኩስና (ተሐራሚ ነበርና) በብሉይ ኪዳን መሠረትን የጣለ ነቢይ ይባላል። መቼም በብሉይ ኪዳን የቅዱስ ኤልያስን፣ በዘመነ ክርስቶስ የመጥምቁ ዮሐንስን፣ በዘመነ ሊቃውንት ደግሞ የአፈ ወርቅ ዮሐንስን ያህል ደፋርና መገሥጽ አስተማሪ አልነበረም። በጊዜው ደግሞ አክአብና ኤልዛቤል የሚባሉ ክፉ ባልና ሚስት በእስራኤል ላይ ነግሠው ሕዝቡን ጣዖት አስመለኩት። ይባስ ብለው ደግሞ በወይኑ እርሻ አማካኝነት ኢይዝራኤላዊው ናቡቴን በሐሰት ምስክር ደሙን አፈሰሱት። ናቡቴም "የአባቶቼን ርስት አልሸጥም፤ አልለውጥም።" በማለቱ እንደ ሰማዕት ይቆጠራል። ኤልያስ ግን ይህንን ሲሰማ ወደ አክአብና ኤልዛቤል ቀርቦ "የናቡቴ ደም በእናንተ ላይ አይቀርም። የአንቺንም ደም ውሻ ይልሰዋል።" አላቸው። በዚህ ምክንያትም ኤልዛቤል ልትገድለው ብትፈልገውም እርሱ የእግዚአብሔር ነውና አላገኘችውም። በዚህ ብስጭትም ይመስላል አንድ ሺህ ነቢያትን ሰብስባ "ፍጇቸው" አለች። ዘጠኝ መቶው ሲታረዱ አንድ መቶውን ግን ቅዱስ አብድዩ በዋሻ ውስጥ ደብቆ እየመገበ አተረፋቸው። በእስራኤል ውስጥ ግን ዓመጻና ኃጢአት እየተስፋፋ ሔደ። የእግዚአብሔርን ስጦታ እየተመገበ ሕዝቡ ለቤል (ለበዓል) ሰገደ። ይህን ጊዜ ግን ቅዱስ ኤልያስ እንዲህ አለ፦ "ሕያው እግዚአብሔር አምላከ ኃይል ዘቆምኩ ቅድሜሁ ከመ ኢይረድ ጠል በእላ መዋዕል ዘእንበለ በቃለ አፉየ።" ብሎ ዝናም ከሰማይ እንዳይወርድ ከለከለ። ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ዝናም ለዘር ጠል ለመከር ከመስጠት ተከለከለ። ሕዝቡ በኃጢአቱ ምክንያት ተጐዳ። እርሱን ቁራ ይመግበው ምንጭ ፈልቆለት ይጠጣ ነበር። ይሔው ቢቀርበት ጸለየ። እግዚአብሔርም ከፈለገ ኮራት ወደ ሰራፕታ እንዲወርድ አዘዘው። በዚያም የነቢዩ ዮናስ እናት እንጐቻ ጋግራ ብታበላው ቤቷ በበረከት ተሞላ። ልጇ ሕፃኑ ዮናስ ቢሞትም በጸሎቱ አስነሳላት። ቀጥሎም ሰባት ጊዜ በትጋት ጸልዮ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር የዘጋውን ሰማይ ከፍቶታል። ሕዝቡም ዕለቱኑ ከበረከቱ ቀምሰዋል። ከዚያ አስቀድሞ ግን ከኤልዛቤል ስምንት መቶ ሃምሳ ነቢያተ ሐሰትና ካህናተ ጣዖት ጋር ተወዳድሮ አሸንፏቸዋል። መስዋዕት ሰውተው የእርሱን ብቻ እሳት ከሰማይ ወርዳ በልታለታለችና ሕዝቡ ስምንት መቶ ሃምሳውን ሐሰተኛ ነቢያት በወንዝ ዳር በሰይፍ መትተዋቸዋል። ይህንን የሰማች ኤልዛቤልም ትገድለው ዘንድ አሳደደችው። "አቤቱ ከአባቶቼ አልበልጥምና ውሰደኝ! ብቻዬን ቀርቻለሁና።" ብሎ ቢጸልይ እግዚአብሔር ለጣዖት ያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎችን እንዳተረፈ እርሱንም ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደሚወስደው ብሥራትን ነገረው። ደክሞት ተኝቶ ሳለም ቅዱስ መልአክ (ሚካኤል) ቀስቅሶ ታየው። እንጐቻ ባገልግል ውኃ በመንቀል አቅርቦ "ብላ! ጠጣ!" አለው። በላ፣ ጠጣ፣ ተኛ። እንደ ገና ቀስቅሶ አበላው። በሦስተኛው ግን "ብላዕ እስከ ትጸግብ እስመ ርሑቅ ፍኖትከ - ጐዳናህ ሩቅ ነውና እስክትጠግብ ብላ።" አለው። ኤልያስም ለአርባ ቀናት ያለ ምግብ ተጉዟል። ከዚያ በኋላም ምድራዊ ሕብስትን አልተመገበም። እግዚአብሔር አክአብና ኤልዛቤልን ከተበቀላቸው በኋላም ቅዱስ ኤልያስ በክፋተኞች ላይ ሁለት ጊዜ እሳትን አዝንሟል። የሚያርግበት ጊዜ ሲደርስም ደቀ መዝሙሩን ኤልሳዕን "የምትሻውን ለምነኝ።" ቢለው "እጥፍ መንፈስህን።" አለው። ሦስት ጊዜ ሊያስመልሰው ሞከረ። ቅዱስ ኤልሳዕ ግን በብርታት ተከተለው። ዮርዳኖስን ከፍለው ከተሻገሩ በኋላ ግን ቅዱስ ኤልያስን ሠረገላ እሳት ወርዶ ነጠቀው። ለኤልሳዕም እኩሉን ግምጃውን ጣለለት። ዛሬ ቅዱስ ኤልያስ በብሔረ ሕያዋን ያለ ሲሆን በዘመነ ሐሳዌ መሲሕ መጥቶ በሰማዕትነት ከቅዱስ ሄኖክ ጋር ያርፋል። ለተጨማሪ ንባብ (ከ፩ነገ. ፲፯ - ፪ነገ. ፪ እና ዕርገተ ኤልያስን ያንብቡ።) ነቢዩ ኤልያስ በእውነት ታላቅ ነው! አምላከ ኤልያስ ለሃገራችንና ለሕዝቧ ርኅራኄውን ይላክልን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                      7. ቅድስት ሥላሴ
                        ሥሉስ ቅዱስ  ምሥጢራት በእምነት ለማይኖር በትሕትናም ለማይቀርብ የሚገለጡ አይደሉም። እግዚአብሔር አንድም ነው፤ ሦስትም ነው። ጊዜ ሣይሠፈር ዘመንም ሳይቆጠር እግዚአብሔር በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስትነቱ፤ በባሕርይ፣ በሕልውና፣ በመለኮትና በሥልጣን አንድነቱ የጸና አምላክ ነው። ከዓለም መፈጠር በፊት ስለ ነበረው ነገር የሚያውቅ ራሱ ሥላሴ ብቻ ነው። ዓለምን ከፈጠረ በኋላም ምሥጢረ ሥላሴ (መለኮት) ብለን የምንማረው ትምህርት እንድንና እንጠቀም ዘንድ እርሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ ነው። ይኸውም በየጊዜው እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ቅዱሳኑ የገለጠው ምሥጢር ነው። ከዚህ አልፈን በሥጋዊ አዕምሯችን ጌታን "እንመርምርህ" ብንለው ግን ፍጻሜአችን ሞት ማደሪያችንም ገሃነመ እሳት መሆኑ አይቀርም። እግዚአብሔር በአንድነቱና ሦስትነቱ ሳለ ይህንን ዓለም ፈጠረ። እግዚአብሔር ዓለምን ለምን ፈጠረ ቢሉ ስሙን ቀድሰን ክብሩን እንድንወርስ ነው። ከዚህ የተረፈውን ምክንያት ግን ራሱ ያውቃል። በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት) በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት) የሌለበት የዘላለም አምላክ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው። አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስትነት በባሕርይ፣ በሕልውናና በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው። በዚህ ጊዜ ተገኙ በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም። መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና። ርኅሩኀን ናቸውና በእናት ሥርዓት "ቅድስት ሥላሴ" እንላቸዋለን። የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም። የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል። በቤቱም መጥተው ያድራሉ። ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም። አባታችን ቅዱስ አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል። አባታችን አብርሃም በዘጠና ዘጠኝ ዓመቱ እናታችን ሣራ በሰማንያ ዘጠኝ ዓመቷ ሥላሴን በድንኳናቸው አስተናገዱ። አብርሃም እግራቸውን አጠበ። (ወይ መታደል!) በጀርባውም አዘላቸው። (ድንቅ አባት!) ምሳቸውንም አቀረበላቸው። እንደሚበሉ ሆኑለት። በዚያው ዕለትም የይስሐቅን መወለድ አበሠሩት። ሥላሴን ያስተናገደች ድንኳን (ሐይመት) የድንግል እመቤታችን ማርያም ምሳሌ ናት። በድንግል ላይ አብ ለአጽንኦ፣ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፣ ወልድ በተለየ አካሉ ለሥጋዌ በእርሷ ላይ አርፈዋል (አድረዋልና)። በዓለ ሥላሴ በዚህ ቀን የሚከበረው ስለ ሁለት ምክንያቶች ነው። ቀዳሚው ሕንጻ ሰናዖርን ማፍረሳቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቅዳሴ ቤታቸው ነው። ሰናዖር ከሺህዎች ዓመታት በፊት በአሁኗ ኢራቅ አካባቢ እንደ ነበረ የሚነገርለት ግዛት ሲሆን ስሙ ለሃገሪቱም ለንጉሡም በተመሳሳይ ያገለግል ነበር። ከናምሩድ ክፋት በኋላ ሰናዖርና ወገኖቹ ከሰይጣን ተወዳጁ። ከጥፋት ውኃ (ከኖኅ ዕረፍት) በኋላ በሥፍራው በአንድነት ይኖሩ ነበርና እርስ በርሳቸው "ኑ ሳንበተን ስማችን የሚጠራበትን ሕንጻ እንሥራ። በዚያውም አባቶቻችን በውኃ ያጠፋ እግዚአብሔርን እንውጋው።" ተባባሉ። ቀጥለውም ሰማይ ጠቀስ ፎቅን ገነቡ። ከሕንጻው መርዘም የተነሳ በፀሐይ አብስለው በልተዋል ይባላል። ቀጥለውም ጦር እያነሱ ፈጣሪን ሊወጉ ወርውረዋል። መቼም የእነዚህን ሰዎች ክፋትና ቂልነት ስንሰማ ይገርመን ይሆናል። ግንኮ ዛሬ ሰለጠንኩ በሚለው ዓለም እየተሠራ ያለው ከዚህ የከፋ ነው። ቸርነቱ ቢጠብቀን እንጂ እንደ ክፋታችንስ ጠፊ ነበርን። ርኅሩኀን ሥላሴ ግን የሰናዖር ሰዎች የሠሩትን አይተው ማጥፋት ሲችሉ አላደረጉትም። የባሪያቸውን የኖኅን ቃል ኪዳን አስበዋልና። ይልቁኑ "ንዑ ንረድ ወንክአው ነገሮሙ ለከለዳውያን - ቋንቋቸውን እንደባልቀው።" አሉ እንጂ። ከለዳውያን ልሳናቸው ተደበላልቆ ሰባ አንድ ቋንቋዎች ተፈጠሩ። እነርሱም ስምምነት አጥተው ተበተኑ። ሥላሴም ያን ሕንጻ በነፋስ ትቢያ እንዲሆን በተኑት። ስለዚህም እስከ ዛሬ ሥፍራው "ባቢሎን (ዝሩት)" ሲባል ይኖራል። ዳግመኛ በዚህች ዕለት አድያም ሰገድ ኢያሱ በኢትዮጵያ በነገሡ በአሥረኛው ዓመት (በ፲፮፻፹፬ ዓ/ም) በጐንደር ከተማ ንግሥተ አድባራት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተሰርታ ተጠናቃለች። ጥር ፯ ቀንም ሊቁ ክፍለ ዮሐንስን ጨምሮ በርካታ ምዕመናን፣ ሠራዊት፣ መሳፍንትና ሊቃውንት ባሉበት ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሯል። በዕለቱም ታላቅ ሐሴት ተደርጓል። ኢያሱ አድያም ሰገድ ኃያል፣ ደግ፣ ጥበበኛ፣ አስተዋይ፣ መናኝ ንጉሥ ነውና። ቤተ ሥላሴን አስጊጿታልና ከዚህ ቀን ጀምሮ ጥር ሥላሴ በድምቀት የሚከበር ሆኗል። ነገር ግን በተሠራች በአሥራ ስድስት ዓመቷ ደጉ ኢያሱ ከተገደለ በኋላ ቤተ ክርስቲያኑ በአደጋ ፈርሷል። ዛሬ የምናየው በ፲፯፻፰ ዓ/ም በልጁ በአፄ ዳዊት ሣልሳዊ የታነጸውን ነው። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                      11. በዓለ ጥምቀት
                        12. በዓለ ቅዱስ ሚካኤል
                          12. ቃና ዘገሊላ
                            "ቃና" የሚለው ቃል በሃገራችን ልሳን (በአማርኛ) የምግብን፣ የመጠጥን ጥፍጥና ወይም በጐ መዓዛን የሚያመለክት ነው። ምናልባትም ከዚህ በዓል ምሥጢር የተወሰደ ሳይሆን አይቀርም። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ግን ቃና ከገሊላ አውራጃዎች አንዷ ናት። ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ በዚህች ሥፍራ ተገኝቶ በድንግል እናቱ ምልጃ ታላቅ ተአምርን በዚህች ዕለት ሠርቷል። "ተአምር" የሚለውን ቃል በቁሙ "ምልክት" ብሎ መተርጐም ይቻላል። መሠረታዊ መልዕክቱ ግን ነጮቹ በልሳናቸው (Miracle) የሚሉት ዓይነት ነው። ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ (በላይ) ከፍጡራንም ችሎታ የላቀ ነገር ሲሠራ (ሲፈጸም) ተአምር ይባላል። ተአምር የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው። እርሱ ዓለምን ከመፍጠሩ ጀምሮ እያንዳንዷ ተግባሩ ለእኛ ተአምራት ናቸው። ስለዚህም ነው "ኤልሻዳይ /ከሐሌ ኩሉ/ ሁሉን ቻይ" እያልን የምንጠራው። እግዚአብሔር ፍጡራኑን ይወዳልና እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ተአምራት ማድረግን ሰጥቷል። በብሉይ ኪዳን እነ ሙሴ ባሕር ሲከፍሉ፣ መና ሲያዘንሙ፣ ውኃ ሲያፈልቁ (ኦሪትን ተመልከት።) እነ ኤልያስ ሰማይን ሲለጉሙ፣ እሳትን ሲያዘንሙ፣ ሙታንን ሲያስነሱ (፩ነገሥትን ተመልከት።) እንደ ነበር ይታወቃል። እንዲያውም በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተአምር መጽሐፍ ነው ብሎ ለመናገርም ያስደፍራል። በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ብዙ ተአምራትን ሠርቶ ለሐዋርያቱ የተአምራት ጸጋውን ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. ፲፥፰ ፤ ፲፯፥፳ ማር. ፲፮፥፲፯ ፣ ሉቃ. ፲፥፲፯ ዮሐ. ፲፬፥፲፪) እነርሱም በተሰጣቸው ሥልጣን ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል። (ሐዋ. ፫፥፮ ፤ ፭፥፩ ፤ ፭፥፲፪ ፤ ፰፥፮ ፤ ፱፥፴፫-፵፫ ፤ ፲፬፥፰ ፤ ፲፱፥፲፩) ቅዱስ ዮሐንስ ሐዋርያ በወንጌሉ ምዕራፍ ፪ ላይ እንዳስቀመጠው የቃና ዘገሊላው ተአምር የመጀመሪያው ነው። "ወዝንቱ ቀዳሜ ተአምር....." እንዲል። (ዮሐ. ፪፥፲፩) ያ ማለት ግን ጌታ ከዚያ በፊት ተአምራትን አልሠራም ማለት አይደለም። ይልቁኑ ራሱን ከገለጠና ከተጠመቀ በኋላ የሠራው የመጀመሪያው ተአምር ነው ሲል ነው እንጂ። ምክንያቱም መድኃኒታችን እንደ ተጠመቀ ዕለቱኑ ገዳመ ቆረንቶስ ገብቷልና። (ማቴ. ፬፥፩) አንድም በቃና ሌሎች ተአምራትን የሚሠራ ነውና ይህ ተአምር በቃና የመጀመሪያው ሆነ። ትክክለኛው የቃና ዘገሊላ ቀን የካቲት ፳፫ ነው። ጥር ፲፩ ተጠምቆ የካቲት ፳፩ ቀን ከጾም ተመልሷል። ከዚያም የካቲት ፳፫ ቀን ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ ሒዷል። ነገር ግን አበው መንፈስ ቅዱስ እንደ መራቸው የውኃ በዓል ከውኃ በዓል ጋር ይስማማል ብለው ጥር ፲፪ አድርገውታል። በቃና ዘገሊላ ሙሽራው ዶኪማስ ሲሆን ባለ ሠርጉ ደግሞ አባቱ ዮአኪን ነው። ይህም ለሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል አጐቱ ነው። የልጁ ጋብቻ የተቀደሰ ይሆን ዘንድም ጌታ ክርስቶስን፣ ድንግል እናቱንና ባለሟሎቹ ሐዋርያትን ወደ ሠርጉ ጠራ። ምንም እንኳ መድኃኒታችንና እመቤታችን ከድግሱ የማይበሉ ቢሆኑም (በትሕርምት ኗሪዎች ነበሩና።) ጠሪውን ደስ ለማሰኘት ሠርጉን ለመቀደስና የጋብቻን ክቡርነት ለማሳየት አብረው ታደሙ። የሠርጉ ሥነ ሥርዓት ሲጀመር በድንኳኑ ውስጥ ጌታ ከመካከል ተቀመጠ። ድንግል በቀኙ፣ ዮሐንስ በግራው ሲቀመጡ፣ ሌሎች ሐዋርያት ግራና ቀኝ ከበው ተቀመጡ። ሲበላና ሲጠጣ ድንገት የተደገሰው ምግብና መጠጥ አለቀ። ደጋሾቹ በጭንቅ ላይ ሳሉም አይጠና ሆዷ ድንግል እመ ብርሃን የሆነውን አወቀች። እንዴት አወቀች ቢሉ፦ በጸጋ፣ አንድም "ከልጅሽ አማልጂን።" ብለው ቢለምኗት ነው ይሏል። እመቤታችን በዚያ ጊዜ ወደ ልጇ ቀርባ ቸር ልጇን "ወይንኬ አልቦሙ - ወይኑኮ አልቆባቸዋል።" አለችው። ለጊዜው ወይኑም፣ ምግቡም ስላለቀባቸው እንዲህ አለች። በምሥጢሩ ግን ወይን ያለችው ፍቅርን፣ ቅዱስ ቃሉንና ክቡር ደሙን ነው። ጌታም ይመልሳል፦ "ምንት ብየ ምስሌኪ ኦ ብእሲቶ ዓዲ ኢበጽሐ ጊዜየ - አንቺ ሆይ! (እናቴ ሆይ!) ያልሽኝን አላደርግ ዘንድ ካንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ? ነገር ግን ጊዜው ገና አልደረሰም ብየ ነው እንጂ።" አላት። ምክንያቱም ጌታ የወይን ጋኖቹ እስኪያልቁ ይጠብቅ ነበር። (አበረከተ ይሉታልና።) አንድም ይሁዳ ወጥቶ ነበርና እርሱ እስኪመለስ ነው። (እኔ ስወጣ ጠብቆ ተአምር ሠራ ብሎ ለክፋቱ ምክንያት እንዳያቀርብ።) አንድም "ወይን (ቅዱስ ደሜን) የምሰጠው በቀራንዮ አንባ ነው።" ሲል "ጊዜዬ ገና ነው።" ብሏታል። አንዳንድ ልቡናቸው የጠፋ ወገኖቻችን ጌታ እመቤታችንን እንዳቃለላት (ሎቱ ስብሐት! ወላቲ ስብሐት!) አስመስለው ይናገራሉ። ይህንን እንኳን ጌታ ባለጌዎቹ እነርሱም አያደርጉት። "አባትህንና እናትህን አክብር።" (ዘጸ. ፳፥፲፪) ያለ ጌታ እንዴት ለእናቱ ክብርን ይነፍጋል? ልቡና ይስጠን! ወደ ጉዳያችን ስንመለስ መድኃኒታችን እንዲህ ሲል መለሰላት። ተግባብተዋልና እመ ብርሃን አሳላፊዎቹን "ኩሎ ዘይቤለክሙ ግበሩ - የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ።" አለቻቸው። (ዮሐ. ፪፥፭) ጌታም በስድስቱ ጋኖች ውኃ አስሞልቶ በተአምራት ወይን አደረጋቸው። እንጀራውን ወጡን በየሥፍራው ሞላው። ታላቅ ደስታም ሆነ። የአሳላፊዎቹ አለቃም (ለአባታችን አብርሃም ምሳሌ ነው።) ከወይኑ ጥፍጥና የተነሳ አደነቀ። በዚህም የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የመድኃኒታችን ከሃሊነት ታወቀ፤ ተገለጠ። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                          13. ቅዱስ ሩፋኤል
                          13. የቃና ዘገሊላ በዓል መታሰብያ
                          14. አቡነ አረጋዊ
                            ጻድቁ ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮጵያ ቢሆንም ሃገረ ሙላዳቸው የጥንቱ የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ናት። አቡነ አረጋዊ ከዘጠኙ (ተስዓቱ) ቅዱሳን አንዱ ናቸው። ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው። ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው። በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር፦ ፩.የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ፣ ፪.ዓላማ (የእግዚአብሔር መንግሥት) እና ፫.ገዳማዊ ሕይወት ነው። አቡነ አረጋዊን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግሥት ነው። እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል። አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል። በምናኔ ቅድሚያውን አባ ጰንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ። ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ። በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮጵያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም። ስለዚህም በ፬፻፸ዎቹ ዓ/ም አልዓሜዳ በኢትዮጵያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ። ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው። ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው። ይህች ቦታ ቤተ ቀጢን ትባላለች። አቡነ አረጋዊና ስምንቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር። ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዚያው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ። በወቅቱ በአቡነ ሰላማ፣ በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አቡነ አረጋዊ እንደገና አቀጣጠሉት። ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት። የካደውን እየመለሱ የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ። ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ። ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው። በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አቡነ አረጋዊ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማኅበር ነበር። በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር። ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም። የነ አቡነ አረጋዊ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ። ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው። እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ። ጰንጠሌዎን በጾማዕት፣ ገሪማ በመደራ፣ ሊቃኖስ በቆናጽል፣ አባ ይምዓታ በገርዓልታ፣ ጽሕማ በጸድያ፣ ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ። አባ አረጋዊ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ዳሞ (እዚያው ትግራይ) ሆነ። በሃገራችን ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ እኒህ ጻድቅ ናቸው። ጻድቁ የተወለዱት በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው ንጉሥ ይስሐቅና ቅድስት እድና ይባላሉ። የተለወለዱበት አካባቢም ሮም ነው። ስማቸው ብዙ ዓይነት ነው። ወላጆቻቸው "ዘሚካኤል" ሲሏቸው በበርሃ "ገብረ አምላክ" ተብለዋል። በኢትዮጵያ ደግሞ "አረጋዊ" ይባላሉ። አቡነ አረጋዊ ምንም የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም በልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው ነበርና ጠፍተው ገዳም ገቡ። በዚያም በገዳመ ዳውናስ (ግብጽ) የታላቁ ቅዱስ ጳኩሚስ ደቀ መዝሙር ሆነው ከነ አባ ቴዎድሮስ ጋር ሥርዓተ መነኮሳትን ተምረዋል። ከመነኮሱ ከዓመታት በኋላም ወደ ሃገራቸው ሮም ተመልሰው በማስተማር ሰባት ያህል የቤተ መንግሥት ሰዎችን ወደ ምናኔ ማርከዋል። "የት ልሒድ?" ብለው ሲያስቡም ቅዱስ መልአክ በክንፉ ጭኖ ወስዶ ኢትዮጵያን አሳያቸው። ተመልሰውም ለስምንት ባልንጀሮቻቸው "ሃገርስ ባሳየኋችሁ! ሐዋርያ ሳያስተምራት በሕጉ በሥርዓቱ ጸንታ የምትኖር።" ብለው ከስምንቱ ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጡ። በዚህ ጊዜም እናታቸው ቅድስት እድናና ደቀ መዝሙራቸው አባ ማትያስ አብረው ነበሩ። ወደ ሃገራችን የመጡ በ፬፻፸ዎቹ አካባቢ ሲሆን አልዓሜዳ በክብር ተቀብሏቸዋል። በቤተ ቀጢን (አክሱም) ተቀምጠውም መጻሕፍትን እየተረጐሙ፣ ወንጌልን እየሰበኩ ቆይተዋል። ለሥራ በተለያዩ ጊዜም አቡነ አረጋዊ በዓት ፍለጋ ብዙ ደክመዋል። በመጨረሻ ግን ደብረ ዳሞን (ደብረ ሃሌ ሉያን) አይተው ወደዷት። የሚወጡበት ቢያጡም ጅራቱ ስልሳ ክንድ የሚያህል ዘንዶ ተሸክሞ ከላይ አድርሷቸዋል። እንደ ወጡም "ሃሌ ሉያ ለአብ፣ ሃሌ ሉያ ለወልድ፣ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ" ብለው ቢያመሰግኑ ከሰማይ ሕብስት ወርዶላቸው ተመግበዋል። በዚህም ቦታዋ "ደብረ ሃሌ ሉያ" ተብላለች። ጻድቁ ቦታውን ከገደሙ በኋላ ከተለያየ ቦታ መጥተው ስድስት ሺህ ያህል ሰዎች በእጃቸው መንኩሰዋል። ምናኔን በማስፋፋታቸውና ሥርዓቱን በማስተማራቸውም "አቡሆሙ ለመነኮሳት ዘኢትዮጵያ - የኢትዮጵያ መነኮሳት አባት" ይባላሉ። አቡነ አረጋዊ በሕይወታቸው ከተጋድሎ ባሻገር በወንጌል አገልግሎትና መጻሕፍትን በማዘጋጀትም ደክመዋል። ቅዱስ ያሬድና አፄ ገብረ መስቀልም ወዳጆቻቸው ነበሩ። በተራራው ግርጌ ያለችውን ኪዳነ ምሕረትን ለሴቶች ሲገድሟት ቀዳሚዋ መነኮስ እናታቸው ንግሥት እድና ሁናለች። ጻድቁ ንጹሕ ሕይወታቸውን ፈጽመው በተወለዱ በዘጠና ዘጠኝ ዓመታቸው በገዳሙ በስተ ምሥራቅ አካባቢ ተሰውረው ብሔረ ሕያዋን ገብተዋል። ጌታም አሥራ አምስት ትውልድን የሚያስምር የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። ዛሬ ጻድቁ የተወለዱበት ቀን ነው። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                          15. ቅዱስ ቂርቆስ እየሉጣ
                            ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካሏት ዐበይት ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ቂርቆስ ነው። በተለይ በዘመነ ሰማዕታት ተነስተው እንደ ከዋክብት ካበሩትም አንዱ ነው። ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል፦ "መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራል።" (ማቴ. ፯፥፲፯) መልካም ዛፍ ቅድስት ኢየሉጣ መልካም ፍሬ ብፁዕ ቂርቆስን አፍርታ ተገኝታለችና ክብር ይገባታል። ቡርክተ ማኅጸንም እንላታለን። የተባረከ ማኅጸኗ የተባረከ ልጅን ለዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ተሸክሟልና። በዚያ ክርስቲያን መሆን መከራ በነበረበት ዘመን ይህንን ደግ ሕፃን እርሷን መስሎ እርሷንም አህሎ እንዲገኝ አስችላለችና። አበው በትውፊት እንዳቆዩልን ከሆነ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እናታችን ቅድስት ኢየሉጣ ብፁዕ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስን ወልዳለች። በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮም ግዛት ክርስትና ቢስፋፋም በዚያው ልክ መምለክያነ ጣዖቱ የገነኑ ነበሩ። በተለይ ከነገሥታቱ ጀምሮ ዋና ዋና የሥልጣን ቦታዎች በአሕዛብ እጅ በመሆናቸው ለዘመኑ ክርስቲያኖች ፈታኝ ነበር። ማንኛውም ክርስቲያን መሠረታዊ ፍላጐቶቹ እንዲሟሉለት አሕዛብ ላቆሟቸው ጣዖቶች መንበርከክ ነበረበት። መብቱን ከመገፈፉ ባሻገር "ተበድያለሁ" ብሎ ወደ ፍርድ ቤት ሔዶ እንኳ የመጮህ እድል አልነበረውም። ምክንያቱም የሚሰማው የለም። በዚያ ላይ በየጊዜው ለክርስቲያኖች ፈታኝ የሆኑ አዋጆች ይወጣሉ። የክርስትናን ጐዳና ይበልጥ የሚያጠቡ ሕጐችም ዕለት ዕለት ይፈበረኩ ነበር። ስለዚህም በወቅቱ የነበረ አንድ ክርስቲያን ሃይማኖቱን ከወደደ ወይ እስከ ሞት መታገስ ካልሆነ ደግሞ ሃገሩ ጥሎ በዱር በገደል መሰደድ ነበረበት። እውነት ለመናገር ዜና ሰማዕታትን የማያውቅ ክርስቲያን ክርስቶሳዊ ነው ሊባል አይችልም። ምክንያቱም ዛሬ እንዲህ እንደ ዋዛ የያዝናት ሃይማኖታችን እንዴት እንደ መጣችና ምን እንደ ተከፈለባት አብዛኛው ትውልድ አያውቅምና። ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ብፅዕት ኢየሉጣም የዚህ ዘመን (የዘመነ ሰማዕታት) ፍሬ ናቸው። በጊዜው በሮም ግዛት ሥር እስክንድሮስ የሚሉት ክፉ ንጉሥ ነግሦ ነበርና ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ። ጣዖትን ላለማምለክም ተሰው። በዚህ ጊዜ አንጌቤናይት (ኢጣልያዊት) ብፅዕት ኢየሉጣም በመበለትነት (ባሏ በሕይወት ባለ መኖሩ) ትኖር ነበር። ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ ምንም ገና ሦስት ዓመቱ ቢሆንም ነገረ ሃይማኖትን ታስተምረው ፍቅረ ክርስቶስን ትስልበት ነበር። እስክንድሮስ የክህደት አዋጅን ሲያውጅም ቅድስቲቱ ለሕፃን ልጇ ራርታ ሽሽትን መረጠች። ሃብት ንብረቷን፣ ወገንና ርስቷንም ትታ ሕፃን ልጇን ተሸክማ ተሰደደች። መከራው ግን በሔደችበት አለቀቃትም። እስክንድሮስ ተከትሎ ባለችበት ቦታም አገኛት። ወታደሮች ልጇን ሳያገኙ እርሷን ብቻ ይዘው ወደ መኮንኑ አቀረቧት። መኮንኑም "ስምሽን ንገሪኝ?" ቢላት "ስሜ ክርስቲያን ነው።" አለችው። ተቆጥቶ "ትክክለኛውን ስምሽን ተናገሪ?" ቢላት "እውነተኛው ስሜ ክርስቲያን ነው። ሞክሼ (ሞክሲ) ስም ከፈለግህ ኢየሉጣ እባላለሁ።" አለችው። "ለጣዖት ልትሰግጂ ይገባል።" ሲላትም "እውነትን ይነግረን ዘንድ የሦስት ዓመት ሕፃን ፈልገህ አምጣና ተረዳ።" ስላለችው ወታደሮቹን እንዲፈልጉ ላካቸው። የሃገሩ ሰዎች ልጆቻቸውን ስለደበቁ የተገኘ ቅዱስ ቂርቆስ ነበር። ቅዱሱ ሕፃን በወታደሮች ተይዞ ሲቀርብ መልኩ ያበራ ነበርና መኮንኑ "በሐከ ፍሡሕ ሕፃን - ደስ የተሰኘህ ሕፃን እንዴት ነህ?" ቢለው "ትክክል ነህ! እኔ በጌታዬ ክርስቶስ ዘንድ ደስታ ይጠብቀኛል። አንተ ግን በክህደትህ ወደ ገሃነም ትወርዳለህ።" አለው። በሕፃኑ ድፍረት የደነገጠው መኮንኑ በብስጭት "እሺ! ስምህን ንገረኝ?" አለው። ያን ጊዜ "ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ ስሜ ክርስቲያን ነው። እናቴ የሰየመችኝን ከፈለክ ግን ቂርቆስ ነው።" ሲል መለሰለት። ከዚያም እየደጋገመ "እኔ ክርስቲያን ነኝ።" ብሎ በመጮሁ መኮንኑ ስቃይን በቅዱሱ ሕፃን እና በቡርክት እናቱ ላይ አዘዘ። ከዚህ በኋላ በእነርሱ ላይ የተፈጸመውን ግፍና የወረደባቸውን የመከራ ዶፍ እናገር (እጽፍ) ዘንድ ግን የሚቻለኝ አይመስለኝም። በግርፋት የጀመረ ስቃይ ሊሰሙት ወደ ሚጨንቅ መከራ ቀጠለ። ሰባት ብረት አግለው በዓይናቸው፣ በጆሯቸው፣ በአፋቸውና በልባቸው ከተቱ። በአራት ችንካሮች ላይ አስቀመጧቸው። በእሳት አቃጠሏቸው። ጸጉራቸውን ከቆዳቸው ጋር ገፈፉ። ከዚህ በላይ ብዙ ስቃይንም አመጡባቸው። እናትና ልጅ ግን ለክርስቶስ ታምነዋልና ጸኑ። ቅድስት ኢየሉጣ ብትደነግጥ ልጇ አጸናት። ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት ሲያርፉ ጌታ እንደ ቃሉ የሕፃኑን ሥጋ በሠረገላ ኤልያስ አኑሮታል። ለእኛ የሚጠቅም ብዙ ቃል ኪዳንንም ሰጥቶታል። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                          18. ቅዱስ ጊዮርጊስ /ዝርዎተ አጽሙ/
                            መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰባት ዓመታት ስቃይ በኋላ ተሰይፏል። ይህስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ፦ ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም (ልዳ) ውስጥ ነው። የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ሃያ ዓመት ሲሞላው የአባቱን ሥልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት (የአሁኗ ቤይሩት - ሊባኖስ) ሰዎች ዘንዶ/ደራጎን ሲያመልኩ አገኛቸው። እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ፣ አሳምኖ፣ ደራጎኑንም በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና ሰባ ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር። በዚያች ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው። እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) ደረሰ። ከዚያም ለተከታታይ ሰባት ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን ተቀበለ። ሦስት ጊዜ ሙቶ ተነሳ። ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ የሰማዕታት አለቃቸው፣ ፀሐይና የንጋት ኮከብ በሚል ይጠራል። "ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ።" እንዲል መጽሐፍ። ከሰባት ዓመታት መከራ በኋላም ከብዙ ተዓምራት ጋር ተሰይፎ ደም፣ ውኃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል። ሰባት አክሊላትም ወርደውለታል። ይህቺ ዕለት ለሰማዕቱ "ዝርወተ አጽሙ" ትባላለች። በቁሙ "አጥንቱ የተበተነበት" እንደ ማለት ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዘመናት በብዙ ስቃያት ሲያስጨንቁት ኖረው በጽናቱ አሸነፋቸው። ሰባ ነገሥታትን ከነ ሠራዊታቸው ከማሳፈሩ ባሻገርም በርካታ (በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ) አሕዛብን ማርኮ ለሰማዕትነት አበቃ። በዚህ የተበሳጨ ዱድያኖስም ኮከበ ፋርስ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲቆራርጡት አዘዘ። ወታደሮቹም ቅዱሱን ቆራርጠው በብረት ምጣድ ላይ ጠበሱት። ያለ ርኅራኄም አካሉን አሳረሩት። ቀጥለውም ፈጭተው አመድ አደረጉት። በአካባቢው ወደ ነበረው ትልቅ ተራራ ጫፍ (ደብረ ይድራስ) ወጥተውም በነፋስ በተኑት። "ሐረድዎ ወገመድዎ ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ዓመድ" እንዲል። (ምቅናይ) እነርሱ ይህንን ፈጽመው ዘወር ሲሉ ግን የቅዱሱ ዓጽም ባረፈባቸው ዛፎች፣ ቅጠሎችና ድንጋዮች ሁሉ "ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት" የሚል ጽሑፍ ተገኘ። ስለዚህም ይህቺ ዕለት ቅዱሱ አለቅነትን የተሾመባት ናት ማለት ነው። ወዲያው ግን ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተበተነበት ተነስቶ ወታደሮችን አገኛቸውና "በክርስቶስ እመኑ" ብሎ አስደንቆ ወደ ሕይወት መራቸው። ሰባው ነገሥታት ግን አፈሩ። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                          21. የእመቤታችን በዓለ እረፍት
                            እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር ነበር። ከነገር ሁሉ በፊት እግዚአብሔር እናቱን ያውቃት ነበር። ዓለም ተፈጥሮ አዳምና ሔዋን ስተው መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ አግኝቷቸው በኀዘን ንስሐ ቢገቡ "እትወለድ እም ወለተ ወለትከ - ከአምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት) በኋላ ካንተ ባሕርይ ከምትገኝ ንጽሕት ዘር ተወልጄ አድንሃለሁ።" ብሎ ተስፋ ድኅነት ሰጠው። ከአዳም አንስቶ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት አበው፣ ነቢያትና ካህናት ስለ ድንግል ማርያም ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን ተናገሩ። መዳኛቸውን ሱባኤ ቆጠሩላት፤ ምሳሌም መሰሉላት። ከሩቅ ዘመን ሁነውም ሊያገኟት እየተመኙ እጅ ነሷት። "እምርሑቅሰ ርእይዋ ወተአምኅዋ" እንዲል።  የድንግል ማርያም ሐረገ ትውልድ  ከአዳም በሴት ከያሬድ በሄኖክ ከኖኅ በሴም ከአብርሃም በይስሐቅ ከያዕቆብ በይሁዳና በሌዊ ከይሁዳ በእሴይ፣ በዳዊት፣ በሰሎሞንና በሕዝቅያስ ወርዳ ከኢያቄም ትደርሳለች። ከሌዊ ደግሞ በአሮን፣ አልዓዛር፣ ፊንሐስ፣ ቴክታና በጥሪቃ አድርጋ ከሐና ትደርሳለች። አባታችን አዳም ከገነት በወጣ በአምስት ሺህ አራት መቶ ሰማንያ አምስት ዓመት ወላዲተ አምላክ ንጽሕና ሳይጐድልባት፣ ኃጢአት ሳያገኛት፣ ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ከደጋጉ ኢያቄም ወሐና ትወለዳለች። (ኢሳ. ፩፥፱ ፣ መኃ. ፬፥፯) "ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ" እንዳለ። (ቅዱስ ቴዎዶጦስ ዘዕንቆራ) ከዚያም ከእናት ከአባቷ ቤት ለሦስት ዓመታት ቆይታ ወደ ቤተ መቅደስ ትገባለች። በቤተ መቅደስም ለአሥራ ሁለት ዓመታት ፈጣሪዋን እግዚአብሔርን እያመሰገነችና እያገለገለች እርሷን ደግሞ መላእክተ ብርሃን እያገለገሏት ሕብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ እየመገቧት ኑራለች። አሥራ አምስት ዓመት በሞላት ጊዜ አረጋዊ ዮሴፍ ያገለግላት ዘንድ ወደ ቤቱ ወሰዳት። በዚያም መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዜና ድኅነትን ነግሯት አካላዊ ቃልን በማኅጸንዋ ጸነሰችው። ነደ እሳትን ተሸከመችው፤ ቻለችው። "ጾርኪ ዘኢይትጸወር ወአግመርኪ ዘኢይትገመር" እንዳለ። (ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ለብሐዊ) ወልደ እግዚአብሔርን ለዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ጸንሳ እንበለ ተፈትሆ (በድንግልና) ወለደችው። (ኢሳ. ፯፥፲፬) "ኢየሱስ" ብላ ስም አውጥታለት በገሊላ ለሁለት ዓመታት ቆዩ። አርዌ ሄሮድስ እገድላለሁ ብሎ በተነሳበት ወቅትም ልጇን አዝላ በረሃብ እና በጥም፣ በላበትና በድካም፣ በዕንባና በኀዘን ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ከገሊላ እስከ ኢትዮጵያ ተሰዳለች። ልጇ ጌታችን አምስት ዓመት ከስድስት ወር ሲሆነው ለድንግል ደግሞ ሃያ አንድ ዓመት ከሦስት ወር ሲሆናት ወደ ናዝሬት ተመለሱ። በናዝሬትም ለሃያ አራት ዓመት ከስድስት ወር ልጇን ክርስቶስን እያሳደገች ነዳያንን እያሰበች ኑራለች። እርሷ አርባ አምስት ዓመት ልጇ ሠላሳ ዓመት ሲሆናቸው ጌታችን ተጠምቆ በጉባኤ ትምህርት፣ ተአምራት ጀመረ። ለሦስት ዓመት ከሦስት ወርም ከዋለበት እየዋለች ካደረበትም እያደረች ትምህርቱን ሰማች። የማዳን ቀኑ ደርሶ ልጇ ክርስቶስ ሲሰቀልም የመጨረሻውን ፍጹም ኀዘን አስተናገደች። አንጀቷ በኀዘን ተቃጠለ። በነፍሷም ሰይፍ አለፈ። (ሉቃ. ፪፥፴፭) ጌታ በተነሳ ጊዜም ከፍጥረት ሁሉ ቀድማ ትንሣኤውን አየች። ለአርባ ቀናትም ሳትለይ ከልጇ ጋር ቆየች። ከልጇ ዕርገት በኋላ በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትን ሰብስባ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ አበቃች። በጽርሐ ጽዮንም ከአደራ ልጇ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ለአሥራ አምስት ዓመታት ኖረች። በእነዚህ ዓመታት ሥራ ሳትፈታ ስለ ኃጥአን ስትማልድ፣ ቃል ኪዳንን ከልጇ ስትቀበል፣ ሐዋርያትን ስታጽናና፣ ምሥጢርም ስትገልጽላቸው ኑራለች። ዕድሜዋ ስልሳ አራት በደረሰ ጊዜ ጥር ፳፩ ቀን መድኃኒታችን አእላፍ ቅዱሳንን አስከትሎ መጣ፤ ኢየሩሳሌምን ጨነቃት። አካባቢውም በፈውስ ተሞላ። በዓለም ላይም በጐ መዓዛ ወረደ። እመ ብርሃን ለፍጡር ከዚያ በፊት ባልተደረገ ለዘላለምም ለማንም በማይደረግ ሞገስ፣ ክብርና ተአምራት ዐረፈች። ሞቷ ብዙዎችን አስደንቋል። "ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ።" እንዲል። ከዚህ በኋላ መላእክት እየዘመሩ ሐዋርያቱም እያለቀሱ ወደ ጌቴሴማኒ በአጐበር ሥጋዋን ጋርደው ወሰዱ። ይህንን ሊቃውንት፦ "ሐራ ሰማይ ብዙኃን እለ አልቦሙ ሐሳበ እንዘ ይዜምሩ ቅድሜኪ ወመንገለ ድኅሬኪ ካዕበ ማርያም ሞትኪ ይመስል ከብካበ።" ሲሉ ይገልጡታል። በወቅቱ ግን አይሁድ በክፋት ሥጋዋን እናቃጥል ስላሉ ቅዱስ ገብርኤል (ጠባቂ መልአክ ነው።) እነርሱን ቀጥቶ እርሷን ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወስዶ በዕጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል። በዚያም መላእክት እያመሰገኗት ለሁለት መቶ አምስት ቀናት ቆይታለች። ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ ለሐዋርያቱ ክብረ ድንግልን ቢነግራቸው በጐ ቅንአት ቀንተው በነሐሴ ፩ ሱባኤ ጀመሩ። ሁለተኛው ሱባኤ ሲጠናቀቅም ጌታ የድንግል ማርያምን ንጹሕ ሥጋ ሰጣቸው። እየዘመሩም በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል። በሦስተኛው ቀን (ነሐሴ ፲፮) እንደ ልጇ ባለ ትንሣኤ ተነስታ ዐርጋለች። ትንሣኤዋንና ዕርገቷንም ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ አይቶ መግነዟን ተቀብሏል። ሐዋርያቱም መግነዟን ለበረከት ተካፍለው እንደ ገና በዓመቱ ነሐሴ ፩ ቀን ሱባኤ ገቡ። ለሁለት ሳምንታት ቆይተው ሁሉንም ወደ ሰማይ አወጣቸው። በፍጡር አንደበት ተከናውኖ የማይነገር ተድላ፣ ደስታና ምሥጢርንም አዩ። ጌታ ራሱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው። የበዓሉን ቃል ኪዳን ሰምተው ከድንግል ተባርከው ወደ ደብረ ዘይት ተመልሰዋል። ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን። አእምሮውን፣ ለብዎውን፣ ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                          22. ቅዱስ ኡራኤል ቃል ኪዳን የተቀበለበትና የተሸመበት ቀን
                            በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዑራኤል፦ ፪.ድንግል ማርያም በአካለ ሥጋ እያለች ወደ ሰማይ አሳርጓታል። በሠረገላ ብርሃን ጭኖ በክንፎቹም ተሸክሞ አስቅድሞ ገነትን ቀጥሎም ሲዖልን አስጐብኝቷታል። በዚህም ምክንያት እመ ብርሃን ስለ ኃጥአን የምታለቅስ፣ የምትለምንና የምትማልድ ሆናለች። ለምናም አልቀረች የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብላለች። ፪.ቅዱሱ መልአክ እመ ብርሃንን በስደቷ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መርቶ አምጥቷታል። በክንፉ ተሸክሞ በአራት አቅጣጫ አዙሮ አሳይቶ አሥራት እንድትቀበል አድርጓል። ፫.ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ደሙን በጽዋዕ አድርጐ በኢትዮጵያ ወንዞች ላይ አፍስሷል። ፬.ለብዙ ቅዱሳን (አባ ጊዮርጊስን ጨምሮ) ጽዋዐ ልቡናን አጠጥቷል። አምላከ ቅዱሳን ስለ ወዳጆቹ በጐ ምኞታችንን ይፈጽምልን። ከበረከታቸውም ያድለን።
                          23. ሐዋርያው ጢሞቲዋስ (እረፍቱ)
                            ይህ ቅዱስ ሐዋርያ አንድ የቤተ ክርስቲያናችን መብራት ነው። ወደ ክርስትና የመጣው በ፵ዎቹ ዓ.ም አካባቢ ሲሆን አሳምኖ ለቅድስና ያበቃው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ነው። በጊዜውም በነበረው ትጋትና ተጋድሎ ፍሬ አፍርቷል። ሆዱንም እጅግ ያመው ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ሲጠራው "የምወድህ ልጄ" እያለ ነበር። በኤፌሶንም ጵጵስናን ሹሞ ሁለት መልእክታትን ልኮለታል። ቅዱስ ጢሞቴዎስ ቤተ ክርስቲያንን ለብዙ ዘመናት አገልግሎ በሰማዕትነት ዐርፏል። ከሐዋርያው ቅዱስ ጢሞቴዎስ በረከትን እንሳተፍ ዘንድ ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ጢሞቴዎስ ከላካቸው መልእክቶች ጥቂት እናንብብ። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                          24. አቡነ ተክለሃይማኖት
                            28. ቅዱስ አማኑኤል ለ5000 ሰዎች ጌታችን ህብስቱን ያበረከተበት
                            የካቲት
                              3. አባ ያዕቆብ (እረፍቱ)
                                ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ዳዊት "ለስሒት መኑ ይሌብዋ - ስሕተትን ማን ያስተውላታል።" (መዝ. ፲፰፥፲፪) ሲል የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ታላቅ ቅዱስ ሰው በኃጢአት ብዙ ተፈተነ። ወደ በርሃ ወጥቶ በምናኔ ጸንቶ በጾምና በጸሎት ተግቶ ዘመናትን ስላሳለፈ ሰይጣንን አሳፈረው። ግን ደግሞ ክፉ ጠላት ባልጠረጠረው መንገድ መጥቶ መከራ ውስጥ ከተተው። የአገረ ገዢው ልጅ ታማ "ፈውሳት" አሉት፤ እርሱም ፈወሳት። ወደ ቤቷ ስትመለስ ግን አመማት። "ከአንተ ጋር ትቆይ።" ብለው ትተዋት ቢሔዱ ከመለማመድ የተነሳ በዝሙት ወደቀ። እንዳይገለጥበት ስለ ፈራም ገደላት። በሆነው ነገር ተስፋ ቆርጦ ወደ ዓለም ሲመለስ ቸር ፈጣሪ የሚናዝዝ አባትን ልኮ ንስሐ ሰጠው። ጉድጓድ ምሶ ድንጋይ ተንተርሶ ለሠላሳ ዓመታት አለቀሰ። እግዚአብሔርም ምሮት የቀደመ ጸጋውን ቢመልስለት ዝናምን አዝንሞ ሕዝቡን ከእልቂት ታድጓል። በዚህች ዕለት ዐርፎም ለርስቱ በቅቷል። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                              8. በዓለ ስምዖን ጌታችን አምላካችን መድሀኒታችን ወደ ምኩራብ የገባበት ቀን(የአረጋዊው የስምዖን ታሪክ ልብ ይበሉ)
                                ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ጌታ በተወለደ በአርባ ቀኑ ራሱ የሠራውን ሕግ ይፈፅም ዘንድ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቷል። እንደ ሥርዓቱም እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምና አገልጋዩዋ ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ የርግብ ግልገሎችና ዋኖስ አቅርበዋል። ለሁለት መቶ ሰማንያ አራት ዓመታት የአዳኙን (የመሲሑን) መምጣት ይጠብቅ የነበረው አረጋዊው ስምዖን በዚህች ዕለት ስላየውና ስለታቀፈው ዕለቱ "በዓለ ስምዖን" ይባላል። (ሉቃ. ፪፥፳፪) ከዘጠኙ የጌታ ንዑሳን በዓላት አንዱ ነው። ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ ከዓለም ፍጥረት በአምስት ሺህ ሁለት መቶ ዓመታት (ማለትም ከክርስቶስ ልደት ሦስት መቶ ዓመታት በፊት) በጥሊሞስ የሚሉት ንጉሥ በግሪክ ነገሠ። በጊዜውም በኃይለኝነቱ ሁሉን አስገብሮት ነበርና "ዓለሙን እንደ ሰም አቅልጬ እንደ ገል ቀጥቅጬ ገዛሁት። ምን የቀረኝ ነገር አለ?" ሲል ተናገረ። ባሮቹም "አንድ ነገር ቀርቶሃል። በምድረ እስራኤል ጥበብን የተሞሉ አርባ ስድስት መጻሕፍት አሉ። እነርሱን አስተርጉም።" አሉት። ያን ጊዜ እስራኤላውያንን አስገብሯቸው ነበርና አርባ ስድስቱን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከሰባ ሁለት ምሑራን (ተርጓሚዎች) ጋር እንዲያመጡለት አዛዦቹን ላከ። እነርሱም አርባ ስድስቱን መጻሕፍተ ብሉይ ኪዳን ከሰባ ሁለት ምሑራን ጋር አመጡለት። አይሁድ ክፋተኞች መሆናቸውን ሰምቷልና ሠላሳ ስድስት ድንኳን አዘጋጅቶ ጥንድ ጥንድ ሆነው እንዲሠሩ ሲተረጉሙ እንዳይመካከሩ ሠላሳ ስድስት ጠባቂዎችን ሾመባቸው። ይህ ነገር ለጊዜው ከንጉሡ ቢመስልም ጥበቡ ግን ከእግዚአብሔር ነው። ምክንያቱም በጊዜ ሒደት መጻሕፍተ ብሉያት በአደጋ እንደሚጠፉ ያውቃልና ሳይበረዙ ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች (ለእኛ) እንዲደርሱ ነው። ስለዚህም ከክርስቶስ ልደት ሁለት መቶ ሰማንያ አራት ዓመታት በፊት አርባ ስድስቱም (ሁሉም) መጻሕፍተ ብሉያት ከዕብራይስጥ በሰባው ሊቃናት አማካኝነት ወደ ጽርዕ ልሳን ተተረጐሙ። (በእርግጥ ከዚያ አስቀድሞ መጻሕፍት (ብሉያት) ወደ ሃገራችን መምጣቸውና ወደ ግዕዝ ልሳን መተርጐማቸውን ሳንዘነጋ ማለት ነው!) ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንመለስ ከሰባው ሊቃናት መካከል በእድሜው አረጋዊ የሆነ (እንደ ትውፊቱ ከሆነ ሁለት መቶ አሥራ ስድስት ዓመት የሆነው) ስምዖን የሚሉት ምሑረ ኦሪት ነበር። በፈቃደ እግዚአብሔር ለእርሱ መጽሐፈ ትንቢተ ኢሳይያስ ደርሶት እየተረጐመ ምዕራፍ ሰባት ላይ ደረሰ። ቁጥር ሰባት ላይ ሲደርስ ግን "ናሁ ድንግል ትጸንስ ወትወልድ ወልደ" የሚል አይቶ "አሁን እንኳን የአሕዛብ ንጉሥ የእስራኤልስ ቢሆን ድንግል በድንግልና ጸንሳ ትወልዳለች ብለው እንዴት ያምነኛል!" ሲል አሰበ። "በዚያውስ ላይ ኢሳይያስ በምናሴ የተገደለው ስለዚህ አይደል!" ብሎ ቃሉን ሊለውጠው ወሰነ። አመሻሽ ላይም "ድንግል" የሚለውን "ወለት (ሴት ልጅ)' ብሎ ቀየረው። እርሱ ሲያንቀላፋ ቅዱስ መልአክ ወርዶ "ድንግል" ብሎ አስተካከለው። ከእንቅልፉ ሲነቃ ግራ ተጋብቶ እንደ ገና ፍቆ ቀየረው። አሁንም መልአኩ "ድንግል" ሲል ቀየረበት። ሦስት ጊዜ እንዲህ ከሆነ በኋላ ግን መልአኩ ተገልጦ ገሰጸው። በዚያውም ላይ "ይህችን ድንግልና መሲሑን ልጇን ሳታየውና ሳትታቀፈው ሞትን አታይም።" ብሎት ተሰወረው። አረጋዊ ስምዖን ከዚያች ዕለት በኋላ የመድኅን ክርስቶስን መምጣት ሲጠብቅ ለሁለት መቶ ሰማንያ አራት ዓመታት የአልጋ ቁራኛ ሁኖ ኖረ፤ አካሉም አለቀ። ለስም አጠራሩ ስግደት የሚገባው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው በሆነበት በዚያ ሰሞን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ። ሕግን የሠራ ጌታ እርሱ "ፈጻሜ ሕግ" ይባል ዘንድ የርግብ ግልገሎችን (ዋኖሶችን) ይዘው በተወለደ በአርባ ቀኑ ወደ ቤተ መቅደስ አስገቡት። በዚህች ቀንም ቅዱስ መልአክ መጥቶ ቅዱስ ስምዖንን ከአልጋው ቀሰቀሰው። ተስፋ የሚያደርገው አዳኙ (መሲሑ) እንደ መጣም ነገረው። ይህን ጊዜ አረጋዊው አካሉ ታድሶ እንደ ሠላሳ ዓመት ወጣት እመር ብሎ ከአልጋው ተነሳ። እንደ በቅሎ እየሠገረም ወደ መቅደስ ወጣ። በዚያ መሲሑን (ፈጣሪውን) ሲመለከት እንደ እንቦሳ ዘለለ። ቀረብ ብሎም ሕፃን ጌታን ከድንግል እናቱ እጅ ተቀበለው። ከደስታው ብዛት የተነሳም "ይእዜ ትስዕሮ ለገብርከ በሰላም እግዚኦ በከመ አዘዝከ - አቤቱ ባሪያህን እንደ ቃልህ በሰላም አሰናብተው።" ሲል ጸለየ። ትንቢትንም ተናገረ። በዚያችው ዕለትም ዐርፎ ተቀበረ። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                              9. አባ በርሱማ (እረፍቱ)
                                ታላቁ (THE GREAT ይሉታል።) አባ በርሱማ በሶርያ ቤተ ክርስቲያን ምንኩስናና ገዳማዊ ሕይወትን ያስፋፋ አባት ነው። በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ምድረ ሶርያን ጨምሮ በብዙ ቦታዎች የቅድስና ሕይወትን ያስፋፋው ቅዱስ በርሱማ ለቤተ ክርስቲያን ምሰሶ ከሆኑላት አበው አንዱ ነው። እርሱ ከተጋድሎው ብዛት ለሃምሳ አራት ዓመታት ያለ እንቅልፍ ቆይቷል። በእነዚህ ዘመናትም ግድግዳ ላይ ጠጋ ብሎ ከማረፉ በቀር መቀመጥን እንኳ አልመረጠም። በመዓልትም በሌሊትም በፍቅር አብዝቶ ስለ ራሱና ስለ ሕዝቡ በመጸለዩ የብዙዎቹን ነፍስ ወደ ሕይወት ማርኳል። ገዳማትን ከማስፋፋትና ደቀ መዛሙርትን ከማብዛቱ ባለፈ በስብከተ ወንጌልም የተመሰከረለት አባት ነበር። በ፬፻፴፩ (፬፻፳፫) ዓ.ም በኤፌሶን በተደረገው የቅዱሳን ጉባኤ ላይ ከተገኙ ሊቃውንትም አንዱ ነው። በቅድስና ሕይወቱ የተገረመው የቁስጥንጥንያው ንጉሥ (ትንሹ ቴዎዶስዮስ) የንግሥና ቀለበቱን እና ማኅተሙን ሸልሞታል። ቅዱሱም የዋዛ አልነበረምና በንጉሡ ማኅተም እያተመ "ተፋቀሩ" የሚሉ ብዙ አዋጆችን ወደ መላው ዓለም ልኳል። በ፬፻፶፩ (፬፻፵፫) ዓ.ም በኬልቄዶን ስድስት መቶ ሠላሳ ስድስት ሰነፍ ጳጳሳት ጉባኤ አድርገው አባ ዲዮስቆሮስን እንደ ገደሉት ሲሰማም ወደ ቤተ መንግሥት ሒዶ ከሃዲዎቹን (መርቅያንና ሚስቱ ብርክልያን) በአደባባይ ዘልፏቸዋል። ስለ አዘነባቸውም ተቀስፈዋል። ታላቁ ቅዱስ አባ በርሱማ ፀሐይን ማቆሙን ጨምሮ በርካታ ተአምራትን ሠርቶ በዚህች ቀን ዐርፏል። ቸር አምላኩ ከበረከቱ ይክፈለን።
                              15. ነቢዩ ዘካርያስ (እረፍቱ)
                                ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር)፣ መጻዕያትን (ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው። ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው በጸጋ ይሰጠዋል። እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ። ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም። በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ። (ሐዋ. ፲፩፥፳፯) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ፤ ይገስጻሉ። ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል። "እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ። (ቅዳሴ ማርያም) የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው። እውነትን ስለ ተናገሩ አንዳንዶቹም በእሳት፣ አንዳንዶቹም በሰይፍ፣ አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል። ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል። ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል። ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ። እናንተ በድካማቸው ገባችሁ።" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል። (ዮሐ. ፬፥፴፮) ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል፤ ሽተዋልም። "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ።" እንዳለ ጌታ በወንጌል። (ማቴ. ፲፫፥፲፮ ፣ ፩ጴጥ. ፩፥፲) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ። ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት፣ አራቱ ዐበይት ነቢያት፣ አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ። አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት ማለት፦ ቅዱስ አዳም አባታችን ሴት ሔኖስ ቃይናን መላልኤል ያሬድ ኄኖክ ማቱሳላ ላሜሕ ኖኅ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ ሙሴና ሳሙኤል ናቸው። አራቱ ዐበይት ነቢያት፦ ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል ቅዱስ ኤርምያስ ቅዱስ ሕዝቅኤልና ቅዱስ ዳንኤል ናቸው። አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት፦ ቅዱስ ሆሴዕ አሞጽ ሚክያስ ዮናስ ናሆም አብድዩ ሶፎንያስ ሐጌ ኢዩኤል ዕንባቆም ዘካርያስና ሚልክያስ ናቸው። ካልአን ነቢያት ደግሞ፦ እነ ኢያሱ ሶምሶን ዮፍታሔ ጌዴዎን ዳዊት ሰሎሞን ኤልያስና ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው። ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ። የይሁዳ (ኢየሩሳሌም)፣ የሰማርያ (እስራኤል)ና የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ። በዘመን አከፋፈል ደግሞ፦ ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት)፣ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)፣ ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት)፣ ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ። ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ። ቅዱስ ዘካርያስ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ፬፻፶ ዓ.ዓ አካባቢ ነው። "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው። አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ አሥራ አራት ምዕራፍ ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል። ነቢዩ ቅዱስ ዘካርያስ፦ ከክርስቶስ ልደት አራት መቶ ሃምሳ ዓመታት በፊት የነበረ፣ በጻድቅነቱ የተመሰከረለት፣ አሥራ አራት ምዕራፎች ያሉት ሐረገ ትንቢት የተናገረ፣ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ በስፋት የተነበየ ነቢይ ሲሆን ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትም አንዱ ነው። የአባታችን በረከት ይደርብን።
                              16. ኪዳነምህረት /እመቤታችን ቃልኪዳን የተቀበለችበት/
                                "ተካየደ" ማለት "ተስማማ፣ ተማማለ" እንደ ማለት ሲሆን "ኪዳን" በቁሙ "ውል፣ ስምምነት" እንደ ማለት ነው። ይኸውም እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ሰዎችም ከሰዎች ጋር የሚያደርጉት ሊሆን ይችላል። ልዩነቱ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ቅዱስና የማይለወጥ መሆኑ ነው። እግዚአብሔር አምላክ ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ በየጊዜው ከብዙ ወዳጆቹ ጋር ኪዳንን አድርጓል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እነዚህን ኪዳናት ጥቅልል አድርጋ ሰባት እንደ ሆኑ ታስተምራለች። ስለዚህም ዛሬ ፈጣሪ ቢረዳን እነዚህን ሰባት ኪዳናት በጥቂቱ እንመለከታለን። "ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ - ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳንን አደረግሁ።" (መዝ. ፹፰፥፫) ፩. ኪዳነ አዳም አዳም ማለት የእግዚአብሔር ድንቅ ፍጥረት፣ የፍጡራን አስተዳዳሪ፣ ነቢይ፣ ካህንና ንጉሥ ነው። እግዚአብሔር ከአዳም ጋር አስቀድሞ በእጸ በለስ አማካኝነት ቃል ኪዳን ነበራቸው። ነገር ግን አባታችን በዲያብሎስ ሴራ በመረታቱ ኪዳኑ ፈረሰ። (ዘፍ. ፫፥፩) አዳምና ሔዋን ተጸጽተው ቢያለቅሱ ግን አዲስ የኪዳን ተስፋ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ።" የሚል ኪዳንን ተቀበሉ። (ቀሌምንጦስ፣ ገላ. ፬፥፬) ፪. ኪዳነ ኖኅ ከአዳም እስከ ኖኅ ድረስ ባሉት አሥር ትውልድ ዓለም በዓመፃ ተሞላች። ቅዱስ ኖኅ በደግነቱ መርከብ ሠርቶ ቤተሰቡን ሲያተርፍ ዓለም በማየ ሥራዌ ጠፋች። ከመርከቡ ከወጣ በኋላ ኖኅና እግዚአብሔር በቀስተ ደመና ምልክትነት ቃል ኪዳን ተጋቡ። "ኢያማስና ለምድር ዳግመ በማየ አይኅ" እንዲል። (ዘፍ. ፱፥፲፪) ፫. ኪዳነ መልከ ጼዴቅ መልከ ጼዴቅ የእግዚአብሔር ካህኑ የክርስቶስም ምሳሌው የሆነ የሳሌም ንጉሥ ነው። በአሥራ አምስት ዓመቱ መንኖ አጽመ አዳምን ይዞ በቀራንዮ በሕብስትና በወይን ያስታኩት ነበር። እግዚአብሔር ለመልከ ጼዴቅ በሐዲስ ኪዳን ለምትሠራው ክህነትና ምሥጢረ ቁርባን ምሳሌ አድርጐ በቃል ኪዳን አትሞታል። በዚህም ተሰውሮ ይኖራል እንጂ ሞትን እስካሁን አልቀመሰም። ይህም ካህኑ መልከ ጼዴቅ ከአብርሃም ጋር በተገናኙበት ጊዜ ተገልጧል። (ዘፍ. ፲፬፥፲፯፣ ዕብ. ፯፥፩) ፬. ኪዳነ አብርሃም ቅዱስ አብርሃም የሕዝብና የአሕዛብ አባት፣ ሥርወ ሃይማኖት፣ የጽድቅም አበጋዝ ነው። ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲል ከርስቱና ከወገኖቹ ተለይቶ በቅድስና ኑሯልና እግዚአብሔር "በዘርህ አሕዛብ ይባረካሉ።" አለው። (ዘፍ. ፲፪፥፩) የቃል ኪዳን ምልክትም ይሆነው ዘንድ ግዝረትን ሰጠው። (ዘፍ. ፲፯፥፩-፬) ፭. ኪዳነ ሙሴ ቅዱስ ሙሴ የነቢያት አለቃ፣ የእሥራኤል እረኛ፣ የእግዚአብሔር ሰው እና ፍጹም ትሑት (የዋህ) ሰው ነው። በፈጣሪው ትዕዛዝ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት አውጥቶ ለአርባ ዘመናት በበርሃ ሲመራቸው ከእግዚአብሔር የኪዳንን ጽላትና አሠርቱን ትዕዛዛት ተቀብሏል። (ዘጸ. ፳፥፩፣ ፴፩፥፲፰) ፮. ኪዳነ ዳዊት ቅዱስ ዳዊት ሥርወ ነገሥት፣ ጻድቅ፣ የዋህና ቡሩክ የሆነ አባት ነው። እግዚአብሔር ከእረኝነት ጠርቶ ንጉሥ አድርጐ ሹሞት "ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አኖራለሁ።" ሲል ምሎለታል። (መዝ. ፻፴፩፥፲፩) አክሎም ሰፊ ቃል ኪዳን ሰጥቶ "አልዋሽህም" ብሎ ሲምልለት እንመለከታለን። (መዝ. ፹፰፥፴፭) ፯. ኪዳነ ምሕረት በብሉይ ኪዳን የነበሩ ስድስቱ ኪዳናት በዘመናቸው ክቡርና ሕዝቡን ከመቅሰፍት ይታደጉ የነበሩ ቢሆንም ከሲኦል ማዳን ግን አልቻሉም። ስለዚህም አንድ ፍጹም ኪዳን ያስፈልግ ነበር። ይህን ፍጹም ኪዳን ይፈጽም ዘንድም ከቅድስት ሥላሴ አንዱ ወልድ ከሰማያት ወርዶ በድንግል ማርያም ማኅጸን አደረ። በፍጹም ተዋሕዶም በሕቱም ድንግልና ተወልዶ፣ አድጎ፣ ተጠምቆ፣ አስተምሮ፣ ሙቶ፣ ተነስቶና ዐርጐ ሥጋ ማርያምን በዘባነ ኪሩብ አስቀመጠው። ኪዳነ ምሕረት (የምሕረት ኪዳን) የምንለው አንዱ ታዲያ ይሔው ነው። የጌታችን መጸነሱ፣ መወለዱ፣ መሰደዱ፣ መጠመቁ፣ ማስተማሩ፣ ሥጋውንና ደሙን መስጠቱ፣ መሰቀሉ፣ መሞቱና መነሳቱ፣ ማረጉና መንፈስ ቅዱስን መላኩ በአንድ ላይ ኪዳነ ምሕረት ይባላል። ታዲያ ይህ ሁሉ የተደረገው በሥጋ ማርያም ነውና የኪዳኑ ባለቤት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። የእርሷ ኪዳን የስድስቱን አበው ኪዳናት ፍጹም በማድረጉ "የኪዳናት ማሕተም" ይባላል። የድንግል ማርያም ኪዳኗ ከሲኦልና ከገሃነም ሊታደገን አቅሙ አለውና። መድኃኒታችን ክርስቶስ ለድንግል እናቱ ቃል ኪዳኑን ያጸናላት ደግሞ ካረገ ከዓመታት በኋላ ጐልጐታ ላይ ነው። እመ ብርሃን በዚያ ቁማ ስለ ኃጥአን ስታለቅስ "እናቴ ሆይ! በስምሽ ያመነውን በቃል ኪዳንሽ የተማጸነውን እምርልሻለሁ።" ብሎ ደስ አሰኝቷታልና። ይሔው በእመ ብርሃን ምልጃና ቃል ኪዳን ምዕመናን ከመቅሰፍትና ከገሃነመ እሳት ማምለጥ ከጀመሩ ሁለት ሺህ ዓመታት ሆኑ። ዛሬም እኛ ኃጥአን ልጆቿ ከእሳት እንደምታድነን አምነን በጥላዋ ሥር እንኖራለን። "ኢትዝክሪ ብነ አበሳነ ኃጢአተነ ወጌጋየነ ማርያም እሙ ለእግዚእነ በኪዳንኪ ወበስደትኪ ድንግል ተማሕጸነ።" "ድንግል ሆይ! ኃጢአታችን፣ አበሳችንና በደላችንን አታስቢብን ዘንድ በስደትሽና በኪዳንሽ ተማጽነናል።" የአርያም ንግሥት፣ የሰማያውያንና ምድራውያን ሁሉ እመቤት፣ የአምላክ እናት፣ ቅድስት፣ ስብሕት፣ ክብርት፣ ልዕልት፣ ቡርክት፣ ፍስሕትና ጥዕምት የሆነች ድንግል ማርያም የድኅነታችን መሠረት ላመኑባት አንገት የማታስደፋ እውነተኛ አማላጅ ናት። በዚህች ዕለት የካቲት ፲፮ ስለ ወገኖቿ የሰው ልጆች ፍቅር በእንባ ያቀረበችውን ልመና የባሕርይ አምላክ የሆነ ልጇ ተቀብሎ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ገብቶላታል። በስምሽ ያመነ በቃል ኪዳንሽ የተማመነ እሳትን አያይም ብሏታል። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                              20. ቅዱስ ፊልሞን
                                ይህን ቅዱስ "ፊልሞን መዓንዝር" ብሎ መጥራቱ የተለመደ ነው። እርሱ በቀደመ ሕይወቱ አዝማሪ (ዘፋኝ) ነበርና። ዘፋኝነት (አዝማሪነት) ደግሞ በክርስትና ከተከለከሉ ተግባራት አንዱና ዋነኛው በመሆኑ ዘፈን (ሙዚቃ) መስማትም ሆነ ማዳመጥ ኃጢአት ነው። ነገር ግን ሁሉ እንዲድን የሚፈቅድ ጌታችን ጥሪውን ወደ ሁሉም ሰው በየጊዜው ይልካል። ቅዱስ ፊልሞንም የክርስቶስ ጥሪ የደረሰው በከንቱ የዘፋኝነት (የአዝማሪነት) ኑሮ ውስጥ ሳለ ነው። ነገሩ እንዲህ ነው፦ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ (በ፪፻፺ዎቹ) አርያኖስ የሚባል ሹም በግብጽ (እንዴናው) ክርስቲያኖችን ጨፈጨፈ። ባለማወቅም ክርስቶስን የሚያመልኩ ሚሊየኖችን በሰይፍ በላቸው። ከዚህ ድርጊቱ መልስ ደግሞ በጣዖቱ (አጵሎን) ፊት እያስዘፈነ ከንቱነትን ይሰዋ ይዝናናም ነበር። ከዘፋኞቹ መካከል ደግሞ ይህ ፊልሞን አንዱ ሆኖ ለዘመናት በፊቱ ተጫወተለት። አንድ ቀን ግን እንዲህ ሆነ። አስቃሎን የሚባል ቅዱስ ክርስቲያን ለጣዖት እንዲሰዋ ታዘዘ። ይህ አስቃሎን (አብላንዮስም ይባላል።) ወንድሙን ፊልሞንን ያድነው ዘንድ ተጠበበ። ወደ ፊልሞን ሒዶ "እኔ ገንዘብ እሰጥሃለሁ። የእኔን ልብስ ለብሰህ እኔን መስለህ ለጣዖት ሰዋልኝ።" አለው። አስቃሎን ይህንን ያለው ለጥበቡ ሲሆን ፊልሞን ግን "ገንዘብ ካገኘሁ" ብሎ የባልንጀራውን ልብስ ተሸፋፍኖ ወደ ጣዖቱ ፊት ቀረበ። ያን ጊዜ ተሸፍኖ መስዋዕት ማቅረብ ክልክል ነውና ሹሙ አርያኖስ ግለጡት ሲል አዘዘ። ቢገልጡት ፊልሞን ሁኖ ተገኘ። መኮንኑ ገርሞት "ምን እያደረክ ነው?" ቢለው "እኔ ክርስቲያን ነኝ።" ሲል አሰምቶ ተናገረ። ለጊዜው ሁሉም እየቀለደ መስሏቸው ነበር። ፊልሞን ግን ይህንን ያለው ከልቡ ነው። ምክንያቱም በቅዱስ አስቃሎን ልብስ ተመስሎ መንፈስ ቅዱስ ልቡን ለውጦለት ነበር። ተገልጦ ቀና ሲልም ቅዱሳን መላእክት ከበውት አይቶ ልቡ ጸንቶለታል። ሹሙ አርያኖስም የቀልዱን እንዳልሆነ ሲያውቅ "ታብዳለህ?" ቢለው ፊልሞን "ምን አብዳለሁ! ዛሬ ገና ከእብደቴ ሁሉ ዳንሁ እንጂ።" ሲል መልሶለታል። አሕዛብ ሁሉ እያዩም በዚያች ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ በደመና አምሳል ወርዶ አጥምቆታል። በሆነው ሁሉ የተበሳጨው ሹሙም ቅዱስ ፊልሞንን ከክርስቶስ ፍቅር ይለየው ዘንድ ደበደበው፣ ገረፈው፣ ጥርሱን አረገፈው፣ ደሙንም መሬት ላይ አፈሰሰው። በዚህ ሁሉ ግን ጸና። ቅዱስ አስቃሎንም ፈጥኖ መጥቶ በመከራው መሰለው። በመጨረሻም ሁለቱም ቅዱሳን በቀስት ተነድፈው ይገደሉ ዘንድ ተፈረደባቸው። ነገር ግን ለእነርሱ የተወረወረ ቀስት መንገዱን ስቶ የሹሙን (የአርያኖስን) ዓይን በማጥፋቱ ወታደሮቹ በንዴት ሁለቱንም ሰይፈው ገድለዋቸዋል። ዓይኑ የጠፋበት አርያኖስም ስቃዩ ሲበዛበትና ከሚያመልካቸው የረከሱ ጣዖታት መፍትሔ ሲያጣ ከቅዱሳኑ ደም ተቀባ። ዓይኑም ፈጥኖ በራለት። በዚህም ምክንያት ምድራዊ ሹመቱን፣ ሃብት ንብረቱን፣ ትዳርና ቤቱን፣ ጣዖት አምልኮውን ትቶ በክርስቶስ አምኖ ለሰማዕትነት በቅቷል። አምላከ ቅዱሳን በወዳጆቹ አማላጅነት የምናስተውልበትን አዕምሮ አይንሳን። በረከታቸውንም ያድለን።
                              23. ቅዱስ ጊዮርጊስ
                                በዚህች ዕለት በ፲፰፻፹፰ ዓ.ም በቅዱስ ጊዮርጊስ ምልጃና ረዳትነት አባቶቻችን አድዋ ላይ ጣልያንን ድል አድርገዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ደጉን ንጉሥ ዳግማዊ አፄ ምኒልክን እናስባቸው ዘንድ ይገባል። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                              26. ነቢዩ ሆሴዕ (እረፍቱ)
                                ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር)፣ መጻዕያትን (ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው። ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው በጸጋ ይሰጠዋል። እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ። ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም። በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ። (ሐዋ. ፲፩፥፳፯) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ፤ ይገስጻሉ። ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል። "እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ። (ቅዳሴ ማርያም) የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው። እውነትን ስለ ተናገሩ አንዳንዶቹም በእሳት፣ አንዳንዶቹም በሰይፍ፣ አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል። ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል። ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል። ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ። እናንተ በድካማቸው ገባችሁ።" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል። (ዮሐ. ፬፥፴፮) ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል፤ ሽተዋልም። "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ።" እንዳለ ጌታ በወንጌል። (ማቴ. ፲፫፥፲፮ ፣ ፩ጴጥ. ፩፥፲) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ። ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት፣ አራቱ ዐበይት ነቢያት፣ አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ። አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት ማለት፦ ቅዱስ አዳም አባታችን ሴት ሔኖስ ቃይናን መላልኤል ያሬድ ኄኖክ ማቱሳላ ላሜሕ ኖኅ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ ሙሴና ሳሙኤል ናቸው። አራቱ ዐበይት ነቢያት፦ ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል ቅዱስ ኤርምያስ ቅዱስ ሕዝቅኤልና ቅዱስ ዳንኤል ናቸው። አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት፦ ቅዱስ ሆሴዕ አሞጽ ሚክያስ ዮናስ ናሆም አብድዩ ሶፎንያስ ሐጌ ኢዩኤል ዕንባቆም ዘካርያስና ሚልክያስ ናቸው። ካልአን ነቢያት ደግሞ፦ እነ ኢያሱ ሶምሶን ዮፍታሔ ጌዴዎን ዳዊት ሰሎሞን ኤልያስና ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው። ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ። የይሁዳ (ኢየሩሳሌም)፣ የሰማርያ (እስራኤል)ና የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ። በዘመን አከፋፈል ደግሞ፦ ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት)፣ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)፣ ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት)፣ ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ። ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ። ቅዱስ ሆሴዕ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ፰፻ ዓ.ዓ አካባቢ ነው። "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው። አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ አሥራ አራት ምዕራፍ ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል። ነቢይና ጻድቅ ቅዱስ ሆሴዕ 'ዖዝያ' በመባልም ይታወቃል። ቅዱሱ ነቢይ የቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል ባልንጀራ የነበረ ሲሆን በአራት ነገሥታት ዘመን (ዖዝያን፣ ኢዮአታም፣ አካዝና ደጉ ሕዝቅያስ) ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን ተናግሯል። የትንቢት ዘመኑም ከሰባ ዓመት በላይ ነው። ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሆሴዕ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራም በስፋት ተንብዩዋል። አሥራ አራት ምዕራፎች ያሉት የትንቢቱ ጥራዝ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። ሆሴዕ ማለት መድኃኒት ማለት ነው። የመዳን ትምህርትንና ትንቢትን ሊናገር ተመርጧልና። ቸር አምላከ ነቢያት የነቢያቱን መከራ አስቦ ከመከራ፣ በእንባቸውም ከእንባ ይሰውረን። ከተረፈ በረከታቸውም አያጉድለን።
                              28. ሮማዊው ቅዱስ ቴዌድሮስ(እረፍቱ)
                                አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (ቅዱሱ ሊቅ) በመጽሐፈ ሰዓታት ሰማዕታትን፦ "መስተጋድላን ከዋክብት ብሩሃን ማኅትዊሃ ለቤተ ክርስቲያን።" ይላቸዋል። በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሮም መንግሥት ዓለምን የሚያስተዳድረው በሁለት ከተሞች ማለትም በራሷ በሮምና በአንጾኪያ ነበር። የወቅቱ ንጉሥ ኑማርያኖስ ሲሆን የቤተ መንግሥቱ ልዑላንና የጦር አለቆች ቅዱሳኑ፦ ፋሲለደስ፣ ገላውዴዎስ፣ ፊቅጦር፣ መቃርስ፣ አባዲር፣ ቴዎድሮስ (ሦስቱም)፣ አውሳብዮስ፣ ዮስጦስ፣ አቦሊና ሌሎቹም ነበሩ። ሴቶቹ ደግሞ ቅዱሳቱ፦ ማርታ፣ ሶፍያ፣ ኢራኢ፣ ታኡክልያና ሌሎቹም ነበሩ። ለእነዚህ ሁሉ የበላይ ደግሞ ቅዱስ ፋሲለደስ ነበር። ወቅቱ ከፋርስ፣ ከቁዝና ከበርበር ጦርነት የሚበዛበት ነበርና ባጋጣሚ ንጉሡ ኑማርያኖስ በሰልፍ መካከል ተመትቶ ወደቀ (ሞተ)። የሮም መንግሥትም ባዶ ሆነች። ዙፋኑን መያዝ ለቅዱስ ፋሲለደስም ሆነ ለሌሎቹ ቅዱሳን ቀላል ነበር። ግን እነርሱ ዝም ብለው ጠላትን ለመዋጋት ወጡ። በዘመኑ ደግሞ በግብጽ የፍየል እረኛ የነበረና ከልጅነቱ ሰይጣን የሚያናግረው አንድ አግሪጳዳ የሚሉት ጉልበተኛ ሰው ነበር። ንጉሡ ከወለዳቸው ልጆች ሁለቱ ሴቶች ክፉዎች ነበሩና ትንሿ አግሪጳዳን ማንም በሌለበት አንግሣ ጠበቀቻቸው። ስሙንም ዲዮቅልጢያኖስ አለችው። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሰይጣን ቀጥሎ እንደዚህ የከፋ ስም የለም። የዓለም ክርስቲያኖችን የጨፈጨፈ ሰው ነው። ትልቋ ደግሞ የትንሿን አይታ መክስምያኖስ የሚባል አውሬ አግብታ አነገሠችው። ዓለምም በእነዚህ ጨካኝ ሰዎች እጅ ወደቀች። ሠራዊቱ ሁሉ በሚሊየን ይቆጠራሉ። የተደረገውን ሲያዩ ተበሳጩ። ይህንን የተመለከተው ቅዱሱ ፋሲለደስ ግን ልዑላኑንና አለቆችን ሰብስቦ "ይህ ዓለም ከነ ክብሩ ጠፊ ነው። ስለዚህ የተሻለውን የክርስቶስን መንግሥት እንምረጥ።" አላቸው። ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ ደስ ተሰኝተው ምድራዊ ክብራቸውን ሊተው ወሰኑ። ቀጥለውም በአንድ ቤት ተሰብስበው ይጾሙ ይጸልዩ ገቡ። ወደ ውጪ የሚወጡት ለምጽዋት ብቻ ነበር። ከሃዲውም ይህንን ሲያይ የልብ ልብ ተሰማው። ከድሮ ያሰበውንና ክርስቲያኖችን የማጥፋቱን እቅድ ሊፈጽም ምክንያት አገኘ። አባ አጋግዮስ በሚባል መነኩሴ ምክንያት "አብያተ ክርስቲያናት ይትዐጸዋ አብያተ ጣዖታት ይትረኀዋ - ቤተ ክርስቲያኖች ይዘጉ፤ ቤተ ጣዖቶችም ይከፈቱ።" አለ። አጵሎን፣ አርዳሚስ የሚባሉ ጣዖቶችንም አቆመ። በዚህ አዋጅ ምክንያትም የክርስቲያኖች ሰቆቃ ጀመረ። ምድር በደም ታጠበች። ቅዱሳኑ ቀባሪ አጡ። እኩሉ ተገደለ። እኩሉ ተቃጠለ። እኩሉ ታሠረ። እኩሉም ተሰደደ። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተጻፈው በብራናና በብዕር አይደለም። ይልቁኑ እንደ ቀለም የሰማዕታት ደማቸው፣ እንደ ብዕር አጥንታቸው፣ እንደ ብራና ቆዳቸው ሆኖ ተጽፏል እንጂ። ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው የከፈሉት ዋጋ እጅግ ታላቅ ነው። ስለዚህም "ተጋዳዮች፣ የሚያበሩ ኮከቦች፣ የቤተ ክርስቲያን ሻማዎች" ተብለው እነርሱ እየቀለጡ አብርተዋል። ሰማዕትነት በብሉይ ኪዳን የጀመረና እስከ ዳግም ምጽዐተ ክርስቶስም የሚቀጥል ቢሆንም "ዘመነ ሰማዕታት" የሚባለው ከ፻፶ እስከ ፫፻፲፪ ዓ/ም ድረስ ያለው ዘመን ነው። በተለይ ግን ከ፪፻፸ዎቹ እስከ ፫፻፲፪ ዓ/ም ድረስ ያሉ ዓመታት እጅግ የከፉ ነበሩና። የአርባ ሰባት ሚሊየን ክርስቲያኖች ደም በምድር ላይ ፈሷል። የሰማዕታት ምሥጢራቸው ቃለ ወንጌል፣ የጌታ ስብከትና ሕይወት እንጂ ሌላ አይደለም። (ማቴ. ፲፥፲፮ ፣ ማር. ፲፫፥፱ ፣ ሉቃ. ፲፪፥፬ ፣ ዮሐ. ፲፮፥፩ ፣ ሮሜ. ፰፥፴፭ ፣ ራእይ. ፪፥፱) የቅዱሳን ሰማዕታት መነሻቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ፍጻሜአቸው ደግሞ ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት ነው። ቅዱስ ቴዎድሮስ በዘመነ ሰማዕታት (በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን) በቀድሞው የሮም ግዛት ውስጥ ከተነሱ ታላላቅ ሰማዕታት አንዱ ነው። በወቅቱ መሪ የነበረው ክሀዲው መክስምያኖስ "ክርስቶስን ክደህ ለጣኦት ስገድና በከተማዋ ላይ እሾምሃለሁ።" ቢለው "ለእኔ ሃብቴም ሹመቴም የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።" በማለቱ ንጉሡ ተቆጥቶ በብረት ዘንግ አስደበደበው። በመንኮራኩር አበራየው። ለአናብስት ጣለው። አካላቱን ቆራረጠው። በእሳትም አቃጠለው። ቅዱስ ቴዎድሮስ ስቃዮችን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በትዕግስት ተቀበለ። በፍጻሜውም አንገቱን በሰይፍ ተመትቶ ሦስት አክሊላት ወርደውለታል። ከፈጣሪው ዘንድም ነጭ መንፈሳዊ ፈረስና ቃል ኪዳን ተቀብሏል። ስሙን የጠራ፣ መታሠቢያውን ያደረገ ዋጋው አይጠፋበትም። (ማቴ. ፲፥፵፩) አምላከ ቅዱሳን ከቅዱሱ ሰማዕት በረከት ይክፈለን። አይተወን፣ አይጣለን፣ ጾሙንም ለበረከት ያድርግልን።
                            መጋቢት
                              4. ቅዱስ ጊዮርጊስ /ደብረዘይት/
                                5. ተዝካረ ልደቱ ለአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ
                                  ጻድቁ የተወለዱት ግብጽ (ንሒሳ አካባቢ) ሲሆን አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ይባላሉ። አባታችን ገብረ ሕይወት የጻድቃን አለቃ፣ የቅዱሳን የበላይ፣ ተጋድሎአቸውና ድንቅ ተአምራቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ቅዱስ ሰው ናቸው። የጻድቁን ክብር መናገር የሚችል ምን አንደበት ይኖራል? እንደ ምንስ ባለ ብራና ይጻፋል? ዜናቸውንስ ለመስማት የታደለ እንደ ምን ዓይነት ሰው ይሆን? አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለአምስት መቶ ስልሳ ሁለት ዓመታት በዚህች ዓለም ሲኖሩ እህል ያልቀመሱ ምግባቸው ምስጋና ነውና። ልብስ ያልለበሱ ጠጉር አካላቸውን ይሸፍን ነበርና። ሐዋርያዊ ሆነው ከግብጽ እስከ ኢትዮጵያ ብዙ ነፍሳትን ያዳኑ አባት ሲሆኑ ሃገራችንን አስምረው አስራት እንድትሆናቸውም ተቀብለው ምድረ ከብድ አካባቢ ዐርፈዋል። ጻድቁ ገብረ መንፈስ ቅዱስም ገብረ ሕይወትም ይባላሉ። በአምስት መቶ ስልሳ ሁለት ዓመታት ሕይወታቸው እንደ ሐዋርያት ከምድረ ግብጽ እስከ ኢትዮጵያ ወንጌልን ሰብከዋል። በዚህም በሚሊየን (አእላፍ) ለሚቆጠሩ ነፍሳት የድኅነት ምክንያት ሆነዋል። ጻድቁ እንደ ሰማዕታትም ከከሃዲ ሰዎች ብዙ መከራን ተቀብለዋል። እንደ ባሕታውያን ለብዙ መቶ ዓመታት ሰው ሳያዩ ቆይተዋል። ለየት የሚለው ግን የጽድቅ ሕይወታቸው ነው። ከእልፍ አዕላፍ አጋንንት ጋር ተዋግተው ድል ማድረግ ችለዋልና። የንሒሳው ኮከብ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር አላቸው። ስለ ሃገሪቱና ሕዝቧ ፍቅር ሲሉ ለመቶ ዓመታት በደብረ ዝቋላ መከራን ተቀብለዋል። ምሕረትን ሲለምኑ ሥጋቸው አልቆ በአጥንታቸው ቁመው ነበርና ሃገራችን አሥራት ሆና ተሰጠቻቸው። ስለዚህም ነው በሃገሪቱ ውስጥ ከሁለት ሺህ በላይ የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳማትና አድባራት ዛሬም ድረስ ያሉት። በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ የተወለዱት አባታችን ያረፉት በአሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ነው። ፍጥረታትን ሁሉ አዝዘው መጋቢት ፭ ቀን ሲያርፉ ግሩማን መላእክት ገንዘው አካላቸውን ሠውረዋል። ሥላሴን የተሸከመ አካላቸው በጐልጐታ ተቀብሯል የሚሉም አሉ። "ሰላም ለመቃብሪከ ዘኢተከሥተ ለባዕድ ከመ መቃብሩ ለሙሴ ወልደ ዮካብድ ዜና መቃብሪከሰ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸማድ ቦ ዘይቤ በኢየሩሳሌም አጸድ ወቦ ዘይቤ ኀለወ በከብድ።" እንዲል። የጻድቁ በዓል ጥቅምት ፭ ቀን የሚከበረው ብዙ ጊዜ መጋቢት ፭ ቀን ዐቢይ ጾም ውስጥ ስለሚውል ተውላጥ (ቅያሪ) ሆኖ ነው። ቸር አምላክ ከጻድቁ ዋጋና በረከት ይክፈለን።
                                10. መስቀሉን ንግስት እሌኒ ቆፍሬ ያገኘችበት ቀን መድሀኔአለም
                                  ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ቸር አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ከሰማያዊ ክብሩ ወደ ምድር ወርዶ: በማሕጸነ ማርያም እግዝእት በኪነ ጥበቡ ተጸንሶ: በኅቱም ድንግልና ተወልዶ: በፈቃዱ መከራ መስቀልን ተቀብሎ: ከግራ ቁመት: ከገሃነመ እሳት: ከሰይጣን ባርነት: ከኃጢአት ቁራኝነትም አድኖናል:: "እምእቶነ እሳት ዘይነድድ አንገፈነ" እንዳለ ሊቁ:: ምንም መስቀል በብሉይ የወንጀለኞች መቅጫ ሆኖ ቢቆይም እግዚአብሔር ለዓለም መዳኛነት የመረጠው ነውና ሕብረ ትንቢቶች ሲነገሩለት: በብዙ ሕብረ አምሳልም ሲመሰል ኑሯል:: ከተፈጥሯችን ጀምሮ ዓለም ራሷ አርአያ ትዕምርተ መስቀል ናት:: እግዚአብሔር ለቃየን እንዳይገድሉት ከሰጠው ምልክት (ዘፍ. 4:15) ጀምሮ ይስሐቅ ሊሰዋ የተሸከመው እንጨት(ዘፍ. 22:6): ቅዱስ ያዕቆብ ያያት የወርቅ መሰላል (ዘፍ. 28:12): ያዕቆብ የዮሴፍን ልጆች የባረከበት መንገድ(ዘፍ. 48:14): ባሕረ ኤርትራን የከፈለችው የሙሴ በትር (ዘጸ. 14:15): የናሱ ዕባብ የተሰቀለበት እንጨትን (ዘኁ. 21:8) ጨምሮ በርካታ ምሳሌዎች ለቅዱስ መስቀሉ መኖራቸውን መተርጉማን ተናግረዋል:: ቅዱስ ዳዊትን የመሰሉ ነቢያት ደግሞ "ለሚፈሩሕ ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ምልክትን ሰጠሃቸው" እያሉ መስቀሉን ከርቀት ተመልክተዋል:: (መዝ. 59:4) በሐዲስ ኪዳን ግን ምሳሌው ገሃድ ሆኖ: ጌታ በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥጋውን ቆረሰበት:: ደሙን አፈሰሰበት:: ዓለምንም አዳነበት:: ስለዚህም "መስቀል ብርሃን ለኩሉ ዓለም: መሠረተ ቤተ ክርስቲያን" ተብሎ የሚመሰገን ሆኗል:: ቅዱስ ያሬድ ሊቁ አክሎ "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር: ያድኅነነ እምጸር" ብሎ ጠላትን ማሳፈሪያ መሆኑን ይነግረናል:: ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ስለ መስቀሉ አምልቶ አጉልቶ አስተምሯል:: መመኪያችን ነውና:: (1ቆሮ. 1:18, ገላ. 6:14) አንዳንዶቹ እኛን "የተሰቀለውን ትታቹሃል" ይሉናል:: የተሰቀለውማ የጌቶች ጌታ: የነገሥታት ንጉሥ: የአማልክት አምላክ: ሁሉ በእጁ የተያዘ: ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ከኦርቶዶክስ በላይ የሚያመልክ በወዴት አለና:: ነገር ግን መስቀሉን ንቆ የተሰቀለውን ማክበር አይቻልምና እኛ ለመስቀሉ የጸጋ ስግደትን እንሰግዳለን:: እናመሰግነዋለን:: እናከብረዋለን:: "ቤዛ: ጽንዕ: መድኃኒት: ኃይል" እያልንም እንጠራዋለን:: አባቶቻችን በመስቀሉ ምርኩዝነት ማዕበለ ኃጢአትን: ባሕረ እሳትን ተሻግረዋል:: በመስቀሉ ቢመኩ አጋንንትን ድል ነስተዋል:: ጠላትንም አሳፍረዋል:: እኛም በመስቀሉ አምነን: ከብረን: ገነን እንኖራለን:: ተጠቅመንበታልና ከራሳችን ሕይወት በላይ ምስክርን አንፈልግም::  በዓለ መስቀል  መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ካረገ ከዓመታት በኋላ አይሁድ በአንድ ነገር ተቸገሩ:: የክርስቶስን ሐዋርያት እያሳደዱ ቢገድሉም ከመስቀሉና ሥጋ ክርስቶስ አርፎበት ከነበረው ጐልጐታ ላይ የሚደረገውን ተአምር ግን መግታት አልተቻላቸውም:: መቼም ለተንኮል አያርፉምና ቅዱስ መስቀሉን ሽፍቶቹ ከተሰቀሉባቸው ጋር ደርበው አርቀው ቀበሩት:: አካባቢው የጉድፍ መጣያ እንዲሆንም አዋጅ ነገሩ:: ለክፋት ሲሆን ተባባሪው ብዙ ነውና ለ300 ዓመታት ያህል ቆሻሻ ቢጥሉበት ተራራ ሆነ:: ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ እናታችን ቅድስት እሌኒ (ሔለና) በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት: በቅዱስ ኪራኮስ መሪነት: በቅዱስ ሚካኤል ረዳትነት ደመራ አስደምራ: እጣን አጢሳ መካነ መስቀሉን አገኘች:: መስከረም 17 ቀን የተጀመረው ቁፋሮ መጋቢት 10 ቀን ተጠናቆ: ንጹሕ መስቀሉ ወጥቶ ብርሃን በርቷል: ሙታን ተነስተዋል:: ከ10 ዓመት በኋላም የመስቀሉ ቤተ መቅደስ ታንጾ መስከረም 17 ቀን ተቀድሷል:: ይህ ቅዱስ ዕፀ መስቀልም በደጉ አፄ ዳዊት ዘመን ወደ ሃገራችን መጥቶ: በጻድቁ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ አማካኝነት በደብረ ከርቤ (ግሸን ማርያም) ተለብጦ ተቀምጧል:: አምላከ ቅዱሳን በኃይለ መስቀሉ: በሞገሰ መስቀሉ ይጠብቀን:: ከበረከቱ አሳትፎ በዓሉን የሰላም ያድርግልን:: ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                15. ቅድስት ሳራ(እረፍቷ)
                                  22. ጥንተ ሆሳእና
                                    "ጥንተ በዓል" ማለት በዓሉ : ተአምሩ (የማዳን ሥራው) የተፈፀመበት የመጀመሪያው ቀን ማለት ነው:: በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሆሳዕና ጀምሮ እስከ ዸራቅሊጦስ ድረስ ያሉ ዐበይት በዓላትን ሁለት ጊዜ ታከብራለች:: 1ኛው. "ጥንተ በዓል" ሲሆን 2ኛው. ደግሞ "የቀመር በዓል" ይሠኛል:: መሠረቱ የቅዱሳን ሐዋርያት ቀኖና እና የአባታችን የድሜጥሮስ መንፈሳዊ ቀመር ነው:: ስለሆነም ዓለም ከተፈጠረ በ5,534 ዓመት : የዛሬ 1,974 ዓመት : ልክ በዛሬዋ ቀን (መጋቢት 22) ስም አጠራሩ ከፍ ከፍ ይበልና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ትሕትና በአህያዋና በውርንጫዋ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም (ቤተ መቅደስ) ገብቷል:: ታላቅ የምስጋና መስዋዕትም ከመላዕክት : ከሐዋርያት : ከሕጻናት : ከአረጋውያን : ከፀሐይ : ከጨረቃ : ከከዋክብት : ከቢታንያ ድንጋዮች . . . በአጠቃላይ ከፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ቀርቦለታል:: ጌትነቱንም በገሃድ ገልጧል:: ††† ከበዓሉ በረከት ይክፈለን:: እኛንም ለጣዕመ ምስጋናው የተዘጋጀን ያድርገን::
                                  27. ቸሩ መድሃኒአለም (የጌታችን ጥንተ ስቅለቱ መታሰቢያ)
                                    ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ለእኛ ሲል በፈጸመው የማዳን ሥራ ክፉዎች አይሁድ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ጌቴሴማኒ ውስጥ ያዙት። ሙሉውን ሌሊት ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አስረው ሲደበድቡት አድረዋል። ዝም ቢላቸው ዓይኑን ሸፍነው በጥፊ መቱት። ምራቃቸውን ተፉበት፤ ዘበቱበት። ራሱንም በዘንግ መቱት። እርሱ ግን ሁሉን ታገሰ። በጧት ከገዢው ዘንድ ሞት እንዲፈረድበት አቀረቡት። በሠለስት (ሦስት ሰዓት ላይ) አካሉ እስኪያልቅ እየተዘባበቱ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት ገረፉት። ሊቶስጥሮስ አደባባይ ላይ እርጥብ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት። ስድስት ሰዓት ላይ በረዣዥም ብረቶች አምስት ቦታ ላይ ቸንክረው ሰቀሉት። ሰባት ታላላቅ ተአምራት በምድርና በሰማይ ታዩ። ዓለም በጨለማ ሳለች ጌታ በመስቀል ላይ ሰባት ቃላትን ተናገረ። ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ በባሕርይ ሥልጣኑ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ። በዚያች ሰዓትም ወደ ሲዖል ወርዶ የታሠሩትን ሁሉ ፈታ። አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ደጋጉ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብርና ሐዘን ጋር በአዲስ መቃብር ቀበሩት። በዚያች ቀን ድንግል ማርያም ልቧ በሐዘን ተቃጠለ። ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስም ፍፁም ልቅሶን አለቀሰ። ቅዱሳት አንስት በዋይታ ዋሉ። (ማቴ. ፳፯፥፩ ፣ ማር. ፲፭፥፩ ፣ ሉቃ. ፳፫፥፩ ፣ ዮሐ. ፲፱፥፩) ለእኛ ለኀጥአን ፍጡሮቹ ሲል ይህንን ሁሉ መከራ የታገሰ አምላክ ስለ አሥራ ሦስቱ ኅማማቱ፣ አምስቱ ቅንዋቱ፣ ስለ ቅዱስ መስቀሉ፣ ስለ ድንግል እናቱ ለቅሶና ስለ ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስ ብሎ ይማረን። ከቅዱሳኑ በዚህች ዕለት ከሰማንያ ዓመታት በላይ በገዳም የኖረ የገዳማውያን ሞገሳቸው የመነኮሳትም ሁሉ አለቃ ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ዐርፏል። ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (ቅዱስ መቃሬ) 'ጽድቅ እንደ መቃርስ' የተባለለት፣ የመነኮሳት ሁሉ አለቃ፣ ከሰማንያ ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ፣ በግብጽ ትልቁን ገዳም (አስቄጥስን) የመሠረተ፣ ከሃምሳ ሺህ በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው። በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብጽ ወደ እስያ በርሃ ከጓደኛው ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል። በዚያ ለሁለት ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በኋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነንጉሣቸው አጥምቀዋል። በተሰደዱባት ሃገርም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ስም አጠራሩ ይክበርና) እመቤታችንን፣ ቅዱሳን ሐዋርያትን፣ አዕላፍ መላእክትን በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን ዳዊትን፣ ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን፣ ማርቆስን፣ ጴጥሮስን፣ ጳውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል። በቅዱስ አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል። ታላቁ ቅዱስ መቃርስና ባልንጀራው መቃርዮስ ከሁለት ዓመታት ስደትና መከራ በኋላ ስደት በወጡባት ዕለት መልአኩ ኪሩብ በክንፉ ተሽክሞ ወደ ግብጽ መልሷቸዋል። በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከሃምሳ ሺህ በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል። ስለ ታላቁ ቅዱስ መቃርዮስ ቅድስና ለመጻፍ መነሳት በረከቱ ብዙ ነው። ግን 'ዓባይን በጭልፋ' እንዲሉ አበው ከብዛቱ የተነሳ የሚዘለቅ አይሆንም። ቅዱስ መቃርስ ከዘመናት በላይ በቆየበት የበርሃ ሕይወቱ፦ ፩.አባ ብሶይ፣ አባ ባይሞይ፣ አባ ሳሙኤል፣ አባ በብኑዳን ጨምሮ እርሱን የመሰሉ (ያከሉ) ቅዱሳንን ወልዷል። ፪.ለሕይወታችን መንገድ የሚሆኑንን ብዙ ቃላትን ተናግሯል። ፫.ከገዳማት እየወጣ በብዙ ቦታዎች ቅዱስ ወንጌልን ሰብኳል። ፬.አጋንንትን ድል ከመንሳት አልፎ እንደ ባሪያ ገዝቷቸዋል። ፭.ለዓይንና ጀሮ ድንቅ የሆኑ ብዙ ተአምራትን ሰርቷል። በእነዚህና ሌሎች ምክንያቶችም ቤተ ክርስቲያን "ርዕሰ መነኮሳት (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)" ስትል ትጠራዋለች። በዘጠና ሰባት ዓመቱ መጋቢት ፳፯ ቀን ሲያርፍ መላእክት ብቻ ሳይሆን አጋንንትም ስለ ድል አድራጊነቱ ዘምረውለታል። ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ካረፈ በኋላ ከክቡር ሥጋው ብዙ ተአምራት ይታዩ ነበርና የሃገሩ (የሳስዊር) ሰዎች ሊወስዱት ፈለጉ። ሳስዊር ማለት ቅዱሱ ተወልዶ ያደገባት ወላጆቹ (አብርሃምና ሣራ ይባላሉ።) የኖሩባት ቦታ ናት። የምትገኘውም ግብጽ ውስጥ ነው። በምድረ ግብጽ በተለይም በገዳመ አስቄጥስ የአባ መቃርስን ያህል ክቡርና ተወዳጅ የለምና የሃገሩ ሰዎች የነበራቸው አማራጭ መስረቅ ነበር። መሥረቅ ኃጢአት ቢሆንም እነሱ ግን ስለ ፍቅር አንድም ለበረከት (በረከትን ሲሹ) አደረጉት። ወደ ሳስዊርም ወስደው ቤተ ክርስቲያን በቅዱሱ ስም አንጸው በክብር አኖሩት። በዚያም ለመቶ ስልሳ ዓመታት ተቀመጠ። በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግን ተንባላት (እስላሞች) መጥተው ቤተ ክርስቲያኑን አጠቁ። በዚህ ጊዜም ሕዝቡ የጻድቁን አጽም ይዘው ሸሹ። በሌላ ቦታም እንደ ገና በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጸው በዚያ አኖሩት። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የመንፈሳዊ አባታቸውን ሥጋ ያጡት የገዳመ አስቄጥስ ቅዱሳን ያዝኑ ይጸልዩ ነበርና ልመናቸውን ፈጣሪ ሰማ። አባ ሚካኤል ሊቀ ጳጳሳት በነበረበት ዘመን ከገዳሙ ለሌላ ተግባር ወደ ሳስዊር የተላኩ አበው ከታላቁ አባት ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ሰውነታቸው ታወከ። ይዘው ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉ ሊሳካላቸው አልቻለም። ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ደወል ደውሎ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ ነበርና። ሕዝቡና ሃገረ ገዢው የሆነውን ሲሰሙ "የቅዱሱን ሥጋ ብትነኩ እንገላችኋለን።" ብለው ሰይፍ፣ ዱላ፣ ጐመድና ጦር ይዘው መጡባቸው። መነኮሳቱ ግን ባዷቸውን ሊመለሱ አልፈቀዱምና ሌሊቱን ሲያለቅሱና ሲጸልዩ አደሩ። መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜም ታላቁ መቃርስ በግርማ ወርዶ መኮንኑን "ለምን ወደ ልጆቼ እንዳልሔድ ትከለክለኛለህ?" ሲል በራእይ ተቆጣው። በዚህ ምክንያትም መነኮሳቱ የቅዱሱን ሥጋ ተቀበሉ። ሕዝቡም በዝማሬና በማኅሌት ከብዙ እንባ ጋር ሸኟቸው። ታላቁ መቃሬ ወደ ገዳሙ ሲደርስም ታላቅ ደስታ ተደረገ። ቅዱሳን ልጆቹ ከመንፈሳዊ አባታቸው ተባርከው በክብር አኑረውታል። አምላከ ቅዱሳን የታላቁ ቅዱስ መቃርስን ትሕትናውን፣ ትእግስቱንና ቅንነቱን ያድለን። በበረከቱም ይባርከን። ዳግመኛ በዚህ ቀን ንግሥናን ከሊቅነት ጽድቅን ከሰማዕትነት ጋር የደረበው ሰማዕቱ ቅዱስ ገላውዴዎስ አንገቱን ተከልሏል። ቅዱስ ገላውዴዎስ የጻድቁ ዐፄ ልብነ ድንግል ልጅ ነው። መድኃኔ ዓለም ከወዳጆቹ ጸጋ ክብርን ያድለን።
                                  29. የበዓለ ወልድ /የጌታችን ጽንሰት/
                                    ይህች ቀን ለቤተ ክርስቲያን በእጅጉ ልዩ ናት። በዓመቱ ከሚከበሩ በዓላትም አንደኛውን ሥፍራ ትይዛለች። በዚህች ዕለት አምላካችን እግዚአብሔር ፩.ሰማይና ምድርን ፈጠረ። (ዘፍ. ፩፥፩) ፪.በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት በድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ (ተጸነሰ)። በዓሉም "በዓለ ትስብእት" ይባላል። "አምላክ ሰው፣ ሰው አምላክ የሆነበት" ማለት ነው። (ሉቃ. ፩፥፳፮) ፫.የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ። (ማቴ. ፳፰፥፩ ፣ ማር. ፲፮፥፩ ፣ ሉቃ. ፳፬፥፩ ፣ ዮሐ. ፳፥፩) ፬.ጌታችን ዳግመኛ ለፍርድ በዚህች ቀን ይመጣል። (ማቴ. ፳፬፥፩) በእነዚህ ታላላቅና ድርብርብ በዓላት ምክንያት ቀኑ "ርዕሰ በዓላት" (የበዓላት ራስ)፣ "በኩረ በዓላት" እየተባለም ይጠራል። ቸሩ እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩ፣ ከጽንሰቱ፣ ልደቱና ትንሣኤው በረከትን ይክፈለን። በጌትነቱም ሲመጣ በርኅራኄው ያስበን። ዳግመኛ በዚህች ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እልዋሪቆን ገብቷል። ይህች ሃገር የምድራችን መጨረሻ ናት። ከዚያ በኋላ ሰውና ሃገር የለም። እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን የሰበከ ሐዋርያ የለም። ከቅዱሱ ሐዋርያ ትጋት፣ ቅናት፣ መንፈሳዊነትና ንጽሕና አምላካችን ይክፈለን።
                                ሚያዝያ
                                  22. አባ ይስሀቅ(እረፍቱ)
                                    23. የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓለ እረፍት
                                      መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰባት ዓመታት ስቃይ በኋላ በዚህች ቀን ተሰይፏል። ይህስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ፦ ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም (ልዳ) ውስጥ ነው። የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ሃያ ዓመት ሲሞላው የአባቱን ሥልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት (የአሁኗ ቤይሩት - ሊባኖስ) ሰዎች ዘንዶ (ደራጎን) ሲያመልኩ አገኛቸው። እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ፣ አሳምኖ፣ ደራጎኑንም በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና ሰባ ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር። በዚያች ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው። እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) ደረሰ። ከዚያም ለተከታታይ ሰባት ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን ተቀበለ። ሦስት ጊዜ ሙቶ ተነሳ። ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ የሰማዕታት አለቃቸው፣ ፀሐይና የንጋት ኮከብ በሚል ይጠራል። "ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ።" እንዲል መጽሐፍ። ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዘመናት በብዙ ስቃያት ሲያስጨንቁት ኖረው በጽናቱ አሸነፋቸው። ሰባ ነገሥታትን ከነ ሠራዊታቸው ከማሳፈሩ ባሻገርም በርካታ (በመቶ ሺ የሚቆጠሩ) አሕዛብን ማርኮ ለሰማዕትነት አበቃ። በዚህ የተበሳጨ ዱድያኖስም ኮከበ ፋርስ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲቆራርጡት አዘዘ። ወታደሮቹም ቅዱሱን ቆራርጠው በብረት ምጣድ ላይ ጠበሱት። ያለ ርኅራኄም አካሉን አሳረሩት። ቀጥለውም ፈጭተው አመድ አደረጉት። በአካባቢው ወደ ነበረው ትልቅ ተራራ ጫፍ (ደብረ ይድራስ) ወጥተውም በነፋስ በተኑት። "ሐረድዎ ወገመድዎ ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ዓመድ" እንዲል። (ምቅናይ) እነርሱ ይህንን ፈጽመው ዘወር ሲሉ ግን የቅዱሱ ዓጽም ባረፈባቸው ዛፎች፣ ቅጠሎችና ድንጋዮች ሁሉ "ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት" የሚል ጽሑፍ ተገኘ። ወዲያው ግን ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተበተነበት ተነስቶ ወታደሮችን አገኛቸውና "በክርስቶስ እመኑ።" ብሎ አስደንቆ ወደ ሕይወት መራቸው። ሰባው ነገሥታት ግን አፈሩ። ከሰባት ዓመታት መከራ በኋላም በዚህች ቀን ከብዙ ተዓምራት ጋር ተሰይፎ ደም፣ ውኃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል። ሰባት አክሊላትም ወርደውለታል። በ፫፻፺ዎቹ አካባቢ ሰማዕት ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በዚያው በሃገሩ ደብር አንጸው አጽሙን አፍልሠው ቀድሰዋታል። ቅዱሱ ሰማዕት ከሰማዕትነቱ በፊትም ሆነ በኋላ ተአምረኛ ነው። በዘመኑ የክርስቲያኖችን ደም ሲያፈሱ ከነበሩ አራዊት (ነገሥታት) መካከል አንዱ የሆነው ዲዮቅልጢያኖስ ርጉም የአርባ ሰባት ሚሊየን ክርስቲያኖችን ደም አፍስሶ ነበርና ፈጣሪ ደመ ሰማዕታትን የሚበቀልበት ጊዜ ደረሰ። በ፫፻፭ ዓ.ም አካባቢ አረመኔው ንጉሥ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተአምረኛነት ሰምቶ እንዲያፈርሱት ሠራዊት ላከ። የሠራዊቱ አለቃም ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገብቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል ላይ ተሳለቀ። ከፊቱ የነበረውን ቀንዲል በሰይፍ እመታለሁ ሲል ግን ቀንዲሉ ተገልብጦ መሐል አናቱን መታው። እንደ እብድ ሆኖ ሞተ። ሠራዊቱም ሰምቶ ወደ ንጉሡ ሸሸ። ይህን ሰምቶ የተበሳጨው ዲዮቅልጢያኖስ ግን ራሱ ሊያፈርሰው ሔደ። ከቤተ ክርስቲያኑ በር ላይ ሲደርስ ሚካኤልና ገብርኤል ዓይኑን አጠፉት። እገባለሁ ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከላይ መረዋውን (ደወሉን) ለቀቀበት። ራሱን ቢመታው ደነዘዘ። የብዙ ቅዱሳንን ደም የጠጣው ርጉሙ ንጉሥም አብዶ ለሰባት ዓመታት ፍርፋሪ ሲለምን ኑሮ ሰይጣን ከገደል ጫፍ ወርውሮ ገድሎታል። አምላካችን እግዚአብሔር ከኃያሉ ሰማዕት ጽናትና ትዕግስት፣ በረከትም ይክፈለን።
                                    27. ምስካየ ሕዙናን /ስደተኛው መድሀኒአለም/
                                      30. ቅዱስ ማርቆስ በሰማዕትነት ያረፈበት ቀን ነው
                                        በዚህች ዕለት፦ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የሆነ ወንጌላዊ፣ ሐዋርያ፣ ሰማዕት፣ ዘአንበሳና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የተባለ ቅዱስ ማርቆስ በሰማዕትነት ግብጽ ውስጥ ዐርፏል። ቅዱስ ማርቆስ እናቱ ማርያም አባቱ አርስጥቦሎስ ይባላሉ። በልጅነቱ ኦሪትንና የዘመኑን ጥበብ ሥጋዊ በሚገባ ተምሮ ክርስቶስን ከቤተሰቦቹ ጋር ተከትሏል። የመጀመሪያ ስሙ ዮሐንስ ሲሆን ከመቶ ሃያው ቤተሰብ በእድሜ በጣም ትንሹ (ሃያ ዓመት) እርሱ ነበር። ለሦስት ዓመታት ከጌታ እግር ሥር ተምሮ በበዓለ ሃምሳ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ብዙ ደክሟል። በተለይ የግብጽና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አባት ነው። ክህነትን ያገኘን ከእርሱ ነውና። ቅዱስ ማርቆስ አሥራ ስድስት ምዕራፍ ያለውን ወንጌሉን ሲጽፍ ኪሩብ ገጸ አንበሳ በቀኙ ሊቀ ሐዋርያት በግራው ሆነው ይራዱት ነበር። ቅዱሱ ከቅዱስ ጳውሎስ፣ ከበርናባስና ጴጥሮስ ጋር ተጉዟል። ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላ ሰሜን አፍሪካ አካባቢ በዚህች ቀን አረማውያን ገድለውታል። ዳግመኛ በዚህች ቀን የቅዱስ ማርቆስን ወላጆችን እናስባቸው ዘንድ ይገባል። ቅዱስ አርስጥቦሎስ (አባቱ) የጌታ ቅን አገልጋይ የነበረ፤ ቅድስት ማርያም (እናቱ) ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ፣ ጌታችንን ያገለገለች፣ ቤቷን ለሐዋርያትና ለጌታ በስጦታ ያበረከተች ቅድስት ናት። ቤቷም (ጽርሐ ጽዮን) የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን ይህች ቤት መንፈስ ቅዱስ ወርዶባታል። የእመቤታችን ግንዘትም ተከናውኖባታል። እግዚአብሔር ከሐዋርያዊው ቅዱስ ቤተሰብ በረከትን ያድለን።
                                    ግንቦት
                                      1. ልደታ እመቤታችን የተወለደችበት ቀን ነው
                                        ኢያቄም ወሐና ወለዱ ለነ ሰማየ። ሰማዮሙኒ አስረቀት ለነ ፀሐየ። ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱልን። ሰማያቸው ደግሞ ፀሐይን አወጣችልን። (ወለደች - አስገኘችልን።)" የዓለማችን ወላጆች ነቢያት ሐዋርያትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ወልደው ከብረዋል፤ ተመስግነዋል። ኢያቄምና ሐና ግን ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ቢሰበሰብ በእግሯ የረገጠችውን ትቢያ እንኳ መሆን የማይችል የሰማይና የምድር ንግሥት የእግዚአብሔርን እናት እመቤታችን ማርያምን ወለዱልን። ኢያቄም ወሐና ለእግዚአብሔር የሥጋዌ አያቶቹም ተባሉ። እስኪያረጁ ድረስ በመካንነት አዝነው ጸልየዋል። ንጽሕናቸውና ደግነታቸው ተመስክሮላቸው ድንግል ማርያምን አግኝተዋል። ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተወለደች የመጀመሪያዋ ሰው ድንግል ማርያም ሆናለች። (ኢሳ. ፩፥፱) ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህች ቀን በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች። "ሙሽራዬ ሆይ! ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ።" (መኃ. ፬፥፰) ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ (አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ በሕጉ ጸንተው በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር። ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች ልጅ የላችሁም በሚል ይናቁ ነበር። ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት - ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር። ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ። እነርሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም። የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው። አንድ ቀን እርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች። "እንስሳትና አራዊትን እጽዋትን ሳይቀር በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች። ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ። ለአርባ ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ። በአርባኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ። እርሱ ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ በሐና ቀኝ ጆሮ ገብታ በማኅጸኗ ስትደርስ አየ። እርሷ ደግሞ የኢያቄም በትር አብቦ አፍርቶ ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች። ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን።" አሉ። ለሰባት ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ። በሰባተኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ ሰባት) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ። "ዓለም የሚድንባት የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ።" ብሏቸው ተሠወረ። እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ። እንደ ሥርዓቱም አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች። "ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ..... ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም።" እንዳለ ሊቁ። (ቅዳሴ ማርያም) "ለጽንሰትኪ በከርሥ እንበለ አበሳ ወርኩስ ወለልደትኪ እማኅጸን ቅዱስ....." "ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው፤ የተወለድሽበት ማኅጸንም ቅዱስ ነው።" (መጽሐፈ ሰዓታት፣ ኢሳ. ፩፥፱) እመቤታችን ነሐሴ ሰባት ቀን ተጸንሳ ግንቦት አንድ ቀን ተወልዳለች። የእመቤታችን የዘር ሐረግ፦ አዳም - ኖኅ - አብርሃም - ይስሐቅ - ያዕቆብ በእናቷ፦ ሌዊ - ቀዓት - እንበረም - አሮን - ቴክታና በጥሪቃ - ሔኤሜን - ዴርዴን - ቶና - ሲካር - ሔርሜላና ማጣት - ሐና። በአባቷ በኩል፦ ይሁዳ - ፋሬስ - ሰልሞን - ቦኤዝ - እሴይ - ዳዊት - ሰሎሞን - ሕዝቅያስ - ዘሩባቤል - አልዓዛር - ቅስራ - ኢያቄም ይሆናል።  ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ ወላዲተ አምላክ ተወለደች።  የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟ፣ ፍቅሯ፣ ጸጋዋና በረከቷ ይደርብን።
                                      7. ሊቁ አቡነ አትናቲዎስ (እረፍቱ)
                                        በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት ቀጥሎ የቅዱስ አትናቴዎስን ያህል ስለ ሃይማኖት የተዋጋ ቅዱስ ፈልጐ ማግኘት አይቻልም። ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት በዘመነ ሰማዕታት መጠናቀቂያ (በሦስት መቶ ዓ.ም አካባቢ) እስክንድርያ ግብጽ ውስጥ ነው የተወለደው። ወላጆቹ አረማውያን በመሆናቸው ክርስትናን አልተማረም ነበር። ሕፃን እያለ ለጨዋታ ከቤቱ ሲወጣ የክርስቲያን ልጆች ሃይማኖታዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ተመለከተ። ሊቀላቀላቸው ቢፈልግም ክርስቲያን ባለመሆኑ ከለከሉት። አትናቴዎስም ክርስቲያን ልሁንና አጫውቱኝ ብሏቸው እሺ ስላሉት ሕፃናቱ ዕጣ ተጣጣሉ። ለአንዱ ቄስ፣ ለአንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው ለአትናቴዎስ ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕፃናት ይሰግዱለት ጀመር። በአጋጣሚ ሕፃናቱ ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ የወቅቱ ፓትርያርክ ቅዱስ እለእስክንድሮስ በመገረም ያያቸው ነበርና ለሕፃኑ አትናቴዎስ ትንቢት ተናገረለት። ከዚያም የአትናቴዎስ አባቱ ሲሞት ሊቀ ጳጳሳቱ ከእናቱ ወስዶ አጥምቆ የሚገባውን መንፈሳዊ ትምህርት ሁሉ በልቡናው ላይ ቀረጸበት። ከዚህ በኋላ ዲቁናን ሹሞ አስተምር አለው። ምንም ሕፃን ቢሆንም ከሊቅነቱ፣ ከአመላለሱና ከአንደበቱ ጣፋጭነት የተነሳ የሰማው ሁሉ ይደነቅ ነበር። ጸጋ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ አድራለችና። ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ዲቁና በተሾመ ወራት አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ ጸሐፊ አድርገው ሾሙት። በጊዜውም በዕድሜ የስንት ጊዜ ትልቁ የሚሆነውን አርዮስን ተከራክሮ ምላሽ አሳጣው። ቅዱስ አትናቴዎስ ከሊቃውንቱ ጋር ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ መሠከረ። ጸሎተ ሃይማኖትንም ያረቀቀው እርሱ ነው። ከዚህ በኋላ የእስክንድርያ (የግብጽ) ሃያኛ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾመ። ቤተ ክርስቲያንን በመልካም እረኝነት ለአርባ ስምንት ዓመታት ሲመግብ ብዙ መከራዎችን ተቀበለ። ለአምስት ጊዜ ከመንበሩ አፈናቅለው ወደ በርሃ ሲያግዙት በስደት ከአሥራ አምስት ዓመታት በላይ አሳልፏል። በተሰደደባቸው ቦታዎች መከራን እየተቀበለ ያላመኑትን አሳምኗል። በጎቹ እንዳይባዝኑበት ደግሞ በጦማር (በደብዳቤ) ይጠብቃቸው ነበር። ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናገኘው ቃለ ሃይማኖት በዚህ ዘመን የተጻፈ ነው። በወቅቱ የነበረው ንጉሥ (ትንሹ ቆስጠንጢኖስ) የአባቱን (ታላቁ ቆስጠንጢኖስን) ዕረፍት ተከትሎ ነገሠ። ወዲያውም አርዮሳዊ መናፍቅ ሆነ። ሃይማኖታቸው የቀና አባቶችንም ያሳድድ ገባ። ከአበው ቅዱሳን መካከል ግን የዚህ መከራ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ አትናቴዎስ ነበር። በተለይ አንድ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሱን ወደ በርሃ አግዞ መናፍቅ ጳጳስ በግብጽ ሹሞ ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ ሲያስገድል ቅዱሱን ለስድስት ዓመታት አሰቃየው። የወገኖቹ (የልጆቹን) ስቃይ የሰማው ቅዱስ አትናቴዎስ ግን በድፍረት ወደ ቤተ መንግሥት ገብቶ ተናገረው። ሁለት አማራጭን አቅርቦ "ወይ ግደለኝና እንደ አባቶቼ ሰማዕት ልሁን፤ ካልሆነ ግን ወደ መንጐቼ (ምዕመናን) መልሰኝ።" አለው። መናፍቁ ንጉሥም ቢገድለው ብጥብጥ እንደሚነሳ ስለሚያውቅ በስልት ሊያጠፋው ወሰነ። ቀዛፊ፣ መቅዘፊያ፣ ምግብና ውኃ በሌላት ጀልባ ውስጥ ከቶም ሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጣለው። ድንገት ግን ከሰማይ ጌታችን መላእክቱን አስከትሎ ወረደ። ሚካኤልና ገብርኤል ባሕሩን እየቀዘፍ ሌሎች መላእክት እየመገቡት እስክንድርያ(ግብጽ) አድርሰውት ተሠውረዋል። ሕዝቡም በታላቅ ሐሴት እየዘመሩ አባታቸውን ተቀብለውታል። ሐዋርያዊው ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋግቶ ብዙ ስቃይንም ተቀብሎ በሦስት መቶ ሰባዎቹ ዓ.ም አካባቢ ዐርፏል። ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ሊቃውንት፣ ርዕሰ ሊቃውንት፣ የቤተ ክርስቲያን /የምዕመናን/ ሐኪም (Doctor of the Church)፣ ሐዋርያዊ ብላ ታከብረዋለች። አምላከ አበው ምሥጢራቸውን አይሰውርብን። ከበረከታቸውም ያድለን።
                                      11. ቅዱስ ያሬድ(የተሰወረበት)
                                        ቅዱስ ያሬድ ከእግዚአብሔር ያገኘነው አባታችን፣ ክብራችን፣ ሞገሳችን ነውና በምን እንመስለዋለን? አንደበቱ ጣፋጭ (ጥዑም)፣ ልቡናው የቅድስና ማኅደር፣ ሕሊናው የምሥጢራት ሠረገላ ነው። እስከ አርያም ተነጥቆ የማይፈጸም ምሥጢርን የተመገበ ማን እንደ እርሱ! ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሐዲስ እንደሚሉት "ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ ሙሉ አካሏ ነው።" ቅዱስ ያሬድ የተወለደው በ፭፻፭ ዓ.ም አክሱም አካባቢ ሲሆን እናቱ ክርስቲና (ታኡክልያ) አባቱ ደግሞ ይስሐቅ (አብድዩ) ይባላሉ። ሊቁ በሕፃንነቱ ምሥጢር (ትምህርት) አልገባው ብሎ ይቸገር ነበር። ትምህርት እንቢ ያለው ሰነፍ ስለ ነበር አይደለም። በጥበበ እግዚአብሔር እንጂ። ምንም ትምህርት ባይገባው ጾምና ጸሎትን ያዘወትር ነበር። ልቡናው ደግሞ በእመቤታችንና በልጇ ፍቅር የታሠረ ነበር። አንድ ቀን ግን መምህሩ የነገሩት ቀለም አልያዝህ አለው። ሲፈትኑትም ባለመመለሱ ተገረፈ። ዱላው በጣም ስለ ተሰማው ቅዱሱ ከመምህሩ ኮብልሎ ማይ ኪራሕ አካባቢ ሲደርስ ደክሞት አርፎ እግዚአብሔር ትጋትንና ተስፋ አለመቁረጥን ከትል አስተማረው። ትሏ ስድስት ጊዜ ወድቃ በሰባተኛው ፍሬዋን ስትበላት ተመልክቷልና። ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ መምህሩ ተመልሶ ይቅርታ ጠይቆ ትምህርት ጀመረ። ሊቁም ትጋትንና ጸሎትን ከሰጊድ ጋር አበዛ። እግዚአብሔር ደግሞ በድንግል እናቱ አማካኝነት የምሥጢር ጽዋን አጠጣው። ካህኑ ያሬድ እንዲያ አልገባህ ያለው ምሥጢር ተገልጦለት በጥቂት ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ወሰነ። በምሥጢር ባሕርም ይዋኝ ጀመር። ያን ጊዜ ሰማያዊ ዜማ አልተገለጠም ነበርና በጸሎት ላይ ሳለ ተደሞ መጣበት። ሦስት መላእክት በሦስት ወፎች አምሳል መጥተው አነጋገሩት። ድንገትም ነጥቀው ወደ ሰማያት ወደ ልዑላኑ መላእክት ዘንድ አደረሱት። ሊቁ በሰማያት ልዩ ምሥጢር፣ ልዩ ምስጋናና ልዩ ዜማን አዳመጠ። ይህንን ምስጋና ብዙ ቅዱሳን ቢሰሙትም ቅዱስ ያሬድ ግን ይዞት እንዲወርድ ተፈቀደለት። ሊቁ ወደ ምድር ተመልሶ በታላቅ ተመስጦ አክሱም ጽዮን ውስጥ በሃሌታ አመሰገነ። ሕዝቡና ንጉሡም ከጣዕሙ የተነሳ አደነቁ። ቅዱስ ያሬድ ለተወሰነ ጊዜ በአክሱምና ደብረ ዳሞ ሲያገለግል ቆይቶ ከመሬት ክንድ ከስንዝር ከፍ ብሎ ለእመቤታችን አንቀጸ ብርሃንን ደርሶላት ከሃገሩ ወጣ። ቅዱስ ያሬድ በቀሪ የሕይወቱ ዘመናት ፩. አምስት ያሕል መጻሕፍትን ጽፏል። ፪. በጣና ቂርቆስ፣ በዙር አባና በሌሎችም ቦታዎች ወንበር ዘርግቶ ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርቷል። ፫.በሰሜን ተራሮች አካባቢ በትጋሃ መላእክትና በተባሕትዎ ኑሯል። በ፭፻፸፮ (፭፻፸፩) ዓ.ም በተወለደ በሰባ አንድ ዓመቱ በዚህች ቀን ተሰውሯል። አባቶቻችን፦ ጥዑመ ልሳን ንሕብ ሊቀ ሊቃውንት የሱራፌል አምሳያ የቤተ ክርስቲያን እንዚራ ካህነ ስብሐት መዘምር ዘበድርሳን ማኅሌታይ ልዑለ ስብከት እያሉ ይጠሩታል። የቅዱሱ ጸሎትና በረከት ሃገራችንን ከክፉው ሁሉ ይጠብቅልን።
                                      12. አቡነ ተክለሃይማኖት /አፅማቸው የፈለሰበት
                                        12. ክርስቶስ ሳምራ
                                          14. አቡነ አረጋዊ
                                          14. ቅዱስ ገብረክርስቶስ
                                          17. አባ ኤጲፋንዮስ(እረፍቱ)
                                            ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ጽድቅ ከቅድስና፣ ድርሰት ከጥብቅና የተሳካለት አባት ነው። "ኤጲፋንያ" ማለት የመለኮት መገለጥ ሲሆን "ኤጲፋንዮስ" ማለት ደግሞ ምሥጢረ መለኮት የተገለጠለት ማለት ነው። ቅዱስ ኤጲፋንዮስ የተወለደው ክርስቶስን ከሚጠሉ አይሁዳውያን ቤተሰቦች ቤተ ገብርኤል ውስጥ ነው። ቤተሰቦቹ ከአንድ አህያ በቀር ምንም የሌላቸው ድሆች ነበሩ። በዚያ ላይ በልጅነቱ አባቱ በመሞቱ ከእናቱና ከአንዲት እኅቱ ጋር በረሃብ ሊያልቁ ሆነ። ሕፃኑ ኤጲፋንዮስ በአህያው እንዳይሠራ አህያው ክፉ ነበርና ሊሸጠው ገበያ አወጣው። ፊላታዎስ ከሚባል ክርስቲያን ጋር ለግዢ ሲደራደሩ አህያው የኤጲፋንዮስን ኩላሊቱን ረግጦት ለሞት አደረሰው። በዚህ ጊዜ አብሮት ያለው ክርስቲያኑ በትእምርተ መስቀል አማትቦ አዳነው። በፈንታው ግን አህያው ሞተ። ሕፃኑ ኤጲፋንዮስ እያደነቀ ሔደ። ከቆይታ በኋላ ሀብታም አጎቱ ገንዘቡን አውርሶት በመሞቱ ገና በአሥራ ስድስት ዓመቱ ባለጠጋ ሆነ። ያቺ ገበያ ላይ ያያት ተአምር ግን በልቡ ውስጥ ትመላለስ ነበር። አንድ ቀን ደግሞ ሉክያኖስ ከሚባል ክርስቲያን ጋር ሲሔዱ ነዳይ አገኙ። ባለጠጋው ኤጲፋንዮስ አለፈው። ያ ድሃ ክርስቲያን ግን የለበሳትን አውልቆ መጸወተው። በዚህ ጊዜ መልአኩ መጥቶ የብርሃን ልብስ ሲያለብሰው ኤጲፋንዮስ ተመለከተ። ኤጲፋንዮስ ጊዜ አላጠፋም። ከእኅቱ ጋር በክርስቶስ አምኖ ተጠመቀ። ሃብት ንበረቱን ግማሹን መጸወተ። በተረፈው ደግሞ መጻሕፍትን ገዝቶ ወደ አባ ኢላርዮን ገዳም ገባ። በዚያም መናንያኑ እስኪያደንቁት ድረስ በፍጹም ትጋትና ቅድስና ተጋደለ። በጸሎቱ ዝናም አዘነመ፣ ድውያንን ፈወሰ፣ ብዙ ተአምራትንም አደረገ። እግዚአብሔር ደግሞ ለሌላ አገልግሎት ሽቶታልና በቆጵሮስ ደሴት ላይ ጳጳስ ሆኖ ተሾመ። ብሉይ ከሐዲስ የወሰነ ሊቅ ነውና ብዙ መጻሕፍትን ተረጎመ። በሺህ የሚቆጠሩ ድርሳናትን ደረሰ። በአፍም በመጽሐፍም ብሎ መናፍቃንንና አይሁድን ምላሽ በማሳጣቱ ቤተ ክርስቲያን "ጠበቃዬ" ትለዋለች። ከደረሳቸው መጻሕፍት መካከል "ሃይማኖተ አበው ዘኤጲፋንዮስ፣ መጽሐፈ ቅዳሴውና አክሲማሮስ (ሥነ ፍጥረት)" ዛሬም በቅርብ ይገኛሉ። ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በመልካም እረኝነትና በሚደነቅ ቅድስና ተመላልሶ በአራት መቶ ስድስት ዓ.ም ዐርፏል። እድሜውም ዘጠና ስድስት ዓመት ያህል ነበር። አምላካችን ከቅዱሱ ሊቅ በረከት ያድለን።
                                          21 . እመቤታችን ማርያም /እመቤታችን በድብረ ምጥማ በምትባል ቦታ ወርቅ ወንበር ላይ ተቀምጣ ለአራት ቀን የታየችበት ነው
                                            24. ቁስቋም ማርያም /የስደቷ መነሻ/
                                              የአርያም ንግሥት የፍጥረታት ሁሉ እመቤት ድንግል ማርያም የባሕርይ አምላክ ልጇን አዝላ በዚህች ቀን ወደ ምድረ ግብጽ ወርዳለች የአርያም ንግሥት የፍጥረታት ሁሉ እመቤት ድንግል ማርያም የባሕርይ አምላክ ልጇን አዝላ በዚህች ቀን ወደ ምድረ ግብጽ ወርዳለች። በወንጌል ላይ ማቴ. ፪፥፩-፲፰ እንደተጻፈው ጌታችን በተወለደ በሁለት ዓመቱ የጥበብ ሰዎች (ሰብአ ሰገል) ወደ ቤተ ልሔም መጥተው ሰግደውለት ወርቅ እጣን ከርቤውን ገበሩለት፤ አገቡለት። ንጉሥ ተወልዷል መባሉን የሰማ ሄሮድስ መቶ አርባ አራት ሺህ ሕፃናትን ሲፈጅ በቅዱስ ገብርኤል ትዕዛዝ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን አዝላ በአንዲት አህያ ጥቂት ስንቅ ቋጥራ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ስደት ወጣች። ከገሊላ ተነስታ በጭንቅ በመከራ፣ በረሃብና በጥም፣ በሐዘንና በድካም፣ በላበትና በእንባ ተጉዛ በዚህች ቀን ምድረ ግብጽ ገብታለች። የአምላክ እናቱ እሳትን አዝላ በብርድ ተንገላታለች። ለእኛ የሕይወት እንጀራን ተሸክማ እርሷ ተራበች። የሕይወትን ውኃ ተሸክማ ተጠማች። የሕይወት ልብስን ተሸክማ ተራቆተች። የሕይወት ፍስሐን ተሸክማ አዘነች። እመ አምላክ ተራበች፣ ተጠማች፣ ታረዘች፣ ደከመች፣ አዘነች፣ አለቀሰች፣ እግሯ ደማ፣ ተንገላታች። ለሚገባው ይህ ሁሉ የተደረገው ለእኛ ድኅነት ነው። በእውነት ይህንን እያወቀ ለድንግል ማርያም ክብር የማይሰጥ ሰይጣን ብቻ ነው። አራዊት፣ ዕፀዋትና ድንጋዮች እንኳ ለአምላክ እናት ክብር ይሰጣሉ። አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍና ቅድስት ሰሎሜ ደግሞ የክብር ክብር ይገባቸዋል። ከአምላክ እናት ከድንግል ማርያምና ከቸር ልጇ ጋር መከራ መቀበልን መርጠዋልና። መድኃኔ ዓለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተሰደደ? ለምንስ ስደቱን ወደ ግብጽና ኢትዮጵያ አደረገ? ፩.ትንቢቱን ይፈጽም ዘንድ በፈጣን ደመና ወደ ግብጽ እንደሚወርድ ተነግሯልና። (ኢሳ. ፲፱፥፩ ፣ ዕን. ፫፥፯) ፪.ምሳሌውን ለመፈጸም። የሥጋ አባቶቹ እነ አብርሃም፣ ያዕቆብ (እስራኤል)፣ ኤርምያስ ወደዚያው ተሰደዋልና። ፫.ከግብጽ ጣዖት አምልኮን ያጠፋ ዘንድ። (ኢሳ. ፲፱፥፩) ፬.የግብጽና የኢትዮጵያ ገዳማትን ይቀድስ ዘንድ። ፭.ሰው መሆኑ በአማን እንጂ ምትሐት እንዳልሆነ ለማጠየቅ። ሰው ባይሆን ኑሮ አይሰደድም ነበርና። ሄሮድስ ቢያገኘው ደግሞ ሊገድለው አይችልም። ያለ ፈቃዱና ያለ ዕለተ ዓርብ ደሙ አይፈስምና። ፮.ስደትን ለሰማዕታት ባርኮ ለመስጠትና ፯.የአዳምን ስደት በስደቱ ለመካስ ነው። ቸሩ መድኃኔ ዓለም የድንግል እናቱን ስደት አስቦ ከመንግሥተ ሰማያት ስደት ይሠውረን። ከስደቱ በረከትም ያድለን።
                                            28. ቅዱስ አማኑኤል
                                              28. ቅድስት አመተ ክርስቶስ (እረፍቷ)
                                                ቅድስቷ እናታችን በነገድ እስራኤላዊ ስትሆን የተወለደችው ኢየሩሳሌም ውስጥ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ነው። ወላጆቿ ክርስቲያኖች በመሆናቸው በሚገባው ፈሊጥ አሳድገው ወደ ትምህርት አስገቧት። አስተማሪዋ ገዳማዊ መነኮስ ነበርና ከተማ ውስጥ አያድርም። አስተምሯት ዕለቱኑ ወደ በዓቱ ይመለስ ነበር እንጂ። ዓመተ ክርስቶስ ብሉይ ከሐዲስ ጠንቅቃ ተማረች። አንድ ቀን እንደ ልማዷ ልትማር ብትጠብቀውም መምህሯ ሊመጣ አልቻለም። ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ መነኮሱን ልትጠይቅ አንድም ልትማር ወደ በዓቱ ሔደች። በሩ ላይ ደርሳ ብታንኳኳም መልስም የሚከፍትም አልነበረም። ከውስጥ ግን ምርር ያለ የለቅሶ ድምጽ ተሰማት። "ጌታ ሆይ! ይቅር በለኝ?" እያለ በተደጋጋሚ ይጮሃል። ያ ደጉ መነኮስ ነበር። ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ በቅጽበት አንድ ሐሳብ መጣላት። "እርሱ በንጽሕና እየኖረ ስለ ነፍሱ እንዲህ ከተማጸነ እኔማ እንደምን አይገባኝ!" ብላ ወደ ቤቷ ተመለሰች። የለበሰችውን ልብስ አልቀየረችም። ቤተሰቦቿን አልተሰናበተችም። ከቤቷ አተር በዘንቢል እና ውኃ በትንሽ እቃ ይዛ ወደ ጐልጐታ ገሰገሰች። ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ላይ ወድቃ አለቀሰች፤ ጸለየችም። "ጌታ ሆይ! ነፍሴን ወደ ዕረፍት አድርሳት? ከክፉ ጠላትም ጠብቀኝ? ይህንን አተርና ውኃ ለእድሜ ዘመን ሁሉ ባርክልኝ።" ይህን ብላ እየፈጠነች ከኢየሩሳሌም ተነስታ በእግሯ ቃዴስን ሲናይ በርሃን አቋርጣ ግብጽ ደረሰች። ምርጫዋ ብሕትውና ሆኗልና ልምላሜ ከሌለበት ፀሐዩ እንደ ረመጥ ከሚፋጅበት በርሃ ገባች። በዚያም ከያዘችው አተር ለቁመተ ሥጋ እየበላች ከውኃውም በጥርኝ እየተጐነጨች ማንንም ሰው ሳታይ በፍጹም ተጋድሎ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ቆየች። የቀኑ ሐሩር የሌሊቱ ቁር (ብርድ) ልብሷን ቆራርጦ ቢጨርሰው እግዚአብሔር ፀጉሯን አሳድጐ አካሏን ሸፈነላት። ጊዜ ዕረፍቷ ሲደርስ የቅዱሳንን ዜና የሚጽፈው ታላቁ አባ ዳንኤል ወደ እርሷ ደረሰ። እንዳያት ተከተላት። እርሷ ግን በተሰነጠቀ አለት ውስጥ ገብታ ተደበቀች። አባ ዳንኤል በውጪ ሆኖ ተማጸነ። "እባክህ አባቴ! ውጣና ባርከኝ?" አለ። ሴት መሆኗን አላወቀም ነበርና። እርሷ ግን "ራቁቴን ነኝና አልወጣም።" አለችው። ልብሱን አውጥቶ ሰጥቷት ወጥታ ተጨዋወቱ። በፈቃደ እግዚአብሔር ዜናዋን ሁሉ አወቀ። ወደ በዓቷ ዘወር ሲል በዘንቢል የሞላ አተር ተመለከተ። ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ተበልቶ ዛሬም ሙሉ ነው። አባ ዳንኤል ይፈትነው ዘንድ ከአተሩ በደንብ በላለት፤ ከውኃውም ጠጣለት። ግን ሊጐድል አልቻለም። እያደነቀ "እናቴ ሆይ! ልብሴን ውሰጅው።" ቢላት "ሌላ አዲስ አምጣልኝ።" አለችው። ይዞላት በመጣ ቀን ግን ተሠውራለችና አላገኛትም። አንድ ቀን ግን (ማለትም ግንቦት ፳፰) አረጋውያን መነኮሳት መጥተው የገጠማቸውን ነገር ነገሩት። እንዲህ ሲሉ፦ "ሰው ተመልክተን ወደ በዓቱ ስንገባ አተር በዘንቢልና ውኃ በመንቀል አገኘን። ስንበላው ወዲያው አለቀ።" አባ ዳንኤል ነገሩን ገና ሳይጨርሱለት አለቀሰ። አተሩ አለቀ ማለት ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ ዐርፋለች ማለት ነውና። አረጋውያኑ ግን ቀጠሉ፦ "ከበዓቱ ስንወጣ በጸጉሯ አካሏ ተሸፍኖ ወደ ምሥራቅ ሰግዳ ዐርፋ አግኝተን ከሥጋዋም ተባርከን ቀበርናት።" አሉ። አባ ዳንኤል ዜናዋን ጽፎላት ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ታከብራታለች። አምላካችን በቅድስት ዓመተ ክርስቶስ ጸሎት ይማረን። ከበረከቷም ያድለን።
                                            ሰኔ
                                              8. ከደረቅ ዓለት ላይ ውሃን ያፈለቀበት ከ33ቱ ከእመቤታችን በዓል አንዱ
                                                እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓሉ ከሠላሳ ሦስቱ ዓበይት የእመቤታችን በዓላት አንዱ ሲሆን በዚህች ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል እናቱ እግር ሥር ጠበል አፍልቋል። ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ ድንግል ማርያም አምላክ ልጇን አዝላ ስደት ወጥታ ምድረ ግብጽ ትደርሳለች። በወቅቱ ከደረሱባት ችግሮች አንዱ ደግሞ ረሃብና ጽሙ ነበር። እንኳን ለስደተኛ በቤቱ ላለም ረሃብና ጥም እንዴት እንደሚከብድ የደረሰበት ያውቀዋል። ለዛም ነው ሊቁ በቅዳሴው፦ "አዘክሪ ድንግል ረሃበ ወጽምዐ ምንዳቤ ወኀዘነ ወኩሎ ዐጸባ ዘበጽሐኪ ምስሌሁ" ያለው። ታዲያ አንድ ቀን የበርሃው ፀሐይ አቃጥሏቸው ባረፉበት ድንግል እመቤታችን ውኃ ልመና ወጣች። ብዙ ለመነች ግን ጥርኝ እንኳ የሚሠጣት አጥታ በሐዘን ተመለሰች። ስትመለስ ግን ይባስ ብሎ የልጇን ጫማ ሽፍቶች ወስደውት ደረሰች። ያን ጊዜ ልጇን ታቅፋ "ውኃ ሳላገኝልህ ጫማህንም አሰረቅኩብህ።" ብላ ምርር ብላ አልቅሳለች። "በከየት ወትቤ ማርያም ማዕነቅ። እምሰብአ ሃገር አልቦ ዘየአምራ ለጽድቅ። ሰአልክዎሙ ማየ ኢወሀሐቡኒ በሕቅ። ወአሕጎልኩ ለወልድየ አሳእኖ ዘወርቅ።" እንዳለ ደራሲ። ይህንን የተመለከተ ልጇ የቆመችበትን መሬት ቢባርከው ሕይወትነት ያለው ማይ (ጠበል) ፈለቀ። ጌታችን፣ እመቤታችን፣ ዮሴፍና ሰሎሜ ከውኃው ጠጥተዋል። ሲሔዱ ግን ለእንግዶች ጣፋጭ (መድኃኒት) ለአካባቢው ሰዎች ግን መራራ ሁኗል። "ከመ ኢይስተይዋ ሰብአ ሐገር ለይእቲ ማይ አምረራ። ወለርኁቃንሰ ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ።" እንዳለ መጽሐፍ። (ሰቆቃወ ድንግል) ከመቶዎች ዓመታት በኋላም ጌታ ጠበል ያፈለቀበት ድንግል እመቤታችን የቆመችበት ቦታ ላይ በእመ ብርሃን ስም ቤተ ክርስቲያን ታንጿል። ቅዳሴ ቤቱም ተከብሯል። ጠበሉም ሲባርክና ሲፈውስ ይኖራል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                              9. ታላቁ ነብይ ሳሙኤል(እረፍቱ)(የሐና ልጅ)
                                                እስራኤል ከግብጽ ባርነት ወጥተው ከነዓንን ከወረሱበት ዘመን ጀምረው መሳፍንትና ካህናት ያስተዳድሯቸው ነበር። በወቅቱ ታዲያ ክህነት ከምስፍና ተስማምቶለት ኤሊ የተባለ ሊቀ ካህናትና ልጆቹ (አፍኒና ፊንሐስ) ያስተዳድሩ ጀመር። በዘመኑ ደግሞ ማኅጸኗ ተዘግቶባት ዘወትር የምታለቅስ ሐና የሚሏት ደግ ሴት ነበረች። እግዚአብሔር የእርሷን ጸሎትና የሊቀ ካህናቱን ምርቃት ሰምቷልና ቅዱስ ልጅን ሰጣት። "ሳሙኤል" አለችው። "ልመናዬን አምላክ ሰማኝ።" ማለት ነውና። ሐና ስዕለቷን ትፈጽም ዘንድ ሳሙኤልን በሦስት ዓመቱ ለቤተ እግዚአብሔር ሰጠችው። በዚያም ስብሐተ እግዚአብሔርን እየሰማ፣ ማዕጠንቱን እያሸተተ፣ ከደብተራ ኦሪቱ ሳይለይ በሞገስ አደገ። የኤሊ ልጆች (አፍኒና ፊንሐስ) ግን በበደል ላይ በደልን አበዙ። ወቅቱ የአሁኑን ዘመን ይመስል ነበር። ሁሉም ሰው ክፋተኛ የሆነበት በመሆኑ እግዚአብሔር ርቆ ስለ ነበር ትንቢትና ራእይ ብርቅ ነበር። አምላክ ተቆጥቷልና ሳሙኤልን በሌሊት ሦስት ጊዜ ጠራው። ነቢዩም ታጥቆ የፈጣሪውን ቃል ሰማ። በዚህም የተነሳ ታቦተ ጽዮን ለመጀመሪያ ጊዜ በአሕዛብ ተማረከች። ከሠላሳ አራት ሺ በላይ ሕዝብ በኢሎፍላውያን አለቀ። አፍኒና ፊንሐስም ተገደሉ፤ ኤሊም ወድቆ ሞተ። ከዚህች ቀን በኋላ ቅዱስ ሳሙኤል በእስራኤል ላይ ነቢይና መስፍን ሆኖ ተሾመ። በዘመኑ ሁሉ እንደሚገባው እየኖረ የእግዚአብሔርን ለእስራኤል የእስራኤልን ለእግዚአብሔር ሲያደርስ ኑሯል። ሕዝቡ ንጉሥ በፈለጉ ጊዜ ሳዖልን ቀብቶ አነገሠላቸው። እርሱ (ሳዖል) እንደ ሕጉ አልሔደምና ፈጣሪ ናቀው። ሳሙኤል ግን ደግ አባት ነውና ክፋተኛውን (ሳዖልን) ከጌታው ጋር ያስታርቅ ዘንድ ብዙ ደከመ፤ አለቀሰም። እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፦ "አትዘን! እንደ ልቤ የሆነ ፈቃዴን የሚፈጽም ዳዊትን አግኝቸዋለሁና እርሱን በእስራኤል ላይ አንግሠው።" አለው። ቅዱስ ሳሙኤልም ወደ ቤተ ልሔም ሔዶ ከእሴይ ልጆችም መርጦ ልበ አምላክ ዳዊትን ቀባው፤ አነገሠውም። ቅዱስ ሳሙኤል በተረፈው ዘመኑ ለፈጣሪው እየተገዛ ኑሯል። ነቢዩ ዘወትር ከእጁ የሽቱ ሙዳይና የቅብዐት እቃ (ቀንድ) አይለይም ነበረ። እነዚህም የድንግል ማርያም ምሳሌዎች ናቸውና አባ ሕርያቆስ፦ "ሙዳየ ዕፍረት ወቀርነ ቅብዕ ዘሳሙኤል" ብሎ አመስግኗታል። ነቢዩም በወገኖቹ መካከል በዚህች ቀን ዐርፏል። እስራኤልም አልቅሰውለታል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                              11. ሰማዕቱ ቅዱስ ገላውድዮስ (እረፍቱ)
                                                ቅዱስ ገላውዴዎስ የተወለደው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በድሮው የሮም ግዛት በአንጾኪያ (አሁን ሶርያ ውስጥ) ነው። አባቱ አብጥልዎስ የሮም ቄሣር የኑማርያኖስ ወንድም ነበር። በዚህ ምክንያት ቅዱሱ ያደገው በቤተ መንግሥት ውስጥ ነው። ወቅቱ መልካምም ክፉም ነገሮች ነበሩት። መልካሙ ነገር በቤተ መንግሥት አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ልዑላኑ አብዛኞቹ በፍቅረ ክርስቶስ የታሠሩ ነበሩ። ከእነዚህ መካካከል "ቅዱስ ፋሲለደስ፣ ቅዱሳኑ፦ ፊቅጦር፣ ቴዎድሮስ፣ አባዲር፣ አውሳብዮስ፣ ዮስጦስ፣ አቦሊ፣ እስጢፋኖስ....." ነበሩ። ቅዱሳቱ "ማርታ፣ ታውክልያ፣ ኢራኢ፣ ሶፍያ....." ነበሩ። አስቸጋሪው ነገር ደግሞ ነጋ መሸ ኑሯቸው ጦርነት ነበር። የዘመኑ የፋርስና የቁዝ መሪዎች ጦረኞች ነበሩና ዕለት ዕለት ፍልሚያ ነበር። በዚህ ምክንያት ቅዱስ ገላውዴዎስ የተመሠከረለት አርበኛና የተባረከ ንጹሕ ክርስቲያን ሆኖ አድጓል። ከልጅነቱ ጀምሮ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጥናቱ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ጨውነት ታሽቷል። እርሱ የነገሥታቱ ቤተሰብ ነው። ማዕዱ በየዓይነቱ ሞልቶ ካልመሸ እህል አይቀምስም። ጸሎቱ ስሙር፣ ስግደቱ ከምድር፣ አኗኗሩ በፍቅር ሆነ። በዚያውም ላይ በድንግልናው የጸና ኃያል ነበር። በጊዜው የቅዱስ ገላውዴዎስን ያህል መልኩ ያማረ (ደመ ግቡ) በአካባቢው አልነበረም። ይህ ግን ሊያታልለው አልቻለም። ሁሉ በእጁ ቢሆንም ለእርሱ ግን ብቸኛ ምርጫው ሃይማኖተ ክርስቶስ ነበር። ቅዱስ ገላውዴዎስ ለጦርነት ወጥቶ ሲመለስ ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ሃይማኖቱን ክዶ ሕዝቡን ለጣዖት ሲያሰግድ ክርስቲያኖችን ሲገድል ደረሰ። ቅዱሱ ኃያል የጦር ሰው ነውና ንጉሡን መግደል ሲችል ተወው። በዚያ ሰሞንም ለገላውዴዎስ ሁለት ምርጫዎች ቀረቡለት። ፩.ክርስቶስን ክዶ የንጉሡ ተከታይ መሆን፣ ፪.በክርስትናው ደሙን ማፍሰስ። የቅዱሳኑ ምርጫቸው የታወቀ ነውና ታስሮ ወደ ግብጽ ተጋዘ። በዚያ ከመኮንኑ ጋር ስለ ሃይማኖት ተከራክረው መኮንኑ ስለተበሳጨ ቅዱሱን በረዥም ጦር ጐኑን ወጋው። ዘለፍ ብሎ ነፍሱን ሰጠ። ሕዝበ ክርስቲያኑ በድብቅ መጥተው የቅዱሱን ሥጋ ሽቱ ቀብተው ከዝማሬ ጋር ገነዙት። የጓደኛው እናት ቅድስት ሶፍያ መጥታ ወደ ሶርያ ወስዳዋለች። ተወዳጅ፣ ኃያል፣ ቡሩክና መልካም ሰው ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት በሆነባት በዚህች ዕለት በመላው ኦርቶዶክሳውያን ይከበራል። አምላካችን የቅዱሱን መንኖ ጥሪት፣ ትዕግስት፣ ጸጋና በረከት ያሳድርብን። አሜን።
                                              12. ቅዱስ ሚካኤል ባሕራንን ከውሃ ያወጣበት ቀን ነው(አፎምያን ከሰይጣን ያዳነበት)
                                                ቅዱስ ሚካኤል በጥንተ ተፈጥሮ በኢዮር ኃይላት በተባሉት ነገደ መላእክት ተሹሞ ነበር። ሳጥናኤል በካደ ጊዜ እግዚአብሔር ባወቀ አንድም በትሕትናውና ደግነቱ በዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ላይ ሁሉ ተሹሟል። ከፍጥረት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የቅዱስ ሚካኤልን ያህል ክብርና ርኅሩኅ የለም። በምልጃውም በረዳትነቱም የታወቀ መልአክ ነው። መጽሐፍ "መልአከ ምክሩ ለእግዚአብሔር" ይለዋል። "ወስሙ መስተሣሕልም" ይለዋል። ቂም የሌለው ለምሕረት የሚፋጠን ደግ መልአክ ነውና። በብሉይ ኪዳን በመከራ ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ሞገስ፣ ረዳትና አዳኝ ቢሆናቸው "መጋቤ ብሉይ" ተሰኝቷል። እስራኤልን አርባ ዘመን በበርሃ መርቷል፤ መግቧልም። ቅዱስ መጽሐፍ ስለ እርሱ ብዙ ይላል። (ዘፍ. ፵፰፥፲፮ ፣ ኢያ. ፭፥፲፫ ፣ መሳ. ፲፫፥፲፯ ፣ ዳን. ፲፥፳፩ ፤ ፲፪፥፩ መዝ. ፴፫፥፯ ፣ ራእይ. ፲፪፥፯) ደስ የሚለው ደግሞ ርኅሩኁ መልአክ ከእመቤታችን ጋር ልዩ ፍቅር አለው። ከእናቷ ማኅጸን ጀምሮ እስከ ዛሬ እነሆ አብሯት አለ። ደስ ብሎት ይታዘዛታል። ማማለድ ሲፈልግም "እመቤቴ ሆይ! ቅደሚ።" ይላታል። ወደ እሳት መጋረጃ አብረው ገብተው ለዓለም ምሕረትን በረከትን ያወርዳሉ። ቅዱስ ሚካኤልን በዚህች ዕለት ስለ እነዚህ ነገሮች እናከብረዋለን። ፩.በመላእክት ሁሉ ላይ አለቃ ሆኖ መሾሙን ፪.ቅዳሴ ቤቱን (ግብጽ ውስጥ) ፫.ቅድስት አፎምያን መርዳቱን ፬.ቅዱስ ባሕራንን መጎብኘቱን ፭.ቅዱስ ላሊበላን ወደ ሰማያት ማሳረጉን ፮.ለፍጥረታት ሁሉ ምሕረት የሚጠይቅበት ዕለት ነውና። ሊቀ መላእክት በክንፈ ረድኤቱ ከክፉ ሁሉ ይጠብቀን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                              12. ቅዱስ ላሊበላ(እረፍቱ)
                                                በአሥራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ በሃገራችን የነገሠው ቅዱስ ላሊበላ፦ በብሥራተ መልአክ ተወልዷል። ቅዱሳት መጻሕፍትን ገና በልጅነቱ አጥንቷል። የንጉሥ ዘር ቢሆንም በጾምና ጸሎት በትሕርምት አድጓል። በወንድሙ ቢገረፍም ቂም አልነበረውም። ስለ ወዳጆቹ ፍቅር መርዝ ጠጥቷል። በዙፋን ላይ የኢትዮዽያ ንጉሥ ሆኖ ቢቀመጥም እርሱስ አኗኗሩ ገዳማዊ ነበር። ከተባረከች ሚስቱ ቅድስት መስቀል ክብራ ጋር አንዲት ማዕድ ብቻ በቀን ይቀምሱ ነበር። ለዚያውም ለምለሙን ለነዳያን ሰጥተው እነርሱ የሚበሉት የእንጀራውን ቅርፍት (ጠርዝ) ብቻ ነበር። በአካለ ሥጋ ወደ ሰማያት ተነጥቆ ብዙ ምሥጢራትን አይቷል። በምሳሌውም ሃገረ ሮሃን (ላስታን) ገንብቷል። ዛሬም ድረስ ምሥጢር የሆኑት ፍልፍል አብያተ መቃድስ የእጆቹ ሥራዎች ናቸው። ሥራውን ከፈጸመ በኋላ መንግሥቱን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አውርሶ በመንኖ ጥሪትና በቅድስና ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል። ጌታችን ስምህን ያከበረ ዝክርህን የዘከረ ከቤትህ ያደረውን ከርስተ መንግሥተ ሰማያት አካፍለዋለሁ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል። በረከቱን፣ ክብሩን ያድለን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                              20. ሕንፀተ ቤተ ክርስቲያን
                                                በዚህች ቀን በሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በአምላክ እናት ስም ታንጻለች። ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን "ሑሩ ወመሐሩ ኩሎ አሕዛበ - አሕዛብን ሁሉ ሒዱና አስተምሩ።" (ማቴ. ፳፰፥፲፱) ባላቸው ቃል መሠረት ዓለምን በወንጌል ያርሷት ዘንድ በዕጣ ተካፍለዋታል። የሰው ልጅ ድኅነቱ የሚፈጸመው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበል ነውና። (ዮሐ. ፮፥፶፮) አበው ሐዋርያት ቁርባንን በተመረጡ ሰዎች ቤት እያዘጋጁ ቀድሰው ያቆርቡ ነበር። በመጀመሪያ በጽርሐ ጽዮን ቀጥሎም በተለያዩ ሰዎች ቤት እንዲህ ይከናወን ነበር። ለጸሎት ሥራ ደግሞ አንዳንዴ ምኩራበ አይሁድን ይጠቀሙ ነበር። እየቆየ ሲሔድ ግን ከአሕዛብ ያመኑ ሰዎች ቁጥር እጅጉን በዛ። በተለይ ቅዱስ ጳውሎስ ያሳመናቸው ለጸሎት እያሉ ወደ ጣዖት ቤት መግባት አመጡ። በዚህ ምክንያት መምሕራን ሕዝቡን "ካመናችሁ በኋላ እንዴት ወደ ጣዖት ቤት ትገባላችሁ?" ቢሏቸው "እኛ ምን እናድርግ! የምንጸልይበት እንደሆን የለን።" ሲሉ መለሱላቸው። ነገሩ ሲያያዝ ከደጋጉ ሐዋርያት ጳውሎስና በርናባስ ደረሰ። ወዲያውኑ አንዳንድ ወንድሞች "ለምን አናንጽም።" ብለው ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ግን "ሊቀ ሐዋርያቱ ሳይፈቅድ አይሆንም።" አለ። (ለዚህ ነው ዛሬም ሊቀ ጳጳስ ካልፈቀደ ቤተ ክርስቲያን የማይታነጸው።) ከዚያ ቅዱሳን ጳውሎስና በርናባስ ሐዋርያቱ ወዳሉበት ሔደው ነገሩን ለቅዱስ ጴጥሮስ አስረዱ። ሊቀ ሐዋርያቱም "የጌታችን ፈቃዱ መሆኑን እናውቅ ዘንድ ተያይዘን ሱባዔ እንግባ።" ብሎ አዋጅ ነገረ። በዓለም ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ በአንድ ልብ ሱባዔ ገቡ። በሱባዔአቸው መጨረሻም ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግርማ ወደ እነርሱ ወረደ። ሁሉንም ሐዋርያት በደመና ጭኖ ፊልጵስዩስ አደረሳቸው። ከከተማ ወጣ ብሎ ባለ መሬት ላይም "ቤተ ክርስቲያንን በእናቴ ስም አንጹ።" ብሎ አዘዛቸው። ለቅዱስ ጴጥሮስም ሦስት ዓለቶችን ሰጠው። እነዚያን መሬት ላይ ተክሎ ጌታችን ቆሞለት ሐዋርያቱ እየተራዱት ግርምት የምትሆን ሦስት ክፍል ያላትን የመጀመሪያዋን ቤተ ክርስቲያን በ፶፪ ዓ.ም በዚህች ቀን አንጿል። ቤተ ክርስቲያኗን ነገ ጌታችን ቀደሳት የምንል ነንና ይቆየን። አምላካችን የድንግል እናቱን ፍቅር የተቀደሰች ቤቱን ጸጋ የቡሩካን ሐዋርያቱን በረከት ያሳድርብን።
                                              21. ጌታችን /የእመቤታችንን ቤት ያነጸበት ቀን ነው፡፡ ግሽን ማርያም/ በጎልጎታ በጌታችን መቃብር የጸለየችበት
                                                ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም በዚህ ቀን (ሰኔ ፳፩) ልጇን ወዳጇን ጐልጐታ ላይ ለኃጥአን ምሕረትን ለምናዋለች። ጌታችንም "ስምሽን የጠራውን፣ በቃል ኪዳንሽ ያመነውን ሁሉ እምርልሻለሁ።" ብሏታል። የድንግል እመቤታችን ልመናዋ፣ ክብሯ፣ ጣዕመ ፍቅሯና በረከቷ በሁላችን ላይ ይደርብን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                              23. ጠቢቡ ሰሎሞን እረፍቱ
                                                መፍቀሬ ጥበብ፣ ጠቢበ ጠቢባን፣ ንጉሠ እስራኤል፣ ነቢየ ጽድቅ፣ መስተሣልም (ሰላማዊ) እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ሰሎሞን የታላቁ ነቢይና ንጉሥ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እና የቅድስት ቤርሳቤህ (ቤትስባ) ልጅ ነው። ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት የተወለደው ቅዱስ ሰሎሞን እስከ አሥራ ሁለት ዓመቱ ድረስ በቤተ መንግሥት ከአባቱ ጋር አድጓል። ቅዱስ ዳዊት ሰባ ዘመን በሞላው ጊዜ የአካሉን መድከም አይቶ አዶንያስ በጉልበት እነግሣለሁ ቢልም አልተሳካለትም። እግዚአብሔር ሰሎሞንን መርጧልና ገና በአሥራ ሁለት ዓመቱ ነገሠ። ልበ አምላክ አባቱ ዳዊት ነፍሱ ከሥጋው ከመለየቷ በፊት መከረው። "ልጄ ሆይ! ልብህን ስጠኝ። ፈጣሪህንም አምልክ።" አለው። ቅዱስ ሰሎሞን እንደ ነገሠ በገባዖን ለእግዚአብሔር መስዋዕትን አቀረበ። ጌታም ተገልጾ "ምን ትፈልጋለህ?" አለው። ሰሎሞንም ልክ እንደ አባቱ ማስተዋልን ልቡናን ለመነ። በዚህም ጌታ ደስ ስለተሰኘ "አልቦ እምቅድሜከ ወአልቦ እምድኅሬከ - ከአንተም በፊት ከአንተም በኋላ እንዳንተ ያለ ጠቢብና ባለጠጋ ሰው የለም፤ አይኖርም።" ብሎት ተሠወረ። ቅዱስ ሰሎሞን ለአርባ ዓመታት በእስራኤል ላይ ነገሠ። ግሩም በሆነ ፍትሑ በልዩ ጥበቡ ዓለም ተገዛለት። እግዚአብሔር የመረጣት የእኛዋ ንግሥተ ሳባ /አዜብ/ ማክዳም ትፈትነው ዘንድ ሒዳ ምኒልክን (እብነ መለክን) ጸነሰች። በኋላም ታቦተ ጽዮንና ሥርዓተ ኦሪት መጣልን። ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን ድንግል ማርያም ከእነርሱ ዘር እንደምትወለድ ነግሮት ነበርና ያበጀሁ መስሎት ሴቶችን አብዝቶ ነበር። ነገር ግን፦ አንደኛ ሰው (ሥጋ ለባሽ) ነውና። ሁለተኛ ደግሞ ከብዙ ሴቶች መካከል ከአንዷ እመ ብርሃን ትገኛለች መስሎት ነበር። ነገሩ መንገድ ስቶበት ከአሕዛብ (ከፈርዖን ልጅ) ጋር በመወዳጀቱ ለጣዖት አሰገደችው። እግዚአብሔር እጅግ አዘነ። በራእይ ተገልጦ "ስለ ወዳጄ ስለ ዳዊት ስል በአንተ ላይ ክፉን አላደርግም።" አለው። ታላቁ ነቢይ ሰሎሞን ይህንን ሲሰማ ወደ ልቡ ተመለሰ። ማቅ ለብሶ አመድ ነስንሶ በፍጹም ልቡ አለቀሰ። ንስሐ ገባ። መፍቀሬ ንስሐ ጌታችንም ንስሐውን ተቀበለው። የይቅርታው መገለጫም ተወዳዳሪ የሌላቸውን አምስት መጻሕፍት ገለጠለት፤ ተናገራቸው። ጻፋቸው። እሊሕም፦ ፩.መጽሐፈ ጥበብ ፪.መጽሐፈ ተግሣጽ ፫.መጽሐፈ መክብብ ፬.መጽሐፈ ምሳሌ ፭.መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ናቸው። ቅዱስ ሰሎሞን ልዩ የሆነውን ቤተ መቅደስ በመስራቱም ይደነቃል። ደጉ ንጉሥ፣ ጠቢብና ነቢይ ሰሎሞን በዚህች ዕለት በሃምሳ ሁለት ዓመቱ ዐርፎ ወደ ፈጣሪው ሔዷል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                              24. አባ ሙሴ ፀሊም(እረፍቱ)
                                                ግብጻውያን ስማቸውን ጠርተው ከማይጠግቧቸው ቅዱሳን መካከል አንዱ ኢትዮጵያዊው አባ ሙሴ ጸሊም ነው። በእኛ ኢትዮጵያውያን ግን ይቅርና በወርኀዊ በዓሉ (በ፳፬) በዓመታዊ በዓሉ እንኳ ሲከበር ብዙም አይታይም። ቅዱሱ ሰው በትውልዱ ኢትዮጵያዊ ሲሆን ያደገውም እዚሁ ሃገራችን ውስጥ እንደሆነ ይታመናል። ገና በወጣትነቱ ሃገር የሚያሸብር ሽፍታ ነበር። ሙሴ ጸሊም ወደ ግብጽ የሔደበት ምክንያት በግልጽ ባይታወቅም መምለክያነ ጣዖት (ፀሐይን ከሚያመልኩ ሰዎች) ጋር ይኖር ስለ ነበር ምናልባት እነርሱ ወስደውት ሊሆን ይችላል። ቅዱስ ሙሴ በምድረ ግብጽም በኃይለኝነቱ ምክንያት የሚደፍረው አልነበረም። ፀሐይን ያመልካል። እንደ ፈለገ ቀምቶ ይበላል። ያሻውን ሰው ይደበድባል። ነገር ግን በሕሊናው ስለ እውነተኛው አምላክ ይመራመር ነበርና አንድ ቀን ፀሐይን "አምላክ ከሆንሽ አናግሪኝ?" አላት። እርሷ ፍጡር ናትና ዝም አለችው። ቅዱስ ሙሴ ምንም አስቸጋሪ ሰው ቢሆንም ፈጣሪን መፈለጉን ግን ቀጥሏልና አንድ ቀን ተሳካለት። መልካም ክርስቲያኖችን አግኝቶ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ቢሔድ በዛ ያሉ መነኮሳት ወደ እውነት እንደሚመሩት ነገሩት። እርሱም ሰይፉን እንደታጠቀ ወደ ገዳም ገባ። መነኮሳቱ ፈርተውት ሲሸሹ ታላቁ አባ ኤስድሮስ ግን ተቀብለው አሳረፉት። "ምን ፈለግህ ልጄ?" አሉት። "እውነተኛውን አምላክ ፊት ለፊት ማየት እፈልጋለሁ።" የሙሴ ጸሊም መልስ ነበር። አባ ኤስድሮስም "የማዝዝህን ሁሉ ካደረግህ ታየዋለህ።" ብለው ወደ መነኮሳት አለቃ ቅዱስ መቃርስ ታላቁ ወሰዱት። መቃሬም ክርስትናን አስተምረው አጠመቁትና ለአባ ኤስድሮስ መለሱላቸው። ከዚህ ጊዜ በኋላ ነበር የአባ ሙሴ ጸሊም ሕይወት ፍጹም የተለወጠው። በጻድቁ እጅ ምንኩስናን ተቀብሎ ይጋደል ጀመር። በጠባቧ በር ይገባ ዘንድ ወዷልና ያ በሽፍትነት የሞላ አካሉን በገድል አረገፈው። ከቁመቱ በቀር ከአካሉ አልተረፈለትም። ወገቡን በአጭር ታጥቆ መነኮሳትን አገለገለ። አጋንንት በቀደመ ሕይወቱ በሕልም አንዳንዴም በአካል እየመጡ ይፈትኑት ነበር። እንዳልቻሉት ሲረዱ ተሰብስበው መጥተው በእሳት አለንጋ ገርፈው አቆሳስለውት ሔዱ። እርሱ ግን ታገሰ። በበርሃ ለሚኖሩ አበው መነኮሳት ሁሉ ብርሃን በሆነ ሕይወቱ ሞገስ ሆነላቸው። ለኃጥአን ደግሞ መጽናኛ ሆነ። "በተራራ ላይ ያለች ሃገር ልትሠወር አይቻላትምና ስም አጠራሩ በመላው ዓለም ተሰማ። ሁሉም 'ሙሴ ጸሊም' ይል ጀመር።" በየበርሃው ያሉ አበው ብቻ ሳይሆን ዓለማውያን መኳንንት ሳይቀሩ ሊያዩት ይመኙ ነበር። እርሱ ግን ራሱን "አንተ ጥቁር ባሪያ ስለ ኃጢአትህ አልቅስ።" እያለ ይገስጽ ከውዳሴ ከንቱም ይርቅ ነበር። ከቆይታ በኋላም በመነኮሳት ላይ እረኛ (አበ ምኔት) ሆኖ ተሾመ። እንደሚገባም አገለገለ። የበርካቶችን ሕይወት ጨው በሆነ ሕይወቱና ምክሩ አጣፍጦ ድርሳናትንም ደርሶ እያረጀ ሔደ። ከቁመቱ መርዘም የጽሕሙ ነጭነትና አወራረዱን ያዩ ሁሉ ሲያዩት ያደንቁት ነበር። በመጨረሻም በ፫፻፸፭ ዓ.ም በርበሮች (አሕዛብ) ገዳመ አስቄጥስን ሲያጠፉ ሌሎች መነኮሳት ሸሹ። እርሱ ግን አልሸሽም ብሎ ከሰባት ደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚህች ቀን ተሰይፎ በሰማዕትነት አልፏል። ቅዱስ ሙሴ ጸሊምን ለርስቱ ያበቃ ጌታ ለእኛም ዕድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሃን አይንሳን። ከበረከቱም ፈጣሪው ያድለን።
                                              25. የዮሴፍ ልጅ ሐዋርው ይሁዳ እረፍቱ
                                                በዘመነ ሐዋርያት ይሁዳ ተብለው ይጠሩ ከነበሩት አንዱ የሆነው ቅዱሱ የአረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ልጅ ሲሆን እናቱ ማርያም ትባል ነበር። እናቱ ስትሞትበት ተጎድቶ የነበረ ቢሆንም ገና በልጅነቱ ድንግል ማርያም አግኝታው በፍጹም ጸጋ አሳድጋዋለች። አስተዳደጉም ከጌታችን ጋር በአንድ ቤት ነበር። ጌታችን እርሱንና ወንድሞቹን (ያዕቆብና ስምዖንን) ከሰባ ሁለቱ አርድእት ቆጥሯቸዋል። ቅዱስ ይሁዳ ወንጌል ላይ ከጌታችን ጋር መነጋገሩን ዮሐንስ ወንጌላዊ መዝግቧል። (ዮሐ. ፲፬፥፳፪) ቅዱስ ይሁዳ ከጌታችን እግር ሦስት ዓመት ተምሮ መንፈስ ቅዱስንም ተቀብሎ ብዙ አሕጉራትን ዙሯል። አይሁድንም አረማውያንንም ወደ ክርስቶስ ይመልስ ዘንድ ብዙ ድካምና ስቃይን በአኮቴት ተቀብሏል። አንዲት አጭር (ባለ አንድ ምዕራፍ) መልእክትም ጽፏል። አጭር ትምሰል እንጂ ምሥጢሯ እጅግ የሠፋ ነው። ቅዱስ ይሁዳን በዚህች ቀን አረማውያን ገድለውት በሐዋርያነቱ ላይ የሰማዕትነትን ካባ ደርቧል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                              26. ኢያሱ እረፍቱ
                                                ቅዱሱ የተወለደው በምድረ ግብጽ በባርነት ከነበሩ እስራኤላውያን ሲሆን የቀደመ ስሙ "አውሴ" ይባላል። ዘመኑ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከሁለት መቶ አሥራ አምስት ዓመታት ባርነት ሊያወጣ የተቃረበበት ነውና ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከምድያም ሲመለስ ከመረጣቸው ተከታዮቹ ዋነኛው ኢያሱ ነበር። እስራኤል ከባርነት ሲወጡ ሙሴ ሰማንያ ዓመቱ ኢያሱ ደግሞ አርባ ዓመቱ ነበር። ሕዝቡ አንገተ ደንዳና ነበርና ለአርባ ቀን የታሠበላቸውን መንገድ አርባ ዓመት እንዲሆን አደረጉት። በዚህ ጊዜ ኢያሱ ከመምህሩ ከሙሴና ከሕዝቡ አልተለየም። አውሴን "ኢያሱ" ብሎ ስም የቀየረለት ሙሴ ሲሆን ይሔውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነው። ኢያሱ ማለት "መድኃኒት" ማለት ነው። ለዚህም ምክንያቶች አሉት። ለጊዜው አማሌቃውያንን ድል ነስቶ ሕዝቡን አድኗል። ምድረ ርስትን አውርሷል። ለፍጻሜው ግን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ (ጥላ) እንዲሆን ነው። ቅዱስ ኢያሱ በበርሃ ለአርባ ዘመናት እግዚአብሔርን አምልኮታል። ሊቀ ነቢያትን ታዝዞታል (አገልግሎታል)። እስራኤልንም የጦር አለቃ ሆኖ ከአሕዛብ እጅ አድኗቸዋል። በዚህም በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ዘንድ ሞገስን አግኝቷል። ቅዱስ ሙሴ ደብረ ናባው ላይ ባረፈ ጊዜ ሕዝቡን፣ ካህናቱንና ታቦተ ጽዮንን ተረከበ። ይህን ጊዜ ዕድሜው ሰማንያ እየሆነ ነበር። እግዚአብሔርም ኢያሱን "ከአንተ ጋር ነኝ።" ብሎ በሕዝቡ ላይ ነቢይና መስፍን (አስተዳዳሪ) እንዲሆን ሾመው። ቅዱሱም ሰላዮችን ልኮ አስገምግሞ፣ ባሕረ ዮርዳኖስን ከፍሎ፣ ሕዝቡን አሻግሮ፣ የኢያሪኮን ቅጥር ሰባት ጊዜ ዙሮ፣ በኃይለ እግዚአብሔር አፍርሶ፣ የኢያሪኮን ነገሥታት አጥፍቶ ለሕዝቡ ምድረ ርስትን አወረሰ። የገባዖን ሰዎች "አድነን" ብለው በላኩበት ጊዜ ነገሥተ አሞሬዎንን ይወጋ ዘንድ ኢያሱ ወጣ። እነዚያን ግሩማን ነገሥታት በፈጣሪው ኃይል፣ በጦርና በተአምራት ድል ነስቶ የእግዚአብሔር ስሙ ከፍ ከፍ አለ። በዚያች ዕለትም ለአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ርስትን ሲያካፍል ፀሐይን በገባዖን ጨረቃን ደግሞ በቆላተ ኤሎም (በኤሎም ሸለቆ) አቆመ። ሰባት አሕጉራተ ምስካይ (የመማጸኛ ከተሞችን) ለየ። ነቢይና መስፍን ሆኖ ሕዝቡን ለአርባ ዓመታት አገለገለ። በመጨረሻም ለሕዝቡ አላቸው። "እኔና ቤቴ እግዚአብሔርን እናመልካለን። (ኢያ. ፳፬፥፲፭) እናንተስ?" አላቸው። እነርሱም "እኛም እንዳንተ ነን።" አሉት። ለዚህም ምልክት ይሆን ዘንድ ሦስት ገጽ ያላት ሐውልትን በመካከላቸው አቆመ። ይህችውም የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። ሐውልቷ ሦስት ገጽ እንዳላት እመቤታችንም በሦስት ወገን (በነፍስ፣ በሥጋ፣ በልቡና) ድንግል ናት። አንድም በሦስት ወገን (ከኃልዮ፣ ከነቢብ፣ ከገቢር ኃጢአት) ንጽሕት ናት። ለዚህም ነው አባ ሕርያቆስ "ሐውልተ ስምዕ ዘኢያሱ" (የኢያሱ የምስክር ሐውልት አንቺ ነሽ።) ሲል ያመሰገናት። ታላቁ ነቢይ ኢያሱ ግን ከግብጽ በወጡ በሰማንያ ዓመት በተወለደ በመቶ ሃያ ዓመቱ (ጥሬው መጽሐፍ ቅዱስ በመቶ አሥር ዓመቱ ይላል።) በወገኖቹ መካከል ዐርፎ በያዕቆብ መቃብር ተቀበረ። እስራኤልም ለሠላሳ ቀናት አለቀሱለት። በወዳጁ በኢያሱ እጅ የአሕዛብን ቅጥር ያፈረሰ እግዚአብሔር የእኛንም የኃጢአታችንን ግንብ በወዳጆቹ ምልጃ ያፍርስልን። ከቅዱሱ ነቢይም በረከትን ያሳትፈን።
                                              27. እረፍቱ ለሐናንያ ሐዋርያ
                                                ሐናንያ ቁጥሩ ከሰባ ሁለቱ አርድእት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስማቸው ተመዝግቦ ከተቀመጠልን ከጥቂቶቹ ዋነኛው ነው። ከነገደ እስራኤል ተወልዶ በሕገ ኦሪት አድጐ ከወጣትነት ዕድሜው ትንሽ እልፍ ሲል ጌታችን ወንጌልን ማስተማር ጀምሯልና ጠራው። እርሱም በበጐ ፈቃድ ተከትሎታልና ከሰባ ሁለቱ አርድእት ደመረው። ለሦስት ዓመታት ከጌታ እግር ተምሮ ከዕለተ ስቅለት በፊት ሃብተ ፈውስም ተሰጥቶት ነበር። ምክንያቱም ቅዱስ ሉቃስ እንደ ጻፈልን ሰብዐው አርድእት "ጌታ ሆይ! አጋንንት በስምህ ተገዙልን።" ማለታቸውን አስቀምጦልናል። (ሉቃ. ፲፥፲፯) ቅዱስ ሐናንያ በበዓለ ዕርገት ተባርኮ በሃምሳኛው ቀንም መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል። በሚያስተምር ጊዜ የሶርያዋን ደማስቆን ማዕከል አድርጐ ነበር። በኋላም አበው ሐዋርያት የዚህች ከተማ የመጀመሪያው ጳጳስ አድርገው ሹመውታል። ጌታ ባረገ በስምንተኛው ዓመት ክርስቲያኖችን ያሰቃይ የነበረው ሳውል (የኋላው ቅዱስ ጳውሎስ) ወደ ደማስቆ የተጓዘው ክርስቲያኖችን በተለይም ቅዱስ ሐናንያን ለማሠር ነበር። ለእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃ ይሆን ዘንድ መብረቅ ዓይኑን አጠፋው። ወዲያውም ጌታችን ሳውልን ወደ ሐናንያ እንዲሔድ ነገረው። ከሦስት ቀናት በኋላ ጌታችን ለሐናንያ ተገልጦ አነጋግሮታል። ሳውል (ጳውሎስ) ወደ ሐናንያ የደረሰው በመሪ ነበር። ሁለቱ እንደተገናኙ ቅዱስ ሐናንያ ሳውልን አስተማረው፣ ፈወሰው፣ አጠመቀው፣ በጐ መንገድንም መራው። በዚህ ምክንያት ቅዱሱ ሐዋርያ የቅዱስ ጳውሎስ የንስሐ አባቱ ይሰኛል። (ሐዋ. ፱፥፩-፲፱) ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሐናንያ ለብዙ ዓመታት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወንጌልን አስተማረ። መከራንም ተቀበለ። በመጨረሻም በዚህ ቀን ክፉዎች ከብዙ ስቃይ በኋላ በድንጋይ ወግረው ገድለውታል። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                              30. ልደተ ዮሐንስ መጥምቅ
                                                ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል። ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል። "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ።" ይላቸዋል። (ሉቃ. ፩፥፮) የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል! እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ ዘጠና (ሰባ አምስት) የዘካርያስ ደግሞ መቶ (ዘጠና) ደርሶ ነበር። ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተእርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ፣ ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. ፵፥፫ ፣ ሚል. ፫፥፩) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው። ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ። ቅድስቲቷ ግን መስከረም ፳፮ ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለስድስት ወራት ራሷን ሠወረች። በስድስተኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች። ሁለቱ ቅዱሳት የእኅትማማች ልጆች ናቸው። የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና ዮሐንስ ደግሞ ገና በማኅጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ)። ከዚህ በኋላ በዚህች ቀን (ሰኔ ፴) ተወልዶ አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል። መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ፦ የቅዱሳኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ፣ በማኅጸን ሳለ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት፣ በበርሃ ያደገና በገዳማዊ ቅድስና ያጌጠ፣ እስራኤልን ለንስሐ ያጠመቀ፣ የጌታችንን መንገድ የጠረገ፣ ጌታውን ያጠመቀና ስለ እውነት አንገቱን የተቆረጠ ታላቅ ሰው ነው። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን፦ ነቢይ፣ ሐዋርያ፣ ሰማዕት፣ ጻድቅ፣ ገዳማዊ፣ መጥምቀ መለኮት፣ ጸያሔ ፍኖት፣ ቃለ ዐዋዲ ብላ ታከብረዋለች። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                            ሐምሌ
                                              2. ሐዋርያው ታዴዎስ(እረፍቱ)
                                                ቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተከተሉበት ሰዓት እድሜአቸው በሦስት ደረጃ የተከፈለ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያሳያል። እንደ ዮሐንስ ወንጌላዊ ያሉት በሃያዎቹ ውስጥ፣ ቅዱስ ታዴዎስን የመሰሉት ደግሞ በሠላሳና በአርባዎቹ ውስጥ የነበሩ ሲሆን እነ ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ በሃምሳዎቹ ውስጥ የሚገኙ ነበሩ። ደቀ መዛሙርቱ ከወጣቶችም፣ ከጐልማሶችም ከአረጋውያንም የተዋቀሩ ነበሩ ማለት ነው። ቅዱስ ታዴዎስ በቀደመ ስሙ ልብድዮስ ይባል የነበረ ሲሆን በአንዳንድ መጻሕፍት ውስጥ (በተለይ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች) ስምዖን እና ይሁዳ እየተባለም ተጠርቷል። ቅዱሱ ጌታችንን ተከትሎ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ሆኖ በፈጣሪው ተመርጦ፣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታ እግር ተምሮ፣ በዕርገቱ ተባርኮ፣ በበዓለ ሃምሳም ሰባ አንድ ልሳናትን ተቀብሎ፣ ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ የበኩሉን አሕጉረ ስብከት ተካፍሎ ዓለምን ዙሯል። ቅዱስ ታዴዎስ አንድ ቀን ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ወደ አንዲት ሃገር ይገባሉ። ታዲያ ለቀናት ያለ ምግብ ወንጌልን ሲሰብኩ ቆይተው ነበርና ደጐቹ ሐዋርያት ራባቸው። ወደ ከተማዋ ሳይገቡ አንድ ሽማግሌ ሲያርስ አይተው ሰላምታን ሰጡትና "እባክህ እርቦናልና አብላን።" አሉት። እርሱም ምንም ወገኑ ከአሕዛብ ቢሆነ አሳዝነውት በሬዎቹን ሳይፈታ እየሮጠ ሔደ። ያን ጊዜ ቅዱስ ታዴዎስ ሊቀ ሐዋርያትን "እርሱ እስኪመጣ ለምን አናርስም።" አለው። ሁለቱ ተነስተው ታዴዎስ ሞፈር፣ ጴጥሮስ ደግሞ ስንዴውን ያዘ። ቅዱሳኑ እየዘሩ ያረሱት ሰውየው ምግብ ይዞ እስኪመጣ አድጐ፣ አፍርቶ፣ እሸት ሆኖ ቆየው። ገበሬው የተደረገውን ተአምራት ባየ ጊዜ ደነገጠ። ሊያመልካቸውም ወደደ። እነርሱ ግን "እኛ የልዑል ባሮች ነን።" ብለው በክርስቶስ ማመንን አስተማሩት። "ልከተላችሁ?" ቢላቸው "የለም! ከእሸቱ ይዘህ ወደ ከተማ ግባና ራት አዘጋጅልን። እኛ እንመጣለን።" አሉት። እርሱ ወደ ቤቱ ሲመለስ አሕዛብ ነገሩን ተረዱ። ተሠብስበውም "እነዚህ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እሳትም ሰይፍም አይበግራቸውም።" ብለው ወደ ከተማ እንዳይገቡ ከበሩ ላይ ራቁቷን የሆነች ዘማ አቆሙ። ቅዱስ ታዴዎስ ገና ከርቀት ስላያት ቀና ብሎ ቅዱስ ሚካኤልን "እርዳን" አለው። ሊቀ መላእክትም ድንገት ወርዶ ዘማዋን ሴት በጸጉሯ በዓየር ላይ ሰቀላት። በከተማዋ ያሉ አሕዛብም ይህንና ሌሎች ተአምራትን አይተው ሁሉም በጌታችን አምነው ተጠመቁ። ለሐዋርያቱም ሰገዱላቸው። አንድ ቀን ግን አንድ ጐረምሳ ባለ ጠጋ ቅዱስ ታዴዎስ "ሀብት ንብረታችሁን መጽውቱ።" ሲል ሰምቶት ዘሎ የሐዋርያውን ጉሮሮ አንቆ ከሞት አድርሶት ነበር። ያን ጊዜ "ጌታዬ! ለካ ሀብታም ከሚጸድቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል ያልክ ለዚህ ነው!" ብሏል። ባለ ጠጋው "እንዴት ይሆናል?" ቢለው መርፌ አሠርቶ ግመሉን ከነ ባለቤቱ በሰው ሁሉ ፊት ሦስት ጊዜ አሳልፎታል። ያም ማለት ጌታችን እንዳለው "በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል።" (ማር. ፲፥፳፫) በዚህ ምክንያትም ያ ክፉ ባለ ጸጋ ወደ ልቡናው ተመልሶ ከቅዱስ ታዴዎስ እግር ሥር ወደቀ። ሐዋርያውም አለው "ሀብትህን ለነዳያን ስጥ። ይህንንም በትር እንካና እየዞርክ ወንጌለ መንግሥትን ስበክ።" ባለ ጸጋውም የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ በክብር ዐርፏል። ቅዱሳኑ ታዴዎስና ጴጥሮስ ግን በሃገሪቱ አብያተ ክርስቲያናትን አንጸው፣ ካህናትን ሹመው፣ ያቺን በዓየር ላይ የሰቀሏትን ዘማም የተባረከች መበለት አድርገው በሌሎች አሕጉራት ወንጌልን ለማዳረስ ወጥተዋል። ቅዱስ ታዴዎስም እስከ እርጅናው ድረስ ለወንጌል ሲተጋ ኑሯል። ጌታችንም በየጊዜው በአካል እየተገለጸ አጽናንቶታል። ከብዙ የድካምና የመከራ ዘመናት በኋላም በዚህች ቀን ዐርፏል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሱ ሐዋርያ በረከት ይክፈለን።
                                              3. አባ ቄርሎስ(እረፍቱ)
                                                ቅዱስ ቄርሎስን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን "ዓምደ ሃይማኖት- የሃይማኖት ምሰሶ" ይሉታል። ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ ሊቁ የተወለደው በእስክንድርያ (ግብጽ) በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። እናቱ የወቅቱ ፓትርያርክ ቅዱስ ቴዎፍሎስ እኅቱ ነበረችና አጎቱ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ወስዶ አሳድጐታል። ገና በልጅነቱ ወደ አባ ሰራብዮን ገዳም ገብቶ ቅዱሳት መጻሕፍትንና ገዳማዊ ሕይወትን ተምሯል። በጾም፣ በጸሎትና በትሕትና የታሸ ነውና ሲማር አንድ ጊዜ ካነበበው በሕሊናው ተስሎ ይቀር ነበር። ቅዱስ ቴዎፍሎስ "ምዕመናንን አስተምርልኝ።" ብሎ ወደ ከተማ አመጣው። መንፈስ ቅዱስ አድሮበታልና ሲያስተምር ወይ ደግሞ መጻሕፍትን ሲያነብ ከምዕመናን ወገን ስንኳን የሚያወራና የሚንቀሳቀስ ቀርቶ የሚቀመጥም አልነበረም። ጣዕመ ስብከቱም ብዙዎችን ለወጠ። ከዚያም በ፬፻፲፪ ዓ.ም አጎቱ የነበረው ፓትርያርክ አባ ቴዎፍሎስ ሲያርፍ ጳጳሳትና ሊቃውንት በአንድነት ቅዱስ ቄርሎስን መረጡ። የእስክንድርያም ሃያ አራተኛ ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ ተሾመ። በዘመኑ ቤተ ክርስቲያን አበራች። በቅድስናው፣ በሊቅነቱ፣ በስብከቱ፣ በድርሰቶቹና በትጋቱ በፍጹም አገለገላት። በወቅቱ ስመ ክፉ መናፍቅ ንስጥሮስ ተነስቶ የእስያ አብያተ ክርስቲያናትን አወካቸው። ትምህርቱ ክርስቶስን "ሁለት አካል፣ ባሕርይ ነው።" (ሎቱ ስብሐት!) የሚል ነበር። በእውነት እንየው ከተባለ ግን ጠቡና ጥላቻው ከድንግል ማርያም ጋር ነበር። ምክንያቱም ጌታችንን ወደ ሁለት የከፈለው እመቤታችንን የአምላክ እናት አይደለሽም ለማለት ነው። (ላቲ ስብሐት!) ነገሩን ቅዱስ ቄርሎስ በሰማ ጊዜ ወዳለበት ሒዶ ቢመክረውም ንስጥሮስ ሊሰማ አልፈለገም። በዚህ ምክንያት በትንሹ ቴዎዶስዮስ (የቁስጥንጥንያ ንጉሥ) ትዕዛዝ በኤፌሶን ታላቅ ጉባኤ እንዲሰበሰብ ሆነ። ይህ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻው የተቀደሰ ጉባዔ ነው። በ፬፻፴፩ ዓ.ም በኤፌሶን ከተማ የመናፍቃኑን ጥርቅም ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና ሁለት መቶ ቅዱሳን ሊቃውንት ተገኙ። የሚገባው ጸሎትና ሱባዔ ከተፈጸመ በኋላ ጉባዔው ተጀመረ። አፈ ጉባዔው ሊቀ ማኅበር ማር (ቅዱስ) ቄርሎስ ነበርና በጉባዔ ፊት ንስጥሮስን ተከራክሮ ረታው። ምላሽም አሳጣው። ከቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቶስ አንድ ባሕርይ መሆኑን ድንግል ማርያምም ወላዲተ አምላክ መሆኗን እየጠቀሰ በምሳሌም እያሳየ አስረዳ። የሰይጣን ማደሪያ ንስጥሮስ ግን እንቢ አላምንም በማለቱ ተወግዞ ተለየ። ቅዱሳን ሊቃውንቱም በቅዱስ ቄርሎስ አርቃቂነት አሥራ ሁለት አንቀጾችን አዘጋጅተው ወደ ዓለም ሁሉ ላኩ። እሊህ አንቀጾች ዛሬም በሊቃውንቱ እጅ አሉ። ይነበባሉ፤ ይተረጎማሉ። ከእነዚህም አንዱ ድንግል ማርያም "ታኦዶኮስ (የእግዚአብሔር እናቱ) ናት።" የሚል ነው። እመቤታችንን፦ የአምላክ እናት፣ ዘላለማዊት ድንግል፣ ፍጽምት፣ ንጽሕትና አማላጅ ብሎ ማመን ለሰማያዊ ርስት የሚያበቃ በጐ ሃይማኖት ነውና። ጉባዔው ከተጠናቀቀ በኋላ ቅዱስ ቄርሎስ ንስጥሮስን ጠርቶ "በድንግል ማርያም እመን። እርሷ ከልጇ ታስታርቅሃለች።" ቢለው በድጋሚ "እንቢ" አለው። ያን ጊዜ ሊቁ "ለአምላክ እናት ያልታዘዘ ምላስህ ላንተም አይታዘዝህ።" ብሎ ረገመው። ወዲያው ምላሱ ተጐልጉሎ ወጥቶ ደረቱ ላይ ወደቀ። እንደ ውሻ እየተዝረከረከ ሒዶ ከወዳጆቹ ጋር ቁሞ ሳለ መሬት ተከፍታ ውጣዋለች። ቅዱስ ቄርሎስ ግን ለሠላሳ ሁለት ዘመናት በመንበሩ ላይ አገልግሎ፣ ፍሬ ትሩፋት አፍርቶ፣ ብዙ ድርሰቶችንም ደርሶ በ፬፻፵፬ ዓ.ም በዚህች ቀን ዐርፏል። ከድርሰቶቹም ቅዳሴው፣ ድርሳነ ቄርሎስና ተረፈ ቄርሎስ ይጠቀሳሉ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቶቻችን ጸሎት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን። ከሊቁም በረከቱን ይክፈለን።
                                              4. ነቢዩ ሶፎንያስ እረፍቱ
                                                5. ጴጥሮስና ጳውሎስ እረፍታቸው
                                                  የዮና ልጅ ስምዖን ጴጥሮስ (ኬፋ) የተባለው በጌታችን ንጹሕ አንደበት ነው። ይሔውም ዓለት (መሰረት) እንደ ማለት ነው። በቤተ ሳይዳ ከወንድሙ እንድርያስ ጋር ዓሣ በማጥመድ አድጐ፣ ሚስት አግብቶ ዕድሜው ሃምሳ ስድስት ሲደርስ ነበር ጌታችን የተቀበለው። በዕድሜውም ሆነ በቅንዐቱ፣ በአስተዋይነቱም መሠረተ ቤተ ክርስቲያን ተብሏል። ለሐዋርያትም አለቃቸው ሆኗል። (ማቴ. ፲፮፥፲፯ ፣ ዮሐ. ፳፩፥፲፭) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተያዘባት ሌሊት ለሠራው ስሕተት ንስሐ ገብቶ ምሳሌም ሆኗል። ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ እረኝነቱ ሐዋርያትን ጠብቆ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ ሲያበቃ ከበዓለ ሃምሳ በኋላም ለሁሉም ሃገረ ስብከት አካፍሏል። ምንም የእርሱ ክፍል ሮሜ ብትሆንም አርድእትን ስለ ማጽናት በሁሉም አሕጉራት ዙሯል። በስተእርጅናው ብዙ መከራዎችን ተቀብሏል። አሕዛብ ግብራቸው እንደ እንስሳ ነውና በአባታችን ላይ ቀልደዋል። እርሱ ግን ሁሉንም ታግሷል። የቅዱሱን ታሪክ ለመናገር ከመብዛቱ የተነሳ ይከብዳልና ልቡና ያለው ሰው ሊቃውንትን ሊጠይቅ እንደሚገባ እመክራለሁ። ቅዱስ ጴጥሮስ መልካሙን ገድል ተጋድሎ በ፷፮ ዓ.ም የኔሮን ቄሳር ወታደሮች ሲሰቅሉት ለመናቸው። "እባካችሁን? እኔ እንደ ጌታዬ ሆኜ መሰቀል አይገባኝም።" አላቸው። እነርሱም ዘቅዝቀው ሰቅለው ገድለውታል። በበጐ እረኝነቱም የማታልፈውን ርስት ከነመክፈቻዋ ተቀብሏል። በሰማዕትነት ሲያርፍም ዕድሜው ወደ ሰማንያ ስምንት አካባቢ ደርሶ ነበር። የቅዱስ ጴጥሮስ መጠሪያዎች ፩.ሊቀ ሐዋርያት ፪.ሊቀ ኖሎት (የእረኞች/ሐዋርያት/ አለቃ) ፫.መሠረተ ቤተ ክርስቲያን ፬.ኰኩሐ ሃይማኖት (የሃይማኖት ዐለት) ፭.አርሳይሮስ (የዓለም ሁሉ ፓትርያርክ) ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                7. አጋእዝተ ዓለም ስላሴ በአብርሃም ቤት
                                                  በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት) በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት) የሌለበት የዘላለም አምላክ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው። አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስትነት፤ በባሕርይ፣ በሕልውናና በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው። በዚህ ጊዜ ተገኙ በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም። መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና። ርኅሩኀን ናቸውና በእናት ሥርዓት "ቅድስት ሥላሴ" እንላቸዋለን። የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም። የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል። በቤቱም መጥተው ያድራሉ። ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም። አባታችን ቅዱስ አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል። ሥላሴ አኀዜ ዓለም (ዓለምን በእጁ የያዘ) ነው። ነገር ግን በፍቅር ለሚሻው በፍቅር ይመጣል። አባታችን አብርሃም በዘጠና ዘጠኝ ዓመቱ እናታችን ሣራ በሰማንያ ዘጠኝ ዓመቷ ሥላሴን በድንኳናቸው አስተናገዱ። አብርሃም እግራቸውን አጠበ። (ወይ መታደል!) በጀርባውም አዘላቸው። (ድንቅ አባት!) ምሳቸውንም አቀረበላቸው። እንደሚበሉ ሆኑለት። በዚያው ዕለትም የይስሐቅን መወለድ አበሠሩት፤ ቅድስት ሣራ ሳቀች። እንደ ዘንድሮ ወገኖቻችን የማሾፍ አይደለም። ደስታና ጉጉት የፈጠረው እንጂ። ሥላሴ "ምንት አስሐቃ ለሣራ በባሕቲታ" ብለው ነበርና በዚህም ምክንያት ነው "ይስሐቅ" የተባለው። ሥላሴን ያስተናገደች ድንኳን (ሐይመት) የድንግል እመቤታችን ማርያም ምሳሌ ናት። በድንግል ላይ አብ ለአጽንኦ፣ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፣ ወልድ በተለየ አካሉ ለሥጋዌ በእርሷ ላይ አርፈዋል (አድረዋልና)። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                7. አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እረፍቱ
                                                  ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅና ጻድቅ የተወለደው ወሎ ጋስጫ ውስጥ በ፲፫፻፶፰ ዓ.ም ነው። ከልጅነቱ ትምህርት አልገባህ ቢለውም በልቡናው ግን ቅን እና ታዛዥ ነበር። መምህሩ "ትምህርት አይገባውምና ውሰዱት።" ቢላቸው "የእግዚአብሔር ነውና ያገልግላችሁ።" ብለው መለሱት። መገፋቱን የተመለከተ አባ ጊዮርጊስ እመቤታችንን ከልቡ ይወዳት ነበረና ይማጸናት ገባ። ቀን ቀን ገዳሙን ሲረዳ፣ እሕል ሲፈጭና ሲከካ፣ ላቡንም ሲያፈስ ውሎ ሌሊት ደግሞ ሲጸልይ ያነጋ ነበር። ድንግል እመቤታችን ጸሎቱን ሰምታለችና ቅዱስ ዑራኤልን አስከትላ መጣችለት። በንጹሐት እጆቿ ባርካው ምሥጢርንም ነገረችው። "ወነገረቶ ሐምስተ ቃላተ" እንዲል። ጽዋዐ ልቡናን አጠጥታው ተሠወረችው። ከዚህች ሰዓት ጀምሮ አባ ጊዮርጊስ ፍጹም ተለወጠ። በጽድቁ ላይ የሊቅነትን ካባ ደረበ። ቅዱሳት መጻሕፍትን ይተነትናቸው መናፍቃንንም ምላሽ ያሳጣቸው ገባ። የተረጐማቸውና ያተታቸውን ሳይጨምር አርባ አንድ ድርሰቶችን ደረሰ። (መጽሐፈ ሰዓታት፣ መጽሐፈ ምሥጢር፣ አርጋኖን፣ ኆኅተ ብርሃን፣ ውዳሴ መስቀል፣ ወዘተ የእርሱ ድርሰቶች ናቸው።) ስለ ሃይማኖትም ጠበቃ ነበር። ስለ ቅድስናውና ውለታው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ትጠራዋለች። ፩.ሊቀ ሊቃውንት ፪.በላዔ መጻሕፍት ፫.ዓምደ ሃይማኖት ፬.ዳግማዊ ቄርሎስ ፭.ጠቢብ ወማዕምር ጻድቁ ሊቅ በተወለደ በስልሳ ዓመቱ በ፲፬፻፲፰ ዓ.ም በዚህች ቀን ዐርፏል። አባ ጊዮርጊስ የተወለደውም ያረፈውም ሐምሌ ፯ ቀን ነው። የሥላሴ ቸርነት፣ የአብርሃም ደግነት፣ የአበው አባ ጊዮርጊስና አባ ሲኖዳ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን።
                                                8. አባ ኪሮስ
                                                  የጻድቁን ስም የሚጠራ አፍ ንዑድ ነው፤ ክቡር ነው። በእውነት የቅዱሱን አባት ክብር ለማግኘት መፋጠን ይበጃል። አቡነ ኪሮስ የተወለዱት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን ወላጆቻቸው ነገሥታት ናቸው። ተወልደው ባደጉባት ሃገር ቁስጥንጥንያ ገና በልጅነት ምቾት ሳያሳሳቸው መጻሕፍትንና ትሕርምትን ተምረዋል። ወንድማቸው (ታላቁ ቴዎዶስዮስ) በነገሠባቸው የመጀመሪያ ዓመታት በቤተ መንግሥቱ ዙሪያ ግፍ በዝቶ ነበርና አቡነ ኪሮስ ከኃጢአት ለመራቅና ለጌታ ለመገዛት ከከተማው ጠፍተው አሕጉር አቋርጠው ወደ ግብጽ (ገዳመ አስቄጥስ) መጡ። እርሳቸውን ለመፈለግ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም። ይባስ ብሎ የንጉሡ ልጅ ገብረ ክርስቶስ ሙሽርነቱን ጥሎ ወደ ሌላ ሃገር መነነ። "የቅኖች ትውልድ ይባረካል።" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት። አቡነ ኪሮስ ለሙሽራው ገብረ ክርስቶስ አጎቱ ናቸው። አቡነ ኪሮስ በገዳም ውስጥ የታላቁ አቡነ በብኑዳ ደቀ መዝሙር ሆነው ለዘመናት ቆይተዋል። ቅዱስ በብኑዳን አንበሳ በበላው ጊዜ በጣም አዝነው "ለምን ጌታ ሆይ?" በሚል መሬት ላይ ወድቀው አለቀሱ። "ምክንያቱ ካልተነገረኝ አልነሳም።" ብለው ከወደቁበት መሬት ላይ ሳይነሱ ለአርባ ዓመታት አልቅሰዋል። በዚህ ምክንያት ግማሹ አካላቸው አፈር ሆኖ ሣር በቅሎበታል። ጌታችን ተገልጦ ምክንያቱን ነግሯቸዋል። አካላቸውንም እንደነበረ መልሶላቸዋል። አንድ ቀን ጻድቁ ለቅዱስ በብኑዳ ሞት ምክንያት የሆነው መነኮስ ታንቆ መሞቱን ሰምተው በጣም አዘኑ። ሱባዔ ገብተው፣ ፍጹም አልቅሰው፣ ከጌታም አማልደው፣ የዚያን ኃጥእ ነፍስ ከሲዖል አውጥተዋል። በሌላ ጊዜ ደግሞ ኃጥአን የሞሉበት አንድ ገዳም በግብጽ ነበርና መቅሰፍት ወርዶ ሁሉንም በአንድ ቀን ሲያጠፋቸው አዩ። ጻድቁ በዚህም ምክንያት ለሠላሳ ዓመታት አልቅሰው፣ ሙታኑን አስነስተው፣ ንስሐ ሰጥተው፣ ገዳሙን የጻድቃን ሕይወታቸውንም የፍቅር አድርገውታል። ጻድቁ እመቤታችንን ከመውደዳቸው የተነሳ በሥዕሏ ፊት አብዝተው ይሰግዱና ያለቅሱ ነበር። እመ አምላክም ተገልጣ ትባርካቸው ነበር። ከዚህ በኋላ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ሒደው ለሃምሳ ሰባት ዓመታት ማንንም ሳያዩ ተጋደሉ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና።) በየቀኑ ይጐበኛቸው ቁጭ ብሎም ያወራቸው ነበር። በመጨረሻም በዚህች ቀን ጌታ አእላፍ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን፣ ድንግል እመቤታችንና ቅዱስ ዳዊትን አስከትሎ ወረደ። ቅዱስ ዳዊት ቀርቦ እያጫወታቸው በበገናው እየደረደረላቸው ከዝማሬው ጣዕም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው በፍቅር ተለየች። ጌታችንም ታቅፎ ስሞ ይዟቸው አረገ። ሥጋቸውን አባ ባውማ ቀበሩት። የአቡነ ኪሮስ ቁመታቸው ቀጥ ያለ ጽሕማቸውም የተንዠረገገ ነበር። እድሜአቸውን ግን መገመት የሚቻል አይመስለኝም። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                10. ሓዋርያው ናትናኤል እረፍቱ
                                                  በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ዘግይቶ ሰማዕትነትን የተቀበለ ይህ ቅዱስ ሐዋርያ ነው። ቅዱሱ ሐዋርያ የተወለደው ከእስራኤላውያን ወላጆቹ ጌታችን በተወለደበት ዘመን አካባቢ ነው። ይህ በምን ይታወቃል ቢሉ እርሱ ሕፃን እያለ ሔሮድስ መቶ አርባ አራት ሺህ ሕፃናትን ሲፈጅ እርሱ ግን በእግዚአብሔር ጥበብ ተርፏል። እናቱ በቅርጫት ውስጥ አድርጋ የበለስ ዛፍ ላይ አስቀምጣው ተደብቃ ታጠባው ነበር። ለሐዋርያው ወላጆቹ ያወጡለት ስም ስምዖን ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ናትናኤል ብሎታል። በባልንጀሮቹ ሐዋርያት ደግሞ የቃናው ስምዖን (ገሊላ ቃና አካባቢ ስላደገ) አንዳንዴም ቀናተኛው ስምዖን ይሉት ነበር። ምሑረ ኦሪት ነበርና ዘወትር ለሕግ ይቀና ነበር። በገሊላ ቃና ሰርግ የደገሰው ዶኪማስ የቅዱስ ናትናኤል የአጎት ልጅ ነው። ጌታና ደቀ መዛሙርቱን ዶኪማስ የጠራበት አንዱ ምክንያትም ይሔው ነው። ቅዱስ ናትናኤል ኦሪትን ከገማልያል ተምሮ ከበለስ ቁጭ ብሎ ይተክዝ ነበር። "መሲሕ ምነው ቀረህ?" እያለም ይተክዝ ነበር። ማዕምረ ኅቡዓት አምላካችን ክርስቶስ ይህንን አውቆ በፊልጶስ አማካኝነት ጠርቶታል። ናትናኤል ለጊዜው ተከራክሮ ነበር። በኋላ ግን የጌታችንን ማንነት በደቂቃዎች ተረድቶ አምኗል። ጌታችንም "ክዳት ሽንገላ በልቡ ውስጥ የሌለበት ንጹሕ እስራኤላዊ" ሲል አመስግኖታል። ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ከጌታችን እግር ሥር ምሥጢረ መንግሥተ ሰማያትን ተምሮ በጸጋ መንፈስ ቅዱስም ሰክሮ ብዙ አሕዛብን ከጨለማ (ጣኦት አምልኮ) ወደ ብርሃን (አሚነ ክርስቶስ) መልሷል። እጅግ ብዙ መከራንም ተቀብሏል። የጌታችን ወንድም የተባለ ቅዱስ ያዕቆብ በአይሁድ ከተገደለ በኋላም ቅዱስ ናትናኤል የኢየሩሳሌም ሁለተኛ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ አገልግሏል። ከአይሁድም ዘንድ ብዙ መከራ ደርሶበታል። በመጨረሻም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት አልፏል። በገድለ ሐዋርያት ላይ እንደተጠቀሰው ቅዱሱ ሰማዕት የሆነው በመቶ ሃምሳ ዓመቱ ነው። ያ ማለት ደግሞ ከሐዋርያት አባቶች በመጨረሻ ያረፈው እርሱ ነው ያሰኛል። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                15. ኤፍሬም ሶርያዊው እረፍቱ
                                                  እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ቅዱስ ኤፍሬም የተወለደው ንጽቢን በምትባል የሶርያ ግዛት ውስጥ በ፪፻፺፰ (፫፻፮) ዓ.ም ነው። ወላጆቹ በክርስቶስ የማያምኑ አላውያን ነበሩ። (ምንም አንዳንድ ምንጮች ክርስቲያኖች ነበሩ ቢሉም።) ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ንጽቢን ጵጵስናን የተሾመ ቅዱስ ያዕቆብ የሚባል ታላቅ ሰው ነበር። የሰማዕትነት፣ የሐዋርያነት፣ የጻድቅነትና የሊቅነት ግብር ያለው አባት ነው። ታዲያ ቅዱስ ኤፍሬም ይሔ አባት ሁሌ ሲያስተምር ይሰማው ነበርና በስብከቱ ተማርኮ ደቀ መዝሙሩ ለመሆን በቃ። ቅዱስ ኤፍሬም በቅዱስ ያዕቆብ እጅ ከተጠመቀ በኋላ ሙሉ የወጣትነት ጊዜውን ያሳለፈው በትምህርት ነው። የሚገርመው መምህሩ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን እመቤታችን ድንግል ማርያምን በፍጹም ልቡ የሚወድና ጠርቷት የማይጠግብ አባት ነውና ለልጁ ለቅዱስ ኤፍሬም ይህንኑ አጥብቆ አስተምሮታል። ቅዱስ ኤፍሬም ክርስትናን ሲመረምር የእመቤታችን ፍቅር ይበዛለት ጀመር። ምክንያቱም እመ ብርሃንን ሳይወዱ ክርስትና የለምና። እንደ እርሱ የሚወዳት የለም እስኪባል ድረስ ያገለግላት ይገዛላትም ገባ። እንዲህ እንደ ዛሬ የድንግል ማርያም ምስጋና በአንደበት እንጂ በመጽሐፍ አይገኝም ነበር። እርሱ ግን ከወንጌለ ሉቃስ በስድስተኛው ወርን (ይዌድስዋን) እና ጸሎተ ማርያምን(ታዐብዮን) አውጥቶ በየዕለቱ በዕድሜዋ ልክ ስልሳ አራት ስልሳ አራት ጊዜ ያመሰግናት ነበር። በእንዲህ ያለ ግብር እያለ አርዮስ በመካዱ እርሱን ለማውገዝና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለማጽናት በ፫፻፲፯ (፫፻፳፭) ዓ.ም ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት በኒቅያ ሲሰበሰቡ አንዱ መምህረ ኤፍሬም ቅዱስ ያዕቆብ ነበር። በዚህ ምክንያት ቅዱስ ኤፍሬም ከሊቃውንቱ ትምህርትና በረከትን አግኝቷል። ከጉባዔ መልስ መንገድ ላይ በራእይ የብርሃን ምሰሶ አይቶ "ጌታ ሆይ! ምንድን ነው?" ብሎ ቢጠይቅ "ይህማ ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ነው።" አለው። እርሱም መምህሩን ቅዱስ ያዕቆብን ተሰናብቶ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ (ቂሣርያ) ወረደ። ተገናኝተውም በአንድ ሌሊት ቋንቋ ተገልጦላቸው ሲጨዋወቱ አድረዋል። በቦታው ብዙ ተአምራት ተደርጓል። ቅዱስ ኤፍሬም ከታላቁ ባስልዮስ ከተማረ በኋላ ሃገረ ስብከት ተሰጥቶት ያስተምር ጀመር። ሁል ጊዜ ታዲያ ጸሎቱ ይሔው ነበር። "እመቤቴ ሆይ! ምስጋናሽ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ባሕር አሽዋ በዝቶልኝ እንደ እንጀራ ተመግቤው፣ እንደ ውኃ ጠጥቼው፣ እንደ ልብስም ተጐናጽፌው" እያለ ይመኝ ነበር። አፍጣኒተ ረድኤት ፈጻሚተ ፈቃድ እመ ብርሃንም በገሃድ ተገልጻ የልቡን ፈቃድ ፈጸመችለት። ዛሬ ጸጋ በረከት የምናገኝበትን ውዳሴ ማርያምን ደረሰላት። ሲደርስላትም እርሷ አእላፍ መላእክትን ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትላ ወርዳ በፊቱም ተቀምጣ ሲሆን እርሱ ደግሞ ባጭር ታጥቆ፣ በፊቷ ቆሞ፣ በመንፈስ ቅዱስም ተቃኝቶ ነው። ውዳሴዋን በሰባት ቀናት ከደረሰላት በኋላ በብርሃን መስቀል ባርካው ሊቀ ሊቃውንትም እንዲሆን ምሥጢር ገልጣለት ዐረገች። ከዚህ በኋላ በምሥጢር ባሕር ውስጥ ዋኝቶ አሥራ አራት ሺህ ድርሰቶችንም ደርሷል። ዛሬ ሶርያ ውስጥ የምንሰማውን ዜማም የደረሰው ይህ ቅዱስ ነው። እንዲያውም አንድ ቀን የምሥጢር ማዕበል ቢያማታው "አሃዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ" ብሎ ጸልዩዋል። "የጸጋህን ማዕበል ያዝልኝ።" እንደ ማለት ነው። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በመጨረሻ ሕይወቱ ተክሪት በምትባል ሃገር ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሹሟል። በጣፋጭ ስብከቱ ብዙዎችን ካለማመን መልሷል። የምዕመናንንም ሕይወት አጣፍጧል። ለመናፍቃንና ለአርዮሳውያን ግን የማይጋፉት ግድግዳ ሆኖባቸው ኑሯል። በዘመኑም ብዙ ተጋድሎ አፍርቷል። ተአምራትንም ሠርቷል። በተወለደ በስልሳ ሰባት ዓመቱ በ፫፻፷፭ (፫፻፸፫) ዓ.ም ዐርፎ ተቀብሯል። ቅዱሱ ለሶርያ ብቻ ሳይሆን እመቤታችንን ለምንወድ የዓለም ክርስቲያኖች ሁሉ ሞገሳችን ሆኗል። ስለዚህም እንዲህ እያልን እንጠራዋለን፦ ፩.ቅዱስ ኤፍሬም ፪.ማሪ ኤፍሬም ፫.አፈ በረከት ኤፍሬም ፬.ሊቀ ሊቃውንት ኤፍሬም ፭.ጥዑመ ልሳን ኤፍሬም ፮.አበ ምዕመናን ኤፍሬም ፯.ርቱዐ ሃይማኖት ኤፍሬም አባታችን አንተ ነህ። ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ለቅዱስ ኤፍሬም የሰጠሽውን ጸጋውን፣ ክብሩን፣ አእምሮውን፣ ለብዎውን በልቡናችን ሳይብን፤ አሳድሪብን። አሜን። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                16. ወንጌላዊው ዮሐንስ እረፍቱ
                                                  ቅዱሱ "ወንጌሉ ዘወርቅ" እየተባለ የሚጠራው ከሌሎች ዮሐንስ ከሚባሉ ቅዱሳን ለመለየት ቢሆንም ዋናው ምክንያት ግን እድሜ ልኩን የሚያነበው፣ ከእጁ የማይለየውና አቅፎት የሚተኛ በወርቅ የተለበጠ ወንጌል ስለ ነበረው ነው። የቅዱስ ዮሐንስ ታሪኩ ከመርዓዊ (ሙሽራው) ገብረ ክርስቶስ እና ከቅዱስ ሙሴ ሮማዊ ጋር ተመሳሳይነት አለው። ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ በሮም ግዛት ሥር የሚኖሩ አጥራብዮስና ብዱራ የሚባሉ ደጋግ ክርስቲያኖች ነበሩ። እግዚአብሔር በቀደሰው ትዳር የሚኖሩና ነዳያንን የሚዘከሩ ነበሩና ይህንን ቅዱስ ወለዱ። ስሙን ዮሐንስ ብለው እንደሚገባም አሳድገው ምሥጢረ መንግሥተ ሰማያትን እንዲረዳ ለመምህር ሰጡት። ቅዱስ ዮሐንስ ከመምህሩ ዘንድ ቁጭ ብሎ መጻሕፍተ ቤተ ክርስቲያንን ተማረ። ለወላጆቹ ቅንና ታዛዥ ነበርና አባቱ "ልጄ! የምትፈልገውን ጠይቀኝ። ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?" አለው። ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድሮ እኛን የሚያምረን ሁሉ አላሰኘውም። አባቱን "ቅዱስ ወንጌልን ግዛልኝ፤ በወርቅም አስለብጠው።" አለው። አባትም የተባለውን ፈጸመ። ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ከዚህ ዓለም ተለይቶ እስካረፈባት ቀን ድረስ ቅዱስ ዮሐንስና የወርቅ ወንጌሉ ተለያይተው አያውቁም። ሁሌም ያለመታከት ያነበዋል። ሲቀመጥም፣ ሲነሳም፣ ሲሔድም፣ ሲተኛም አብሮት ነበር። ቅዱስ ዮሐንስ ወጣት በሆነ ጊዜ ወላጆቹ ይድሩት ዘንድ ተዘጋጁ። ልብሰ መርዐም (የሙሽራ ልብስ) አዘጋጁ። በዚያው ሰሞን ግን አንድ እንግዳ መነኮስ ወደ ቤታቸው መጥቶ ያድራል። በዚያች ሌሊት መነኮሱ በጨዋታ መካከል ስለ ቅዱሳን መነኮሳት ተጋድሎና ክብር ነገረው። የሰማው ነገር ልቡናውን የማረከው ቅዱስ ዮሐንስ ከዚያች ቀን ጀምሮ ወደ ፈጣሪው ይለምን ነበር። አንድ ቀን ግን ያ መነኮስ በድጋሚ መጥቶ አደረ። ቅዱስ ዮሐንስ መነኮሱን ወደ ገዳም እንዲወስደው ቢጠይቀው "አይሆንም አባትህ ያዝንብኛል።" አለው። ቅዱሱ ግን "በእግዚአብሔር ስም አማጽኜሃለሁ።" ስላለው ሁለቱም በሌሊት ወጥተው ወደ ገዳም ሔዱ። አበ ምኔቱ "ልጄ! የበርሃውን መከራ አትችለውም ይቅርብህ።" ቢለውም "አባቴ! አይድከሙ ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር አይለየኝም።'' ስላላቸው እንደሚገባ ፈትነው አመንኩሰውታል። ቅዱስ ዮሐንስ ከመነኮሰ በኋላ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደትና በትሕርምት ያሳየው ተጋድሎ በርካቶችን አስደነቀ። ለሥጋው ቦታ አልሰጣትምና በወጣትነቱ አካሉ ረገፈ። ቆዳውና አካሉም ተገናኘ። ሥጋውን አድርቆ ነፍሱን አለመለማት። በእንዲህ ያለ ሕይወት ለሰባት ዓመታት ከተጋደለ በኋላ በራእይ "ወደ ወላጆችህ ተመለስ።" እያለ ሦስት ጊዜ አናገረው። ቅዱስ ዮሐንስ ወደ አበ ምኔቱ ሒዶ ቢጠይቀው "ራእዩ ከእግዚአብሔር ነው።" ብሎ ወደ ቤተሰቦቹ አሰናበተው። ቅዱስ ዮሐንስ በላዩ ላይ የነበረችውን ልብስ በመንገድ ለነዳይ ሰጥቶ በፈንታው ቆሻሻ ጨርቅ ለብሶ ከወላጆቹ በር ላይ ለመነ። "እባካችሁ አስጠጉኝ።" አላቸው። ወላጆቹ በጭራሽ ሊለዩት አልቻሉም። ነገር ግን አሳዝኗቸዋልና በበራቸው አካባቢ ትንሽ ቤት ሠሩለት። በዚያች በዓት ውስጥ እንዳስለመደ በትጋት ለሰባት ዓመታት ተጋደለ። በእነዚህ ዓመታት እንኳን ሌላው ሰው ወላጆቹም ቢሆኑ ፍርፋሪ ከመስጠት በቀር አይቀርቡትም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ "ይሸተናል" የሚል ነበር። በመጨረሻም መልአከ እግዚአብሔር ከሰማይ ወርዶ "ከሰባት ቀናት በኋላ ታርፋለህ።" አለው። እናቱን ጠርቶ "አንድ ነገር ልለምንሽ።" አላት:: "እሺ" አለችው። "ከሞትኩ በኋላ በለበስኳት ጨርቅ እንድትገንዙኝ በበዓቴ ውስጥም እንድትቀብሩኝ።" አላትና የወርቅ ወንጌሉን አውጥቶ ሰጣት። ያን ጊዜ አባቱም ደርሶ ነበርና ደነገጡ። የወርቅ ወንጌሉን ለዩት። ልጃቸውን ግን መለየት አልቻሉምና እያለቀሱ ስለ ልጃቸው የሚያውቀው ካለ እንዲነግራቸው ለመኑት። እርሱም "ልጃችሁ ዮሐንስ እኔ ነኝ።" አላቸው። በዚያች ቅጽበት ወላጆቹ የሰሙትን ማመን አልቻሉም። በፍጹም ዋይታ እየጮሁ አለቀሱ። ለቅሷቸውን የሰሙ ሁሉ ተሰበሰቡ። ለሰባት ቀናት እኩሉ እያለቀሰ እኩሉ እየተባረከ በዓቱን ከበው ሰነበቱ። በሰባተኛው ቀን መልአኩ መጥቶ በክብር ነፍሱን ተቀበለ። እናቱ የልጇን አደራ ረስታ (እርሷስ መልካም አደረግሁ ብላ ነው።) ለሠርጉ ባዘጋጀችው የወርቅ ልብስ ገነዘችው። ወዲያው ግን በጽኑ ታመመች። አባት ግን ፈጠን ብሎ በዚያች ጨርቅ ገንዞ በበዓቱ ውስጥ ቀበረው። ያን ጊዜ እናት ፈጥና ዳነች። ከቅዱሱ መቃብርም ብዙ ተአምራትና ፈውስ ተደርጓል። ቸሩ አምላካችን ከቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ ጸጋ በረከትን ይክፈለን።
                                                18. የጻድቁ የዮሴፍ ልጅ ሐዋርያው ያዕቆብ እረፍቱ
                                                  ይህ ቅዱስ ሐዋርያ በአባቶቻችን ሐዋርያት መካከል ትልቅ ሞገስ የነበረውና "የጌታችን ወንድም" ተብሎ የተጠራ ነው። ቅዱስ ያዕቆብ ወላጅ አባቱ አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ (የእመቤታችን ጠባቂ) ሲሆን በልጅነቱ የሞተችው እናቱ ደግሞ ማርያም ትባላለች። በቤት ውስጥም ስምዖን፣ ዮሳና ይሁዳ የተባሉ ወንድሞችና ሰሎሜ የምትባል እኅትም ነበረችው። እናቱ ማርያም ከሞተች በኋላ ዕጓለ ማውታ (ድሃ አደግ) ሆኖ ነበር። ነገር ግን በፈቃደ እግዚአብሔር አረጋዊ ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከቤተ መቅደስ ሊጠብቃት (ሊያገለግላት) ተቀብሎ ሲመጣ ያ ቤተሰብ ተቀየረ። የበረከት፣ የምሕረትና የሰላም እመቤት የአምላክ እናቱ ገብታለችና ያ የሐዘን ቤት ደስታ ሞላው። እመ ብርሃን ግን ገና ወደ ዮሴፍ ልጆች ስትደርስ አለቀሰች። የአክስቷ ልጆች የሚንከባከባቸው አጥተው ቆሽሸው ነበር። በተለይ ደግሞ ትንሹ ቅዱስ ያዕቆብ ያሳዝን ነበር። እመ ብርሃን ማረፍ አልፈለገችም። ወዲያው ማድጋ አንስታ ወደ ምንጭ ወርዳ ውኃ አምጥታ የሕፃኑን ገላ አጠበችው። (በአምላክ እናት የታጠበ ሰውነት ምስጋና በጸጋ ይገባዋል።) እመቤታችን ጌታ ከመወለዱ በፊት ለዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ከተወለደ በኋላ ደግሞ ለሁለት ዓመታት ሕፃኑን ያዕቆብን ተንከባከበችው። ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ግን ድንግል ማርያም አምላክ ልጇን ይዛ ተሰዳለችና ተለያዩ። ከስደት መልስ ግን ለሃያ አምስት ዓመታት ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ጋር ሲያድግ ወላጅ እናቱ ትዝ ብላው አታውቅም። አማናዊቷ እናት ከጐኑ ነበረችና። ሊቃውንት እንደ ነገሩን እመቤታችን ለቅዱስ ያዕቆብ ያልሰጠችው ነገር ቢኖር ሐሊበ ድንግልናዌ (የድንግልና ወተትን) ብቻ ነው። ስለዚህም፦ "እመ ያዕቆብ በጸጋ ማርያም ንግሥተ ኩሉ" ይላል መጽሐፍ። (መልክዐ ስዕል) ቅዱስ ያዕቆብ "የጌታ ወንድም" ተብሎ በተደጋጋሚ በሐዲስ ኪዳን ተጠርቷል። ለዚህም ምክንያቱ ፩.ለሠላሳ ዓመታት ሳይነጣጠሉ አብረው በማደጋቸው፣ ፪.የጌታችን የሥጋ አያቱ (የቅድስት ሐና) የእኅት ልጅ በመሆኑ፣ ፫.በዮሴፍ በኩልም የአንድ ቅድመ አያት ልጆች በመሆናቸው፣ ፬.ጌታችን ከትኅትናው የተነሳ ደቀ መዛሙርቱን "ወንድሞች" ይላቸው ስለ ነበር ነው። (ሥጋቸውን ተዋሕዶ ተገኝቷልና።) ራሱ ቅዱስ ያዕቆብ ግን "የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ነኝ።" ብሎ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት ገልጧል። (ያዕ. ፩፥፩) ቅዱስ ያዕቆብ ጌታችን ሲያስተምር ተከተለው። ከሰባ ሁለቱ አርድእት ተቆጠረ። ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን ተማረ። ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንግል ማርያምና ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ሆኖ "የጌታን ትንሣኤ ሳላይ እህል አልቀምስም።" ብሎ ማክፈልን አስተማረ። መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ወንጌልን አስተማረ። የኢየሩሳሌም የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ሆኖ አገለገለ። በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት የሐዋርያት ሲኖዶሶችን በሊቀ መንበርነት መራ። ሙታንን አስንስቶ፣ ድውያንን ፈውሶ፣ የመካኖችን ማኅጸን ከፍቶ፣ አጋንንትንም አስወጥቶ ብዙ ተአምራትን ሠራ። እጅግ ብዙ አይሁዳውያንን ወደ አሚነ ክርስቶስ መልሶ መልካሙን ገድል ተጋደለ። በመጨረሻ ዘመኑ ያላመኑ የአይሁድ አለቆች ወደ ቤቱ ተሰብስበው "የናዝሬቱ ኢየሱስ ማነው? የማንስ ልጅ ነው?" ሲሉ ጠየቁት። እነርሱ ሰይጣን በሰለጠነበት ልቡናቸው "የዮሴፍ ልጅ ነው፤ የእኔም ወንድሜ ነው።" እንዲላቸው ጠብቀው ነበር። (ሎቱ ስብሐት ወአኮቴት) በልቡናቸው ያሰቡትን ተንኮል የተረዳው ሐዋርያ ወደ ቤቱ ጣራ ወጥቶ መናገር ጀመረ። "ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ አምላክ፣ ወልደ አምላክ፣ ወልደ አብ፣ ወልደ ማርያም፣ ሥግው ቃል፣ እግዚአብሔር ነው። እኔም ፍጡሩና ባሪያው እንጂ እንደምታስቡት ወንድሙ አይደለሁም።" አላቸው። ንዴታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉት አይሁድ ከላይ ወጥተው ወደ መሬት ወረወሩት። በገድል የተቀጠቀጠ አካሉንም እየተፈራረቁ ደበደቡት። አንዱ ግን ከእንጨት የተሠራ ትልቅ ገንዳ አምጥቶ የቅዱሱን ራስ ደጋግሞ መታው። ጭንቅላቱም እንዳልነበር ሆነ። ሰማዕቱ ሐዋርያ ቅዱስ ያዕቆብ ወደ ወደደው ክርስቶስ በዚህች ቀን ሔደ። ቅዱሱ ሐዋርያ ያዕቆብ ቤቱን እንደ ቤተ መቅደስ አበው ሐዋርያት ይጠቀሙባት ነበር። በመላ ዘመኑ የሚያገድፍ ነገር (ጥሉላት) ቀምሶ፣ ጸጉሩን ተላጭቶ፣ ገላውን ታጥቦና ልብሱን ቀይሮ አያውቅም። "ወዝንቱ ጻድቅ እኅወ እግዚእነ ኢያብአ ውስተ አፉሁ ሥጋ ወወይነ ወኢገብረ ሎቱ ክልኤተ ክዳነ" እንዲል። ከጾም፣ ከጸሎትና ከመቆሙ ብዛትም እግሩ አብጦ አላራምድህ ብሎት ነበር። ስለዚህም አበው "ጻድቁ (ገዳማዊው) ሐዋርያ" ይሉታል። ቅዱሱ ሐዋርያ "የያዕቆብ መልእክት" የሚለውን ባለ አምስት ምዕራፍ መልእክት ጽፏል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሙ ይባል ዘንድ ካደለው ሐዋርያ በረከትን ያድለን። በምልጃውም ምሕረትን ይላክልን።
                                                19. በዓለ ቅዱስ ገብርኤል ቂርቆስና እየሉጣን ከእሳት ያዳነበት ቀን ነው/ቁልቢ ገብርኤል/
                                                  ቅድስት ኢየሉጣ እናታችን በዘመነ ሰማዕታት ከነበሩና በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳት አንዷ ናት። በወቅቱ ቅዱስ ቂርቆስ የሚባል ደግ ልጅ ወልዳ ባሏ ባለመኖሩ በመበለትነት ትኖር ነበር። የዚያ ዘመን ክርስቲያኖች ለክርስቶስ የነበራቸው ፍቅር ከመነገር በላይ ነው። በዚያው ልክ ደግሞ መከራው በጸጉራቸው ቁጥር ልክ ነበር። ከሮም ግዛት በአንዱ ከቅዱስ ልጇ ጋር የምትኖረው ቅድስት ኢየሉጣ የስደቱ ዘመን ሲመጣ እርሷም እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ተሰደደች። እስክንድሮስ የተባለው ከሃዲ ንጉሥ ግን ያለችበት ድረስ ተከትሎ እንድትያዝና እንድትቀርብ አደረገ። ወዲያውም "ስምሽ ማን ይባላል?" ቢላት "ክርስቲያን እባላለሁ።" አለችው። ንጉሡ ተቆጣ። "መዋቲ ስሜን ከፈለክ ኢየሉጣ ይባላል።" አለችው። ንጉሡ መልሶ "አሁን ለጣዖት ካልሠዋሽ ሲጀመር ስቃይ ቀጥሎም ሞት ይጠብቅሻል።" ቢላት ቅድስቲቱ መልሳ "በከተማ ውስጥ የሦስት ዓመት ሕፃን አለና እርሱን አምጣው። ማንን ማምለክ እንዳለብን ይነግረናል።" አለችው። አስፈልጐ ቅዱስ ቂርቆስን አስመጣው። "ስምህ ማን ይባላል?" አለ ንጉሡ። "ከማይደፈርስ ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ ጥሩ ምንጭ ስሜ ክርስቲያን ይባላል። መዋቲ ስሜን ከፈለግህ ግን ቂርቆስ ይባላል።" አለው። ንጉሡ ሊያታልለው "ደስ የተሰኘህ ሕፃን" ቢለው ቅዱሱ ሕፃን "ትክክል ተናገርክ ለእኔ በሰማያት ደስታ ይጠብቀኛል። አንተ ግን እውነተኛው አምላክ ይፈርድብሃል።" አለው። በሦስት ዓመት ሕፃን አንደበት ዘለፋ የገጠመው ከሃዲ ተቆጣ። እናትና ልጅን በብዙ መክፈልተ ኩነኔ አሰቃያቸው። ሰውነታቸውን ቸነከረ፣ አካላቸውን ቆራረጠ፣ ዓይናቸውን አወጣ። ሌላም ሊናገሩት የሚጨንቅ ስቃይን አሰቃያቸው። በዚህች ቀን ግን ትልቅ ድስት አሰርቶ ባሩድ፣ አረር፣ ስብና የመሳሰሉትን ጨምረውበት በእሳት አፈሉት። የእሳቱ ወላፈን አካባቢውን በላው። በድስቱ ውስጥ ያለው ነገር እየፈላ ሲገላበጥ እንደ ክረምት ነጐድጓድ ይጮህ ነበር። የስድስት ሰዓት የእግር መንገድ ድረስም ተሰምቷል። ቅድስት ኢየሉጣ ይሔኔ ነበር ልቧ ድንግጥ ያለው። ሕፃኑ ቂርቆስ የእናቱን ፍርሃት ሲመለከት ጸለየ። "ፈጣሪዬ! ፍሬው ያለ ግንዱ አይቆምምና እኔን እንዳጸናህ እናቴንም አጽናት።" ሲል ለመነ። "እግዚኦ ትፈቅድኑ ለፍሬሁ ተአልዶ እንዘ በእሳት ታውኢ ጉንዶ" እንዲል። በዚያች ሰዓት ቅድስት ኢየሉጣ ዓይኖቿ ተከፍተው ሰማያዊ ክብርን ተመለከቱና ልቧ ወደ ድፍረቱ ተመለሰ። ልጇንም "አንተ አባቴ ነህ፤ አንተን የተሸከመች ማኅጸኔ የተባረከች ናት።" አለችው። ከዚያም ሁለቱንም ወደ ፈላው ድስት ውስጥ ቢጨምሯቸው ፍጡነ ረድኤት ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደላቸው። በበትረ መስቀሉ ባርኮ የፈላውን አቀዘቀዘው። የነደደውን ውኃ አደረገው። ቅዱሳኑ ቂርቆስና ኢየሉጣ ከብዙ መከራ በኋላ በሰማዕትነት አልፈዋል። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                22. ቅዱስ ኡራኤል
                                                  22. አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት የተቀበሉበት
                                                    ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ምንም እንኳ ለሃገራቸውና ሃይማኖታቸው ያን ያህል ዋጋ ቢከፍሉም ትውልዱም፣ መንግሥቱም፣ ራሷ ቤተ ክርስቲያናችንም ተገቢውን ክብር ሰጥተው እያሰቧቸው አይደለም። እስኪ እንዲያው ቢያንስ እንደ ክርስቲያን አንድም እንደ ኢትዮጵያዊ እነዚህ ነገሮቻቸውን እናስብ። ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ከልጅነታቸው ጀምረው ትምህርት፣ ትሕርምትና ደግነት ወዳጅ እንደ ነበሩ ይነገራል። ወቅቱ ኢትዮጵያ የራሷን ጳጳሳት የምትሻበት ጊዜ ነበርና በፈቃደ እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ የሃገራችን አራት አባቶች ጵጵስናን ተሾሙ። እነርሱም ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስና አበው አባ ሚካኤል፣ አባ አብርሃምና አባ ይስሐቅ ናቸው። የተሾሙትም ግንቦት ፲፰ ቀን ፲፱፻፳፩ ዓ.ም ነው። አቡነ ጴጥሮስ ከተሾሙ በኋላ በሐዋርያዊ አገልግሎትና በጸሎት ተግተው ኑረዋል። በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ፋሺስት ጣልያን ሃገራችንን በወረረች ጊዜ ቆራጡ ጳጳስ በዱር በገደል ለመሔድ ተነሱ። በየበርሃው እየሔዱ አርበኞችን ሲያጽናኑ፣ ሲናዝዙ፣ ሲባርኩም ቆይተዋል። ለሃገራቸውና ለሃይማኖታቸው ረሃብ፣ ጥምና እንግልትን ታግሰዋል። በተያዙባት በዚያች ሌሊትም በጣልያኖች ለሮም እምነትና ለአገዛዙ እንዲያጐበድዱ ተጠየቁ። ቆራጡ ሰው ግን እንቢ ቢሉ የሚደርስባቸውን እያወቁ "አይደረግም" አሉ። በማግስቱ በአደባባይ መትረየስ ተደግኖባቸው አሁንም ጥያቄ ቀረበላቸው። አቡነ ጴጥሮስ አፋቸውን ከፍተው ሊናገሩ ጀመሩ፦ "የሃገሬ ሕዝብ ሆይ! ለሃገርህ ለሃይማኖትህ ባትጋደል ትውልድ ይፋረድህ። ለጣልያን ግን እንኳን ሰው ዛፍ ቅጠሉ መሬቱ እንዳይገዛለት አውግዣለሁ።" አሉ። በደቂቃዎች ልዩነት በግራዚያኒ ትዕዛዝ የመትረየስ ጥይት ዘነበባቸው። አካላቸው ተበሳስቶ በሰንሰለት እንደ ታሠሩ መሬት ላይ ወደቁ። አንዱ ወታደር ቀርቦ ቢመለከት ትንሽ ትንፋሽ ነበረቻቸው። "ይሔ ቄስ አልሞተም።" ብሎ ጭንቅላታቸው ላይ ተኮሰባቸው። አቡነ ጴጥሮስ ለሃገራቸውና ሃይማኖታቸው ተሠው። ነገሩ በአርበኞች ዘንድ ሲሰማ ትግሉ ተቀጣጠለ። ይሄ የተደረገው ሐምሌ ፳፪ ቀን በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ነው። አቡነ ጴጥሮስም በተ/መ/ድ (UN) የሺህ ዓመቱ ምርጥ ሰማዕት (MARTYR OF THE MILLENIUM) በመባል ይታወቃሉ። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                  23. ቅዱስ ጊዮርጊስ
                                                    ጊዮርጊስ ኃያል አስተበቁዓከ፡፡ ከመ ታድኅነኒ እግዚእየ ለእሩቅ ገብርከ፡፡ አልባሰ ዚአከ በደመ በግዕ ዘኀፀብከ፡፡ ወእምሰረቀት ፍጹመ ዐቀብከ፡፡" (ኃያሉ ሰማዕት ሆይ እኔን ምስኪኑን አገልጋይህን ከሃይማኖት መራቆት ከምግባር እጦት ታድነኝ ዘንድ እማልድሃለሁ፡፡ ልብሰ ተጋድሎህን በበጉ በክርስቶስ አጥበህ ከአላውያን ቀማኞች ከከሐድያን ወንበዴዎች ጠብቀህ ክብረ ልብስህን በክብር ለመልበስ በቅተሃልና፡፡) መልክአ ጊዮርጊስ  ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                  26. ቅዱስ ዮሴፍ (እረፍቱ)
                                                    በሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ አካባቢ ስም አጠራራቸው ከከበረ ደጋግ እስራኤላውያን አንዱ የእመቤታችን ጠባቂ ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ ነው። ትውልዱ ከነገደ ይሁዳ ሲሆን አባቱ ያዕቆብ ይሰኛል። በጉብዝናው ወራት የእመቤታችንን አክስት ማርያምን አግብቶ ብዙ ልጆችን ወልዶ አርጅቷል። ከልጆቹም ዮሳ፣ ያዕቆብ፣ ይሁዳ፣ ስምዖንና ሰሎሜ በቅዱስ መጽሐፍ ተዘክረዋል። ቅዱስ ዮሴፍ እድሜው ሰባ አምስት ሲሆን ሚስቱ ማርያም ሞተችበት። ከጥቂት ወራት በኋላም በመንፈስ ቅዱስ ድንግል ማርያምን ሊያገለግል ተመረጠ። "እጮኛ" የሚለውም ለዚያ ነው። (ለአገልግሎት ነው የታጨው) እመቤታችን ለአረጋዊ ዮሴፍ በሁለት ወገን ልጁ (ዘመዱ) ናት። ፩.የሚስቱ ማርያም የእኅት (የሐና) ልጅ ናት። ፪.የቅድመ አያቱ የአልዓዛር የልጅ ልጅ ናት። ደጉ ሽማግሌ ቅዱስ ዮሴፍ ምን ቢያረጅ እመቤታችንን ለማገልገል አልደከመውም። አብሯት ተሰደደ፣ ረሃብ ጥማቷን፣ ጭንቅና መከራዋን፣ ሐዘንና ችግሯን ተካፍሏል። ከእመ ብርሃንና አምላክ ልጇ ጋር ለአሥራ ስድስት ዓመታት ኑሯል። ከእነዚህ ዘመናት በኋላም በ፲፮ ዓ.ም በተወለደ በዘጠና አንድ ዓመቱ ሲያርፍ ጌታችን "ሥጋህ አይፈርስም።" ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶለታል። "ኢየሱስ ክርስቶስ በከመ አሠፈዎ ኪዳነ ኢበልየ በመቃብር ወኢሂ ማሰነ እስከ ዮም በድኑ ሐለወ ድኁነ።" እንዳለ መጽሐፈ ስንክሳር። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                  26. አቡነ ሀብተማርያም ዘደብረሊባኖስ
                                                    28. ቅድስት መስቀል ክብራ (እረፍቷ)(የቅዱስ ላሊበላ የትዳሩ አጋር)
                                                    30. ቅድስት ማርያም ክብራ(እረፍቷ)
                                                  ነሐሴ
                                                    7. ፅንሰታ ለማርያም
                                                      ይህችን ዕለት አበው ሊቃውንት "ጥንተ መድኃኒት፤ የድኅነት መነሻ ቀን" ሲሉ ይጠሯታል:: ስለ ምን ነው ቢሉ:- ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነች የአምላክ እናቱ የተጸነሰችበት ዕለት በመሆኑ ነው:: አንድም ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተጸነሰች የመጀመሪያ ሰው እርሷ ናትና እንዲህ ይላሉ:: "ለጽንሰትኪ በከርሥ: እንበለ አበሳ ወርኩስ: ወለልደትኪ እማኅጸን ቅዱስ::" "ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው: የተወለድሽበት ማኅጸንም ቅዱስ ነው::" (መጽሐፈ ሰዓታት, ኢሳ. 1:9, መኃ. 4) ይሕች ዕለት ለኢያቄምና ለሐና ብቻ ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ የተስፋ ድኅነት ቀን ናትና ሐሴትን ልናደርግ ይገባል:: የእመቤታችን መጸነስስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ(አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ: በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም" በሚል ይናቁ ነበር:: ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ:: እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም:: የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን ርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች:: ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለአርባ ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በአርባኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ:: እርሱ:- ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጆሮ ገብታ: በማኅጸኗ ስትደርስ አየ:: እርሷ ደግሞ:- የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለሰባት ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ:: በሰባተኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ 7) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ:: እንደ ሥርዓቱም በዚህች ቀን አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች:: "ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ" "ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ::(ቅዳሴ ማርያም) ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                    13. እግዚአብሔር አብ በደብረታቦር ተራራ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱ ለእነ ሙሴና ኤልያስ የገለጸበት ቀን ነው/የቡሄ በዓል/
                                                      ደብረ ታቦር በቁሙ እሥራኤል ውስጥ ከሚገኙ ተራሮች አንዱ ነው:: ተራራው ብዙ ታሪካዊ ዳራዎች ቢኖሩትም ክብሩ ከፍ ከፍ ያለው ግን ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን ስለ ገለጸበት ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋችንን በተዋሐደባት በዚያች በተወደደች ጊዜ: ደቀ መዛሙርቱ ስለ እግዚአብሔር መንግስት ምሥጢርን ይማሩ ነበር:: በጊዜው ግን አበው ሐዋርያት ምሥጢር ባይገባቸው: አንድም ገና መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ አልወረደም ነበርና እምነታቸው ሙሉ አልነበረም:: ጌታም አምላክነቱን በየጊዜው በቃልም: በተግባርም ይገልጥላቸው ነበር:: በእርግጥ ያንን ነደ እሳት: ሰማያት የማይችሉትን ግሩማዊ አምላክ በትሑት ሰብዕና መመልከቱ ሊከብድ እንደሚችል መገመት አያዳግትም:: ጌታችን ብዙ ተአምራትን በአምላካዊ ጥበቡ ሠርቷል:: እጅግ ድንቅ ከሆኑት መካከል ደግሞ ቅድሚያውን ደብረ ታቦር ይይዛል:: ጌታ ስለ ምን መለኮታዊ ክብሩን በደብረ ታቦር ገለጸ ቢሉ:- 1.ትንቢቱ ሊፈጸም (መዝ. 88:12) 2.ምሳሌው ሊፈጸም (ባርቅና ዲቦራ በሢሣራ ላይ ድልን ተቀዳጅተዋልና::) 3.ሊቀ ነቢያት ሙሴ "ልይህ" ብሎ ከአንድ ሺ አምስት ዓመታት በፊት ጠይቆ ነበርና እርሱን ለመፈጸም 4.አንድነቱን: ሦስትነቱን ለመግለጽ 5.ቤተ ክርስቲያንን በምሳሌ ለማሳየት 6.ተራራውን ለመቀደስ 7.የሐዋርያቱን ልብ ለማጽናት . . . ወዘተ ነው:: ነሐሴ 7 ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቂሣርያ ፊልጶስ ወስዶ "የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?" ብሎ ጠይቋቸው ነበር:: እነርሱም የራሳቸውን ሐሳብ የሌላ እያስመሰሉ "አንዳንዶቹ ኤልያስ: አንዳንዶቹም ሙሴ: ሌሎቹም ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል::" አሉት:: ኩላሊትን የሚመረምር ፈጣሪ ነውና "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" ቢላቸው ደንግጠው ዝም አሉ:: የሃይማኖት አባት: ባለ በጐ ሽምግልና ቅዱስ ጴጥሮስ ግን በመካከላቸው ቆሞ "አንተ ውዕቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው - የሕያው እግዚአብሔር አንድያ የባሕርይ ልጁ ክርስቶስ አንተ ነህ::" አለው:: በዚያን ጊዜ ቃለ ብጽዓን እና የመንግስተ ሰማያት መክፈቻ ተሰጠው:: (ማቴ. 16:13) መጽሐፍ እንደሚል ደግሞ እንዲህ ከሆነ ከስድስተኛው ቀን በኋላ ጌታችን አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ደብረ ታቦር ወሰዳቸው:: ዘጠኙን በእግረ ደብር (ከተራራው ሥር) ትቶ ሦስቱን (ጴጥሮስን: ዮሐንስንና ያዕቆብን) ይዟቸው ወጣ:: እኒሕ ሐዋርያት "አዕማድ: አርዕስት: ሐዋርያተ ምሥጢርም" ይባላሉ:: በተራራው ላይ ሳሉም ድንገት የጌታችን መልኩ ከፀሐይ ሰባት እጅ አበራ፤ ከመብረቅም ሰባት እጅ አበረቀ:: "ወኮነ ልብሱ ጸዐዳ ከመ በረድ" እንዲል ከታቦር የተነሳው ብርሃነ ገጹ አርሞንኤም ደርሷል:: ያንን ተመልክተው መቆም ያልቻሉት ሐዋርያቱ ፈጥነው መሬት ላይ እንደ ሻሽ ተነጠፉ:: በዚያች ሰዓት ሙሴ ከመቃብር: ኤልያስም ከብሔረ ሕያዋን መጡ:: አንዳንዶቹ ጌታን "ነቢይ" (ሎቱ ስብሐት) ብለውታልና ሙሴና ኤልያስ ተናገሩ:- "ስለ ምን አንተን ነቢይ ይሉሃል፤ እግዚአ ነቢያት-የነቢያት ፈጣሪ ነህ እንጂ" እያሉ ተገዙለት: አመሰገኑት:: ነገር ግን በቦታው ጸንተው መቆየት አልቻሉም:: መለኮታዊ ብርሃኑ ቢበዘብዛቸው ቅዱስ ሙሴም ወደ መቃብሩ: ቅዱስ ኤልያስም ወደ ማደሪያው በድንጋጤ ሩጠዋል:: በዚያች ሰዓት ሊቀ ሐዋርያት ጌታን "ሠናይ ለነ ኀልዎ ዝየ:: ንግበር ሠለስተ ማኅደረ: አሐደ ለከ: ወአሐደ ለሙሴ: ወአሐደ ለኤልያስ - ጌታ ሆይ! በዚህ መኖር ለኛ መልካም ነው:: በዚህም ሦስት ዳስ እንሥራ:: አንዱን ለአንተ: አንዱንም ለሙሴ: አንዱን ለኤልያስ" ብሎታል:: ቅዱስ ጴጥሮስ ለራሱ ሳያስብ ለጌታና ለቅዱሳን ነቢያቱ "ቤት እንሥራ" በማለቱ ሲመሰገን ጌታን የመጣበትን የማዳን ሥራ የሚያስተው ጥያቄ በማቅረቡ ከድካም ተቆጥሮበታል:: ለሁሉም ግን ሐሳቡ ድንቅና መንፈሳዊ ነው:: እርሱ ይሕንን ሲናገር መንፈስ ቅዱስ በደመና አምሳል ወረደና ከበባቸው:: አብ ከሰማይ ሆኖ "ዝንቱ ውዕቱ ወልድየ ዘአፈቅር: ወሎቱ ስምዕዎ - የምወደው: የምወልደው: ሕልው ሆኘ የምመለክበት የባሕርይ ልጄ እርሱ ነውና ስሙት::" ሲል ተናገረ:: ደቀ መዛሙርቱም ከፍርሃት የተነሳ በዚያች ሰዓት እንደ በድን ሁነው ነበርና ጌታችን ቀርቦ ቀሰቀሳቸው:: በተነሱ ጊዜ ግን ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት ተመልሶ ነበር:: (ማቴ. 17, ማር. 9, ሉቃ. 9) በደብረ ታቦር የጌታችንን ብርሃነ መለኮት ያዩ ሦስቱ ሐዋርያት ብቻ አይደሉም:: እመ ብርሃን ካለችበት ሆና ስትመለከት ስምንቱ ሐዋርያት ደግሞ በተራራው ሥር ሆነው በተደሞ ተመልክተዋል:: ይሕንን ድንቅ ብርሃነ መለኮት ያላየ ይሁዳ ብቻ ሲሆን እርሱም ስለ ክፋቱ የኢሳይያስ ትንቢት ተፈጽሞበታል:: ኃጢአተኛው የእግዚአብሔርን ክብር እንደማያይ ተነግሮበታልና:: "ያአትትዎ ለኃጥእ ከመ ኢይርዐይ ስብሐተ እግዚአብሔር" እንዲል:: (ኢሳ. 25:10) ሊቁም የደብረ ታቦርን ምሥጢር ሲያደንቅ እንዲህ ብሏል:- "ጸርሐ አብ ኪያከ በውዳሴ: ወበርእስከ ጸለለ መንፈሰ ቅዳሴ: አመ ገበርከ እግዚኦ በታቦር ምስለ ሐዋርያት ክናሴ: መንገለ ሀሎ ኤልያስ ወኀበ ሐለወ ሙሴ: ዘመለኮትከ ወልድ ከሠትከ ሥላሴ::" ለወዳጆቹ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠ ጌታ የእኛንም ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን:: ከበዓሉ በረከትም ያሳትፈን:: ነሐሴ 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት 1.ደብረ ታቦር /ደብረ ምሥጢር/ ደብረ በረከት 2.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት (ልደቱ) 3.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ 4.ቅዱሳን አበው ሐዋርያት 5.አባ ጋልዮን መስተጋድል 6.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ (ልደታቸው) 7.ቅድስት ኦፍራ ሰማዕት ወርኀዊ በዓላት 1.እግዚአብሔር አብ 2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት 3.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት 4.ቅዱስ አስከናፍር 5.አሥራ ሦስቱ ግኁሳን አባቶች 6.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ 7.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ "ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል:: ክንድህ ከኃይልህ ጋር ነው:: እጅህ በረታች: ቀኝህም ከፍ ከፍ አለች::" (መዝ. ፹፰፥፲፪) "ከስድስት ቀንም በኋላ ጌታ ኢየሱስ ጴጥሮስን: ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን ይዞ ወደ ረዥም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው:: በፊታቸውም ተለወጠ:: ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ:: ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ:: እነሆም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው:: ጴጥሮስም መልሶ ጌታ ኢየሱስን:- "ጌታ ሆይ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው:: ብትወድስ በዚህ ሦስት ዳስ: አንዱን ለአንተ: አንዱንም ለሙሴ: አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ" አለ:: እርሱም ገና ሲናገር እነሆ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው:: እነሆም ከደመናው:- "በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው: እርሱን ስሙት" የሚል ድምጽ መጣ:: ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ::" (ማቴ. ፲፯፥፩) ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                                    15. ቅድስት እነባመሪና(እረፍቷ)
                                                      ቤተ ክርስቲያን "እንቁዎቼ" ከምትላቸው ሴት ጻድቃን አንዷ ቅድስት እንባ መሪና ናት:: ጣዕመ ዜናዋ: ሙሉ ሕይወቷ: አስገራሚም: አስተማሪም ነው:: ቅድስቷ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብፅ ተወልዳ ያደገች ክርስቲያን ናት:: ወላጆቿ ከእርሷ በቀር ሌላ ልጅ የሌላቸው ሲሆን በአኗኗራቸውም ደግና ቅን ነበሩ:: ቅድስት እንባ መሪና ትክክለኛ ስሟ "መሪና" ነው:: ምክንያቱም "እንባ መሪና" የወንድ ስም ነውና:: ነገር ግን በወንድ ስም የተጠራችበት የራሱ ታሪክ አለውና እርሱን እንመለከታለን:: ቅድስት መሪና ገና ልጅ ሳለች እናቷ ማርያም ሞተችባት:: ደግ አባት አንድ ልጁን በሥጋዊም: በመንፈሳዊም ሳያጐድልባት አሳደጋት:: ዕድሜዋ አሥራ አምስት ዓመት በሆነ ጊዜ ወደ ፊቱ አቅርቦ "ልጄ! እኔ ወደ ገዳም ስለምሔድ አንቺን መልካም ባል ላጋባሽ::" አላት:: ቅድስት መሪናም "ነፍሰ ዚአከ ታድኅን: ነፍሰ ዚአየኑ ታጠፍእ - የአንተን ነፍስ አድነህ እንዴት የእኔን ትተዋታለህ? እኔም እመንናለሁ::" አለችው:: አባቷ የተናገረችው ከልቧ እንደሆነ ሲያውቅ "ልጄ! ገዳም ሁሉ በአካባቢው የወንድ ብቻ ነውና ስሚኝ::" አላት:: እርሷ ግን "አባቴ! ግዴለህም: ስሜን እንደ ወንድ ቀይረህ: አለባበሴንም ለውጥ::" አለችው:: (እንደ ወንድ ለበሰች ማለት ግን እንደ ዘመኑ ዓይነት እንዳይመስላችሁ አደራ!) ከዚያ አባትና ልጅ ሃብት ንብረታቸውን ሸጠው ለነዳያን አካፈሉ:: በፍጹም ልባቸውም መነኑ:: በደረሱበት ገዳም ቅድስት መሪና በወንድ ስም "እንባ መሪና" በሚል ገባች:: ቀጣዩ ሥራዋ እንደ ወንዶች እኩል መስገድ: መጾምና መጸለይ ነበር:: ይህችን ቅድስት ልናደንቃት ግድ ይለናል:: ማንም በእርሷ አይፈተንም:: አያውቋትምና:: እርሷ ግን ወጣት ሆና: አንድም ሴት በሌለበት ገዳም ጸንቶ መቆየት በራሱ ልዩ ነው:: መልአካዊ ኃይልንም ይጠይቃል:: ተጋድሎዋ በጣም ስለ በዛ ወንድሞች መነኮሳት ይደነቁባት ነበር:: ጺም ስለሌላትና ድምጿ ቀጭን ስለሆነ አልተጠራጠሩም:: ምክንያቱም ጃንደረባ ናት ብለው አስበዋልና:: ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን አባቷ ታሞ ከማረፉ በፊት አበ ምኔቱን ጠርቶ "ወደ ከተማ ልጄን እንዳትልክብኝ: አደራ!" ብሎት ነበር:: ያም ሆኖ አንዳንድ መነኮሳት ቅሬታ በማንሳታቸው ወደ ከተማ ተላከች:: ችግሩ ለተልእኮ ባደሩበት ቤት አንድ ጐረምሳ ገብቶ የአሳዳሪውን ልጅ ከክብር አሳንሷት ሔደ:: ሲወጣም "ድንግልናሽን ያጠፋ ማን ነው? ካሉሽ ያ ወጣት መነኩሴ አባ እንባ መሪና ነው በይ::" አላት:: ከሦስት ወራት በኋላ የዚያች ዘማ ሴት ጽንስ በታወቀ ጊዜ ለአባቷ "አባ እንባ መሪና እንዲህ አደረገኝ::" አለችው:: አባት መጥቶ እየጮኸ መነኮሳትን ተሳደበ:: አበ ምኔቱ ግራ ተጋብቶ ቢጠይቀው "የአንተ ደቀ መዝሙር እንባ መሪና ልጄን ከክብር አሳነሳት::" አለው:: አበ ምኔቱ እውነት መስሎታልና ቅድስቲቱን ጠርቶ ቁጣና እርግማንን አወረደባት:: በዚያች ሰዓት ተንበርክካ አንድ ነገር ወሰነች:: "ሴት ነኝ" ብሎ መናገሩስ ቀላል ነው:: ግን ደግ ናትና የእነዛን አመጸኛ ሰዎች ኃጢአት ልትሸከም ወሰነች:: ቀና ብላ "ማሩኝ ወጣትነት ቢያስተኝ ነው?" አለቻቸው:: ተቆጥተው ዕለቱን እየገፉ ከገዳም አስወጧት:: ከባድ ቀኖናም ጫኑባት:: ከስድስት ወራት በኋላም የእርሷ ልጅ ነው የተባለ ሕፃን አምጥተው ሰጧት:: ይህኛው ግን ከባድ ፈተና ሆነባት:: እንዳታጠባው አካሏ በገድል ደርቁአል:: በዚያ ላይ ድንግል የሆነች ሴት ወተት የላትም:: ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት: የበጋውን ሐሩር: የክረምቱን ቁር ራሷ ታግሣ ለሕፃኑ ከእረኞች ወተት እየለመነች: እየመገበች ሦስት ዓመታት አለፉ:: በዚህ ጊዜ ወደ ገዳሙ ከከባድ ቀኖና ጋር ተመለሰች:: ሕፃኑን ስታሳድግ: ለገዳሙ ስትላላክ: ምግብ ስታዘጋጅ: ውኃ ስትቀዳ: የእያንዳንዱን ቤት ስታጸዳ ሰላሳ ሰባት ዓመታት አለፉ:: ሕፃኑም አድጐ ደግ መናኝ ወጣው:: (የቅድስቷ እጆች ያሳደጉት የታደለ ነው::) በመጨረሻ ቅድስት መሪና (እንባ መሪና) ታማ ዐረፈች:: እንገንዛለን ብለው ቢቀርቡ ሴት ናት:: እጅግ ደንግጠው አበ ምኔቱን ጠሩት:: በዙሪያዋ ከበው እንባቸውን አፈሰሱ:: ጸጸት እንደ እሳት በላቻቸው:: ሥጋዋን በክብር ገንዘው: በአጐበር ጋርደው: በራሳቸው ተሸክመው ምሕላ ገቡ:: ሙሉውን ቀን "ስለ ቅድስት መሪና ብለህ ክርስቶስ ሆይ ማረን?" ሲሉ ዋሉ:: ድንገት ግን ከተባረከ ሥጋዋ "ይቅር ይበለን::" የሚል ድምጽን ሰምተው ደስ ብሏቸው ቀበሯት:: እነዚያ ዝሙተኞችም ከእርሷ ይቅርታን እስካገኙበት ቀን አብደው ኑረዋል:: ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                    16. ኪዳነምህረት
                                                      ይህች ዕለት እጅጉን ታላቅና ክብርት ናት። ምክንያቱም የድንግል ማርያም ሥጋዋ ተነስቶ ዐርጐባታልና። ድንግል እመቤታችን ተነሣች ዐረገች ስንል እንደ እንግዳ ደርሶ እንደ ውኃ ፈሶ ወይም በአጋጣሚ የተደረገ አይደለም። ጥንቱን በአምላክ ልቡና ታስቦ ኋላም ትንቢት ተነግሮለት ነው። ታሪኩ፣ ነገሩ፣ ምሥጢሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር ነበር። ከነገር ሁሉ በፊት እግዚአብሔር እናቱን ያውቃት ነበር። ዓለም ተፈጥሮ አዳምና ሔዋን ስተው መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ አግኝቷቸው በኃዘን ንስሐ ቢገቡ "እትወለድ እም ወለተ ወለትከ - ከአምስት ቀን ተኩል (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት) በኋላ ከአንተ ባሕርይ ከምትገኝ ንጽሕት ዘር ተወልጄ አድንሃለሁ።" ብሎ ተስፋ ድኅነት ሰጠው። ከአዳም አንስቶ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት አበው፣ ነቢያትና ካህናት ስለ ድንግል ማርያም ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን ተናገሩ። መዳኛቸውን ሱባኤ ቆጠሩላት። ምሳሌም መሰሉላት። ከሩቅ ዘመን ሁነውም ሊያገኟት እየተመኙ እጅ ነሷት። "እምርሑቅሰ ርእይዋ ወተአምኅዋ" እንዲል። የድንግል ማርያም ሐረገ ትውልድ ከአዳም በሴት ከያሬድ በሄኖክ ከኖኅ በሴም ከአብርሃም በይስሐቅ ከያዕቆብ በይሁዳና በሌዊ ከይሁዳ በእሴይ፣ በዳዊት፣ በሰሎሞንና በሕዝቅያስ ወርዳ ከኢያቄም ትደርሳለች። ከሌዊ ደግሞ በአሮን፣ አልዓዛር፣ ፊንሐስ፣ ቴክታና በጥሪቃ አድርጋ ከሐና ትደርሳለች። አባታችን አዳም ከገነት በወጣ በአምስት ሺህ አራት መቶ ሰማንያ አምስት ዓመት ወላዲተ አምላክ ንጽሕና ሳይጐድልባት ኃጢአት ሳያገኛት ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ከደጋጉ ኢያቄም ወሐና ትወለዳለች። (ኢሳ. ፩፥፱ ፣ መኃ. ፬፥፯) "ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ" እንዳለ። (ቅዱስ ቴዎዶጦስ ዘዕንቆራ ) ከዚያም ከእናት ከአባቷ ቤት ለሦስት ዓመታት ቆይታ ወደ ቤተ መቅደስ ትገባለች። በቤተ መቅደስም ለአሥራ ሁለት ዓመታት ፈጣሪዋን እግዚአብሔርን እያመሰገነችና እያገለገለች እርሷን ደግሞ መላእክተ ብርሃን እያገለገሏት ሕብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ እየመገቧት ኑራለች። አሥራ አምስት ዓመት በሞላት ጊዜ ጻድቅ አረጋዊ ዮሴፍ ያገለግላት ዘንድ ወደ ቤቱ ወሰዳት። በዚያም መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዜና ድኅነትን ነግሯት አካላዊ ቃልን በማኅጸንዋ ጸነሰችው። ነደ እሳትን ተሸከመችው፤ ቻለችው። "ጾርኪ ዘኢይትጸወር ወአግመርኪ ዘኢይትገመር" እንዳለ። (ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ለብሐዊ) ወልደ እግዚአብሔርን ለዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ጸንሳ እንበለ ተፈትሆ (በድንግልና) ወለደችው። (ኢሳ. ፯፥፲፬) "ኢየሱስ" ብላ ስም አውጥታለት በናዝሬት ገሊላ ለሁለት ዓመታት ቆዩ። አርዌ ሄሮድስ "እገድላለሁ" ብሎ በተነሳበት ወቅትም ልጇን አዝላ በረሃብና በጥም፣ በላበትና በድካም፣ በዕንባና በኃዘን ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ከገሊላ እስከ ኢትዮጵያ ተሰዳለች። ልጇ ጌታችን አምስት ዓመት ከስድስት ወር ሲሆነው ለእርሷ ለድንግል ደግሞ ሃያ አንድ ዓመት ከሦስት ወር ሲሆናት ወደ ናዝሬት ተመለሱ። በናዝሬትም ለሃያ አራት ዓመት ከስድስት ወር ልጇን ክርስቶስን እያሳደገች ነዳያንን እያሰበች ኑራለች። እርሷ አርባ አምስት ዓመት ልጇ ሠላሳ ዓመት ሲሆናቸው ጌታችን ተጠምቆ በጉባኤ ትምህርት ተአምራት ጀመረ። ለሦስት ዓመት ከሦስት ወርም ከዋለበት እየዋለች ካደረበትም እያደረች ትምህርቱን ሰማች። የማዳን ቀኑ ደርሶ ልጇ ክርስቶስ ሲሰቀልም የመጨረሻውን ፍጹም ሐዘን አስተናገደች። አንጀቷ በኃዘን ተቃጠለ። በነፍሷም ሰይፍ አለፈ። (ሉቃ. ፪፥፴፭) ጌታ በተነሣ ጊዜም ከፍጥረት ሁሉ ቀድማ ትንሣኤውን አየች። ለአርባ ቀናትም ሳትለይ ከልጇ ጋር ቆየች። ከልጇ ዕርገት በኋላ በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትን ሰብስባ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ አበቃች። በጽርሐ ጽዮን ከአደራ ልጇ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ለአሥራ አምስት ዓመታት ኖረች። በእነዚህ ዓመታት ሥራ ሳትፈታ ስለ ኃጥአን ስትማልድ ቃል ኪዳንን ከልጇ ስትቀበል ሐዋርያትን ስታጽናና ምሥጢርም ስትገልጽላቸው ኑራለች። ዕድሜዋ ስልሳ አራት ዓመት በደረሰ ጊዜ ጥር ፳፩ ቀን መድኃኒታችን አእላፍ ቅዱሳንን አስከትሎ መጣ። ኢየሩሳሌምን ጨነቃት። አካባቢውም በፈውስ ተሞላ። በዓለም ላይም በጐ መዓዛ ወረደ። እመ ብርሃን ለፍጡር ከዚያ በፊት ባልተደረገ ለዘላለምም ለማንም በማይደረግ ሞገስ፣ ክብርና ተአምራት ዐረፈች። ሞቷ ብዙዎችን አስደንቋል። "ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ" እንዲል። ከዚህ በኋላ መላእክት እየዘመሩ ሐዋርያቱም እያለቀሱ ወደ ጌቴሴማኒ በአጐበር ሥጋዋን ጋርደው ወሰዱ። ይህንን ሊቃውንት፦ "ሐራ ሰማይ ብዙኃን እለ አልቦሙ ሐሳበ እንዘ ይዜምሩ ቅድሜኪ ወመንገለ ድኅሬኪ ካዕበ ማርያም ሞትኪ ይመስል ከብካበ" ሲሉ ይገልጡታል። በወቅቱ ግን አይሁድ በክፋት ሥጋዋን እናቃጥል ስላሉ ቅዱስ ገብርኤል (ጠባቂ መልአክ ነው።) እነርሱን ቀጥቶ እርሷን ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወስዶ በዕጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል። በዚያም መላእክት እያመሰገኗት ለሁለት መቶ አምስት ቀናት ቆይታለች። ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ ለሐዋርያቱ ክብረ ድንግልን ቢነግራቸው በጐ ቅንአት ቀንተው በነሐሴ ፩ ሱባኤ ጀመሩ። ሁለተኛው ሱባኤ ሲጠናቀቅም ጌታ የድንግል ማርያምን ንጹሕ ሥጋ ሰጣቸው። እየዘመሩም በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል። በሦስተኛው ቀን (ነሐሴ ፲፮) እንደ ልጇ ባለ ትንሣኤ ተነስታ ዐርጋለች። ትንሣኤዋንና ዕርገቷንም ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ አይቶ መግነዟን ተቀብሏል። ሐዋርያቱም መግነዟን ለበረከት ተካፍለው እንደ ገና በዓመቱ ነሐሴ ፩ ቀን ሱባኤ ገቡ። ለሁለት ሳምንታት ቆይተው በዚህች ቀንም ሁሉንም ወደ ሰማይ አወጣቸው። በፍጡር አንደበት ተከናውኖ የማይነገር ተድላ፣ ደስታና ምሥጢርንም አዩ። ጌታ ራሱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው። የበዓሉን ቃል ኪዳን ሰምተው ከድንግል ተባርከው ወደ ደብረ ዘይት ተመልሰዋል።  ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን። አእምሮውን፣ ለብዎውን፣ ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን።  ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                    19. አባ መቃርስ የስጋው ፈልሰት
                                                      ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (መቃሬ) "ጽድቅ እንደ መቃርስ" የተባለለት: የመነኮሳት ሁሉ አለቃ: ከሰማንያ ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ: በግብጽ ትልቁን ገዳም (አስቄጥስን) የመሠረተ: ከሃምሳ ሺ በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው:: በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብጽ ወደ እስያ በርሃ ከጓደኛው ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል:: በዚያ ለሁለት ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በኋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነንጉሣቸው አጥምቀዋል:: በተሰደዱባት ሃገርም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ስም አጠራሩ ይክበርና) እመቤታችንን: ቅዱሳን ሐዋርያትን: አዕላፍ መላእክትን: በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን ዳዊትን: ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን: ማርቆስን: ጴጥሮስን: ጳውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል:: በቅዱስ አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል:: ታላቁ ቅዱስ መቃርስና መቃርዮስ ከሁለት ዓመታት ስደትና መከራ በኋላ ስደት በወጡባት ዕለት መልዐኩ ኪሩብ በክንፉ ተሽክሞ ወደ ግብጽ መልሷቸዋል:: በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከሃምሳ ሺ በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል:: ይህች ዕለት ለአባታችን መቃሬ በዓለ ፍልሠቱ ናት:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ካረፈ በኋላ ከክቡር ሥጋው ብዙ ተአምራት ይታዩ ነበርና የሃገሩ (የሳስዊር) ሰዎች ሊወስዱት ፈለጉ:: ሳስዊር ማለት ቅዱሱ ተወልዶ ያደገባት ወላጆቹ (አብርሃምና ሣራ) የኖሩባት ቦታ ናት:: የምትገኘውም ግብጽ ውስጥ ነው:: በምድረ ግብጽ: በተለይም በገዳመ አስቄጥስ የአባ መቃርስን ያህል ክቡርና ተወዳጅ የለምና የሃገሩ ሰዎች የነበራቸው አማራጭ መስረቅ ነበር:: መሥረቅ ኃጢአት ቢሆንም እነሱ ግን ስለ ፍቅር: አንድም ለበረከት (በረከትን ሲሹ) አደረጉት:: ወደ ሳስዊርም ወስደው: ቤተ ክርስቲያን በቅዱሱ ስም አንጸው በክብር አኖሩት:: በዚያም ለመቶዎች ዓመታት ተቀመጠ:: በ7ኛው መቶ ክ/ዘመን ግን ተንባላት (እስላሞች) መጥተው ቤተ ክርስቲያኑን አጠቁ:: በዚህ ጊዜም ሕዝቡ የጻድቁን አጽም ይዘው ሸሹ:: በሌላ ቦታም እንደ ገና በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጸው በዚያ አኖሩት:: በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የመንፈሳዊ አባታቸውን ሥጋ ያጡት የገዳመ አስቄጥስ ቅዱሳን ያዝኑ ይጸልዩ ነበርና ልመናቸውን ፈጣሪ ሰማ:: አባ ሚካኤል ሊቀ ጳጳሳት በነበረበት ዘመን: ከገዳሙ ለሌላ ተግባር ወደ ሳስዊር የተላኩ አበው ከታላቁ አባት ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ሰውነታቸው ታወከ:: ይዘው ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉ ሊሳካላቸው አልቻለም:: ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ደወል ደውሎ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ ነበርና:: ሕዝቡና ሃገረ ገዢው የሆነውን ሲሰሙ "የቅዱሱን ሥጋ ብትነኩ እንገላቹሃለን::" ብለው ሰይፍ: ዱላ: ጐመድና ጦር ይዘው መጡባቸው:: መነኮሳቱ ግን ባዷቸውን ሊመለሱ አልፈቀዱምና ሌሊቱን ሲያለቅሱና ሲጸልዩ አደሩ:: መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜም ታላቁ መቃርስ በግርማ ወርዶ መኮንኑን "ለምን ወደ ልጆቼ እንዳልሔድ ትከለክለኛለህ?" ሲል በራዕይ ተቆጣው:: በዚህ ምክንያትም መነኮሳቱ የቅዱሱን ሥጋ ተቀበሉ:: ሕዝቡም በዝማሬና በማኅሌት: ከብዙ እንባ ጋር ሸኟቸው:: ታላቁ መቃሬ ወደ ገዳሙ ሲደርስም ታላቅ ደስታ ተደረገ:: ቅዱሳን ልጆቹ ከመንፈሳዊ አባታቸው ተባርከው በክብር አኑረውታል:: ይህ የተደረገው በዚህች ዕለት ነው:: ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                    21. ጌቴ ሴማኒ ገዳም እመቤታችን (ሰበታ)
                                                      24. አቡነ ተክለሃይማት እረፍታቸው
                                                        *ልደት* መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው:: እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል:: በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል: ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በሁዋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል:: ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የጸነሱት መጋቢት 24 ቀን በ1206 ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታሕሳስ24 ቀን በ1207 ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል:: *ዕድገት* የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል:: ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት: ሐዲሳትን) ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁናም ከወቅቱ ዻዻስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል:: *መጠራት* አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮስ ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑ በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ:: +የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:: "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን:: ከዚህ በሁዋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በሁዋላ ሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ:: *አገልግሎት* ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዻዻሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ:: ያን ጊዜ ኢትዮዽያ 2 መልክ ነበራት:: +1ኛ ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል:: +2ኛው ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር:: +ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን (ጠንቁዋዮችን) አጥፍተዋል:: *ገዳማዊ ሕይወት* ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮዽያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል:: እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል:: +እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ12 ዓመታት: በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26 ዓመታት አገልግለዋል:: +በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በሁዋላም ወደ ምድረ ሽዋ (ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል:: *ስድስት ክንፍ* ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮዽያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር:: +የወቅቱ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በሁዋላ ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር:: +ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:- -በቤተ መቅደስ ብስራቱን -በቤተ ልሔም ልደቱን -በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን -በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን -በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር:: +የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ:: በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ ተክልየን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው:: +በዚያም:- የብርሃን ዐይን ተቀብለው -6 ክንፍ አብቅለው -የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው -ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው -ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው -ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው -"ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል:: *ተአምራት* የተክልየ ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው:: *ሙት አንስተዋል *ድውያንን ፈውሰዋል *አጋንንትን አሳደዋል *እሳትን ጨብጠዋል *በክንፍ በረዋል *ደመናን ዙፋን አድርገዋል:: +ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕጻናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና:: *ዕረፍት* ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው መከራን በብዙ ተቀብለው: እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው: በተወለዱ በ99 ዓመት: ከ8 ወር: ከ1 ቀናቸው ነሐሴ 24 ቀን በ1306 ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10 ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል:: ††† የጻድቁ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት የቅድስናና የክብር ስሞች ††† 1.ተክለ አብ: ተክለ ወልድ: ተክለ መንፈስ ቅዱስ 2.ፍስሐ ፅዮን 3.ሐዲስ ሐዋርያ 4.መምሕረ ትሩፋት 5.ካህነ ሠማይ 6.ምድራዊ መልዐክ 7.እለ ስድስቱ ክነፊሁ (ባለ ስድስት ክንፍ) 8.ጻድቅ ገዳማዊ 9.ትሩፈ ምግባር 10.ሰማዕት 11.የኢትዮዽያ መነኮሳት አለቃ 12.ፀሐይ ዘበፀጋ 13.የኢትዮዽያ ብርሃኑዋ 14.ብእሴ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ሰው) 15.መናኒ 16.ኤዺስ ቆዾስ (እጨጌ) ††† እነዚህ የአባታችን ስሞች እንደዘመኑ ሰው ለመሞጋገስ የወጡ ሳይሆኑ ሁሉም በትክክል ሥራዎቹንና ለቤተ ክርስቲያን የሆነላትን የሚያዘክሩ ናቸው:: ††† =>አምላከ ቅዱሳን በወዳጆቹ ምልጃ ክብራቸውን ያድለን:: በረከታቸውም በዝቶ ይደርብን:: ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                                      24. ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ
                                                        እጅግ የከበረችና የተመሰገነች እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን እናመሰግናታለን:: እርሷ በሁሉ ጐዳና ፍጹምነትን ያሳየች ኢትዮዽያዊት እናት ናት:: ገና ከልጅነት የነበራት የትሕትናና የመታዘዝ ሕይወት እጅግ ልዩ ነበር:: እናታችን ቅድስናን ያገኘችው ገና በትዳር ውስጥ እያለች ነው:: ከተባረከ ትዳሯ 12 ልጆችን አፍርታ: ምጽዋትን የዕለት ተግባሯ አድርጋ ኑራለች:: በዚህ ደግነቷም ሙት እስከ ማንሳት ደርሳለች:: አብያተ ክርስቲያናትን አንጻ አንድ ልጇን (ዳግማዊ ቂርቆስን) አዝላ ምናኔ ወጥታልች:: በደብረ ሊባኖስ ውስጥ የቆየችው ቅድስት እናት ተጋድሎዋን የፈጸመችው ግን ጣና ሐይቅ ውስጥ ነው:: በተለይ ለ22 ዓመታት ሐይቁ ውስጥ አካሏ አልቆ: አሣ በሰውነቷ ውስጥ እስከሚያልፍ ድረስ ተጋድላለች:: በቀኝና በግራ 12 ጦሮችን ተክላም ጸልያለች:: ብዙ ኃጥአንን አማልዳ: 12 ክንፎችን አብቅላ: ከፍ ከፍ ብላለች:: ከርሕራሔዋ ብዛት የተነሳ ሰይጣንን እንኩዋ ለማስታረቅ ሞክራለች:: ጌታም ከሲዖል ነፍሳትን እንድታወጣ ፈቅዶላታል:: ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ያረፈችው በዚህ ዕለት ሲሆን አጽሟ ዛሬ በራሷ ገዳም (ጣና ዳር) ይገኛል:: ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                                      27. ቅዱስ ሱርያል(4 ሊቀ መላእክት)
                                                        ከታላላቅ ሊቃናት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሱርያል ክብሩ ብዙ ቢሆንም ብዙ ምዕመናን አያውቁትም:: የመላእክት መዓርግ ሲነገር ሚካኤል: ገብርኤል: ሩፋኤል ብሎ ቀጥሎ የሚመጣው ሱርያል ነው:: በሦስቱ ሰማያት ካሉት ዘጠኙ ዓለመ መላእክት የአንዱ (የሥልጣናት) መሪ (አለቃ) ነው:: መልአኩ እጅግ ርሕሩሕ እና ተራዳኢ ነውና አንዘንጋው:: ለኖኅ መርከብርን ያሳራው: ከጥፋት ውኃም ያዳነው ይህ ቅዱስ መልአክ ነው:: በገድለ ሰማዕታትም ላይ እንደተጠቀሰው የሰማዕታት ረዳትና አዳኝም ነው:: ቅዱስ ሱርያል በሌላ ስሙ "እሥራልዩ" ይባላል:: "የእሥራኤል ረዳት" እንደ ማለት ነው:: ቸሩ አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ብሎ ይማረን:: ከበረከታቸውም ያድለን:: ነሐሴ 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት 1.አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ያዕቆብ (እሥራኤል) 2.ቅዱስ ሳሙኤል ነቢይ (የተጠራበት) 3.ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላእክት 4.ቅዱስ ብንያሚንና እኅቱ አውዶከስያ (ሰማዕታት) 5.ቅዱስ ፊቅጦርና እናቱ ሣራ 6.አባ ባስልዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ (የተሾሙበት) "እነዚህም ሁሉ አሥራ ሁለቱ የእሥራኤል ነገዶች ናቸው:: አባታቸው የነገራቸው ይህ ነው:: ባረካቸውም:: እያንዳንዳቸውን እንደ በረከታቸው ባረካቸው::" (ዘፍ. ፵፱፥፳፰) "በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረዥም ተራራ ወሰደኝ:: የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ: ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ . . . አሥራ ሁለት ደጆችም ነበሯት:: በደጆቹም አሥራ ሁለት መላእክት ቆሙ:: የአሥራ ሁለቱም የእሥራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር::" (ራእይ. ፳፩፥፲፩) ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                                      28. አበው አብርሃም ይህሳቅ ያዕቆብ (እረፍታቸው)
                                                        የሃይማኖት፣ የደግነት፣ የምጽዋትና የፍቅር አባት የሆነው አብርሃም በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት አባቱ ታራ ጣዖትን ይጠርብና ይሸጥ ነበር። ሽጦ ገንዘብ የሚያመጣለት ደግሞ ልጁ አብርሃም ነበር። በዚያ ወራት አብርሃም እውነተኛውን አምላክ ፍለጋ ገብቶ ነበር። አንድ ቀን ጣዖቱን ሊሸጥ ወደ ገበያ እየሔደ የተሸከመውን እንጨት ይመራመረው ገባ። "አሁን ይሔ ምኑ ነው አምላክ!" እያለም ያደንቅ ገባ። መንገድ ላይም ደክሞት ካረፈበት "ለምን አልጠይቀውም?" በሚል አናገረው። "እርቦኛል አብላኝ?" አለው። መልስ የለም። "እሺ አጠጣኝ?" አለው። አሁንም ያው ነው። "ባይሆን እሺ አጫውተኝ?" አለው። ጣዖቱ ተራ እንጨት ነውና መልሱ ዝምታ ነበር። ከዚያ ተነስቶ ወደ ገበያው ሲደርስ "ዓይን እያለው የማያይ ጆሮ እያለው የማይሰማ አምላክ የሚገዛ?" እያለ ይጮህ ጀመር። ይህን ሲሰሙ አንዳንዶቹ "የታራ ልጅ አብዶ" ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ "እሱ ያቀለለውን ማን ይገዛዋል።" ብለውት ሔደዋል። ሲመለስም ጣዖቱን ተመልክቶ አብርሃም እንዲህ አለ። "አንተ ቀድሞውን በዕለተ ሠሉስ የተፈጠርክ ዕፅ ነህ።" ብሎ ሰባበረው። ወደ ቤቱ ሲመለስም ሁሉንም ጣዖታት ሠባበራቸው። የመንግሥተ ሰማያት አበጋዝ የእግዚአብሔር ወዳጅ አባታችን አብርሃም የሕዝብና የአሕዛብ አባት የሆነው አብርሃም እግዚአብሔርን አምልኮ ጣዖታትን ሰብሮ ወደ ከነዓን ከወጣ በኋላ ብዙ ችግርን አሳልፏል። በረሃብ ምክንያት ከአንድም ሁለት ጊዜ ወደ ግብጽና ፍልስጥኤም ተሰዷል። በዚያ ግን ፈጣሪው አክብሮታል። ሁለቱ ነገሥታት (ፈርኦንና አቤሜሌክ) ሣራን እንነካለን ቢሉ ተግሣጽ ደርሶባቸዋል። ነቢይ ነውና በአብርሃም ጸሎት ተፈውሰዋል። ቅዱስ አብርሃም ከደግነቱ የተነሳ በኬብሮን (በተመሳቀለ መንገድ) ላይ ድንኳን ሠርቶ እንግዳ ይቀበል ነበር። ምሥክር ሳይዝም እህል አይቀምስም ነበር። ሰይጣን ከፍቶ እንግዳ ቢያስቀርበት ያለ ምግብ ለሦስት ቀናት ቆይቷል። በፍጻሜውም ሥላሴ በእንግድነት መጥተውለት በክብር ላይ ክብር፣ በጸጋ ላይ ጸጋ፣ በጣዕም ላይ ጣዕም ተጨምሮለታል። እርሱ የሥላሴን እግር ያጥብ ዘንድ በጀርባውም ይሸከማቸው ዘንድ አድሎታልና። ሥላሴም በቤቱ ተስተናግደው ልደተ ይስሐቅን አብሥረውታል። ጻድቁ ሰውም በፈጣሪው ፊት ስለ ሰዶምና ገሞራ ለምኗል። አብርሃም በአምልኮው ፍጹም ነውና የሚወደውን ልጁን ይስሐቅን ለመስዋዕት አቅርቧል። በዚህም የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የነገሥታት፣ የካህናት አባት ሥርወ ሃይማኖት (የሃይማኖት ሥር) ተብሏል። ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ አያቱም ተብሏል። አንድ ቀን እግዚአብሔር መላእክቱን "ብየ አርክ አብርሃም በዲበ ምድር - በምድር ላይ ወዳጄ አብርሃም አለ።" አላቸው። ያን ጊዜ ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ፦ "አብርሃም አርከ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅ)" "አብርሃም ብእሴ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር ሰው)" "አብርሃም ገብረ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር አገልጋይ)" "አብርሃም ምዕመነ እግዚአብሔር(አብርሃም የእግዚአብሔር ታማኝ)" "አብርሃም ፍቁረ እግዚአብሔር (አብርሃም የእግዚአብሔር ተወዳጁ ነው።) እያሉ አሰምተው ተናግረዋል። አባታችን አብርሃም በክብር፣ በቅድስናና በሞገስ ከዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራእይ ድረስ ተጠቅሷል። ፈጣሪ በስሙ ለቅዱሳን ተለምኗል። ስለ ክብሩም በሲዖል ውስጥ እንኳ ማረፊያን ሠርቶለታል። አጋንንትም ሊቀርቡት አልተቻላቸውም። ያረፈውም ከክርስቶስ ልደት አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት ነው። እድሜውም መቶ ሰባ አምስት ዓመት ነበር። ፍቅሩን የተረዱ ሊቃውንት ድንግል ማርያምን "ሐይመቱ (ድንኳኑ) ተናግዶቱ (እንግድነቱ) ለአብርሃም" ሲሉ አመስግነዋታል።ሊቁም፦ "አብርሃም ፍጹም በሒሩት ወበአምልኮእግዚአብሔር አዕበየከ ወባረከከ ባርኮእስከ ሰመየከ ዲበ ምድር አርኮ።" ብሎ በምሥጢር ገልጾታል። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                        የደግ ዛፍ ፍሬ የአብርሃም ልጅ ደጉ ይስሐቅ እጅግ ንጹሕ በመሆኑ የወልድ ክርስቶስ ምሳሌ ተብሏል። የይስሐቅ ልደት እጅግ የተጠበቀ ከመሆኑ ባሻገር የተፈጸመውም በብሥራተ አምላክ ነው። ስሙንም ያወጡለት ሥላሴ ናቸው። ቡሩክ ይስሐቅ በብዙ ነገሩ ድንቅ ነው። ለእርሱ ሃያ ዓመት ለአባቱ መቶ ሃያ ዓመት በሆናቸው ጊዜ ጭንቅ ትዕዛዝ ከፈጣሪ ዘንድ ተሰማ። አብርሃም ይሰዋው ዘንድ ወደ ደብረ ምሥጢር ይዞት ከወጣ በኋላ መስዋዕቱ እርሱ እንደ ሆነ አወቀ። ለፈጣሪውና ለአባቱ ይታዘዝ ዘንድ "እሺ" አለ። በዚያውም ላይ አባቱን "አባ ስንፈራገጥ እንዳልጐዳህ እሠረኝ። ዓይኔን አይተህ እንዳትራራ በሆዴ አስተኛኝ።" አለው። አቤት ትሕትና! አቤት መታዘዝ! ወዮ አባታችን ይስሐቅ! ቅንነትህ ምን ይደንቅ! ለዚህ አነጋገርህ አንክሮ ይገባል! "ሰላም ለይስሐቅ ዘኢያግዘፈ ክሳዶለደኒን ወለተሐርዶ"እንዲል። ቸር ፈጣሪ ግን የአብርሃምን አምልኮ የይስሐቅን ንጹሕ መታዘዝ ለዓለም ገለጠ እንጂ እንዲሞት አላደረገም። ቅዱስ ይስሐቅ በዚህች ዓለም ለመቶ ሰማንያ ዓመታት በትዳር ደግሞ ለመቶ ሃያ ዓመታት ቆይቷል። ከቅድስናው የተነሳ በእነዚህ ጊዜያት ከአንድ ቀን በቀር ከሚስቱ ርብቃ ጋር አልተኛም። በዚህቺው ዕለትም ያዕቆብና ኤሳው ተጸንሰዋል። እግዚአብሔር በመቶ ሰማንያ ዓመቱ ወደ ሰማይ ይዞት ወጣ። በዚያም ግሩም ምሥጢርን ተመለከተ። በእሳት መጋረጃ መካከል አብርሃምን አየው። ከአምላክ ዙፋንም እንዲህ የሚል ቃል ወጣ።"ወዳጄን ይስሐቅን የሚያከብረውን አከብረዋለሁ። ልጁን አምኖ "ይስሐቅ" ብሎ የሚጠራውን፣ በስሙ ለነዳያን የሚራራውን፣ ለቤቱ እጣን ያመጣውን፣ በዚህች ሌሊት በጸሎት የተጋውን፣ 'አምላከ ይስሐቅ' እያለ መቶ ጊዜ የሰገደውን፣ ዜና ይስሐቅን የጻፈውን፣ ያነበበውን ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት ዋጋውን እከፍለዋለሁ። ይህንንም ልጁ (አባታችን ያዕቆብ) ተመልክቶ ከትቦታል። ቅዱስ ይስሐቅም ከንጽሕናው ሳይጐድል በበረከት እንዳጌጠ ዐርፏል። ወገኖቼ! ከላይ ካነበባችሁት መርጣችሁ አንዷን በእምነት እንድትፈጽሙ አደራ እላለሁ! ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                    ጳጉሜ
                                                      2. ሐዋርያው ቲቶ (እረፍቱ)
                                                        የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ቅዱስ ቲቶ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ሲሆን በተወሰነ መንገድም ቢሆን የተዘነጋ ሐዋርያ አይደለም:: በተለይ ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ከጻፋቸው አሥራ አራት መልእክታት መካከል አንዷ የተላከችው ለዚህ ቅዱስ በመሆኗ ታሪኩ እንኳ ባይነገር ስሙ አይረሳም:: ቅዱስ ጳውሎስም በመልዕክታቱ በጐ ስሙን እየደጋገመ ያነሳዋል:: ለመሆኑ ሐዋርያው ቅዱስ ቲቶ ማን ነው?ቅዱስ ቲቶ የተወለደው በ1ኛው መቶ ክ/ዘመን እስያ ውስጥ: ቀርጤስ በምትባል ከተማ ነው:: የዘር ሐረጉ ከእሥራኤልም: ከጽርእም (ግሪክ ለማለት ነው::) ይወለዳል:: አካባቢው አምልኮተ እግዚአብሔር የጠፋበት ስለሆነ እሱም: ቤተሰቦቹም የሚያመልኩት ከዋክብትን ነበር:: መዳን በእውቀት ይመስላቸው ስለ ነበር የአካባቢው ሰዎች የግሪክን ፍልስፍና ጠንክረው ይማሩ ነበር:: ቅዱስ ቲቶም በወጣትነቱ ወደ ት/ቤት ገብቶ የግሪክን ፍልሥፍናና የዮናናውያንን ጥበበ ሥጋ ተማረ:: በጥቂት ጊዜም የሁሉ የበላይ ሆነ:: ቅዱሱ በወቅቱ ምንም እውነተኛውን ፈጣሪ አያምልክ እንጂ በጠባዩ እጅግ ቅንና ደግ ነበር:: ምክንያቱን ሳያውቀው ለእኔ ቢጤዎች ያበላ: ያጠጣ: ይንከባከባቸውም ነበር:: እግዚአብሔር ግን የዚህ ቅን ሰው በጐነቱ እንዲሁ እንዲቀር አልወደደምና አንድ ቀን በራዕይ ተገለጠለት:: በራዕይም አንድ ምንነቱን ያልተረዳው ነገር "ቲቶ ሆይ! ስለ ነፍስህ ድኅነት ተጋደል:: ይህ ዓለም ኃላፊ ነው::" ሲለው ሰማ:: ከእንቅልፉ ነቅቶ በእጅጉ ደነገጠ:: የሚያደርገውንም አጣ:: ያናገራቸው ሁሉ ምንም ሊገባቸው አልቻለም:: ለተወሰነ ጊዜም ለጉዳዩ ምላሽ ሳያገኝለት በልቡ እየተመላለሰ ኖረ:: ድንገት ግን በዚያ ሰሞን ከወደ ኢየሩሳሌም አዲስ ዜና ተሰማ:: "ክርስቶስ የሚሉት ኢየሱስ: እርሱም የባሕርይ አምላክ የሆነ ወደ ምድር ወርዶ: ስለ እግዚአብሔር መንግስትም እየሰበከ ነው::" ሲሉ ለቲቶ ነገሩት:: "ሌላስ ምን አያችሁ?" አላቸው:: "በእጆቹ ድውያን ይፈወሳሉ:: ሙታን ይነሳሉ:: እውራን ያያሉ:: ለምጻሞች ይነጻሉ:: ሌሎች ብዙ ተአምራትም እየተደረጉ ነው::" አሉት:: የወቅቱ የሃገረ አክራጥስ መኮንን ፈላስፋ ነበርና ስለ ክርስቶስ ሲሰማ ሊመራመር ወደደ:: እርሱ መሔድ ስላልተቻለው "ብልህ ጥበበኛ ሰው ፈልጉልኝ::" ብሎ ተከታዮችን ቢልካቸው ከቲቶ የተሻለ በአካባቢው አልነበረምና እርሱኑ አመጡት:: መኮንኑ ቲቶን "ነገሩ ትክክል ወይም ስሕተት መሆኑን በጥልቅ መርምረህ ምላሽ አምጣልኝ::" ብሎ ላከው:: ቅዱስ ቲቶም ፈጥኖ ተነስቶ ወደ ኢየሩሳሌም ገሰገሰ:: ወደ ከተማዋ እንደገባም ጌታችንን አፈላልጐ አገኘው:: 1.ጌታችን ክርስቶስ በሥልጣነ ቃሉ ደዌያትን ሲያርቅ: አጋንንትን ሲያሳድዳቸው ተመልክቶ ይህ ሥራ የፍጡር እንዳልሆነ ተረዳ:: 2.ጌታችን የሚያስተምረው ትምሕርት ከግሪክ ፍልሥፍና እጅግ ርቆና መጥቆ አገኘው:: የግሪክ ፍልሥፍና መነሻውም ሆነ መድረሻው ሥጋዊ ነው:: ጌታ ግን በጣዕመ ቃሉ የሚያስተምረው ሰማያዊ: በዚያ ላይ ዘላለማዊ የሆነ ትምሕርት ነው:: በራዕይ "ስለ ነፍስህ ተጋደል::" ያለው ምሥጢር አሁን ተተረጐመለት:: በዚህ ምክንያትም ጊዜ አላጠፋም:: ወዲያውኑ አምኖ ተከታዩ ሆነ:: ጌታም ከሰባ ሁለቱ አርድእት ደመረው:: የአክራጥስ መኮንን "ምነው ዘገየህ?" ቢለው ያየውን ሁሉ ጽፎ: እንደማይመለስም አክሎ ደብዳቤ ላከለት:: ከዚህ በኋላ ቅዱስ ቲቶ ከጌታችን እግር ለሦስት ዓመታት ተምሮ: በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ: በመላው እስያ ለስምንት ዓመታት ወንጌልን ሰብኳል:: ቅዱስ ጳውሎስ ባመነ ጊዜ ደግሞ የእርሱ ደቀ መዝሙር ሆኖ ለሃያ አምስት ዓመታት አስተምሯል:: ቅዱስ ጳውሎስ ሰማዕት ከሆነ በኋላ ደግሞ ወደ አክራጥስ ተመልሶ: ሕዝቡን አሳምኖና አጥምቆ: ቤተ ክርስቲያንን አንጿል:: ዕድሜው በደረሰ ጊዜም መምሕራንን: ካህናትን ሹሞላቸው: ባርኳቸውም በዚህች ቀን ዐርፏል:: አምላከ ቅዱስ ቲቶ መልካሙን የሕይወት ምሥጢር ይግለጽልን:: ከሐዋርያውም በረከቱን ያድለን:: ጳጉሜን 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት1.ቅዱስ ቲቶ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት) "የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ. . . መድኃኒታችን እግዚአብሔር እንዳዘዘ: ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት ቃሉን ገለጠ: በሃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ለሚሆን ልጄ ቲቶ:: ከእግዚአብሔርም አብ: ከመድኃኒታችንም ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት: ሰላምም ይሁን::"(ቲቶ. ፩፥፩)ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                                      3. ቅዱስ ሩፋኤል
                                                        ቅዱስ ሩፋኤል በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት በደረጃው ሦስተኛ ነው:: በመጀመሪያዋ ዕለተ ፍጥረት እግዚአብሔር መቶ ነገደ መላእክትን ፈጥሮ በአሥር ከተማ ሲያኖራቸው የቅዱስ ሩፋኤል ዕድል ፈንታው ራማ ሆነች:: በዚያም "መናብርት" ተብለው ለሚጠሩ አሥሩ ነገድ አለቃ (መሪ) ሆኖ በፈጣሪው ተሹሟል:: በኋላም "መጋብያን" በሚባሉ በሃያ ሦስቱ ነገድ ላይ ሹሞታል:: ይህች ዕለትም በዓለ ሲመቱ ናት:: አንድ ቀን ጌታችን ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ሐዋርያቱ ቅዱስ ሩፋኤልን እንዲያስተዋውቃቸው ለመኑት:: ጌታም ሦስቱን ሊቃናት (ሚካኤል: ገብርኤል እና ሩፋኤል) ይመጡ ዘንድ አዘዛቸው:: ቀጥሎም ቅዱስ ሩፋኤልን "ክብርህን ንገራቸው::" አለው:: እርሱም ለጌታ ሰግዶ ለሐዋርያት ብዙ ምሥጢር ነገራቸው:: በተለይ ስሙን ለሚጠሩ: መታሰቢያውን ለሚያከብሩ የሚደረገውን ጸጋ አብራርቶላቸው ዐረገ:: በመጽሐፈ ጦቢት ላይ ተጽፎ እንደምናገኘው ቅዱሱ መልአክ ሰው (አዛርያን) መስሎ: ጦብያን ለትዳር አብቅቶ: ሣራን አስማንድዮስ ከሚባል ሰይጣን አድኖ: የጦቢትን ዓይን አብርቷል:: በገድላተ ቅዱሳን እንደምናየውም ለብዙ ቅዱሳን ረዳታቸው ሆኖ ገድላቸውን አስፈጽሟል:: ታሪክ እንደሚለው ይህች ቀን ለቅዱስ ሩፋኤል ቅዳሴ ቤቱም ናት:: በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በቅዱስ ቴዎፍሎስ ዘእስክንድርያ አማካኝነት ቤቱ ታንጿል:: የሚገርመው ደግሞ የታነጸው በዓሣ አንበሪ ጀርባ: ደሴት ላይ ነው:: በመልአኩ አጋዥነትም ለሦስት መቶ ዓመታት አገልግሏል:: ቅዱስ ሩፋኤል ¤መስተፍስሒ (ልቡናን ደስ የሚያሰኝ) ¤አቃቤ ሥራይ (ባለ መድኃኒት ፈዋሽ) ¤መዝገበ ጸሎት (የጸሎት መዝገብ መክፈቻ የተሰጠው) ¤ሊቀ መናብርት (በዙፋን ላይ በክብር የሚቀመጡ መላእክት መሪ) ¤ፈታሔ ማኅጸን (የሰውንም ሆነ የእንስሳትን ማኅጸን የሚፈታ) ¤መወልድ (አዋላጅ: ምጥን የሚያቀል) ይባላል:: "ለሰብእ ወለእንስሳ ፈታሔ ማኅጸኖሙ አንተ" እንዲል:: ወስብሐት ለ እግዚአብሔር
                                                      4. አባ ባይሞን(እረፍቱ)
                                                        ይህ ቅዱስ አባት የአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቤተ ክርስቲያን ፍሬ ሲሆን ተሰምተው በማይጠገቡ መንፈሳዊ ቃላቱ (ምክሮቹ)ና በቅድስና ሕይወቱ ይታወቃል። ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦በተጠቀሰው ዘመን በምድረ ግብጽ የምትኖር አንዲት ደግ ሴት ነበረች። አምላክ በፈቀደው ጋብቻ ውስጥ ገብታ ሰባት ወንዶች ልጆችን አፈራች። እነዚህ ሰባቱ የቁጥር ጭማሪ የጾታም ቅያሪ የላቸውም። ሰባቱም ወንድማማቾች ገና ሕፃን እያሉ አባት በመሞቱ እናት ፈተና ውስጥ ገባች። ነገር ግን ብርቱ ሴት ነበረችና በወዟ ደክማ አሳደገቻቸው። ሥጋዊ ማሳደጉስ ብዙም አይደንቅም። ምክንያቱም ሁሉም እናቶች ይህንን ያደርጉታል ተብሎ ይታመናልና። የዚህች እናት የሚገርመው ግን ሁሉንም ንጹሐን፣ የተባረኩ፣ የክርስቶስ ወዳጆች፣ የቤተ ክርስቲያንም አለኝታዎች እንዲሆኑ አድርጋ ማሳደጓ ነው። እነዚህ ሰባት ወንድማማቾች፦ ፩.አብርሃም ፪.ያዕቆብ ፫.ዮሴፍ ፬.ኢዮብ ፭.ዮሐንስ ፮.ላስልዮስና ፯.ባይሞን (ጴሜን) ይባላሉ። ለእነዚህም ዮሐንስ በኩር ሲሆን ባይሞን መቁረጫ ነው። ሰባቱም ወጣት በሆኑ ጊዜ ወገባቸውን ታጥቀው እናታቸውን ያገለግሉ፣ ለፈጣሪያቸው ይገዙ ያዙ። ያየ ሁሉ "ከዓይን ያውጣችሁ።" የሚላቸው ቡሩካንም ሆኑ። አንድ ቀን ግን መንፈስ ቅዱስ በሰባቱ ልብ ውስጥ አንድ ቅን ሃሳብን አመጣ። ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ስለ ምናኔ አወሱ። ይህንን ዓለም ከነ ኮተቱ ይተውት ዘንድ መርጠዋልና ወደ በርሃ ለመሔድ ተስማሙ። እናታቸው ምን መንፈሳዊ ብትሆን የትኛዋም እናት ሁሉን ልጆቿን በአንዴ ማጣትን አትፈልግምና አላማከሯትም። ይልቁኑ እነርሱ ከሔዱ በኋላ እንዳትቸገር የምትታገዝበትን መንገድ አዘጋጅተውላት ተሰወሩ። ሰባት ልጆቿን በአንዴ ያጣችው እናት ብቻ አይደለችም፤ ሁሉም አዘነ። ተፈለጉ ግን አየኋቸው የሚል ሰው አልተገኘም። ሰባቱም ቅዱሳን ከቤታቸው እንደ ወጡ ወደ ገዳም ሔደው አንዲት በዓት ተቀበሉ። ሰባቱም የሚጸልዩ በጋራ፣ የሚሠሩ፣ የሚመገቡ፣ የሚውሉ፣ የሚተኙም በጋራ ነው። በአገልግሎታቸውም ሆነ በፍቅራቸው አበውን ደስ አሰኙ። "እምኩሉ የዓቢ ተፋቅሮ - እርስ በርስ መዋደድ ከሁሉ ይበልጣል።" እንዲሉ አበው። ከዘመናት ተጋድሎ በኋላ ግን ዝናቸው ከገዳሙ አልፎ በከተሞች ተሰማ። ይህንን የሰማችው እናታቸው የእርሷ ልጆች መሆናቸውን በማወቋ ፈጥና ወደ ገዳሙ ገሰገሰች። "ልያችሁ ልጆቼ?" ስትልም ላከችባቸው። እነርሱ ግን "እናታችን በመንግሥተ ሰማያት እንድታይን በዚህ ይቅርብሽ።" አሏት። ምክንያቱም ሰባቱም የሴትን ፊት ላያዩ ቃል ገብተው ነበርና። ይህ ለአንድ እናት ከባድ ቢሆንም እርሷ ግን ተረዳቻቸው። ፈጥናም ወደ ቤቷ ተመለሰች። ከኮከብ ኮከብ ይበልጣልና (፩ቆረ. ፲፭፥፵፩) ከሰባቱ ቅዱሳን ደግሞ ትንሹ አባ ባይሞን የተለየ አባት ሆነ። ከንጽሕናው፣ ቅድስናና ትጋቱ ባሻገር ከአንደበቱ የሚወጡ ቃላት ሕይወትነት ያላቸው ሆኑ። በዘመኑም ከሕፃን እስከ አዋቂ ድረስ ብዙዎች ከመንፈሳዊ ቃላቱ ተጠቅመዋል። እነዚህ ምክሮቹ ዛሬ ድረስ ለምዕመናንም ሆነ ለመነኮሳት ጣፋጮች ናቸው። እልፍ አእላፍ ከሆኑ ምክሮቹ እስኪ አንድ አምስቱን እንጥቀስ፦ ፩."ባልንጀራህ በወደቀ ጊዜ በፍጹም ተስፋ አትቁረጥበት። ይልቅስ አንቃው፣ አበረታታው፣ ሸክሙንም አቅልለት እንጂ።" ፪."ለጥሩ ባልንጀራህ የምታደርገውን ደግነት ለክፉው በእጥፍ አድርግለት። መድኃኒትን የሚሻ የታመመ ነውና። አልያ ግን ለበጐው ያደረከው ከንቱ ነው።" ፫."ባልንጀራህ በበደለ ጊዜ አትናቀው። ያንተ ተራ በደረሰ ጊዜ ጌታህ ይንቅሃልና።" ፬."የማንንም ኃጢአት አትግለጥ (አታውራ)። ካላረፍክ ጌታ ያንተኑ ይገልጥብሃልና።" ፭."አንደበትህ የተናገረውን ሁሉ ለመሥራት ታገል። አልያ ውሸታም ትሆናለህ።" ሰባቱ ቅዱሳን ወንድማማቾች ለብዙ ዓመታት በፍቅርና በተጋድሎ ኑረው በዚህች ቀን ዐርፈዋል። ወስብሐት ለ እግዚአብሔር

                                                    © sinksar apk , facebook ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቀጥተኛዋ መንገድ ናት

                                                    ታህሳስ 6 ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ

                                                    GEDELEKIDUSAN ታህሳስ 3 ቅድስት አርሴማ(ቅዳሴ ቤቷ) ✝እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው።  ✝መድኃኒታችን ክር...